Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም አቀፍ የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓትን መተግበር ላልጀመሩ ተቋማት አራት ዓመታት ተጨመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሒሳብ አያያዝ ሥርዓቱን የሚተገብሩ ድርጅቶች በመሥፈርት ተለይተዋል

መንግሥት የአገሪቱ የሒሳብና የኦዲት ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ስታንዳርድ (ኢንተርናሽናል ፋይናንሺያል ሪፖርቲንግ ስታንድርድ) እንዲመራ በማሰብ፣ ይህንኑ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሪፖርት አደራረግ ሥርዓት እንዲከተሉ የሚያደርግ ሥርዓት መተግበር ጀምሮ ነበር፡፡

ይህንኑ ሥራ የሚመራ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የተሰኘ ተቋም ተመሥርቶም የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ሥርዓቱን ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ እንዳሰበው የአገሪቱ የሒሳብ አያያዝ፣ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ብሎም ኦዲት አሠራር የሚፈለገለው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በ2006 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ የተቋቋመው ቦርድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት ሁሉም የመንግሥት ተቋማት እንደሚተገብሩት ይጠበቅ የነበረው አዲስ የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትም እንደሚፈለገው ባለመተግበሩ ባስቀመጣቸው ግዴታዎች ላይ ማሻሻያዎችን በማስቀመጥ ለማስተግበር ተጨማሪ አራት ዓመታት አስፈልገውታል፡፡

ቦርዱ የአምስት ዓመታት የትግበራ ፕሮግራም በማውጣት በአሁኑ ወቅት ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በዓለም አቀፉ የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት መሠረት ሪፖርት ማድረግ የሚጀምሩብትን ቀነ ገደብ ካስቀመጠ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ዓለም አቀፉን የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ስታንድርድ ተከትለው የሒሳብ መዝገባቸውንም በዚሁ ሥርዓት ቀይረው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የቻሉት የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወይም የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማኅራት ጭምር የሒሳብ አያያዛቸውን ሪፖርት የሚያደርጉበት ሥርዓት ከተረጋጋ ዓመታት ቢቆጠሩም እንደታሰበው የአብዛኞቹ ሒሳብ አቀራረብ አልተለወጠም፡፡

ባለፈው ዓርብ ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ስለዚሁ ጉዳይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ቦርዱን እንዲመሩ በቅርቡ ከተሾሙትና በዘርፉ ከሚታወቁት ከወ/ሮ ሒክመት አብደላ ጋር መግለጫ ሰጥበውበታል፡፡ የታበሰው ውጤት ባለመገኘቱ፣ ይህም የሆነው ሁሉም የመንግሥት ተቋት ሙሉ በሙሉ የዓለም አቀፍ የሒሳብ ሪፖርት ስታንዳርድን ተከትለው ሪፖርት እንዲያደርጉ ማስገደዱ፣ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ፣ በሙያው የሠለጠኑ በርካታ ባለሙያዎች ማስፈለጉና ሌሎችም ታክለውበት ሊፈጸም እንዳልቻለ ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ መሥፈርቶቹ ላይ ማሻሻያዎችን በማካተት ያልተገበሩ ተቋማት እንዲተገብሩ የሚያስችል ማስተካከያ ያደረጉትን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ዓለም አቀፉን የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት መተግበር ያልጀመሩ ተቋማት የሦስት ዓመት ጊዜ እንደተሰጣቸው ወ/ሮ ሒክመት አስታውቀዋል፡፡ በትግበራ ሒደት ላይ ያሉትም በጀመሩበት አግባብ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በዚሁ አግባብ ለቦርዱ ሪፖርትያ ደርጋሉ፡፡ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ተብለው የተደለደሉና ይህንን የሒሳብ ሥርዓት መተግበር የሚጠበቅባቸው ግን ያልጀመሩ ተቋማት የአራት ዓመታት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ለሒሳብ ሥርዓት አመቺነት በዓለም አቀፍ የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስታንዳርድ መሠረት በሁለት መንገድ የተደለደሉ የሪፖርት ዝግጅት ሒደቶች ተብራርተዋል፡፡ አንደኛው ዝርዝር ነጥቦችን ማብራራት የሚጠበቅባቸው ሙሉ በሙሉ የዓለም አቀፍ ይዘቱን ያሟላ የሒሳብ ሪፖርት ማዘጋጀት የሚጠበቅባቸው ተቋማት በአንድ በኩል ተደልድለዋል፡፡ በሌላው ወገን የሒሳብ ሪፖርቱ እንደየአገሮቹ የሚተረጎሙ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት የሚከተሉት የዓለም አቀፍ ሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት በመንግሥት ለትግበራ ዝግጀቱ ተደርጓል፡፡

በዚሁ አግባብ የመንግሥት ጥቅም ያለባቸው ተቋማትና ሌሎች ተቋማት ተብለው የሚጠቀሱ ማለትም ባንኮች፣ መድን ድርጅቶችና የአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ተብለው የተደለደሉትና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት የሚያቀርቡ ተጥሪነታቸውም ለዚሁ ማዕከላዊ ባንክ የሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህን ጨምሮ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ብሎም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመንግሥት ጥቅም ያለባቸው ናቸው፡፡

ሌሎች ከዚህ ውጭ የተደለደሉትም በዓለም አቀፍ የሒሳብ አዘገጃጀትና ሪፖርት ሥርዓት መሠረት ወጪና ገቢያቸውን መመዝገብ የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡

እንደ ቦርዱ ከሆነ ከፍተኛ የመንግሥት ጥቅም እንዳለባቸው የሚታሰቡ ተቋማት አራት ዋና ዋና መመዘኛዎች ተቀምጠውላቸዋል፡፡ ከአራቱ ሁለቱን የሚያሟሉ ከሆነ፣የሒሳብ ሥርዓታቸው ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፉ የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት መሠረት እንዲሆን ይገደዳሉ፡፡ 300 ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ተቋማት ጠቅላላ ሀብታቸው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ያላቸው፣ ያላቸው የብድር ዕዳ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑና ከ200 ሠራተኞች በላይ የሚያስተዳድሩ ተቋማት ከፍተኛ የመንግሥት ጥቅም ያለባቸው ተቋማት ተብለው ተደልድለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሙሉ በሙሉ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዓታቸውና ሪፖርት አቀራረባቸው ዓለም አቀፉን የሒሳብ ስታንዳርድ መተግበር የሚጠበቅባቸውና ትልቅ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው ተብለው ይመድበዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በርካታ ዝርዝር የሒሳብ አያያዝ ሥርዓታቸውን በግልጽ ማሳየት የሚያስችል ሪፖርት መከተል የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡

የሕዝብ ጥቅም የሚያሰኛቸውም እነዚህ ተቋማት፣ ይህን ያህል ሀብት እያንቀሳቀሱ በሚሠሩት አጋጣሚ ኪሳራ ላይ ቢወድቁ  የሚያስከትሉት ጉዳት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡ እንደ ወ/ሮ ሒክመት ከሆነ፣በሌላው ዓለም የሕዝብ ጥቅም ያለባቸውና በካፒታል ገበያው በሕዝብ ባለቤትነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ሙሉ በሙሉ የሒሳብ ሪፖርቶቻቸው በዓለም አቀፉ የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን ይገደዳሉ፡፡ በኢትዮጵያም የካፒታል ገበያ ሊጀመር በመሆኑ እንዲህ ያሉ የግል ተቋማትም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ የዓለም አቀፉን የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዓት የመከተል ሥርዓት እንዲያበጁ ይመከራሉ ብለዋል፡፡ በውጭው ዓለም በኒውዮርክ ወይም በለንደን ስቶክ ገበያ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ፣ በኢትዮጵያ ተዛማጅ ወይም እህት ኩባንያዎች ያሏቸው ተቋማትም ይህንኑ የሒሳብ ሪፖርት ማድረጊያ ሥርዓት እንዲተገብሩ እንደሚገደዱ ወ/ሮ ሒክመት አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ የሚባሉ ተቋማት ትርጓሜና በምን አግባብ እንደሚታዩ አልተቀመጠም ያሉት ወ/ሮ ሒክመት፣ ይሁን እንጂ ቦርዱ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት በማለት የዓለም አቀፉን የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት እንዲተገብሩ የሚገደዱት በአራት መመዘኛዎችን ሲያሟሉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ ከሆነ፣ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ያላቸው ከሆኑ፣ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ብድርና ዕዳ ያለባቸው ከሆኑና ከ20 በላይ ቋሚ ሠራተኛ የሚያስተዳድሩ ሆነው ሲገኙ ለአነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች ተብሎ በተፈረጀው የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ሥርዓት መሠረት የፋይናንስ ሥርዓታቸውን ያስተዳድራሉ፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች ስለተባሉ የሚጠየቁት የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ስታንድርድ ዝቅ እንደማይል ይልቁንም ያላቸውን ሀብትና አቅም መሠረት ባደረገ መሠረት እንደሚያሟሉ የሚጠየቁት ዝርዝር መሥፈርት ላይ ብቻ ለውጥ ተደርጓል በማለት ወ/ሮ ሒክመት አብራርተዋል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወይም የበጎ አድራጎትና የሰቪክ ማኅበራት የሚያዘጋጇቸው የሒሳብ ሪፖርቶችም ይህንኑ ዓለም አቀፍ የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት ይተገብራሉ ተብሏል፡፡

ሌላው የተነሳው ነጥብ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አባላት ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ዓለም አቀፍ የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓትን እንዲከተሉ የሚገደድበት አሠራር በማሻሻያው መሠረት እንደ አቅማቸው የሚስተናገዱበት ማሻሻያ መደረጉ ነው፡፡ አነስተኛ የገንዘብ መጠንና የሀብት አቅም ያላቸው በተቀመጠላቸው ደረጃ መሠረት ይስተናገዳሉ ተብሏል፡፡

ወ/ሮ ሒክመት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ማኅበር የተሰኘው ተቋም ኃላፊ በመሆን ለዓመታት ካገለገሉ በኋላ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ኃላፊ ሆነው እስከ ተሾሙበት ጊዜ ድረስ ‹‹አክሰስ ቱ ትሬድ›› የተሰኘ የግል ተቋም በመመሥረት ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ ቦርዱን ቀደም ብለው ከማቋቋም ጀምሮ ለሒሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የፈቃድና ምዝገባ ማረጋገጫ በመስጠት፣ ፈቃዳቸውን ያላሳደሱትንና የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ያልወሰዱትን እስከማገድ የሚደርስ የኃላፊነት ያለውን ቦርድ ሲመሩ የቆዩት አቶ ጋሼ የማነ የተባሉ ኃላፊ ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች