በአዲስ ዓመት መንፈስ ተሞልተን እነሆ መንገድ ጀምረናል። አዲስ ዓመትን በተስፋና በጥንካሬ የጀመረ ካሰበበት መድረሱ አይቀርም ይባል ነበር ድሮ፡፡ ድሮን አትናቁ፡፡ ድሮን ያስታወሰ የወደፊቱ አይከብደውምና፡፡ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ ልንጓዝ ነው። መንገድ ማጣሪያ እንጂ መቋጫ የለውም ይላሉ የጎዳናው ደንበኞች። የአረማመድ ቄንጥ ከእነ ጫማ ቁጥራችን ተብጠርጥሮ በሚበረብሩበት በዚህ ጎዳና፣ ተጓዥና አጓጓዥ ብዙ ይባባላሉ። ‹‹ታያታለህ እንዴት እንደለበሰች? አሁን ቢጫ ኮት በጥቁር ሱሪ ይደረጋል?›› ይላል ከተሠለፍነው መሀል አንዱ። በሩቅ አውቶሞቢሏን በንቃት እየዘወረች ውበት የለቀቀባትን ቀዘባ እየጠቆመ። ‹‹ኮቱንስ ይሁን፣ ሱሪዋን እንዴት ከዚህ ሆነህ ልታየው ቻልክ?‹‹ ይላል ወዳጁ። ‹‹ቀላል ነው። እንደ እኔ ተደራጅተህ ቡቲክ ስትከፍት ይገለጽልሃል፤›› ይላል ያኛው። ‹‹ምን አልክ? ደግሞ ለዚህም ተደራጁ ተባለ እንዴ?›› ቦርሳ ያንጠለጠለ ጎልማሳ ጠየቀ። ‹‹አቤት? ማናቸው እነሱ?›› ዓይኑ ከዚያች ባለቢጫ ኮት ወጣት አልነቀል ያለው ጠየቀ። ጎልማሳው በኮባ እንደተጠቀለለ ያልበሰለ ሊጥ መልሱ በጥያቄ ተሸፍኖ ተመለሰለት መሰል ዝም አለ። ‹‹ሰው በቃ በተውላጠ ስም እነሱ እኛ እያለ ማነካካቱን ‘ሙድ’ አደረገው አይደል?›› ይለኛል ከኋላዬ የተሠለፈ ቀጭን ጎልተው የሚንከባለሉ ዓይኖች ያሉት ወጣት። ሊያነካካኝ እኮ ነው!
ትከሻዬን ሰብቄ በአልገባኝም ስመልስለት ደግሞ፣ ‹‹ቆይ ለምን አንደኛውን መሀል ገብቶ አስቁሟት ‘ሊፍት’ አይጠይቃትም?›› ይለኛል። ያ የቅርብ ሩቅ አዳሪው ሰምቶት ኖሮ፣ ‹‹ማን በሠራው መንገድ ነው ማን መሀል ገብቶ የሚገጨው?›› ብሎ ዞረበት። ከጀርባዬ የቆመው ደፋር ‹‹አየህ? ወይ ማጥመድ አይችሉ ወይ መጥለፍ አይሳካላቸው፣ ዝም ብለው ዳር ቆመው ቄንጥ ሲያወጡ ሰው ይመስላሉ፤›› ብሎ ጎሸመኝ። “እኮ እነ ማን?” ብሎ ያኛው ሲያፈጥ፣ ‹‹ስለማን ነው የምናወራው? ስለእኛና ስለእነሱ ነዋ፤›› ብሎት ደረቱን ነፋ። ባለቦርሳው ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹አቤት! አቤት! ተናግሮ ሞቷል እባክህ። እዚህ ቆሎ የማይደፋ ቅኔ ዘረፍን እያሉ ሰላማችንን የሚያደፈርሱብንን ምናለበት ቢያጣሩልን፤›› አለ። ሁላችንም እንዳሻን የገጠመ ያልገጠመውን ሁሉ ገጣጥማችሁ ትርጉም ካልሰጣችሁ በምንልበት ጊዜ አጣሪ ‘ኮሚሽን’ ቢቋቋም ማን ሊተርፍ ነው? እንዲያው እኮ!
አሁን ታክሲ ተሳፍረናል። ያ ከጀርባዬ ተሠልፎ በማስኩ ተከልሎ ጆሮዬ ሥር ሲተነፍስብኝ የነበረው ደፋር መሀል መቀመጫ ላይ ከአንዲት ወይዘሮ ኋላ ተሰይሟል። ወይዘሮዋ ደርባባነታቸው ልዩ፣ አለባበሳቸው ደግሞ ማራኪ ጥንቅቅ ያሉ ሴት ናቸው። ‹‹እማማ እባክዎ ይኼን ግርማ ሰው ሁሉ እንዲያየው ይዘውት እንዳይወርዱ አደራ፤›› ይላል ወጣቱ። ‹‹ምን ላድርገው ታዲያ? ልስቀልልህ?›› ይሉታል እያሾፉ። ተጫዋች ናቸው። ‹‹የለም ይፍቀዱልኝና ፎቶ ላንሳው፤›› ዓይን አውጣው ፊት ሲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ነው። ‹‹እንዴ? እናንተ ልጆች የፎቶ አብዮት ነው የያዛችሁት የዕድገት? ጊዜው ሥሩብኝ ይላል እናንተ ደግሞ ቴክኖሎጂ አገዘን ብላችሁ ‹ቀጭ! ቋ!› ያለችውን ሁሉ እንደ ፓፓራዚ በፎቶ ምች ስታሳድዱ መዋል ሆኗል ሥራችሁ። ምን ይሻላችኋል?›› ከናፍራቸውን አጣመው ጥርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ ያዩታል። ድሮ ቄንጠኛ ነበሩ ማለት ነው!
‹‹ምን ይሻለናል እማማ። ይኼም እኮ ሥራ ፈጠራ ነው። ሥራ እስክናገኝ ሥራ መፈለግ ነው ሥራችን፤›› ወጣቱ ሲናገር ይፈጥናል። ‹‹በል ሁለተኛ. . . ሁለተኛ. . . ጊዜ እንኳን ብለኸኛል ይሁን፣ ሦስተኛ እማማ ብትለኝ እኔ ነኝ በጥፊ ጥሩ ፎቶ የማነሳህ፤›› አሉት ኮስተር ብለው። “እሺ እማማ. . .” አለና አረፈው። ‹‹ካሁን በኋላ ድገማትና ታያለህ። የዘመኑ ወጣቶች የተፈቀደላችሁን ቃል በኃላፊነት ከመጠቀም ይልቅ፣ ያልተፈቀደላችሁን መደጋገም ትወዳላችሁ። የፈጃችሁን እሳት እንደ መራቅ መልሳችሁ ትጠጉታላችሁ፣ ይብላኝላችሁ…›› ብለው ትከሻቸው ላይ ጣል ያደረጉትን ባለፈርጥ ሻርፕ ማስተካከል ያዙ። ‹‹እኔ ምለው ግን. . .›› አለ። ‹‹አንተ ምትለው ግን?›› ቀና ብለው አያዩትም። ‹‹እርስዎ በዚህ ዕድሜዎ እንዲህ ጥንቅቅ ብለው ሲለብሱ፣ የእኔ ትውልድ መላ ቅጡ የጠፋው አለባበስ ፋሽን ብሎ የተያያዘው ምን ነክቶት ነው?›› ከማለቱ፣ ‹‹ነገረኛ! ‘የፖለቲካ ተፅዕኖ ነው’ እንድልህ ነው? አንዲያው መልሱ ጠፍቶህ ነዋ የጠየቅከኝ። በል ቶሎ አንሳኝ አሁን!›› ብለው ለፎቶ ተዘጋጁ። ቀጭ አደረጋቸው። እኚህ ‘ዋዘኛ’ ስልኮች እኮ ሰውን ሁሉ በሄደበት ዋዛ አስመሰሉት እናንተ!
ያነሳቸውን ፎቶዎች ሲያሳያቸው ወይዘሮዋ፣ ‹‹ይኼን ደልተው ይኼን በኢሞ ወይም በሜሴንጄር ላክልኝ›› እያሉ ሳሉ ወያላው “ሒሳብ!” ብሎ ከፊታቸው ቆመ። ‹‹እስኪ መጀመርያ ከፊት የተቀመጡትን ተቀበል። ጉልበታችሁ መሀልና ዳር የተቀመጥነው ላይ ብቻ ነው?›› አሉት ሽቅብ እያዩት። ‹‹የለም እርስዎ ተጨማሪ ስለሚከፍሉ ቅድሚያ ከዚህ ነው የምጀምረው፤›› አለ ወያላው የምሩን። ‹‹እኮ ለምን? ማን ሾሞህ ነው ደግሞ አንተን ተጨማሪ ብለህ እኔን ብቻ የምታስከፍለኝ? እናንተ ዘንድሮ እኮ ሿሚና ሻሪውን ማወቅ አቃተን፤›› ወይዘሮዋ ተነሳባቸው። ‹‹የለም ይኼ ሹመት ምናምን አይደለም። ደግሞ ተጨማሪ ክፈሉ አልወጣኝም። ያለ ፈቃድ ታክሲያችን ውስጥ ፎቶ ስለተነሱ ከታሪፉ ጋር አሥር ብር ይከፍላሉ. . .›› ከማለቱ ተሳፋሪዎች በሳቅ አውካኩ። የቀልደኞች ዘመን!
ሁላችንም ቀልድ መስሎን ነበር። ወያላው ግን አምሯል። ‹‹እንዴ! ምን ለማለት ነው አንተ?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተሰየመው ባለቦርሳው ጎልማሳ ለወይዘሮዋ ተደረበ። ‹‹ምናልባት ፎቶው ለሽብር ተግባር እንዳይውል ሰግቶ ይሆናል፤›› አለ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠው ያ አለባበስ ሲተች የነበረው ወጣት። ‹‹ሥራው ገንዘብ መቀበል እንጂ መርማሪነት ነው ታዲያ?›› ብሎ ጎልማሳው ወደ ወጣቱ ሲዞር፣ ‹‹እንዲያ ካልክ ‘ሳታማሃኝ ብላ’ን ጋብዘው፤›› አለው። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ወያላው ድርቅ ብሎ የጠየቀው አሥር ብር ባይከፈለውም ታሪፉን ግን ወሰደ። ወይዘሮዋ፣ ‹‹ዋ ጊዜ! ብለን ብለን በገዛ ካሜራችን ትዝታን በዋጋ የምንሸምትበት ጊዜ ላይ ደረስን?›› ሲሉ ጎልማሳው፣ ‹‹ይተውት በቃ በዚሁ ይለፍ። በዚህ ዓይነት እኮ የዜግነትም ክፈሉ ይመጣ ይሆናል፤›› ቢል ሁሉም በጩኸት አፍጠው አዩት። ይሆናል ብሎ ገመተ እንጂ መቼ ሆነ ወጣው? ለወሬና ለነገር ያለን ችኮላ እኮ!
ጉዟችን ቀጥሏል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት ሴቶች ሲያወሩ ቀሪዎቻችን አዳማጮች ነን። ‹‹ገና ለገና አሜሪካ ቪዛ ተመታልኝ ብላ እንዲህ ፀባዩዋ ይቀየር?›› ትላለች ወደ መስኮቱ ጥግ የተቀመጠችው። ‹‹አትገርምሽም? ብርቅ ነው እንዴ አሜሪካ መሄድ? ባንሄድም ዕድሜ ለሆሊውድና ለሲኤንኤን የማናውቀው ነገር የለም፤›› ትላለች ጫፍ ላይ የተቀመጠችው። ‹‹ውይ ሰው! ሰው ግን . . .›› ስታማትብ ቆይታ፣ ‹‹ሳገኝ ከምከዳ አምላኬ ሆይ መጀመርያውኑም አትስጠኝ፤›› ብላ አጉል ቃል ገባች። ይኼን ጊዜ ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ምንድነው የምትለው ልጅቷ? ቪዛ አግኝቶ ይቅርና በባዶ መስሎኝ ሰው የይሁዳን መንገድ የተቀላቀው። አይደለም እንዴ?›› ይለኛል። ዘንድሮስ ሳይሆን አይቀርም!
‹‹አንቺ ግን . . . ›› ሴቶቹ ጨዋታቸው ቀጥሏል። “እ?” ትላለች ሰሚዋ። ‹‹እንዲች ብለሽ ቅሬታሽን ማሳየት የለብሽም። እንዲያውም እያደር እንዲነዳት ሽሮ፣ በርበሬ፣ ቅቤ፣ ምናምን ቋጥረሽ መስጠት አለብሽ፤›› ስትባል፣ ተመካሪዋ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ፣ ‹‹ማ እኔ ለእሷ! ስንትና ስንት ወገኔ እየተቸገረ ነው ገና ለገና አሜሪካ ልሄድ ነው ብላ ቀባሪ አልፈልግም ላለች ጉረኛ ሽሮና በርበሬ የምቋጥረው? የኑሮ ውድነቱን ተቋቁሜ ለምስኪን ወገኔ መቋጠር በቻልኩ፤›› ብላ ሐሳብ ገባት። ‹‹ምን ቸገረሽ? አንቺም እኮ ያ አሜሪካዊ ነው ያልሽው ልጅ ላግባሽ ብሎ ቢፈርምልሽና ብትሄጂ፣ አገሩን እስክትለምጂ ከእሷ ውጪ ምንም ሰው የለሽም፤›› ስትላት ወዳጇ ቦግ ቦግ ስትል የነበረችው ሴት፣ ‹‹እሱስ ልክ ነሽ. . .›› ማለት ጀመረች። ትርፍና ኪሳራን እያሰሉ በሚኖርበት በዚህ የራስ ወዳድነት ዘመን እንኳን እሷ፣ ስንቱ የተጨበጨበለት ሲሸነፍ አላየንም? አዬ ሰው መሆን!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋ በነገር እየተብሰለሰሉ፣ ቆስቁሶ ባለዕዳ አድርጓአቸው የነበረው ወጣት ድምፁን አጥፍቶ፣ ጎልማሳው ከቀበሌ እስከ ፓርላማ የሚታዘበውን እያወራ፣ እነዚያ ወጣት ጓደኛማቾች መግዛት ስለሚፈልጉት የመኪና ሞዴል እየተወያዩ፣ ካጠገባቸው ደግሞ በዝምታ የተዋጡት ባልና ሚስት እንዳቀረቀሩ መጨረሻችን ቀረበ። ጋቢና ለብቻው የተቀመጠ አንድ ጎረምሳ የአውሮፓ ቡድን ደጋፊ ነኝ እያለ ከሌላ ቡድን ደጋፊ ጋር ደርቢ ገጥሟል። ‹‹እናንተ ምን አለባችሁ? እኛ እዚህ በጠራራ ፀሐይ በረባ ባረባው እንጋጣለን፣ እናንተ ህልውናችሁን እንኳ ዕውቅና ለማይቸሩ ተራጋጮች ታሸበሽባላችሁ፤›› አሉ ወይዘሮዋ። ‹‹ምን እናድርግ? ‘ለራሳችሁ አልቅሱ’ ተብሎ ተጽፏል፤›› ይላቸዋል ከፊታቸው የተቀመጠው። ‹‹ታዲያ ማርገጃ መሬት ጠፋ? ምን ሩቅ ያስኬዳችኋል?›› ወይዘሮዋ ከፍቷቸዋል። ‹‹ስለመሬት ነክ ጉዳይ ባይወራ ደስ ይለኛል፤›› ይለኛል ጎልማሳው። ‹‹ዳይፐር’ አልቆበታል እኮ ማሙሽ. . .›› ትላለች ደግሞ ከኋላ ሚስት ለባሏ። ባል ደግሞ፣ ‹‹ምናለበት ብትገዥለት? ከትናንት ወዲያ የሰጠሁሽን ገንዘብ ምን አደረግሽው?›› ብሎ ያፈጣል። ‹‹ይኼ መፋጠጥ ከቤት ከጀመረ ደግ አይደለም፤›› የሚለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ነው፡፡ እውነቱን ሳይሆን አይቀርም!
‹‹አይደብረውም እንዴ ሰውዬው? በሰው መሀል ‘ሼም’ ያስይዛታል እንዴ?›› ይባባላሉ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙት ሴቶች። የባልና ሚስቱን ወጣቱ ሲያዳምቅ፣ ‹‹ኳስ እኮ ነጋ ጠባ የሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ የለው፣ ፖለቲካ ተኮር ዘገባ አያውቅ፣ የራሱን ድምፅ ለማሰማት ሲል የሰው ድምፅ አያፍን፣ በቃ ምን ልበልዎት ኳስ ማለት የጠራ ግጥሚያ ነው። ደግሞ የአውሮፓ ኳስ? ልዩ . . .›› ሳይጨርስ ወይዘሮዋ፣ “የአገርህስ?” ብለው ዞሩበት። ይኼኔ ወያላው “መጨረሻ!” ብሎ በሩን በረገደው። ‹‹የአገርህስ ነው እኮ የምልህ?›› ወይዘሮዋ አጥብቀው ቢጠይቁም መልስ አልነበረም፡፡ ኑሮው ፖለቲካ፣ መዝናኛው ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ሕይወቱ ፖለቲካ፣ ኳሱ ፖለቲካ በሆነባት ምድር እግር እርሙን በልቶ መርገጡን ቀጠለ። ችግሩን መዘርዘር ቢቀጥል ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ገና አዲስ ዓመት ለመግባት ዳር ዳር እየተባለ ስንቱ ችግር ተነግሮ ይዘለቃል? ይልቁንስ ከችግር በላይ ተስፋ መሰነቅ አይከፋም፡፡ ‹‹ይቅር መባባል ቢለመድ እኮ ችግራችን አይከፋም ነበር፤›› ሲል ያ ወጣት፣ የምክትል ከንቲባዋ ድምፅ፣ ‹‹ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች በከተማዋ አስተዳደር ለተፈጸሙ ስህተቶችና የአስተዳደር ግድፈቶች፣ በጳጉሜን 1 ይቅርታ ቀን ላይ ከፊታችሁ ቆሜ ይቅርታ እንድታደርጉልን በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፤›› ከሬዲዮው እየተሰማ ነበር፡፡ ይቅርታ ማንንም ስለማይጎዳ ይቅርታ ይለመድ! መልካም ጉዞ!