Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለሥልጣኑ የሲም ካርድና የታሪፍ ሥርዓት የሚመራባቸው ሦስት ረቂቅ መመርያዎችን አዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሞኖፖል የሚያዝ የገበያ የበላይነት ይቀራል  

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎችን ወደ ገበያው ለማስገባት በሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ኩባንያዎች በውድድር፣ በታሪፍ እንዲሁም በሲም ካርድ አቅርቦት ረገድ ሊከተሏቸው የሚገቡ አሠራሮችን የሚደነግጉ መመርያዎች በማርቀቅ ለባለድርሻ አካላት አሠራጭቷል፡፡

የውድድር መመርያ ቁጥር 10/2020 ተብሎ የወጣው ረቂቅ ድንጋጌ፣ በቴሌኮም መስክ ትልቅ ወይም ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ያላቸውን ጨምሮ እስከ ታችኛው የቴሌኮም አገልግሎት ግብይት ድረስ ባለው ሒደት የሚሳተፉ አካላትን የገበያ ሥርዓት የሚመሩ አንቀጾችን አካቷል፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የገበያ ጥናት ከማካሄድ ባሻገር፣ በኩባንያዎች መካከል ውህደት ቢፈጠር ወይም አንዱ ኩባንያ ሌላውን መጠቅለል በሚያስፈልገው ጊዜ የሚከተላቸውን ሒደቶች እንደሚከታተል በመመርያው ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት በባለሥልጣኑ ፈቃድ ወይም ዕውቅና ያልተሰጠው ውህድነት፣ ሽያጭና ግዥ ተቀባይት አይኖረውም ተብሏል፡፡

የገበያ ውድድር መመርያው ዓላማ በቴሌኮም ገበያው ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ኦፕሬተሮች በተገቢው ገበያ ውስጥ ድርሻውን ይዘው በምን አግባብ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ማዕቀፍ ለማስቀመጥ ያለመ ከመሆኑም ባሻገር፣ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ተገቢውን ሥነ ምግባር የተከተለ አሠራር መከተላቸውን ለማረጋገጥ ብሎም ፀረ ውድድር ከሆኑ ተግባራትና ድርጊቶች እንዲታቀቡ ለመከታተል ጭምር መዘጋጀቱን መመርያው እንዲወጣ ካስፈለገባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ገበያ በሞኖፖል እንዳይያዝ ይቆጣጠራል፡፡ ኩባንያዎቹም በውድድር ላይ የተመሠረተ አገልግሎት የማቅረብ ግዴታን ይጥልባቸዋል፡፡ ይህም እስካሁን በኢትዮ ቴሌኮም ተይዞ የቆየውን የሞኖፖል የገበያ ድርሻ ሙሉ በሙሉ ሊያስቀረው ይችላል ማለት ነው፡፡

ይህ መመርያ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ በሁሉም የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ተፈጻሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደአስፈላጊነቱ ግን ሰፊ ወይም ወሳኝ የገበያ ድርሻና አቅም ላላቸው ኩባንያዎች የተለዩ ድንጋጌዎች ሊወጡ እንደሚችሉ መመርያው አስፍሯል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከፍተኛ ወሳኝ የገበያ ድርሻ የመያዝ ዕድሉ እንደተጠበቀ ሊዘልቅ እንደሚችል የሚያመላክቱ አንቀጾች ተካተዋል፡፡ በሌሎች ኩባንያዎች የሚተዳደሩ መሠረተ ልማቶችንና የቴሌኮም ግብዓቶችን ተጠቅመው አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችም በዚሁ መመርያ መሠረት ይስተናገዳሉ፡፡

ገበያ መር የሆነውን የቴሌኮም አገልግሎት በመምራት ረገድ የባለሥልጣኑ ሚና ተብለው በረቂቅ መመርያው ከቀረቡት ውስጥ፣ አግባብነት ባለው የቴሌኮም ገበያ ውስጥ ለሚሳተፉ አካላት በከፍተኛ ደረጃ እርግጠኝነትን የሚያሰፍኑ ደረጃዎችና አሠራሮችን በማውጣት፣ ወሳኝ የገበያ የበላይነት ያላቸውን ኩባንያዎችም ወይም አካላት የመሰየም፣ ፀረ ወድድር ተግባራት ለመፈጸማቸው ቅሬታ ሲቀርብ የመመርመርና የመወሰን፣ የውህደት ወይም አንዱ ኩባንያ ለሌላ በሚሸጥበት ወቅት ሊኖሩ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን የመገምገምና ውሳኔ የመስጠት ሚናዎችና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡፡ ባለሥልጣኑ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ ብቻም ሳይሆን በምርቶች አጠቃቀምና በገበያ ውስጥ በሚኖራቸው ድርሻና ሚና ላይም ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡

ከገበያ ውድድር ባሻገር ሲም ካርድ ምዝገባን በሚመለከት የወጣው ረቂቅ መመርያ ቁጥር 11/2020፣ ሲም ካርድ ተመዝግቦ አገልግሎት መስጠት ከሚጀምርበት ጀምሮ ፈቃድ የተሰጣቸው ወኪሎች፣ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት፣ የሲም ካርድ አገልግሎት ተመዝጋቢ ወይም ተጠቃሚ በምን አግባብ እንደሚስተናገዱ ብሎም ሲም ካርድ ከአገልግሎት ውጪ ስለሚደረግበት ሥርዓት ይደነግጋል፡፡ ፈቃድ ስለሚሰጥባቸው ሁኔታዎች፣ ግላዊ መረጃዎች ሌሎችም ኦፕሬተሮች ስለሚይዟቸው መረጃዎች የተደነገጉ አንቀጾች ተካተውበታል፡፡  

ባለሥልጣኑ አገር አቀፍ የሲም ካርድ ተመዝጋቢዎች ወይም ሲም ካርድ ገዝተው የሚጠቀሙ ደንበኞችን መረጃ መዝግቦና የመረጃዎቹን ደኅንነት በሚያረጋግጥ አግባብ በራሱ እንደሚይዝ፣ የደንበኞች መረጃዎች የሚከማችበትን ሥርዓት እንደሚያበጅ፣ ከየቴሌኮም ኦፕሬተሮች ወቅታዊ መረጃዎችን እንደሚቀበል በመመርያው ተጠቅሷል፡፡ አለመግባባት ሲፈጠር አለያም ማጣራት የሚያስፈልጋቸው ሁኔታዎች ሲፈጠሩም የኢንስፔክሽን ሥራዎች የሚሠሩትም በባለሥልጣኑ አማካይነት እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡  

ሦስተኛው ረቂቅ መመርያ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው የታሪፍ ሥርዓትን የሚመለከተው ነው፡፡ መመርያ ቁጥር 9/2020 የተሰኘው ድንጋጌ ባለሥልጣኑ የትኛውም ቴሌኮም ኦፕሬተር ያወጣቸውን ታሪፎች ሕጋዊነት፣ ታሪፍ ሲያወጡ ጣልቃ የመግባት፣ እንዲሁም ያወጧቸውን ታሪፎች የመገምገምና አዳዲስ ታሪፍ ማውጣት በሚያስፈልግ ጊዜም ለባለሥልጣኑ ስለሚያሳውቁባቸው አግባቦች አካቷል፡፡ የታሪፍ ተመንን የሚደነግገው መመርያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ላይ፣ መሠረተ ልማት የማጋራት አገልግሎት የሚሰጡና በሌሎች የቴሌኮም ኩባንያዎች ቁሳቁሶች ተጠቅመው አገልግሎት በሚሰጡ ኩባንያዎች ላይ ተፈጻሚ የሚደረግ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ጉልህ ወይም ወሳኝ የገበያ የበላይነት ያላቸው ኩባንያዎች በተለየ አግባብ የሚስተናገዱበት ዕድል እንዳላቸው ይጠቁማል፡፡

በታሪፍ አወጣጥና አተገባበር ላይ ያተኮረው መመርያ እንደሚያትተው፣ የሚወጡ ታሪፎች በሙሉ በግልጽነት ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው፡፡ ለአንድ ጊዜ የሚወጡ ክፍያዎች፣ በተደጋጋሚ የሚከፈሉ ክፍያዎችና የዋጋ ቅናሾች ላይ የሚጣሉ ታሪፎች በግልጽ ሕዝብ እንዲያውቃቸው ይደረጋሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር የሚወጡ ታሪፎች አገልግሎት የሚሰጥበት ወይም ምርት የሚመረትበትን ወጪ መሠረት በማድረግ የሚጣሉ እንዲሆኑ፣ በችርቻሮ አገልግሎት ላይ የሚጣሉ ታሪፎች ላይ የሚቀመጡ ግዴታዎችና መመርያዎች በተመሳሳይ አግባብ በተጠቃሚዎች ላይም ተፈጻሚ የሚደረግ ሲሆን፣ ወሳኝ የገበያ ድርሻ በሚይዙ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ላይ በባለሥልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ታሪፎች እንደሚኖሩ በረቂቅ መመርያው ተካተዋል፡፡ ወሳኝ የገበያ ድርሻ ያላቸው የቴሌኮም ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን የሚሸጡባቸው ታሪፎች በኩባንያዎቹ ድረ ገጾች በግልጽ ለተጠቃሚዎች ይፋ እንዲደረጉ ባለሥልጣኑ ያስገድዳል፡፡

እንዲህ ያሉት ድንጋጌዎችን በሚመለከት በባለሥልጣኑ የተረቀቁት መመርያዎች ሐሳብ እንዲሰጥባቸው በባለሥልጣኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ተቋሙ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መሠረት፣ ከነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በረቂቅ መመርያዎቹ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የማሻሻያ ሐሳቦቻቸውንና አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡባቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች