አሮጌው ዓመት በሰላም ተሸኝቶ አዲሱን ዓመት በተስፋ ለመቀበል ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት፣ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የሚስተዋለው ፍጥጫ አደገኛ ስለሆነ መርገብ አለበት፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በእሳት ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ ያሰፈሰፉ ኃይሎች ከውጭም ከውስጥም ‹‹ግፋ በለው›› ቅስቀሳ ላይ መጠመዳቸው መወገድ ይኖርበታል፡፡ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዳገት የሆነባቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፣ ከገቡበት አደገኛ የቀውስ መንገድ ውስጥ መውጣት ካልቻሉ መጪው ጊዜ ከባድ ነው፡፡ እልህ፣ ግትርነት፣ ቂመኝነት፣ ክፋትና ኋላ ቀርነት የተፀናወታቸው ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነትና ሰላም ላይ አደጋ ደቅነዋል፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ለሥልጣን በሚያደርጉት ግብግብ አገር ለማፍረስ አሰፍስፈዋል፡፡ በተለይ ከራሳቸው ፍላጎት በላይ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ደንታ የማይሰጣቸው የሥልጣን ጥመኞች፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው የጦርነት ጉሰማ ላይ ናቸው፡፡ ከትግራይ ክልል ምርጫ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰማው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በፍጥነት መቆም አለበት፡፡ ከተገባበት አተካሮ በመላቀቅ በፍጥነት ውይይትና ድርድር መጀመር ይኖርበታል፡፡ አገር በእልኸኞችና በሥልጣን ቀበኞች ምክንያት ትርምስ ውስጥ የምትገባበት ምክንያት መኖር የለበትም፡፡
የእልህ ፖለቲካ አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት ስለሆነ ለሰላማዊ አማራጭ መንገዶች ቅድሚያ ይሰጥ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያስመረረውን ጦርነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመቀስቀስ መወራጨት ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ልጆቻችሁንና የቅርብ ሰዎቻችሁን ወደ ውጭ አሽሽታችሁና ውጭ አገር ሆናችሁ ከምቹ ሳሎናችሁ የጦርነት ነጋሪት የምትጎስሙ፣ ምስኪኑን የኢትዮጵያ ወጣት እሳት ውስጥ ለመማገድ በግልጽ የምታደርጉት ቅስቀሳ አንድ ቀን በጦር ወንጀለኝነት ያስጠይቃችኋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍሬያማ የሆነ የውይይትና የድርድር ባህል እንዲሰርፅ፣ ከትምህርትና ከልምድ ያገኙትን ዕውቀት ማካፈል የሚጠበቅባቸው ሳይቀሩ ጦረኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እየታዩ ነው፡፡ ሥልጣን ወይም ጥቅም እስካልተመቻቸላቸው ድረስ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ደንታ እንደሌላቸው ራሳቸውንም ያጋለጡ አሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆነውም ለውይይትና ለድርድር የሚረዳ ምኅዳር ከማዘጋጀት ይልቅ፣ በተለመደው የጉልበተኝነት መንገድ በመቀጠል ቀውስ እንዲፈጠር የሚያሴሩ መኖራቸው ደግሞ የበለጠ ልብ ይሰብራል፡፡ ማዶ ለማዶ ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች የሚሻኮቱ ኃይሎችም ለመፍትሔ ሳይሆን ትርምስ ለመፍጠር እየተረባረቡ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹ የጦርነት ጉሰማ ተዋንያን ከእሳቱ ራሳቸውን ማራቃቸው ነው፡፡ የጦርነቱ ገፈት ቀማሾች ግን ምስኪን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን አደገኛ ደባ ለማክሸፍ የጦርነት ጉሰማውን ማስቆም አለባቸው፡፡
በዚህ በሠለጠነ ዘመን በሁለንተናዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አማካይ መፈለግ የግድ ነው፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ እያስተናገዱ በበርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይቻላል፡፡ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ትሩፋት እኮ ልዩነትን ማክበርና የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባት መቻል ነው፡፡ ምርጫ ለማካሄድም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ ብሔራዊ ጉዳዮችን ለማከናወን የጉልበት መንገድ አያዋጣም፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚያስገባ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታ በሌለበት አገር ውስጥ፣ ለግለሰቦችና ለቡድኖች ሥልጣን ሲባል ብቻ ሕዝብንና አገርን ሥጋት ውስጥ መክተት አሳዛኝ ነው፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገዶችን እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ በሚገባ ለመጠቀም ትዕግሥትና ቁርጠኝነት በሌለበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ፣ እየገዘፈ የመጣው ዕብሪትና ማናለብኘነት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ከእነ ችግሮቹም ቢሆን ለማክበርና ለማስከበር የሚታየው ዳተኝነት፣ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን ሥር የሰደደ ልዩነትና ጥላቻ ያሳብቃል፡፡ ፖለቲካው በሴረኞች እየተዘወረ በየወቅቱ በሚቀነቀኑ አጀንዳዎች የሚዘራው ጥርጣሬና አለመተማመን፣ በማኅበረሰቦች ውስጥ ጭምር እየዘለቀ ጥልቀት ያለው ልዩነት እየፈጠረ ነው፡፡ ለአገር ዕድገትና ለሕዝብ ኑሮ መለወጥ አንዳችም ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ሳይከናወኑ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስነሳት መቅበዝበዝ ከማስገረም አልፎ ሐዘን ይፈጥራል፡፡
ገዥውን ብልፅግና ፓርቲ ጨምሮ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፣ አገሪቱን የማትወጣበት አዘቅት ውስጥ ለመክተት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን አንድ በአንድ ነቅሰው በማውጣት ለውይይት ለማቅረብ ለምን ጥረት አያደርጉም? በትግራይ ክልል ዝግጅቱ ከተጠናቀቀበት የምርጫ ጉዳይ ጀምሮ የደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎችና በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚስተዋሉ ችግሮች ጭምር ለምን አይመከርባቸውም? ከሕዝብ ደኅንነትና ከአገር ሰላም የሚበልጥ ምንም አጣዳፊ ጉዳይ የለምና ለምን ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የሚያስችል ቀና ልቦና አይኖርም? ለዓመታት በቁርሾና በጥላቻ ውስጥ እየተኖረ እንዴት ስለ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር መነጋገር ይቻላል? በትግራይ ክልል ሕዝብ ለጦርነት ተዘጋጅ ተብሎ ቅስቀሳ እስኪደረግ ድረስ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለምን መፍታት አቃተ? የፌዴራሊስት ኃይሎች ጠበቃ ነን የሚሉት ካለፈው ስህተታቸውና ጥፋታቸው ተምረው ለምን ለሰላም እጃቸውን መዘርጋት አልፈለጉም? ከዚህ በፊት ራሳቸው በግላጭ ሲጥሱት የከረሙትን ሕገ መንግሥት በማስከበር ስም አሁንም ከጦርነት አባዜ ለምን መውጣት አልቻሉም? በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስብ ፖለቲከኛም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላማዊ ውይይትና ድርድር ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉ ፖለቲከኞችም ሆኑ አጋፋሪዎቻቸው፣ አገር የሚያፈርስ የጦርነት ጉሰማ ላይ ናቸው፡፡
በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደሞከርነው ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን መልካም ዕድሎች ማበላሸት አይገባም፡፡ አንዴ ከእጅ ያመለጠን ዕድል ዳግም ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘመን እያስቸገሩ ያሉት ደግሞ ማገናዘብ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ቢያንስ በታሪክ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን ተገንዝበዋል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከታሪካዊ ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ አይመስሉም፡፡ ሥልጣን ላይ ሆነው አገርና ሕዝብ ሲያተራምሱ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ የማያውቁበትን ተቃዋሚ ሆነው ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ በዚያው ሒደት ውስጥ አልፈው በለውጥ ኃይልነት ከወጡ በኋላ መለወጥ ያቃታቸውም አሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ በቅርቡ ዘመን የግፍ እስራትና የስደት ሰለባ ከመሆን አልፈው በለውጡ ዘመን ዕፎይታ ያገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ወቅቱ ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ በጋራ ከመንከባከብና ወደ ተሻለ ደረጃ ከማድረስ ይልቅ፣ ጎራ ለይተው ሕዝብን ለማፋጀትና አገርን መቀመቅ ለመክተት የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ብቅ ባሉ ቁጥር መርዝ ይተፋሉ፡፡ ደጋፊዎቻቸውን ለነውጥ ያነሳሳሉ፡፡ አንድም ቀን ስለሕግ የበላይነት፣ ስለእኩልነት፣ ስለፍትሐዊነት፣ ስለነፃነት፣ ወዘተ ሲያቀነቅኑ አይሰሙም፡፡ ሁልጊዜም ብሶት፣ ምሬት፣ አሉባልታ፣ ሐሜት፣ ጥላቻና አገር ስለማተራመስ ነው የሚያወሩት፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሆነው ሕዝብን ፍጅት ውስጥ የሚከት የጦርነት ነጋሪት ይጎስማሉ፡፡
ኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍትሕና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ አሁን እንደሚታየው በጦርነት ነጋሪት ጉሰማ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምትነግዱ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አፈንግጣችሁ የማንን ዓላማ ነው የምታሳኩት? ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ አስተሳሰብ እንጂ በጠመንጃ አምላኪነት አይደለም፡፡ ሥርዓቱ ዕውን የሚሆነው በሕዝብ ድምፅ ብቻ እንደሆነም ግልጽ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ፀባይ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ዓይንና እጅን በሕገወጥ መንገድ የሚገኝ ሥልጣንና ጥቅም ላይ አድርጎ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ሥልጣንና ጥቅም አያማልላቸውም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ከአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በታች እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እያነሳሱ አያጋድሉም፡፡ የአገርን ሰላም እያደፈረሱ ቀውስ አይፈጥሩም፡፡ ከሴራና ከአሻጥር የፀዱ በመሆናቸው ተግባራቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ጨለማ ውስጥ መሽገው አገር አይበጠብጡም፡፡ ከእንዲህ ዓይነት የማይረባ ድርጊት ነፃ ነን የምትሉ አገር አረጋጉ፡፡ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ተያይዞ ከመጥፋት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ይታወቅ!