Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራትን ያስተሳሰረው የውኃ ፕላስቲኮች ፕሮጀክት

አካባቢን የሚበክሉ የውኃ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መሥራት የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በዚህም ማኅበራትና ድርጅቶች ተሰማርተዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሆነው ፔትኮ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የውኃ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ መልሶ በመጠቀም ላይ ለሚሠሩ ድርጅቶች ያቀርባል፡፡ ድርጅቶቹ ደግሞ ፈጭተው ወደተለያዩ አገሮች ይልካሉ፡፡ ወ/ሮ ምሕረት ተክለ ማርያም የፔትኮ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፔትኮ ኢትዮጵያ ድርጅት እንዴት ተመሠረተ?

ወ/ሮ ምሕረት፡- ፔትኮ ኢትዮጵያ ድርጅት ከተቋቋመ ዓመት አልፎታል፡፡ የተመሠረተውም ከተለያዩ ውኃና የለስላሳ ፋብሪካዎች እንዲሁም የመልሶ መጠቀም ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነው፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራው ከገባ አሥር ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ፈቃድ ከማግኘት በፊትም በዚሁ መንገድ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚጣሉ የውኃ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- መልሶ የመጠቀም ሥራው ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- አካባቢን የሚበክሉ የውኃ ፕላስቲኮችን በመጠቀም ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ እናደርጋለን፡፡ ለወጣቶችና ለሴት ልጆችም የሥራ ዕድልን በመፍጠር በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጥለው የሚገኙ የውኃ ፕላስቲኮችን ሰብስበው ገንዘብ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል፡፡ የውኃ ፕላስቲኮች አካባቢን ከሚበክሉ ይልቅ ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንገድ ከፍተናል፡፡ ይህንንም ሥራ ከውኃና ከለስላሳ አምራች ድርጅቶች፣ ከተለያዩ የውኃ ፕላስቲኮችን ከሚሰበሰቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት እየሠራን ነው፡፡ እነዚህንም ግብዓቶች በማቅረብ ለመልሶ መጠቀም እንዲውሉ የሚያደርጉ ድርጅቶች እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሪሳይክሊንግ ኢንዱስትሪው ሳይቆራረጥ የገበያ ትስስሩን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በቀጣይም ከዚህ በላይ ለመሥራት ዕቅዶችን ይዘናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የምታገኙት እንዴት ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- እኛ የምንደግፋቸው የውኃ ፕላስቲኮችን የሚሰበስቡ ማኅበራትና የመልሶ መጠቀም ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ነው፡፡ ተቋማቱን ከመደገፍ አኳያ ድርጅታችን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ከሆቴል፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከየአካባቢዎች የውኃ ፕላስቲኮችን የሚሰበስቡ ማኅበራትን በማሠልጠን ግብዓቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ሰዎች ጓንቶችንና ማዳበሪያዎችን እንዲሁም መልሶ መጠቀም ላይ ለሚሠሩ ድርጅቶች ማሽኖችን በማቅረብ በዘርፉ ላይ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ያላችሁ አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የውኃ ፕላስቲኮችን ከሚሸጡ አካላት ጋር ስንሠራ ነበር፡፡ አሁን ግን የበለጠ በተቀናጀ መልኩ በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች ውስጥ ፕላስቲክ በመሰብሰብ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ማኅበራት ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡ እነዚህ ማኅበራትም ቁጥራቸው በርከት ያለ በመሆኑ ወደ ሥራው ገብተው እንዲሠሩና ራሳቸውን በኑሯቸው እንዲለወጡ እያደረግን ነው፡፡ ለሥራው የሚያስፈልጓቸው ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው እየተደረገ ነው፡፡ በእንጦጦ አካባቢም በእንጨት ለቀማ ኑሯቸውን ላደረጉ 263 እናቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በቀጣይም በዝቅተኛ የኑሮ  ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች የሥራ  ዕድል የሚፈጠር ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ውጪ ይንቀሳቀሳል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- የተቋሙ ጽሕፈት ቤት መቀመጫው አዲስ አበባ ቢሆንም፣ ሥራውን እየሠራ ያለው በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታዎች ነው፡፡ በቀጣይ ዓመትም በባህር ዳር፣ በድሬዳዋ፣ በጅማ፣ በመቀሌና በሐዋሳ ቢሮዎችን ከፍተን ሥራዎችን ለመሥራት ጥናቶችን አድርገን አጠናቀናል፡፡ በከተሞቹ ላይ ለመሥራት ያሰብንበት ዋነኛ ምክንያት ከፍተኛ የውኃ ፕላስቲክ ክምችት ልቀት የሚካሄድባቸው ቦታዎች እንደሆኑ በመገንዘብ ወደ ሥራው ለመግባት መንገዶችን ጀምረናል፡፡ ወደፊትም ሰፋ ባለ መልኩ ለመሥራት አቅማችንን ማጎልበት ይጠበቅብናል፡፡ ከሠራን በኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች ላይ የአካባቢን ብክለት መቀነስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ቆሻሻዎች ለመልሶ መጠቀም እንዲውሉ የምንሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለሥራችሁ ምን ዓይነት ዕገዛ ያደርግላችኋል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- በአሁን ሰዓት የምንሠራው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ባለሀብቶችም በዚህ ሥራ ላይ ተሳትፏቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲና የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን እንዲሁም የአዲስ አበባ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ በዘርፉ ላይ ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡ የለስላሳና የውኃ አምራች ድርጅቶችም በዚህ ሥራ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ መንግሥትም የተለያዩ ዕገዛዎችን እያደረገልን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በሥራው ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ለውጦችን ማምጣት ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ በሪሳይክሊንግ ላይ የተሠማሩ ተቋማት የግብዓት ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ይኼም ሥራውን ይበድላል፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ ላይ ምን ዓይነት ችግር አጋጥሟችኋል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- በእኛ በኩል ያጋጠሙን ችግሮች ብዙም አይደሉም፡፡ ነገር ግን በመልሶ መጠቀም ላይ ያሉ ተቋማት የሚፈልጉትን ያክል ግብዓት እያገኙ አይደለም፡፡ ማሽኑ የሚፈልገውን ያህል የውኃ ፕላስቲኮችን አለማግኘቱ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡ እነዚህንም ግብዓቶች ለማቅረብ በእኛ በኩል ቀን ከሌሊት እየሠራን ነው፡፡ በተለይም የውኃ ፕላስቲኮችን የሚሰበስቡ ማኅበራትን በማጠናከርና በማገዝ የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን፡፡ በዚህም ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ውጭ አገሮች ለመላክ ምን አስባችኋል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- የእኛ ሥራ የሚሆነው ከየአካባቢው የሚሰበሰቡ የውኃ ፕላስቲኮችንና ግብዓቶችን ማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን ከኮባ ኢንፓክት ጋር አንድ ላይ ሆነን እየሠራን ነው፡፡ ይኼ ተቋምም ወደ ተለያዩ አገሮች እየላከ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም ለተለያዩ ጥቅሞች እንዲውል ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በዚህ የተነሳ ማኅበረሰቡ የተፈጨውን የውኃ ፕላስቲክ ለተለያዩ ጥቅሞች እያዋለው ይገኛል፡፡ ውጭ አገርም ለልብስ፣ ለመጥረጊያ፣ ለምንጣፍና ለተለያዩ ጥቅሞች ይውላል፡፡ ይኼም ከፍተኛ የገንዘብ ምንዛሪን ያስገኛል፡፡ ኮባ ኢንፓክት የውኃ ፕላስቲኮችን አጥቦ ፈጭቶና የዓለም ገበያ በሚፈልገው መልኩ አዘጋጅቶ ወደ ተለያዩ አገሮች ይልካል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ስፔን፣ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡– ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ምን ችግር አጋጠማችሁ?

ወ/ሮ ምሕረት፡- ይህን ሥራ የምንሠራው ከተለያዩ ማኅበራት ጋር ነው፡፡ የኮቪድ-19 ሥርጭት ደግሞ ማኅበራቱ በሚያደርጉት የውኃ ፕላስቲኮችን የመሰብሰብ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በፊት ከሚያገኙት ገንዘብ ቀንሶባቸዋል፡፡ ይህንንም ከግምት በማስገባት ተቋማችን በዚህ ችግር ውስጥ ላሉት ማኅበራት የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ በሚፈለገው መጠንም ግብዓቶች አለመሰብሰባቸው በዘርፉ ላይ ችግር መፍጠሩን ማየት ችለናል፡፡ ከዚህ በኋላም ያሉትን ችግሮች በከፊልም ቢሆን ለመቀነስ የምንሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ አንፃር ምን እያደረጋችሁ ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡– በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመዘዋወር አካባቢን የሚበክሉ የውኃ ፕላስቲኮችን እያነሳን ጥቅም ላይ እያዋልን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌሎች ቆሻሻዎችን ለማስወገድ ከመንግሥት ጋር እየሠራን ነው፡፡ ማኅበረሰቡንም ከማንቃትና ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ማኅበራትም ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...