Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሰው ኃይልና በመዋቅራዊ ችግሮች ፈተና እንደገጠመው አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ትኩረት የሚሻ አሳሳቢ የኬሚካል ክምችት አለ ተብሏል  

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተቋቁሞ በግዥና የማይፈለጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ንብረቶችን በሽያጭ ማስወግድ በኦፕሬሽን ሥራዎች የሚሳተፍ መንግሥታዊ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት፣ በመዋቅራዊ ችግሮች በተለይም በሠራተኞች ደመወዝ ዝቅተኛነት የሚፈልሱ መብዛታቸው አሳሳቢ እንደሆነበት አስታውቋል፡፡

ተቋሙ ከተመሠረተ ከአሥር ዓመታት በላይ በቆየበት የሥራ ዘርፍ፣ ከፍተኛና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቁ የዕቃና የአገልግሎት ግዥዎችን በአግባቡ ለማስፈጸም በሚያከናውናቸው ሥራዎች ላይ የመንግሥት አካላት ትኩረት እንዳልሰጡት ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ከ70 በላይ በግዥና በንብረት ጉዳዮች ላይ ዕውቀቱ ያላቸው ሠራተኞች ያስፈልጉታል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ኃላፊዎችን ጨምሮ 23 ባለሙያዎችን በመያዝ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በተቋሙ የሥራ ድርሻ ካላቸው ዳይሬክቶሬቶች ውስጥ የውል አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ለምሳሌ ባሉት ዘጠኝ ሠራተኞች ብቻ ከ110 ያላነሱ የግዥ ውሎችን ለማስተዳደር ተገዷል፡፡ እያንዳንዱ ባለሙያ የውል አስተዳደር ዳይሬክተሩን ጨምሮ ከ12 በላይ ውሎችን በነፍስወከፍ ማስተዳደር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግዥ ዳይሬክቶሬቱም በተመሳሳይ ሰፊ የሰው ኃይል እጥረት አለበት፡፡ በአብዛኛው ከሚያስፈልጉት 70 ያህል ሠራተኞች ውስጥ ብዙኃኑ በግዥ ዘርፍ መመደብ የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡  

እንዲህ ያሉ ችግሮች ያሉበት ይህ ተቋም፣ በሠራተኞች የደመወዝ ዕርከን ማሻሻያም ላይ ትኩረት እንዳልተሰጠው፣ ለውጦች ሲደረጉ እንኳ የሚታለፍበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ይነገራል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ለእስራት ተዳርገው ሲንገላቱ የቆዩበትና በነፃ የተለቀቁበት ሁኔታ ሌላው ሠራተኛ ላይ ጫና በማሳደር ከሥራ ለመልቀቅ እንዲነሳሱ ጫና ማሳደሩን የተቋሙ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ የሚገኙት ወ/ሮ ፅዋዬ ሙሉነህና የሥራ ባልደረቦቻቸው እንደሚገልጹት፣ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የመንግሥት ተቋማት ለግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ትኩረት እንደማይሰጡ ይገልጻሉ፡፡ በተቋሙ ከ150 በላይ የፌዴራል ተቋማትና 45 ዩኒቨርሲቲዎች የማዕቀፍና የስትራቴጂ ግዥ በሚባሉ አሠራሮች አማካይነት አስፈላጊ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ይቀርብላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ያህል ሰፊና ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም በሚያስፈልገው ልክና ስፋት ተቋማዊ ቁመና አለመያዙ ሠራተኞች ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

መሥሪያ ቤቱ ‹‹መለማመጃ፣ አሠልጥኖ ሸኚ›› እየሆነ መምጣቱን የሚገልጹት ኃላፊዎቹ፣ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ለተቋሙ የተሰጡ ኃላፊነቶችና የሥራ ድርሻዎችን በአግባቡ ካለመገንዘብ ጭምር ጫና እንደሚያሳድሩበት ይጠቅሳሉ፡፡ ለአብነትም በንብረት ማስወገድ መስክ ተቋሙ የተሰጠው ኃላፊነት በሽያጭ እንዲያስወግድ ሲጠየቅ ብቻ እንደሆነ የዋጋ ግመታና ንብረት ማስወገድ ዳይሬክተር አቶ ሹንቃ አዱኛ ይህንኑ ያስረዳሉ፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜም ይህንኑ ያጠናቅራሉ፡፡ ግዥ ሲጠየቅ ይፈጽማል፡፡ ንብረት በሽያጭ እንዲያስወገድ ሲጠየቅ ይህንኑ ያከናውናል፡፡ ድጋፍ ሲጠየቅም ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ድጋፍ በመስጠት ይሳተፋል፡፡

ይሁን እንጂ ግዥ ጥያቄ አቅርበው ያልተፈጸመላቸው ተቋማት ስሞታ እንደሚያቀርቡ፣ ንብረት ይወገድልን የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበው ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር ጉዳይ ሲጠየቁ ምላሽ የማይሰጡ በርካታ ተቋማት በተቋሙ ችግር ምክንያት ግዥ እንዳልተፈጸመላቸውና ንብረት እንዳልተወገደላቸው እንደሚገልጹ ኃላፊዎቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ሹንቃ በዋቢነት ያነሱት የተቋሙ መሠረታዊ የንብረት ማስገወድ ችግር ከተሽከርካሪ አወጋገድ መረጃዎች ዕጦት ጋር የሚያያዘውን ችግር ነው፡፡ ተሽከርካሪ እንዲወገድላቸው የጠየቁ መሥሪያ ቤቶች ለሚወገድላቸው ተሽከርካሪ አስፈላጊውን መረጃ፣ የንብረቱ ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ ሰነድ፣ ሊብሬና ሌሎችም መረጃዎች ሲጠየቁ እንደማይሰጡ፣ በዚህ ምክንያት ንብረቱን በሽያጭ ማስተላለፍ አስቸጋሪ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የተከማቹ ኬሚካሎች አወጋገድ ችግር ነው፡፡ በአገሪቱ የተከማቹ ኬሚካሎች በብዛት እንደሚገኙና ጉዳት የማድረስ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ ቢታወቅም፣ አሁንም እነዚህን ኬሚካሎች እንዲያስወግድ ተቋሙን በመጠየቅ እንዲወገድላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኬሚካል በሽያጭ አይወገድም፣ ተቋሙም ይህንን የሚያደርግበት ኃላፊነት አልተሰጠውም ያሉት አቶ ሹንቃ፣ ይልቁንም ኬሚካሉን በክፍያ የማስገድ ሥራ እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡ ተቋሙ በተፅዕኖ የኬሚካል ማስወገድ ሥራ እንዲሠራ መገደዱን ይህንንም ለመወጣት ጥናት ማስጠናቱን አስታውቀው፣ መወገድ የሚያስፈልገው ከፍተኛ የኬሚካል ክምችት እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

ኬሚካል ለማስወገድ በጀት ይጠይቃል ያሉት ኃላፊው፣ ኬሚካል የሚያስመጡ ተቋማት እንዴት እንደሚጠቀሙበት ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚያስወግዱትም ማሰብ ይጠበቅባቸው እንደነበር አቶ ሹንቃ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የአካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥና የደን ኮሚሽን የኬሚካል ጉዳይ ላይ ኃላፊነት ተሰጥቶት አዲስ ሕግ እያዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ከአሁን በኋላም ኮሚሽኑ ሳያውቀው ምንም ዓይነት ኬሚካል እንዳይገባ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ኃላፊነት ሊሰጠው እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል፡፡  

በየዓመቱ የቢሊዮኖች ገንዘብ ዋጋ ያላቸውን ግዥዎች በመፈጸም ላይ የሚገኘው ይህ ተቋም፣ በተለይም በስንዴ ግዥ ላይ በሰፊው ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ሦስት ጊዜ ግዥ መፈጸሙ ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና በርካታ የግዥ ጨረታዎችን ለመሰረዝ እንደተገደደ ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ፅዋዬ ገልጸዋል፡፡ ይህ እየሆነ ያለውም የዕቃና የአገልግሎት የገበያ ዋጋ ጥናት በማጥናት ለተቋሙ ማቅረብ የሚጠበቅበት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ኃላፊነት ሲሆን፣ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይህንን መረጃ በወቅቱ ለአገልግሎቱ ስለማይሰጠው በገበያ ዋጋ መረጃ ዕጦት ምክንያት ጨረታዎችን ለመሰረዝ እንደሚገደድ ገልጸዋል፡፡

 በተቆጣጣሪው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ኦዲት የሚደረገው አገልግሎቱ፣ በኤጀንሲው ቦርድ በሚወሰኑ ውሳኔዎችም ጨረታዎች ተሰርዘው በድጋሚ እንዲወጣ እንደሚደረግ ይህም የግዥ ሒደቱን እንደሚያጓትተው፣ ከዚህ ይልቅ በቀላሉ መስተካከል የሚችሉ የጨረታ ሒደቶች ላይ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ማድረግ የሚቻልባቸው መንገዶች ብዙም እንደማይተገበሩ ይገለጻል፡፡

ይልቁንም የጨረታ መስፈርቶችን ሳያሟሉ ቀርተው፣ በተለይም ከሰሞኑ ይታይ እንደነበረው በስንዴ የጥራት መስፈርት ላይ የተቀመጠውን ደረጃ ሳያሟሉ ነገር ግን ዝቅተኛ ዋጋ ሰጥተናል በሚሉ ተጫራቾች የቀረቡ ቅሬታዎች በሥራው ላይ ለሚታዩ ጫናዎች ማሳያ ተደርገዋል፡፡ ለ2012 ዓ.ም. ከ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴ ግዥ መፈጸሙ የሚጠቀሰው ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ በንብረት ማስወገድ ረገድም ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶችን አስወግዷል፡፡ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ከተሽከርካሪዎች ሽያጭ ሲያስገኝ፣ ከ8.7 ሚሊዮን ያላነሰው ገቢ ከተለያዩ ንብረቶች አወጋገድ የተገኘ ገቢ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች