Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ ብረታ ብረት አምራቾች ከውጭ በሚገባ ያለቀለት ምርት ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

8.5 ሚሊዮን ዶላር የተገዛ ብረት ተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ ጠይቋል

በብረታ ብረትና በኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ አምራቾች ለጥሬ ዕቃ ግዥ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው በባንክ ዕዳና በሌሎችም ወጪዎች ሳቢያ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ መውደቁን የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ገለጸ፡፡

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምንም እንኳ የጥሬ ዕቃ ለማስመጣት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንዲያገኙ ለአገር ውስጥ አምራቾች ዕድሉ ቢሰጣቸውም በተግባር ግን የውጭ ምንዛሪ እየቀረበላቸው ያለው ያለቀላቸው የብረታ ብረት ውጤቶችን በገፍ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በርካታ ፕሮጀክቶች ከአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግዥ መፈጸም የሚችሉበት የማምረት አቅም ቢፈጠርም፣ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ አለመገኘቱን ተገን በማድረግ ከውጭ ያለቀላቸው የብረታ ብረት ውጤቶችን በተለይም አርማታ ብረት ለማስመጣት እንደሚጣደፉ ተገልጿል፡፡

እንደ አቶ ሰሎሞን ማብራሪያ፣ የመንግሥት ተቋማት እርስ በርስ የማይናበቡ፣ አንደኛው የሚተገብርውን ሌላኛው እየጣሰው የአገር ውስጥ አምራቹ ችግር ላይ በመውደቅ ለህልውና ጥያቄ ተዳርጓል፡፡ ‹‹ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የራሱን ዘርፍ ብቻ እያሰበ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ሁሉ አቀፍ በሆነ ዕይታ መመራት ሲገባው፣ አገር ውስጥ ያለው አቅምና የምርት መጠን ሳይታይና ሳይገመገም ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የማዘንበል ችግር አለ፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ በዚህ የተነሳ ‹‹የአገር ውስጥ ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ሊያጠፉ ነው፤›› በማለት አሳሳቢ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ አባባላቸው ዋቢ የሚያደርጉትም በቅርቡ የወጣ የምርት አቅርቦት ጨረታን ነው፡፡ እንደ አቶ ሰሎሞን አባባል የ100 ኪሎ ግራም የብረት ምርት አቅርቦት ጨረታ ወጥቷል፡፡ ከዚህም ያነሰ መጠን የሚፈልጉ ገዥዎች ለአገር ውስጥ አምራቾች ጥሪ ማቅረባቸው፣ ተሳስተው ሳይሆን ሆነ ብለው የአገር ውስጥ አምራቾች ሊያቀርቡ ባለመቻላቸው ‹‹ከውጭ ለማምጣት ተገደናል›› የሚል ሰበብ ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሚሆን ሥጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡  

ከዚሁ ጎን ለጎን ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኖ የታየው በ8.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገዛ የአርማታ ብረት ለስድስት ወራት በወደብ ቆይቶ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ተጨማሪ ወጪ ተደርጎ እንዲገባ መደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የገዛው 15,400 ሜትሪክ ቶን ብረት፣ በጂቡቲ ወደብ ለስድስት ወራት እንዲቆይ በመደረጉ እንዲከፈል በተጠየቀው የጉምሩክ ቀረጥ እንዲሁም በትራንስፖርት ወጪ መናር እንደሆነ ኮርፖሬሽኑ አስታውቆ ነበር፡፡ በመሆኑም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባገኘው የ500 ሚሊዮን ብር ብድር ወደብ ላይ የከረመውን ብረት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማስገባት እንቅስቃሴ ስለመጀመሩም ተዘግቧል፡፡   

እንዲህ ያሉ ችግሮች እየተስፋፉ የመጡት በአገር ውስጥ የተገነባው የአርታማ ብረት የምርት አቅም አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በደረሰበት ወቅት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ የብረታ ብረት ኢንዲስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የዕቅድ፣ የፖሊሲ ጥናትና የኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ዓባይ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ የአገር ውስጥ አምራቾች በዓመት አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት የማምረት አቅም ፈጥረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአርማታ ብረት የአቅርቦት ፍላጎት 3.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በመሆኑ በማምረት አቅምና በፍላጎት መካከል የ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ትርፍ ምርት ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጥሬ ዕቃነት ለልዩ ልዩ የብረት ውጤቶች የሚውለውን ጥሬ ብረት ወይም ስቲል ቢሌት ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር አምራቾችን እያሽመደመዳቸው ይገኛል፡፡ ይህ ቢባልም ከውጭ ያለቀለት አርማታ ብረትና ሌሎችንም ምርቶች የሚያስገቡ አስጨሚዎች ግን አምራቾች ማግኘት ያልቻሉትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘታቸው እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡

የ2012 ዓ.ም. የ11 ወራት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ 775,415 ሜትሪክ ቶን የአርማታ ምርት ከውጭ ገብቷል፡፡ ባንኮችም 334 ሚሊዮን ዶላር ለአስመጪዎች አቅርበዋል፡፡ በአንፃሩ የአገር ውስጥ አምራቾች 186.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ተፈቅዶላቸው 373 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ጥሬ ብረት በጥሬ ዕቃነት አስገብተዋል፡፡ በጥሬ ብረት ረገድ ከአሥር በመቶ በታች፣ በአርማታ ብረት ምርት አኳያ ከሰባት በመቶ በታች ለማምረት የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ መውደቃቸውን እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡ 

በዚህም ባንኮች በተጨባጭ ከውጭ ለሚያስመጡ ነጋዴዎች እያደሉ ነው በማለት የሚወቅሱት አቶ ጥላሁን፣ በ11 ወራት ውስጥ ያለቀላቸው የብረታ ብረትና የኢንጂነሪግ ውጤቶችን ከውጭ ለማስገባት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ሲፈቀድ፣ ለአገር ውስጥ አምራቾች ግን 471 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መፈቀዱን አቶ ጥላሁን በአስረጅነት ያቀርባሉ፡፡

እንዲህ ያለው አካሄድ በኢትዮጵያ ገንዘብ የውጭ አምራቾች እንዲስፋፉ እንደማገዝ እንደሚቆጠር፣ በርካታ ሠራተኞችን ቀጥረውና የኮሮና ቫይረስ ያመጣውን ጫና ተሸክመው ሠራተኞቻቸው ያቆዩት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች፣ ከውጭ በሚመጡ ያለቀላቸው ምርቶች ሳቢያ አደጋ ላይ በመውደቃቸው መንግሥት ዘርፉን በሚገባ ሊመለከተው እንደሚገባ አቶ ሰሎሞንም ሆኑ አቶ ጥላሁን ያሳስባሉ፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለአሥር ዋና ዋና የገቢ ምርቶች ከወጣው 90 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ፣ 53.5 ቢሊዮን ዶላር ለብረታ ብረትና ኢንጂሪንግ ውጤቶች መዋሉን ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ ከዚህም ውስጥ 29.3 ቢሊዮን ዶላሩ ያለቀላቸው የብረታ ብረት ውጤቶችን ለማስገባት እንደዋለ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ያህል ገንዘብ ለምርት ብታውለው ኖሮ የብረት ማዕድን ከውጭ ከማስገባት በአገር ውስጥ ወደ ሚፈለገው ያለቀለት ምርት ለመወጥ የሚቻልበት፣ ከውጭ የሚገባው ምርት የሚቆምበት አቅም ይገነባ እንደነበር ሲገልጹ፣ የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ብቻም ሳይሆኑ በርካታ የኢንጂነሪንግ ሥራዎችን በማሳደግ ማሽነሪዎችና መሰል ምርቶችን የማምረት አቅም ይፈጠር እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ቻይና የዓለምን ገበያ መቆጣጠር የቻለችበት፣ ጃፓን፣ ህንድ፣ እንዲሁም በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ የምትነፃፅረው ቬትናምም በዚሁ መንገድ ውጤታማ መሆኗን አስታውቀው፣ ከአፍሪካ እነ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ያለፉበት ውጤታማ አካሄድ በኢትዮጵያ ቸል መባሉን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች