Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ በየዓመቱ የሚያወጣውን የቢዝነስ ሥራ ምቹነት ሪፖርት ለጊዜው አቋረጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክ በየዓመቱ ከየአገሮች በሚሰበሰቡ የተለያዩ መለኪያ ያላቸው መረጃዎች ላይ መሠረት በማድረግ የሚያወጣውን የቢዝነስ ሥራ ምቹነት (Doing Business) ሪፖርት ማቋረጡን አስታውቋል፡፡ ባንኩ ይኼንን ውሳኔ ያስተላለፈው ከአሁን ቀደም በተጠቀማቸው መረጃዎች ላይ መዛባት መኖሩን ስለደረሰበት ነው፡፡

በተለይም እ.ኤ.አ. የ2018 እና የ2020 የቢዝነስ ሥራ ምቹነት ሪፖርቶች በ2017 እና በ2019 ሲታተሙ በጥቅም ላይ ውለው በነበሩ መረጃዎች ላይ በርካታ መዛባቶች እንደነበሩ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች (ቅሬታዎች) መቅረባቸውን የጠቀሰው ባንኩ፣ በሪፖርቶቹ የተካተቱት መረጃዎች ላይ የተደረጉ ለውጦች የቢዝነስ ሥራ ምቹነት ሪፖርት ሥነ ዘዴ ጋር የሚሄዱ እንዳልሆነም ገልጿል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን ይፋ ያደረገው የዓለም ባንክ፣ ባለፉት አምስት የባንኩ የቢዝነስ ሥራ ምቹነት ሪፖርቶች ውስጥ በጥቅም ላይ የዋሉ መረጃዎች ላይ የተደረጉ ለውጦችን እመረምራለሁም ብሏል፡፡ በተያያዘም የዓለም ባንክ ግሩፕ ገለልተኛ ኦዲተሮች የመረጃ አሰባሰብና ክለሳ ሒደትን እንደሚመረምሩ ተነግሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 እና በ2019 ይፋ በተደረገው የዓለም ባንክ የቢዝነስ ሥራ ምቹነት ሪፖርቶች ኢትዮጵያ በተከታታይ ከ190 አገሮች 159ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን፣ ከአሁን ቀደም በነበሩ ሪፖርቶች ከፍተኛ 161ኛ ዝቅተኛ ደግሞ 104ኛ ደረጃንን ይዛ ነበር፡፡

የቢዝነስ ሥራ ምቹነት ተብሎ በየዓመቱ የሚወጣው የዓለም ባንክ ሪፖርት አገሮች ያሏቸው አሠራሮች ምን ያህል ለቢዝነስ ምቹ እንደሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር እያነጻጸረ የሚለካ ሲሆን፣ ከቢዝነስ ሥራ ምቹነት በተጨማሪም ለንብረት የሚሰጥ ጥበቃንም ከግምት ያስገባል፡፡

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በዓለም ባንክ የሚወጣውን ሪፖርት ደረጃ ለማሻሻል የተለያዩ ዕርምጃዎችን ስትወስድ የቆየች ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመነ መንግሥት በነበረው ዕቅድ በዚህ መለኪያ ኢትዮጵያን ከ50 ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማስገባት ሪፎርሞች ሲደረጉ ነበር፡፡

ይሁንና ይኼ ዕቅድ ሊደረስበት ከሚቻለው አንፃር ከእውነታ የራቀ ነው በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የተለያዩ ሕጎችን በማሻሻልና የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ኢትዮጵያን ከ100 አገሮች ተርታ ለማሠለፍ እየሠራ እንደሚገኝ በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. አስታውቆ ነበር፡፡ እነዚህ ማሻሻያዎች በንግድ ምዝገባ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድና ቢሮክራሲ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች