በሔለን ተስፋዬ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎችን ምገባ፣ ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት አስተዳደሩ የጀመረውን እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም እንደደገፉና ለ2013 የትምህርት ዘመን ሊደግፉ የሚችሉትን መጠን በቅርቡ እንደሚያስታውቁ የግል ባንኮች ማኅበር ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ዓለሙ ተናገሩ፡፡
አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም. ለተማሪዎች በሚያስፈልገው የተማሪዎች ምገባ፣ ዩኒፎርም፣ ጫማና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ፣ የግል ባንኮች ዕገዛቸውን እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል፡፡
አስተዳደሩ ለ2013 የትምህርት ዘመን ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚያስፈልገው በጀት 2.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 1.7 ቢሊዮን ብሩ አስተዳደሩ መሸፈኑን አስታውቋል፡፡
እስካሁን 350,000 ቦርሳዎች 20,000 ጫማዎች ቃል የተገባ ሲሆን፣ የግል ባንኮችም ድጋፍ እንዲያደርጉ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጥሪ አድርገዋል፡፡
ድጋፉ የተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ጫማ፣ ማብሰያ ቦታና መመገቢያ አዳራሽ ግንባታ፣ የመምህራን ጋዋንን ጨምሮ ለልዩ ልዩ ትምህርት ነክ ጉዳዮች የሚውል መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
ባንኮች በኢንቨስትመንትና አገርን በመገንባት ያላቸውን ሚና የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ ትውልድ በማነፅ በሚደረገው ኢንቨስትመንትም እንዲሳተፉ ጠቁመዋል፡፡
አቶ አስፋው በበኩላቸው የግል ባንኮች አምና የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ በመቀበል ከደብተር ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ለ2013 የትምህርት ዘመን ባንኮች ከቦርድ አባላት ጋር ተመካክረው በቅርቡ የድጋፉን መጠን ያሳውቃሉ ብለዋል፡፡