Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

“የልማት ዕቅዱ ለአገር ውስጥ አቅም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል” ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ

ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው አለማያ እርሻ ኮሌጅ ወይም ባሁኑ አጠራረር ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ በግብርና ኢኮኖሚ በ1972 .. የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት፣ በኦክላሆማ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን፣ በካሳስ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ከአራት አሠርታት በላይ በውጭና በአገር ውስጥ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን፣ የማማከርና የማስተማር እንዲሁም የጽሑፍ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ምሁሩ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎች ላይ በተለይ ደግሞ በግብርናና በአርብቶ አደር ዙሪያ የተለያዩ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ ከነዚሀም መካከል ከወራት በፊትኢኮኖሚው፣ ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ” በሚል ርዕስ ያሳተሙት አዲስ መጽሐፍ የሚገኝበት ሲሆን፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ ሙያዊ አስተያየቶችን በመስጠት በስፋት ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የምትመራበትን የልማት ዕቅድ፣ በመንግሥት ይፋ ተደርጎ ውይይቶች እየተካሄዱበት ይገኛል፡፡ እቅዱን መነሻ በማድረግ ሰሎሞን ይመር ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የፕላንና ልማት ኮሚሽን የኢትዮጵያን የአሥር ዓመታት ጉዞ መልክ ያስይዛል፣ ኢትዮጵያንም ወደተሻለ ምዕራፍ ያሻግራል ያለውንና ኢትዮጵያ አፍሪካዊ የብልጽግና ተምሳሌት” የሚል ስያሜ የተሰጠውን 2013 ዓ.ም እስከ 2022 .ም ድረስ የሚተገበር የልማት ዕቅድ አስተዋውቋል፡፡ እርስዎ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ በመሪ እቅዱ ላይ ያለዎት አስታያየት ምንድነው?

ዶ/ር ደምስ፡- ማንኛውም አገርን ለመቀየር ያለመ እንቅስቃሴ ከነ ችግሮቹም ቢሆን ከመነሻው ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአገራችን የአሥር ዓመታት የልማት ዕቅድ ማዘጋጀት አዲስ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል በደርግ ዘመንም ተመሳሳይ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በኢሕአዴግም የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተብሎ ተግባራዊ ሲሆን ነበር፡፡ ዋናው ነገር ካለፉት የልማት ዕቅዶች ምን መማር ተችሏል? የሚለው ነው፡፡  ብዙዎቹ ያለፉት አገራዊ የልማት እቅዶቻችን ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይህ አዲሱ ዕቅድ በይዘት ደረጃ የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል ለማለት ይከብደኛል፡፡ በዝግጅትና በጽሑፍ ደረጃ ከጥቂት ሐሳቦች በስተቀር ከዚህ በፊት ከምናውቃቸው ዕቅዶቻችን ጋር በብዙ መልኩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ዕቅድ በሚዘጋጅበት ጊዜ በመጀመሪያ እንደ አገር ያሉንን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች እንዲሁም ተቋማትን መዳሰስ ይገባል፡፡ ከዛ በመነሳት እነዚህን ለማስፈጸም የሚረዱ ዝርዝር ዕቅዶችን ወደ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚዘጋጁ የዕቅድ ዶክመንቶች ያሁኑንም ጨምሮ የቅደም ተከተልና ከፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጋር የመናበብ ችግሮች ይታዩባቸዋል፡፡ በሌላ መልኩ “መንግሥት እቅዱን የሚያዘጋጀው ለማንና ለምንድን ነው?” መንግሥት የራሱን ተግባራት ለማከናወን የሚስችለውን ዕቅድ ሊያስቀምጥ ይችላል:: የግል ዘርፉን በሚመለከት በዕቅዱ የሚካተቱ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ የግሉን ዘርፍ በቅጡ መረዳትና “አንዴት ነው ሊደገፍ የሚገባው?” የሚለው ላይ ግልጽነት አላየሁበትም፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ሊደረግ ስለታቀደው የአቅም ግንባታ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ካለፉት ዕቅዶች የተለየ ነገር አላየሁበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ያለፉት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች የሚጠበቀውን ለውጥ እንዳላመጡ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ራሱ ባደረገው ግምገማ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በብዙ መልኩ እንዳልተሳካም ተገልጿል፡፡ አንዳንዶች ይህ “አዲሱ የአሥር ዓመታት መሪ የልማት ዕቅድ ተመሳሳይ ዕጣ እንደማይገጥመው ምን ማረጋገጫ አለ?” በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎን ሐሳብ ቢያካፍሉን፡፡

ዶ/ር ደምስ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚዘጋጅበት ጊዜ ትራንስፎርሜሽን በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ግልጽ የሆነ መግባባት አልተደረሰም ነበር፡፡ አሁንም ድረስ እነዚህን ሐሳቦች የተረዳናቸው አይመስለኝም፡፡ በአዲሱ ዕቅድ ላይም ተመሳሳይ ችግሮች አይቻለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ጽንሰ ሐሳቦችን ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ ካልተቻለ ሊደረስበት የሚፈለገውን ግብ ለማወቅ ይቸግራል፡፡ ባቀድነው መጠን ውጤት አልመጣ ያለው ለምንድን ነው? ለሚለው፣ አንዳንዴ ዕቅዶች ሲዘጋጁ እንዲለጠጡ ይደረጋል፣ ይህ መሆኑ ብዙም ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ቢለጠጥ ችግር የለብኝም፡፡ ዋናው ቸግር ያለው ግን መንግሥት ዕቅዱን የሚያወጣው ለማን ነው የሚለው ጉዳይ ነው? የምታቅደው ለማን አንደሆነ ካላወክ ውጤትህንም ልታውቀውና ልትረዳው አትችልም፡፡ መንግሥት ሊያቅድ የሚችለው ራሱ ለሚሠራቸው ሥራዎች፣ ለሚሰጠው አገልግሎት፣ ለሚዘረጋው መሠረተ ልማት ነው መሆን ያለበት፡፡ የሚያስቀምጠው ግብ ግን ሌላው ተዋናይ የሚሠራውን ነው፡፡  ውጤቱ የሚወሰነውም በዚያው ልክ ነው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ እዚህ ይደርሳል፣ ግብርናው ይህንን ያህል ያመርታል፣ ኢንዱስትሪ እዚህ ይደርሳል በማለት መንግሥት እርግጠኛ በመሆን ማስቀመጥ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ዋነኛው ተዋናይ የግል ዘርፉ አንደመሆኑ መጠን ውጤቱ የሚወሰነው መንግሥት በሚያስቀምጠው ቁጥርና ግብ ብቻ አይደለም፡፡ የግሉ ዘርፍ ምን ያህል በመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ አምኖ ኢንቨስት ለማድረግ ተሰልፏል የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የተቀመጡት ውጤቶች እንዲመጡ መንግሥት  ዘርፉን በምን መልኩ ሊደግፍ ይገባል የሚለው መታሰብ አለበት፡፡  የዕቅድ ዝግጅቱም ይህንን ማዕከል አድርጎ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ መንግሥት ሥራውን መገምገም ያለበትም የግሉን ዘርፍ በአገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታው ላይ በሚፈለገው መልኩ አንዲሳተፍ በምን ያህል መጠን እየደገፈ እንደሚገኝ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በትኩረት ሳይሠራ ዕቅዱ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያለፈው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋነኛ ትኩረት ኢትዮጵያን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ያለመ አንደነበር ይታወቃል፡፡ በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለው ትስስር ምን መምሰል አለበት የሚለው ሐሳብ በራሱ አነጋጋሪ ሆኖ መቆየቱ እንዳለ ሆኖ፡፡ ለመሆኑ እነዚህን ሁለት ግዙፍ ኢኮኖሚ ዘርፎች በምን መልኩ ቢቀናጁ ለአገራችን ኢኮኖሚ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላሉ፡፡ የግብርና ምርታማነት ሳይሻሻል ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ማሰብስ ያስኬዳል ወይ፡፡ አዲሱስ የልማት ዕቅድ ይህን ሐሳብ በምን መልኩ ሊያስታርቀው አስቧል?

ዶ/ር ደምስ፡- በመጀመርያ ግብርና ራሱ ኢንደስትራላይዝድ መሆን አለበት፡፡ ግብርናውን ኢንደስትራላይዝድ ማድረግ ስትችል ነው ሌላው ላይ መድረስ የምትችለው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ በራሱ ግብርና ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ቀደም ባለው ጊዜ ኢንዱስትሪያል ፖሊሲ ተብሎ የወጣውን ዕቅድ ብንመለከተው የስኳር፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የአበባ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች፣ ቆዳ ማቀነባባሪያዎችን ወዘተ ማስፋፋትን ያለመ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ ሴክተሮች ኢንዱስትሪ ብለን ብንወስዳቸውም መሠረታቸው ምንድን ነው? ስኳር ፋብሪካ ብለህ ኢንዱስትሪ ስትል ሰፋፊ የሸንኮራ አገዳ እርሻ ያስፈልግሀል፡፡ ይሄ ግብርና ነው ሌሎቹም እንደዛው፡፡ ኢንዱስትሪ ተብሎ የሚጠቀሱትም በግብርናው ሥር ያሉ ዘርፎች መሆናቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ የግብርናው ዘርፍ እጅግ ሰፊና አብዛኛውን ኢንዱስትሪዎችን አቅፎ እንደያዘ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ የተሳሳተ እይታ ግብርናውን በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ ግብርናው ራሱ ኢንደስትራላይዝድ መደረግ አለበት በማለት ነበር ስንጮህ የነበረው፡፡ ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ ግብርናው ራሱ መዋቅራዊ ለውጥ ያምጣ ወደ ኢንዱስትሪል አግሪካልቸር ትራንስፈር ማድረግ አለበት፡፡

በአሁኑም ዕቅድ ውስጥ ምርታማነታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ወደ ምርታማነታቸው ከፍ ወዳሉ ምርቶች መሸጋገር የሚል ሐሳብ አንስቷል፡፡ ዋናው ነገር ይህ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ዋናው ነጥብ መሆን ያለበት እያንዳንዱ ሴክተር ውስጥ ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በግብርናው ውስጥ በተወሰነ የሰው ኃይል ከፍተኛ ምርት ማምረት ወደሚቻልበት ደረጃ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ግብርናን ለማዘመን ብለህ የውጭ ባለሀብት የምትፈልግ ከሆነ ግን ግብርናውን አትቀይረውም፡፡

ሪፖርተር፡– ታዲያ የአገራችንን ግብርና ምርታማነት በማሳደግ ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ዕድገት ለማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው?

ዶ/ር ደምስ፡- በዘመናዊ ግብርና ምርታማነትን ማሳደግ በእርሻ ቦታ ስፋትና ጥበት የሚወሰን ላይሆን ይችላል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት እኮ ግብርና ቤት ውስጥ ገብቷል፡፡ የማምረት ዘዴ እጅግ ጠባብ በሆነ መሬት ብዙ ምርት ማምረት የሚቻልባቸው  የአርቲፌሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ግብርናን ንግድ ተኮር ለማድረግና ኢንዱስትሪያል አግሪካልቸርን ለማሳደግ ግን ሰፋፊ እርሻ መሬቶችና ግብዓቶችን ስለሚፈልግ የመሬት ፖሊሲዎችን መከለስ ይፈልጋል፡፡

ግብርናንም ሆነ ኢንዱስትሪን ለማዘመን ከውጭ ተፅዕኖ መላቀቅ አለበት፡፡ አሁን በሚዘጋጀው ዕቅድ ላይ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ኢትዮጵያውያን በዋናነት እንዲሳተፉበት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ግብርናውን ለማዘመን ብለህ የውጭ ኢንቨስተር የምትፈልግ ከሆነ ግብርናውን አትቀይረውም፡፡ በመጀመሪያ የእኛ አነስተኛ ገበሬዎች ትክክለኛና ነፃ የግል ገበሬዎች እንዲሆኑ ማድረግ ከዛ አስፈላጊውን ዕቅድ በማዘጋጀት የሚያስፈልጋቸውን ግብዓትና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ አራሾች፣ ከመካከለኛ ወደ ሰፋፈፊ አራሾች እንዲሻገሩ በማድረግ እርሻውን ደግሞ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ሳይሆን ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ግብርና ማለት እርሻ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ በውስጡ ኢንዱስትሪ አለው፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ትራንስፖርት፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ አለው፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ መዘውር ያለው በግብርናው ላይ ነው፡፡ ግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ የሚለው ሐሳብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግብርናው ራሱን ችሎ ትራንስፎርም እንዲሆን ማድረግ በራሱ በርካታ ተያያዥ ዘርፎችን ስለሚያሳድግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መፍጠር ይቻላል፡፡ ብዙ ነገሮችን እንደሚቀይር ግልጽ ነው፡፡

አሁንም ያለው ዕቅድ ያልተረዳው ነገር ይሄንን ነው፡፡ ግብርናውን ከኢንዱስትሪው ነጥሎ የመመልከት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ማለት እስከዛሬ የተሄደበትና ግብርናውን እንዳይንቀሳቀስ ያደረገ ምልከታ ነው፡፡ ይህ ካልተስተካከለ ግብርናውንም ሆነ ኢንዱስትሪውን ማሻሻል ቀላል አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- የድህነት መጠንን አሁን ካለበት 19 ከመቶ ወደ 7 ከመቶ ዝቅ ማድረግ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢን ወደ 8.2 ከመቶ ማሳደግና አጠቃላይ አገራዊ ምርቱን በየዓመቱ በ10.2 ማሳደግ የሚሉትን እንደማሳያ በመጥቀስ የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሊያሳካቸው ያስቀመጣቸው ግቦች የተለጠጡ ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ አንፃር እነዚህን ቁጥሮች ማሳካት ይቻላል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ደምስ፡- አንድ ነገር መተማመን ያለብን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጸጋና አቅም ከዚህም በላይ ሊያስኬድ ይችላል፡፡ አይደለም በአሥር ዓመት ውስጥ በሁለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ ሊደረስበት ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን ያለንን አቅም ተጠቅመን ውጤታማ ሥራ መሥራት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የመልማት አቅም የሚመጥን ሥራ ባለመሥራታችን ነው፣ ከዓለም ኋላ የቀረነው፡፡ እዚሀ አገር ላይ በየዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የውጤታማነት ችግር እያለብን ባለን አቅም ባለን ጊዜ መሥራት ያለብንን ያህል እየሠራን አይደለም፡፡ እንደኛ ያለ ድሀ አገር ሌት ተቀን በጥራት መሥራት ካልተቻለ ከገባበት አዘቅት መውጣት ህልም ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡

ቁጥሮቹ አያሳስቡን፣ መድረስ ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር ጥራት ያለው ሥራ መሠራቱ ላይ ነው፡፡ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ በትኩረት በመሥራት ብቻ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ስንዴን ብንወስድ በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ ምርት ወደ አገር ይገባል፡፡ ይሄን በአገር ውስጥ ማምረትና መተካት ቢቻል እኮ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ውጤት ሊገኝባቸው የሚችሉ ዘርፎችን በጥንቃቄ ለይቶ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ከተቻለ ውጤት የማይመጣበት ምክንያት አይታየኝም፡፡

አንዳንዱ ቁጥር የተጋነነ ሊሆን ይችላል ለምሳሌ የድህነት ምጣኔውን 7 በመቶ ማውረድ የሚለው እየወጡ ካሉ ሌሎች ትንበያዎች አንፃር ቁጥሩ በጣም ዝቅ ያለ ይመስላል፡፡ እንዳልኩት ቁጥሮቹ ላይ ችግር የለብኝም፡፡ ዋናው ነገር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ተግባራትን በመለየት በተጨባጭ መሥራት ይቻላል፡፡ መተማመን ያለብን ባለን አቅም ውጤታማ ሥራ እየሠራን ነው ወይ፡፡ በውጭ ዕርዳታ ተንጠልጥለን ማቀድ አይገባም፡፡ የመንግሥት አሠራሮችን ከፖለቲካ ፍጆታ ነፃ በማድረግ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚፈጠሩ የሥራ ዘርፎችም ውጤታማነትን ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችና በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ መካከል ምን ዓይነት መሠረታዊ አንድነትና ልዩነቶችን አስተውለዋል?

ዶ/ር ደምስ፡- ያለፈውም ሆነ ያሁኑም ዕቅድ፣ ገበያ መር ኢኮኖሚ መገንባትና የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ አሳትፎ ለመሄድ ፍላጎት አለው፡፡ ይሄ አንድነታቸው ሲሆን ያለፈው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ባለሀብቱን ልማታዊና ልማታዊ ያልሆነ በሚል እየከፋፈለ የግሉን ዘርፍ በጥርጣሬ ያይ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የተዘጋጀው ዕቅድ በዚህ በኩል የነበረውን ችግር አስተካክሎ ቀርቧል፡፡ በሌላ በኩል ግን ይህ የ10 ዓመት ዕቅድ ያልተገነዘበው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊ የግል ዘርፍ ተዋናያንን በኢኮኖሚው ውስጥ እንዴት አድርጎ በማሳተፍ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ማምጣት ስለሚቻልበት ሁኔታ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ኢኮኖሚውን ለውጭው አሳልፎ ለመስጠት የሚዘጋጅ ዓይነት ነው የሚመስለው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ በስፋት እየገቡ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ከጨዋታ ውጭ ሊወጡ የሚችሉበት አደገኛ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያሠጋል፡፡ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በልማት ስም የአገሪቱን ሀብት ለመቀራመት ያለመ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ዓይነት ሙከራ ሊያደርጉ ያስባሉ፡፡ አሁን ባለው ግርግር በፖለቲካው ምክንያት ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሄድ ላይ ችግር ያለ ይመስላል፡፡ በአጠቃላይ አገራዊ የልማት ዕቅዱ ኢትዮጵያውያንን የግሉ ዘርፍ ተዋንያንን በመደገፍ በአገር አቅም ለውጥ የሚመጣበትን አካሄድ በሚገባ ሊያጤነው ይገባል፡፡ አሁን ባለንበት ጊዜ የውጭ ኢንቨስትመንት በገፍ መጋበዝ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ የግል ሴክተር በሚል አጠቃላይ ዕይታ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን የሚያዳክም ሥራ እንዳይሆን ያሠጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በዘመናት የተፈራረቁ መንግሥታት አገሪቱን ከድህነት አረንቋ በማላቀቅ ወደ ዕድገት ጎዳና ለመውሰድ ያግዛሉ ያሏቸውን በርካታ የልማት ዕቅዶች ሲያስተዋውቁና ለውጥ ለማምጣት ሲታትሩ አልፈዋል፡፡ ይሁን አንጂ በከተማም ይሁን በገጠር የሚኖረውን ድሀ ሕይወት በቅጡ የለወጠ ተግባራዊ ዕርምጃ ለማየት ብዙም አልታደልንም፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት ሥርዓት ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ግብርናችንን  ከባህላዊ አስተራረስ ዘዴና ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በቂ ምርት ማምረትና በምግብ ራሳችንን መቻል አቅቶናል፡፡  በአገሪቱ 85 በመቶ እንደሆነ የሚነገረውና ኑሮውን በገጠር ያደረገው ማኅበረሰብ አስፈላጊው የመሠረተ ልማት ግብዓትና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ፣ ምርታማነትን ማሳደግና ግብርናውን ማዘመን ብሎም ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ የልማት ዕቅድ ነድፎ ውጤቱን ማየት ከብዶናል፡፡  ለመሆኑ ኢትዮጵያ ካለፉት አገራዊ የልማት ዕቅዶቿ ስኬትና ውድቀት ምን ልትማር ይገባል?

ዶ/ር ደምስ፡- አንዱ ሄዶ ሌላው ሲመጣ ብድግ ብሎ የነበረውን ሲያፈራርስ ነው የኖረው፡፡ በአገራችን የመንግሥት አሠራር ውስጥ ሁልጊዜ ሁሉንም ነገር ከዜሮ የመጀመር አካሄድ ይታያል፡፡ ስትራቴጂ ሺሕ ጊዜ ቢጻፍ አዲስ ለውጥ አይመጣም፡፡ ሁልጊዜ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን፣ የተቋማትን ሁኔታ በመገምገም ክፍተቶችንና ያሉብንን ጉድለቶች ላይ መሥራት ያስፈልጋል፣ ያለንን ጠንካራ አሠራር በመቀጠል ክፍተቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የመሥራት ልምድ ሊዳብር ይገባል፡፡ ዕቅድና ፕሮግራሞች ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ እንዳይውሉ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ ፖሊሲና በሌላ በኩል በዕቅዱ የተቀመጡ ተግባራትን በየጊዜው መከታተልና መደገፍ ላይ ትኩረት መስጠትም ይገባል፡፡ እንዲሁ እቅድ ስለወጣ ብቻ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የኢትዮጵያ ግብርና ያሉበትን ችግሮች በመለየት ዘርፉን ለመደገፍና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮችን በማካተቱ ረገድ ምን ያህል ዘልቋል?

ዶ/ር ደምስ፡- የአገራችን ግብርና ችግር በስፋት ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በግብርናው ትኩረት አንዲሰጠው የሚፈለገው ነፃ ገበሬ መፍጠር ላይ ነው፡፡ የእርሻ መሬት አያያዝንና ግብርናን ማዘመን ያስፈልጋል ሲባል ከሰው ጉልበት ወጥቶ በማሽነሪን መጠቀም ያሻል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፋይናንስ ያስፈልጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግብርናው ላይ ተስፋ ሰጭ ነገሮች ይታያሉ፡፡ በግብርናው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የግሉ ሴክተር ተብሎ ሲቀመጥ ግልጽ የሆነ ጠቋሚ ሊቀመጥለት ይገባል፡፡ ለምሳሌ በግብርናው የግል ዘርፍ ሲባል እነማን ናቸው በዚህ ውስጥ የሚጠቀሱት፣ የትኞቹ ገበሬዎች ናቸው በዚህ የሚካተቱት፣ በውጭ ባለሀብት የተያዙ የእርሻ መሬቶችን የግሉ ዘርፍ ተብለው ነው የሚገለጹት የሚለው፣ በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡

በእርሻ ስፋት ትራንስፎርሜሽን መምጣት አለበት፣ የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚ አቅም እየፈጠረ ሲመጣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ደግሞ ወደ ከፍተኛ የእርሻ ማሳ ማግኘት እንዲችል የሚያስችል የመሬት ፖሊሲ ሊኖር ይገባል፡፡ ገበሬው የገቢው መጠን እያደገ ሲሄድ፣ ያንን የሚመጥን የእርሻ ይዞታ እንዲያገኝ የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ባለመኖሩ ገበሬው ሥራውን እያሰፋ በግብርናው መቀጠል እየፈለገ ወደ ሌላ ዘርፍ ለመሄድ ይገደዳል፡፡ ዕድገት እያሳየ መሄድ ይገባዋል፡፡ ሌላው በግብርናው ላይ ትልቁ ማነቆ የቴክኖሎጂና የግብዓት ችግር ሲሆን የቴክኖሎጂ ጉዳይ ትኩረት ሊደረግበት ይፈልጋል፡፡ ከማውራት ወጥተን ወደ ትክክለኛው ሥራ መግባት አለበን፡፡

ለምሳሌ የወተት፣ የሥጋ፣ የዶሮ ምርቶችን ብንመለከት ምርታችን ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ቴክኖሎጂ አጥተን ነው? አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ አጥተን አይደለም፡፡ ትልቁ ማነቆ ወደ ታች እንዲደርስ የሚያስፈልገው ቻናል መዘርጋት ላይ ትልቅ ችግር ነው ያለው፡፡ የግብዓትና የምርት ግብይቱ ትልቁ ማነቆ ነው፡፡ ይህ የ10 ዓመት ዕቅድ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን አቅዷል የሚለው ነገር ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡

ዕቅዱ በሚዘጋጅበት ወቅት ማምጣት የሚፈለገውን ለውጥ በተጨባጭና ከተናጠል ምርት አኳያ ተለይቶ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ለዚያ የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ፣ ግብዓት ተለይቶ መሠራት አለበት፡፡ ምርጥ ዘር የሚጠቀሙ ገበሬዎች ምን ያህል ናቸው? ከበቆሎና ከስንዴ ውጭ ብንመለከተው ከጠቅላላ አርሶ አደሩ አምስት በመቶ አይሞሉም፡፡ የዘር ችግር ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ እዚህ ላይ በደንብ ሊሠራበት ይገባል፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚሠሩ ሥራዎች ከፖለቲካ ተለይተው መታየት አለባቸው፡፡ ከመሬትና ከጉልበት ወጥተህ ሜካናይዝድ ወደሆነ ግብርና መገባት ካልተቻለ የሚፈለገው ውጤት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡

ለዚህ የሚያስፈልገው ዋና ነገር ፋይናንስ ነው፡፡ ይህ በተወሰነ መልኩ መፍትሔ እያገኘ ነው፡፡ ማሽነሪዎች ላይ የተጣለው ታክስ መነሳቱ በራሱ ለውጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግብርናው በባንኮች አማካይነት ፋይናንስ እንዲደረግ መሆኑም ትልቅ ጅምር ነው፡፡ ይህ ሐሳብ መሬት ወርዶ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን አሠራር መፍጠር ይገባል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...