Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሮና ወረርሽኝ መባባስ የተፈራውን ያህል ባይሆንም በኢኮኖሚው ላይ የተባባሰ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ወረርሽኝ ከዚህ ቀደም ሊያስከትል እንደሚችል የሚተነትኑ አስደንጋጭ አኃዞች ይወጡ ነበር፡፡ ምንም እንኳ የተፈራውን ያህል አደጋ ባይከሰትም የበሽታው ሥርጭት እየተባባሰ መምጣት ግን አሁንም በማኅበራዊና ኢኮኖሚ መስኮች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት አስጊ እንደሚያደርገው ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡

ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ የውይይት መድረክም ይኸው ተነስቷል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ትንታኔ መሠረት፣ የኮሮና ተፅዕኖ እየገፋ እንደሚመጣ አሳይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከወራት በፊት ከሠሩት ትንታኔ አኳያ ይደርሳሉ ተብለው የተፈሩ አደጋዎች ሥጋታቸው ቅናሽ እንዳሳየ አብራርተዋል፡፡

‹‹ጉድ ገቨርናንስ አፍሪካ›› የተሰኘውና በተለያዩ የአኅጉሪቱ አካባቢዎች ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ የሚንቀሳቀሰው ተቋም፣ የምሥራቅ አፍሪካ ጽሕፈት ቤቱ በሆነችው አዲስ አበባ የመልካም አስተዳደርና ተያያዥ ርዕሶችን በማንሳት ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑም ‹‹የኮቪድ-19 ተፅዕኖዎች፣ ምላሾችና የወደፊት የፖሊሲ  ዕርምጃዎች፤›› በሚል ርዕሥ ባካሄደው ውይይት ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት በምን መጠን እንደሚቀንስ፣ በተለይም በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ መስኮች የሚታየው መቀዛቀዝ ምን ያህል እንደሚያሳስብ፣ የክፍያ ሚዛን መዛባት ሊባባስ ስለሚችልበት ሁኔታ፣ ሊታጡ ስለሚችሉ የሥራ ዕድሎችና የገቢ መጠን ቅናሽ እንዲሁም እየተባባሰ ስለሚመጣው የዋጋ ግሽበት፣ በጠቅላላው ማክሮ ኢኮኖሚው ሊያጋጥሙት ስለሚችሉት ሥጋቶች ትንታኔ አቅርበዋል፡፡

መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ይጠበቅ ከነበረው የዘጠኝ በመቶ ዕድገት ወደ ስድስት በመቶ ዝቅ እንደሚል ማስታወቁን ያስታወሱት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ በዚህ ዓመት ይጠበቃል የተባለው ዕድገት ወደ 8.5 በመቶ ከፍ መደረጉ ግን አጠያያቂ ነው ብለዋል፡፡ በእሳቸው ትንታኔ መሠረት፣ በመጪው ዓመት ያውም የበሽታው ሥርጭት ወደ ታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ካልተሸገረ ሊኖር የሚችለው የኢኮኖሚ ዕድገት ከሦስት በመቶ አይበልጥም፡፡

መንግሥት ብቻም ሳይሆን፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎችም ተቋማት ባቀረቧቸው ትንታኔዎች መሠረት፣ በ2012 ዓ.ም. አመዛኙ እንደሚመዘገብ ያስቀመጡትን የስድስት በመቶ ዕድገት ወደ ሦስት በመቶ አለያም ወደ 3.6 በመቶ ዝቅ ያለ ዕድገት እንደሚኖር አስፍረዋል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የእሳቸው ትንታኔና ሙያዊ ግምትም ከእነዚሁ ተቋማት ጋር መሳ ለመሳ እንደሆነ፣ በመጪው ዓመትም ከዚህ ያልዘለለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ይህም ሆኖ የበሽታው ሥርጭት እየከፋ ከሄደና እስከ መጪው ታኅሳስ ከተባባሰ ግን የሚጠበቀው ዕድገት ከዚህም በታች ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ገምተዋል፡፡ ይኸውም የበሽታው ሥርጭት ደገኛ በሚባለው ደረጃ ከሆነ፣ ሊከሰት የሚችለው ቅናሽ ስድስት በመቶ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ሲጠበቅ፣ አስከፊ በሆነ ደረጃ ከተዛመተና ተፅዕኖውም በዚያው ደረጃ ከተባባሰ ግን እስከ 13 በመቶ ቅናሽ ሊመዘገብ እንደሚችል  አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት በመጪው ዓመት የሚመዘገበው ዕድገት 8.5 በመቶ ይሆናል ማለቱ እየታዩ ያሉ ተፅዕኖዎችን ከግምት ውስጥ የማስገባቱ ጉዳይ ግልጽ እንዳልሆነ አብራርተው፣ የኮሮና ወረርሽኝንን ባካተተ መንገድ ኢኮኖሚው የሚያሳየው እንቅስቃሴ የ11.2 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስተናግድ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት የ8.5 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ኢኮኖሚውን በ19.7 በመቶ ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አስቀምጠዋል፡፡ ይህ የማይታሰብ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ አስከፊ የኮሮና ወረርሽኝ መዛመት ቢያጋጥም ግን ኢኮኖሚው ወደ ታች ለማደግ እንደሚገደድ ከዜሮ በታች እስከ 2.5 በመቶ ዝቅ ሊል እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

የኢኮኖሚው ዕድገት መቀዛቀዝ በተለይም በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ያስታወሱት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ በተለይም ከ70 በመቶ ያላነሰውን የከተማ ሥራ ዕድል የፈጠሩት እነዚህ ዘርፎች የሚታየው የዕድገት መቀነስ በሥራ ዕድል መቀነስና በገቢ መታጣት ሊንጸባረቅ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ የሰባት በመቶ ቅናሽ እንደሚያሳይ የሚገመተው የአገልግሎት ዘርፉ፣ በአስከፊ የይሆናል ግምት ከታየ ግን ወደ 13 በመቶ እንደሚያድግ፣ ኢንዱስትሪውም ከዘጠኝ በመቶ እስከ 18 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የወጪ ንግዱም ከስድስት እስከ 13 በመቶ እንደሚቀንስ ትንታኔ ያቀረቡ ሲሆን፣ የገቢ ንግዱም ከስድስት እስከ 112 በመቶ ሊቀንስ ስለሚልባቸው የይሆናል አመክንዮዎች አብራርተዋል፡፡

የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ያልበለጠ ገቢ በሚያስገኝበት ወቅት፣ የ18 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማውጣት ለገቢ ንግድ የሚውለው ሀብት፣ አገሪቱን የ13 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ወጪ እያስከተለባት ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህንን ለማስተካከል ግን የወጪ ንግዱ ሳያቋርጥ በየዓመቱ የ20 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ለስምንት ዓመታት ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅበት አብራርተው፣ ይህ ባልሆነበት ወቅት አገሪቱ ለእህል ሸመታና ለዕዳ ክፍያ የምታውለው ወጪ የክፍያ ሚዛኗን ክፉኛ በማዛባት ሲፈታተናት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ችግር ላይ ኮሮና ሲታከልበት የወጪ ንግዱ እንቅስቃሴ ከ72 በመቶ እስከ 92 በመቶ ሊቀንስ የሚችለበት ሥጋት እንደደቀነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ሊታጡ ስለሚችሉ የሥራ መስኮችም አብራርተዋል፡፡ ምንም እንኳ የዓለም ባንክና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ባካሄዷቸው ጥናቶች ተዘግተው በርካታ የቆዩ ድርጅቶች ዳግም ወደ ሥራ እየተመለሱ ቢሆንም፣ በኮሮና ምክንያት ሁለት ሚሊዮን ሥራዎች ሊታጡ እንደሚችሉ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በየወሩ የ2.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊታጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ከሥራ እንዳያባርሩ አዋጅ በመውጣቱ እንጂ ጥናት ከተካሄባቸው መካከል 23 በመቶ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ለማባረር እንደሚጠባበቁ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የኮሮና ተፅዕኖ እንዲህ በተባባሰበትና ሥጋቶችም በዚህ አግባብ ትንታኔዎች በሚወጡበት ወቅት መንግሥት ለ2013 ዓ.ም. ያፀደው የ476 ቢሊዮን ብር በጀት፣ የካፒታል ወጪ ጭማሪ እንዲሆን ማድረጉ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ አስተዋጽኦ የሚያደርግበት ሥጋት እንዳለ አመላክተዋል፡፡ የ23 በመቶ ጭማሪ ተደርጎበት የፀደቀው በጀት፣ የ143 ቢሊዮን የበጀት ጉድለት ያለበት በመሆኑና የመንግሥት የገቢ ምንጮችም ቅናሽ ባሰዩበትና ወጪው ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ በጨመረበት ወቅት፣ ለካፒታል ወጪ ጭማሪ ማድረጉ ሥጋት አሳድሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበት ወደ 23 በመቶ ማሻቀቡንና የምግብ ዋጋ ግሽበትም ወደ 26 በመቶ መውጣቱን ያስታወሱት አለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የአሥር በመቶ የገንዘብ አቅርቦት ጭማሪና በኢኮኖሚ መዳከም የሚመጣ የአሥር በመቶ የምንዛሪ ተመን ለውጥ፣ የ20 በመቶ የዋጋ ግሽበት በማስከተል ከፍተኛ ኢኮኖሚዊ መናጋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሥጋቶች የመንግሥትን የፖሊሲ ዕርምጃ እንደሚሹ፣ የተጀመሩ የምግብ ማጋራት፣ የኪራይና መሰል ድጋፎችን ተቋማዊ በሆነ መተግበር መተግበር የኮሮና ወረርሽኝን ለመቋቋም እንደሚያግዙ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ወረርሽኝና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተም የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አስናቀ ከፍአለ (ዶ/ር) ጥናታዊ ጽሑፎች በማቅረብ የኮሮና ወረርሽኝ ስላስከተላቸው የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የፖለቲካና መሰል ተፅዕኖዎች አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተቃርኖ ምንጭ በመሆን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ እንዳስነሳ፣ የትግራይ ክልል የተናጠል ምርጫ ለማካሄድ የተሳነበትን ክስተት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡  

የአፍሪካ አገሮችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን የመፍታትና ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት በአኅጉሪቷ በማምጣት መልካም አስተዳደርን በሁለም የአስተዳደዕርከኖችን ማስፈን ወሳኝ ሥራ ነው በሚል ዕምነት የሚንቀሳቀሰው ጉድ ገቨርናንስ አፍሪካ ድርጅት አኅጉራዊ ድርጅት ነው ከኮሮና ተፅዕኖ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያውን የውይይት መድረክ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. አካሂዶ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች