Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሚያምረንና የሚያምርብንን እየለየን!

ሰላም! ሰላም! ይኼ ጊዜ እንዴት ይሮጣል እባካችሁ? አንድ ብለን የጀመርነው አዲስ ዓመት አሮጌ ሊባል ቀናት ሲቀሩት ፍጥነቱ ይገርማል፡፡ ዕድሜያችን እንደ ዋዛ እየነጎደ ቀን በሌላ ቀን ሲተካና ዓመትም ዑደቱን ጠብቆ ሲጓዝ፣ ከርታታው የሰው ልጅ በትውልድ እየተተካ ወደ የማይቀረው መሄዱ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ ግን ይህንን አባባል አይቀበሉም፡፡ ‹‹ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናውላለን›› ይባል የነበረው መፈክር ፊታውራሪዎች ጊዜ ጎድሎባቸው በሰው ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በምሳሌ እያስታወሱ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር የተፈጥሮ ሕግ የሚባለውን ተወውና የፈጣሪ ትዕዛዝ በሚለው ተካው!›› ይሉኛል፡፡ ሳስበው ተፈጥሮ ራሱ በፈጣሪ ትዕዛዝ እንደሚዘወር እንኳን እኔ ምስኪኑ ደላላ፣ አለን የሚሉት ሳይንቲስቶችም በገደምዳሜ ያምናሉ፡፡ ‹‹አንድ ኃይል አለ›› እያሉ ነዋ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የአባቱን እምነት ያን ያህል ባይጋራም እሱም የፈጣሪ አድራጊ ፈጣሪነት ይገባዋል፡፡ ከረጅሙ የትምህርትና የንባብ ዕውቀቱ የተገለጸለት ዓለም በፈጣሪ ይቅርታ ሥር እንዳለች ነው፡፡ ሰውማ ስንትና ስንት ነገር ላይ ቢራቀቅ ኮሮና የሚባለውን ደቃቅ ቫይረስ ማሸነፍ አቅቶት የደረሰውን መዓት እያየን አይደል፡፡ የአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ቆመን የፈጣሪን ይቅርታና ምሕረት ከመለመን በላይ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስልም፡፡ አለ ካላችሁ ወዲህ በሉ!

በአዲሱ ዓመት ሌላው መታሰብ ያለበት የቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የቤተሰብ ጉዳይ ሲነሳ ደግሞ የአባወራውና የእማወራዋ እኩል ተሳትፎ ይታወሳል፡፡ እንደ ባሻዬ አስተያየት ያለ ሴቶች የሚደረግ የሕይወት ጉዞ እንኳን ለሥጋ ለነፍስም አይረባም። ታዲያ ሁሌም የሚገርመኝ ሴቶች እንዲህ ዓይነቱ ማሰሪያ አንቀጽ ላይ ሚናቸው መጉላቱ ብቻ አይደለም። ከእነሱ ውጪ ሕይወት የሚባለው ነገር አሰልቺ መሆኑን ማን ይክዳል? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ዕድሜ ለውዷ ባለቤቴ ለማንጠግቦሽ ሐሳብ አይገባኝም። አንዳንዱ ግን ትዳርን በሚያህል ትልቅ ቁም ነገር ላይኮንትሮባንድይሠራል ይባላል። ይወሰልታል ለማለት ነው።ትዳር ጣፋጭ ነው እንደ ማርባለበት አፉ ሌላ ይስማል። ‹‹ዓይን ያወጣ ዘመን›› አሉ ባሻዬ፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው! እንደመር እያለ ሲቀናነስ እንደሚውለው ዓይነቱ እኮ ነው፡፡ አይደለም እንዴ? ማንጠግቦሽና የባሻዬ ልጅ የፍቅርን ነገር ካነሱ ሳይተራረቡ አይላቀቁም። ‹‹አይ የሴቶች ነገር?›› ይላታል። ‹‹አይ የወንዶች ነገር?›› ትለዋለች። ‹‹ደግሞ ወንዶች ምን አደረጉ?›› ሲላት፣ ‹‹ሴቶችስ ምን ኃጢያት ተገኘባቸው?›› ትለዋለች። ጎራ ለይተው አንዳቸው የአንዳቸውን ፆታ ገመና ሲዘከዝኩ ይኼ ሁሉ ድርጊት ድራማ ነው? ወይስ በዕውኑ ዓለም የተፈጸመ ነው? እላለሁ፡፡ እናም መሀል እሆንና የሁለቱንም ‹‹ጠቅልለህ ውቃ›› ወግ በትዝብት አዳምጣለሁ። የሆነ ሆኖ ትዳር መስመር ሲይዝና መረጋጋት ሲኖር ልጆች በሥርዓት ያድጋሉ፡፡ ሥርዓት እየጠፋ መሰለኝ አገር የዋልጌዎች መጫወቻ የምትሆነው፡፡ ካጠፋሁ ለመታረም ዝግጁ ነኝ!

ለማንኛውም በዚህ ወከባው ፋታ አልሰጥ ባለበት ጊዜ አንዳንዴ ቆም እያሉ እርስ በርስ መገማገምና ራስንም መገምገም ቢለምድብን ጥሩ ነበር። በተለይ የራስን አካሄድ ከማወቅና ከመገምገም በፊት የሌላው ባይቀድም እንዴት ሸጋ ነበር መሰላችሁ? ባሻዬን፣ ‹‹ዘንድሮ እኮ ሰው መጠቋቆሙን አበዛው፤›› አልኳቸው። ፊታቸው በሐሳብ ጉም መስሎ ቆዩና ‹‹እንደ መፍረድ ምን ቀላል ነገር አለ ብለህ ነው ልጅ አንበርብር? እንግዲያማ መጽሐፉ ይል የነበረው የራስህን ጉድፍ ሳታጠራ የጓደኛህን ማጥራት አይቻልህም ነው። አይ እኛ? አሁንም ራሳችን ግራ እየገባን ሌላውን ግራ ማጋባት መደበኛ ሙያ አደረግነው መሰለኝ?›› አሉኝ በከፍተኛ ሐዘን ተውጠው። እውነታቸውን ነው፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የዴሞክራሲ አንዱ ጥቅም የተለያዩ አመለካከቶችን ወይም አስተያየቶችን ሰምቶ የሚጠቅመውን መውሰድ ነው፡፡ ሌሎችም መደመጥ ስላለባቸው ይህንን ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የዴሞክራሲ ግቡ ነው፤›› ብሎኝ ነበር። ታዲያ ይኼ ራስን ሳይገመግሙና ሳይመዝኑ እንዴት ይሆናል? የእኛ ትልቁና ዋናው በሽታ እኮ ስለራሳችን መስማት የማንፈልጋቸው እውነታዎች ብዙ መሆናቸው ነው። እውነቴን እኮ ነው ለምን ብዬ እዋሻለሁ? እናም በዚህ በደረስንበት ዘመን ዕድሉን ተጠቅመን ቁጭ ብለን የነበረውን ተረት፣ አባባል፣ ወግና ልምድ ስንከልስ ከምንውል አኗኗራችንና ስለራሳችን ያለንን አመለካከት ብንቀይር ምን ይለናል? ‹‹የተለየ አስተያየትና ሐሳብ መስማት የማይወዱ ወገኖቻችን በአንድ ማርሽ ብቻ የትም እንደማይደረስ ብንጠቁማቸው ለአገር ትልቅ ነገር እንዳበረከትን ይቆጠራል፤›› የሚል ምክር የለገሰኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ምክር መስማትን የመሰለ ነገር የለም!

በነገራችን ላይ ሰሞኑን የገዥው ፓርቲ አመራሮች ሥልጠና ላይ መክረማቸውን በቴሌቪዥን ብሰማም፣ ያን ያህል ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር፡፡ ነገር ግን አንዱ ቀዥቃዣ ድንገት ይህንን ጉዳይ ደላሎች ድድ ማስጫ ላይ አንስቶት፣ ‹‹እንዴት ነው በግፍ ተወረው የተያዙትን የሕዝብ መሬቶችና ሕዝብ ላቡን ጠብ አድርጎ ያስገነባቸው ኮንዲሚኒየም ጉዳይ በሥልጠናው ላይ ይነሳል ወይ?›› ብሎ አንዱ ጥያቄ ሲያነሳ፣ ‹‹አንተና መሰሎችህ መስላችሁን በደቦ ተደራጅታችሁ መሬቱን ስትሸነሽኑ የከረማችሁት…›› ሲለው የፌዝ ሳቅ ተስተጋባ፡፡ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ እንዳነሳው ልብ በሉ። በአገራችን የሕዝብ ቀበኛ ሞጭላፊዎችን በጉያው ሸጉጦ ተንከባክቦ የሚኖረው መንግሥታችን፣ እንዲህ ያለውን ውይይት አደረገ ቢባል የሚሊዮኖችን ትኩረት መሳቡ አይቀርም። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለአገሩ ድህነትና ኋላ ቀርነት በቁጭት፣ በንዴት፣ አንዳንዴ ደግሞ በስሜት ይናገር የነበረው መቼም አይረሳኝም፡፡ ‹‹በእኛ በኩል ለኋላ ቀርነታችን መንስዔው ያልተለወጠው አስተሳሰባችን ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል የድህነታችን ዋና ምክንያት ሥራን በአግባቡ ከሚሠራው ይልቅ የሕዝቡን ሀብት የሚዘርፈውን በመሰብሰቡ ነው፤›› ማለቱ አይረሳኝም። ስንቱ ጉዳችን ይረሳል!

መቼ ነው መሰላችሁ? ሰዎች በሰዎች ጉዳይ ምን ጥልቅ አድርጎዋቸው ነው የሚፈተፍቱት ተብሎ ወሬ ይጀመራል፡፡ ይኼ ወግ ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ ያለው፣ አንድ ዶዘር መግዛት የሚፈልግ የዘመኑ ወጣት ኢንቨስተር ቀጥሮኝ ቡና እየቀማመስኩ ካፌ በረንዳ ላይ ስጠብቀው ነው፡፡ አንድ ፀጉሩን እንደ ቦብ ማርሌ ያንጨባረረ ጎረምሳ ጣቱን እየወዘወዘ፣ ‹‹በእኔ የግል ፍላጐት ማን ያገባዋል? የፈለግኩትን ብበላ፣ ብጠጣና ባጨስ የራሴ ጉዳይ ነው…›› እያለ ተንጣጣ፡፡ የመብሉና የመጠጡ ጉዳይ በእርግጥም የራሱ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ምን ይሆን ሊያጨስብን የሚፈልገው? ከአካባቢ ተቆርቋሪዎች እስከ አገር መሪዎች ድረስ ይኼንን በየቦታው የሚጨስ ነገር ምነው ዝም አሉ? አካባቢን ከመበከል አልፎ እኮ ትውልድ እያጠፋ ነው፡፡ ለዚህም ‹አትነሳም ወይ› እንባባል እንዴ!

ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ሲባል ክፉ ነገር ከእናንተ ይራቅ መሆኑን የሚነግሩኝ ባሻዬ ናቸው፡፡ ‹‹አንበርብር ውስጥህ ሰላም ከሌለው ቀልብ አይኖርህም፡፡ ከራስህ ጋር እየተጣላህ ሌላውን ትነጅሳለህ፡፡ ብዙዎቻችን ሰላም ሲርቀን ደም ይሸተናል፡፡ ካገኘነው ጋር ሁሉ ካልተጋደልን እንላለን፡፡ ሰው በውስጡ ሰላም ይኖረው ዘንድ ከፈጣሪው ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ያጠፋውን ሁሉ ተናዞ እንደ አዲስ መወለድ አለበት፡፡ በክፋት አዕምሮአቸው የናወዘ ምን እየሠሩ እንደሆኑ እያየህ ለሰላም መቆም ካልቻልክ የዘራኸውን ታጭዳለህ…›› እያሉ ሲመክሩኝ የክፋት አባዜ የሚወልደው ግብዝነት አረመኔነቱ የት ድረስ እንደሚጓዝ ሳስብ ውስጤ ታወከ፡፡ ወይ ነዶ!

ያዘኑትን ማፅናናት፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ግራ የተጋቡትን መምከር የመሳሰሉ የደግነት መገለጫዎች የሆኑ እሴቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ እኔ ያልሆንኩትን ለምን አትሆንም ብለው ዕልቂት የሚያውጁ፣ ግዞት የሚሰዱና የሚያፈናቅሉትን ሳስብ ለእነሱ ጭምር እንዳዝን መንፈሴ ሲወተውተኝ ነው የከረመው፡፡ የባሻዬ ልጅ በምሁር አዕምሮው ሞርዶኛል መሰል ሰው መሆን ምን ማለት ነው እያልኩ እንደ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ማሰብ ይዳዳኛል፡፡ ሐሳቤን በፈለግኩት መንገድ ለመግለጽ ስሞክር አፍ አፌን እያሉ የሚያስፈራሩኝ አሉ፡፡ ጓደኞቼ ‘እንደተገኘ አወራለሁ ብለህ ቂሊንጦ እንዳታመላልሰን’ ሲሉኝ፣ ንግግሬ ያልተመቸው ዘመናይ ደግሞ፣ ‘ምን ለማለት ፈልገህ ነው?’ ብሎ ያጉረጠርጥብኛል፡፡ በፈሪዎችና በኃይለኞች መካከል ትንሽ ሥፍራ ማጣት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሳስብ የሰላም ዋጋ ክብደት ጐልቶ ይሰማኛል፡፡ ኦ ሰላም ትናፍቂያለሽ!

የባሻዬ ልጅ ጊዜው ራቅ ቢልም በአንድ ወቅት ጥቃት ተፈጽሞባቸው  ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን ወገኖች ለማፅናናት ሄዶ ነበር፡፡ እሱ ያኔ እንደነገረኝ አንድ አፅናኝ የሃይማኖት ሰው ለሐዘንተኞቹም ሆኑ ለአፅናኞች አደረጉት ያለው ንግግር ልቤን ነክቶት ነበር፡፡ ልበ ብርሃን የሆኑ ሰዎች በጠፉበት በዚህ ዘመን አንድ ሰው ሲገኝ ተመሥገን ቢባል አይበዛም፡፡ ‹‹አንበርብር ልቤ ነበር የተነካው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እኚህ ሰው ‘ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው ብዬ ሳስብ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው፡፡ እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፡፡ እንደ እንስሳ፡፡ ታላቁ ሊቅ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡፡ ሰው እግዚአብሔር ሲለየው ፀባዩ እንደ አራዊት፣ አመጋገቡ እንደ እንስሳ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሔር ሆኖ ይቀራል፡፡ በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው፡፡ ጥሪ የማይቀበል፡፡ ‹ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሠራም ጆሮ አለ› ሲሉ ልቤ ከመጠን በላይ ተነካ፤›› ሲለኝ እኔ ራሴ ፈዝዤ ነበር ያደመጥኩት፡፡ በእርግጥም ያፈዛል!

የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ሰውየው ከተማ ፈርሶ እየተገነባ ነው እየተባለ ሲወራ እንደሚሰሙ (ዓይነ ሥውር በመሆናቸው)፣ ነገር ግን ፈርሶ መሠራት ያለበት የሰው አስተሳሰብ ነው ማለታቸውን አከለልኝ፡፡ ‹‹የሰው አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሠራ የተሠራው ከተማ ይፈርሳል፡፡ ጃፓንና ቻይና አገራቸውን ያለሙት መጀመርያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው፡፡ አስተሳሰቡ ያልለማ ሕዝብ ያለማውን ያወድማል… ብለው ሲያክሉበት እንዲህ ዓይነት መካሪ አያሳጣን ብዬ በሆዴ ምሥጋናዬን አዥጐደጐድኩት፤›› ብሎ ሲነግረኝ ሳይታወቀኝ ባርኔጣዬን አንስቼ እጅ ነሳሁ፡፡ ‹ቃለ ሕይወት ያሰማልን› ማለት አሁን አይደለም? ‹‹ሰባኪው በዝርዝር ለህሊና ጠቃሚ በሆኑ ምክሮች የሰዎችን ነፍስ ሲያረሰርሱ፣ ዓይኖቻቸው ከንዋይ ላይ አልነቀል ያሉ ደግሞ ምዕመኑን በቀደዱት ቦይ እንደፈለጉት ይነዱታል…፤› እያለ የባሻዬ ልጅ ተብሰከሰከ፡፡ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ሊቅ ተብዬዎች፣ ምሁራን ነን እያሉ የሚኮፈሱት፣ በየአደባባዩ እዩን እዩን የሚሉት፣ ወዘተ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከማበርከት ይልቅ በየተሰማሩባቸው መስኮች ገንዘብ ላይ መረባረባቸው፣ ለዝና መሯሯጣቸው፣ በሐሰት እየመሰከሩ ወገንን የሚያበጣብጡ ገንነው መታየታቸው ያበሳጨዋል፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ያሳዝነኛል፡፡ ውስጡ ብግን ብሎ ደም ሥሮቹ ሲገታተሩ የክፉዎች ተግባር የፈጠረው ሰላም መንሳት ድቅን እያለብኝ አፅናናዋለሁ፡፡ እስቲ ፅናቱን ይስጠን!

ካፌው በረንዳ ላይ ሆኜ ዶዘር የሚገዛውን ደንበኛዬን ስጠባበቅ ስልኬ አቃጨለ፡፡ አንስቼ ‘ሄሎ’ ከማለቴ፣ ‹‹አንበርብር እያየሁህ ነው… መንገዱን ተሻግረህ ና…›› ሲለኝ የደላላ ዓይኖቼ ከዓይኖቹ ጋር ተጋጠሙ፡፡ ዘመናዊው ‘ራቫ ፎር’ መኪና ውስጥ ስገባ ከሰማይ ቁልቁል የሚወረወረው ንዳድ የፈጠረብኝ ትኩሳት በረደ፡፡ ቅዝቃዜው ከምድር የተገኘ ሳይሆን፣ ከሰማየ ሰማያት የተለቀቀ በረከት መሰለኝ፡፡ በእግሬ አዲስ አበባን እያካለልኩ የምሰበስበውን ሙቀት አጠራቅሜ፣ መብራት ሲጠፋ እንድጠቀምበት የሚያስችለኝ መሣሪያ ቢፈለሰፍ ኖሮ የመጀመርያው ገዥ እኔ የምሆን ይመስለኛል፡፡ ሙቀቱ መተንፈስ እስኪያቅተን ድረስ ሲያንገበግበን ምን የማያሰማን ነገር አለ? ደንበኛዬ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የያዘውን የስልክ ወሬ ካጠናቀቀ በኋላ ሞተሩን ቀስቅሶ ማርሹን ሲያስገባ አልተነጋገርንም ነበር፡፡ በፀጥታ ውስጥ መሆን ምንኛ መታደል ነው፡፡ ‹‹አንበርብር ምነው ብቻህን ታወራለህ?›› አለኝ፡፡ ይህች ዓይነቷ ወሬ አትመቸኝም፡፡ በሐሳብ ውስጥ ሆነን የፊታችን ገጽታ ሲለዋወጥ የሚያነቡን ተንኮለኞች፣ ‘ይኼኔ ይኼ መሠሪ ምን እየጎነጐነ ይሆን?’ እያሉ በሐሜት ይሸረክቱናል፡፡ እኛ ሰባኪ እንዳሉት አንዳንዴ ጆሯችን በካርድ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ ሲሰለቅ የሚውለውን ሐሜት ሁሉ እንሰማ ነበር? የምንፈልገውን ብቻ እየሰማን አውርተን ‘ስዊች ኦፍ’ ነበር የምናደርገው ያሉት ታወሰኝ፡፡ አጅሬውም በሐሳብ መመሰጤን አይቶ ‘ብቻህን ታወራለህ’ ሲለኝ ‘እንዴት?’ ማለት አለብኝ፡፡ አለበለዚያ ምን ስል ሰምተህ ነው ብዬ ነገር ባነሳ የእንጀራ ገመዴ ተበጥሶ ሰላሜን አጥቼ መክረሜ አይደለም፡፡ ደስ ይበለው ብዬ ፈገግ አልኩ፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን ፈገግ እንበል እንጂ፡፡ የሚያምብርን እሱ ነው፡፡ ከሚያምረን የሚያምርብን ይሻለናል፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት