ሰሞኑን የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የተወሰነ ዕርዳታ ማቋረጡን አስታውቋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ ፊርማ የተወሰነ ዕርዳታ እንዲቋረጥ የተወሰነው፣ ኢትዮጵያ በተናጠል ዕርምጃ የህዳሴ ግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት በማከናወኗ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በተለይ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ አስፈጻሚውን ግብፅ በመደገፍ የወሰደው ይህ ይሉኝታ ቢስ ዕርምጃ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈርና በገዛ ሀብቷ የመጠቀም መብቷን የሚጋፋ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ ለዓባይ ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ የሌላትን ግብፅ በመደገፍ፣ ለውኃው 86 በመቶ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ የተቃጣ ጥቃት ነው፡፡ አሜሪካ ኢፍትሐዊ ድርጊቷን ማቆም አለባት፡፡ ከ300 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን የሚኖሩባቸውን የተፋሰሱን አገሮችን መብት ጭምር እስከ ወዲያኛው ለመገደብ አሜሪካ ጣልቃ ስትገባ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም እንዲህ ዓይነቱን ዓይን አውጣ ድርጊት ማጋለጥና ማስቆም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን ግድቧን ከመሙላት ለማስቆም የሚደረገውን አጉል ሙከራ ማምከን ይገባል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ እንዲሁም በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአሜሪካን አሳፋሪ ድርጊት ማውገዝ አለባቸው፡፡ በሉዓላዊነት ቀልድ የለም፡፡
ከዚህ ቀደም በሚገባ ለማስረዳት እንደሞከርነው አሜሪካ ገለልተኛና ፍትሐዊ ሳትሆን ጥቅሟን ብቻ በማስላት የገባችበት አደገኛ ጎዳና፣ አካባቢውን ከማተራመስ የዘለለ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ሚና የለውም፡፡ የአሜሪካ የተሳሳተ ፖሊሲ በመካከለኛው ምሥራቅና በተለያዩ ሥፍራዎች ከቀውስ ውጪ የፈየደው ስለሌለ፣ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች አሁንም ጥንቃቄ ቢያደርጉ ይሻላል፡፡ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብት በመደፍጠጥ፣ ጫና ለመፍጠር የሚደረገው ሩጫ በፍጥነት መገታት አለበት፡፡ ለዓለም ስለእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሐዊነት የምትሰብከው አሜሪካ የምትናገረውን በተግባር ታሳይ፡፡ ቃልና ተግባር የማይገጣጠሙበትን ጥቅም አባራሪነት ይዛ፣ ግብፅን ለመደገፍ የሄደችበት ርቀት ተቀባይነት የለውም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 70 በመቶ ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል አጥተውና በጨለማ ተውጠው፣ የግብፅ ከ30 ሺሕ በላይ ከተሞችና መንደሮች በዓባይ ውኃ በኤሌክትሪክ ደምቀው ያድራሉ፡፡ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ፣ ለዓባይ ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ የሌላት ግብፅ ዜጎች ዓሳ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንደ ልብ ያገኛሉ፡፡ አስዋን ግድብ ላይ በዓመት በትነት ከሚባክነው አሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በተጨማሪ፣ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የሚፈሰው ትርፍ ውኃ ግብፅን አንቀባሮ እንደሚያኖር ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ኢፍትሐዊነት የምትደግፈው አሜሪካ ጥቂት ጥናት ብታደርግ እውነቱን ለማወቅ አይቸግራትም ነበር፡፡ ነገር ግን የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ አስፈጻሚ ቃፊሯን ለመደገፍ ስትል፣ ኢትዮጵያን የሚበድል ነውረኛ ተግባር ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር እንደሆነ በሚገባ መታወቅ አለበት፡፡
የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት በጭፍን የገባበትን ለግብፅ ጠበቃ መሆን በፍጥነት አቁሞ፣ በገለልተኝነት መርህ በመመራት ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ የግብፅን ፍትሐዊ ያልሆነ ከንቱ ጩኸት እያስተጋባ በምንም መመዘኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ውኃውን በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት የመጠቀም ዓላማን እያራመደች፣ ለውኃው አንዳችም አበርክቶ ሳይኖራት ኢትዮጵያዊያን በድህነት እንዲማቅቁ የምትፈልገውን ግብፅ ዓይንን ጨፍኖ መደገፍ አሳፋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የገዛ ሀብቷን በእኩልነት እንጠቀም ብላ እጆቿን ዘርግታ ከጀርባዋ መወጋት አልነበረባትም፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ሰሞኑን ያሳለፈው ዕርዳታ የማቋረጥ ውሳኔም ሆነ፣ ከዚህ በፊት በትሬዠሪ ዲፓርትመንት ኃላፊው የተረቀቀው ኃላፊነት የጎደለው ስምምነት ተቀባይነት የለውም፡፡ የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል እየተካሄደ በነበረው ድርድር ያሳየው ባህሪ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው በማጤን፣ ከቻለ ሦስቱ አገሮች በፍትሐዊና በምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ አማካይነት መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ ያግዝ፡፡ ከዚያ ውጪ ለማስፈራራትም ሆነ ለማስገደድ የሚያደርገው ሙከራ አይሠራም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ፕሮጀክታቸውን ለማንም አሳልፈው አይሰጡም፡፡ በግልጽ እንዲታወቅ የሚፈለገው ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መብቷን ለመጠቀም የማንም ፈቃድ አያስፈልጋትም፡፡ ሉዓላዊነት ለድርድር አይቀርብም፡፡
በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል እስካሁን የተደረጉት ድርድሮች ውጤት አልባ የሆኑት፣ በግብፅ ስግብግነት እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ግብፅ የምትፈልገው የኢትዮጵያን ታላቁን የህዳሴ ግድብ መቆጣጠር ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው በተደረጉት ድርድሮች ሁሉ ግብፅ የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዛ እየቀረበች ውጤት አልባ ማድረጓ ነው፡፡ ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች›› የሚለውን መርህ በመጣስ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ አስፈጻሚነት ተላላኪነቷ የአሜሪካን ድጋፍ ለማግኘት ደባ ፈጽማለች፡፡ አሜሪካ በይሉኝታ ቢስነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ስምምነት ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡ ግብፅን ተከትላ የሄደችው ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ጥቃት በመሸሽ እንኳን ስምምነቱን ለመፈረም፣ ለድርድርም ድርሽ አልልም በማለቷ የግብፅ ሙከራ ቢከሽፍም፣ አሜሪካ ግን ኢትዮጵያን እንደ ታሪካዊ ጠላት በመቁጠር አሳፋሪ ውሳኔ አስተላልፋባታለች፡፡ ግብፅ ማጣፊያው ሲያጥራት ከአንዴም ሁለቴ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ብታመራም፣ በሦስትዮሽ ድርድሩ መሠረት ፍቺው ተባለች እንጂ ድጋፍ አላገኘችም ነበር፡፡ አሜሪካን የተማመነችው ግብፅ የሦስቱን አገሮች ድርድር አደናጋሪ አጀንዳ ይዛ በመቅረብ ዓላማውን ለማሳት ሞክራለች፡፡ የግብፅ ዓላማ ኢትዮጵያ ግድቧን ውኃ መሙላት ስለጀመረች የበላይነቷ ስለሚወሰድ፣ በተቻላት መንገድ ሁሉ በማደናቀፍ አንገት ለማስደፋት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ አንገታቸውን ቀና በማድረግ ስለሆነ የሚታወቁት ግድቡን በታላቅ ወኔ ገንብተው ያጠናቅቃሉ፡፡ በሉዓላዊነት ቀልድ የለም፡፡
ኢትዮጵያ ከድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት የምታደርገው ጥረት በማንም እንደማይደናቀፍ ለማሳየት ልጆቿ በታላቅ ወኔ መረባረብ አለባቸው፡፡ አሜሪካ ለዘመናት በተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ምክንያት በዓለም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሷ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያንም በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በሶማሊያ ወረራ ሲፈጸምባት ራሷን ከጥቃት ለመከላከል የከፈለችበትን የጦር መሣሪያ በመከልከል፣ ሳትወድ በግድ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ጉያ እንድትገባ የጂሚ ካርተር መንግሥት የፈጸመባት በደል አይረሳም፡፡ አሁን ደግሞ የትራምፕ መንግሥት ያለ ምንም ይሉኝታ ያንን የታሪክ ጠባሳ እየደገመው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሥፍራ ይህንን ዓይን ያወጣ ኢፍትሐዊ ድርጊት ከማውገዝ ባለፈ፣ በአንድነት በመቆም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ማንነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰሞኑን የትራምፕ መንግሥት ውሳኔ በማስመልከት ከማንም በፊት ቀድመው አስተያየታቸውን የሰጡትን፣ በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ያሉትን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንከር ያለ የፖለቲካ ጨዋታ መጀመር የታሰበውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል፣ ይልቁንም በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለምርጫ በሚፎካከሩት ትራምፕ ላይ በመነሳት የመመረጥ ዕድላቸውን ሊያበላሹባቸው እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮ-አሜሪካዊያን ቁልፍ በሚባሉት ጆርጂያ፣ ቴክሳስና ቨርጂኒያ ውስጥ ይኖራሉ፤›› ሲሉም ተፅዕኖአቸውን አመላክተዋል፡፡ ‹‹ለብልህ አይመክሩም ለአንበሳ አይመትሩም›› ማለታቸው ስለሆነ ይህም በትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ከግንዛቤ ይያዝ፡፡ በሉዓላዊነት ቀልድ የለምና፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ዲፕሎማቶች፣ የውኃና የጂኦ ፖለቲክስ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎችና እያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ የአገር ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም የሚከበረው በአንድነት በመቆም ብቻ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ አሁን ከአገር ሉዓላዊነት በፊት የሚቀድም ምንም ነገር እንደሌለ በመረዳት፣ ለኢትዮጵያ ደኅንነትና ጥቅም ብቻ ሙሉ ጊዜያቸውን መሰዋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነት ካልወጣች ማንም አያከብራትም፡፡ በዓለም አደባባይ ተደማጭነት የሚገኘው በተባበረ ክንድ ከድህነት በመውጣት ብቻ ነው፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመፍታት፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ መረባረብ የግድ ነው፡፡ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በግብፅ ተንኮል ተደናቀፈ ማለት ለኢትዮጵያዊያን ውርደት ነው፡፡ ግብፅ ውስጣዊ ሰላማችንን የምትነሳን፣ በጎረቤት አገሮች የጦር ሠፈር ለመመሥረት በማቀድ የምታስፈራራንና አሜሪካን ከጎኗ በማሠለፍ ጫና የምትፈጥረው ግድቡ እንዳይጠናቀቅ ለማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንገት በማስደፋት በአካባቢው ብቸኛ ኃይል በመሆን ለማንበርከክ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ እንዲህ ያለውን ውርደት የማንቀበል መሆናችንን ማሳየት የምንችለው፣ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ መልክ አስይዘን ስንተባበር ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በማንም እንደማይገሰስ ለዓለም ማሳየት አለብን!