የተክለ ሰውነታቸውን አቋም ከመገመት በላይ፣ በተነፃፃሪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ሁለት ኃያላንና የረዥም ርቀት አይደፈሬ አትሌቶች የሚገናኙበትን ውድድር ማን ያሸንፋል? የሚለውን ጥያቄ ማንም እርግጠኛ ሆኖ መልስ መስጠት አልቻለም፡፡
ማን ያሸነፍ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ጠይቆ መልስ ማግኘት በቀላሉ የሚቻል አይደለም፡፡ ቀነኒሳ በቀለ 38ኛ ዓመት ዕድሜው ላይ ሲገኝ፣ ኤሉድ ኪፕቾጌ በሦስት ዓመት አንሶ 35ኛ ዕድሜው ላይ ይገኛል፡፡ ቀነኒሳ እ.ኤ.አ. 2019 የበርሊን ማራቶን 2፡01፡41 ሲያጠናቅቅ የአየር ሁኔታው እምብዛም አመቺ ባለመሆኑ ኪፕቾጌ በ2018 ላይ ከሮጠበት 2፡01፡39 ሰዓት ይልቅ የቀነኒሳ ተመራጭና የተሻለ መሆኑ ይነገራል፡፡
ከወራት በፊት ሊከናወን የነበረውና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመው የለንደን ማራቶን ውድድር የዓለማችን ሁለት ፈርጦች ሊገናኝ ለእሑድ መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ከመሰማቱ በፊት በ40ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ለመሳተፍ ቀነኒሳ በቀለ ከስምንት ወራት ባላነሰ ዝግጅት ማድረጉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ኪፕቾጌ በተመሳሳይ ሁኔታ ለበርካታ ወራት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ሲደመጥ ቆይቷል፡፡
ሁለቱም አትሌቶች የሚያመሳስላቸው ነገር መኖሩ እከሌ ያሸንፋል ብሎ ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ ለዚህም ማሳያነት ሁለቱም አትሌቶች ያከናወኗቸው የማራቶን ውድድሮች ላይ የመጀመሪያው 21 ኪሎ ሜትር ተመሳሳይ በሆነ ሰዓት መሮጥ መቻላቸው ፉክክሩን የበለጠ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ እንደ አትሌቲክስ ኢሊስትሬትድ ጥናት ከሆነ የመጀመሪያውን አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት 15፡24 እንደሮጡት ያሳያል፡፡
የመጀመርያው ግማሽ ማራቶን ርቀት ቀነኒሳ 61፡06 ሲያጋምስ ኪፕቾጌ ደግሞ 61፡05 እንደሚያጋምስ ጥናቱ ያመለክታሉ፡፡ ቀነኒሳ በቀለ 40 ኪሎ ሜትር 1፡55 30 በሆነ ሰዓት ውስጥ ሲያጋምስ፣ ኪፕቾጌ 1፡55፡32 በማጋመስ ርቀቱን በተቀራራቢ ሰዓት እንደሚሮጥ ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡
ኪፕቾጌ እ.ኤ.አ. 2013 የቺካጎ ማራቶን ጨምሮ አራት የበርሊንና ሦስት የለንደን ማራቶንን ጨምሮ ስምንት ማራቶኖችን ድል መጎናጸፍ ችሏል፡፡
ቀነኒሳም በአንፃሩ ሁለተኛ የፈጣን ሰዓት ባለቤት ሲሆን በ5 ሺሕ ሜትር ክብረ ወሰን 12፡37.85 እንዲሁም 10 ሺሕ ሜትር 26፡17.53 በ2004 እና 2005 ድል የተቀዳጀበት ዘመኑ ቀነኒሳን ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው አስችሎታል፡፡
ቀነኒሳ የ11 ጊዜ የዓለም አገር አቋራጭ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትም ነው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በማራቶን አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፣ ኪፕቾጌ የበላይነቱን ለመውሰድ ችሏል፡፡ መስከረም 24 የሚጠበቀው ውድድር የቀድሞውን መንገድ የሚከተል ሳይሆን ይልቁንም ኤሊት አትሌቶችን ብቻ የሚያሳትፍ እንደሆነ አዘጋጁ አካል አስታውቋል፡፡
ሁለቱም አትሌቶች ተመጣጣኝ አቋም ላይ መኖራቸው ባያጠራጥርም የተለመደው የለንደን ጎዳና ለየትኛው አትሌት አመቺ የአየር ንብረት ይሆናል የሚለው የባለሙያዎች ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ኪፕቾጌ ቬይና ላይ ከሁለት ሰዓት በታች (ምንም እንኳን ባይመዘገብም) የገባበት አቋም ለለንደኑ ውድድርም ከፍተኛ ጉጉት እንዲሰጠው አስችሎታል፡፡
ለሁሉም መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በለንደን ጎዳና ላይ የሚከናወነው የማራቶን ውድድር የረዥም ርቀት የምንጊዜም አይበገሬ አትሌት ማን እንደሚሆን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡