በሳዑዲ ዓረቢያ በእሥር ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች በሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ ቴሌግራፍ ዩኬ ሲዘግብ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ሁለት ሺሕ ስደተኞችን ለመመለስ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ነሐሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በአምባሳደሮች ዓመታዊ ስብሰባና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ አቋም መያዙን አመልክተዋል፡፡
ከመስከረም 8 እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው አንድ ወር ውስጥ 2000 ስደተኞች ከሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚመለሱ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን፣ ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ 2012 ዓ.ም. 3500 በስቃይ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ ዓረቢያ መመለሳቸውን ገልጿል፡፡
ከግንቦት 2009 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 2012 ዓ.ም ድረስ ከ40 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ 165 ኢትዮጵያውያን ከቤይሩት መመለሳቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነትና መብት ለማስጠበቅ ከሳዑዲ ንጉሥና ከሚመለከታቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዲሁም በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉን አምባሳደር ዲና አስታውሰዋል፡፡