Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዘመኑና ዘመነኞች!

እነሆ ውርጩ እየተጋረፈም ቢሆን ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ መንገድ ልንጀምር ነው፡፡ ታሪክን በተንተራሰ የህልውና መስመር፣ ትናንትና ነገ በትውስታ በሚደጋገፉበት ጎዳና ላይ ልንጓዝ ነው። ሥጋ ለባሽ ፍጡር ይይዝ ይጨብጠውን አጥቶ ይራወጣል። የእንጀራ ነገር! ሰማዩ ላይ ጠቁሮ የተቋጠረው ደመና የያዘውን ሊዘረግፈው ለቀብር እንደ ተጠራራ ዕድርተኛ በአንድ ሥፍራ ተሰብስቧል። በዕኩለ ቀን መጣሁ ሄድኩ በሚለው የነሐሴ አጋማሽ ማለቂያ ዶፍ ከመውረዱ በፊት፣ እንጀራ ፈላጊ ነፍሶች ጎዳናው ላይ እንደ ጉንዳን እየተርመሰመሱ ይጣደፋሉ፡፡ ‹‹ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናውላለን›› የሚለውን የኮሙዩኒስቶች መፈክር ዛሬም እንደ ንቅሳት አልለቅ ያላቸው ቢኖሩም፣ የፈጣሪን ትዕዛዝ አክብረው በፀጋው ውስጥ የሚመላለሱ ግን ቅዝቃዜውንም ሆነ ዶፉን እንዳመጣጡ ለማስተናገድ በመረጡት ጎዳና ይራመዳሉ፡፡ በነሐሴ አጋማሽ ወደ አዲሱ ዓመት የሚደረገውን ግስጋሴ ለማሳለጥ ሕይወት በተሰመረላት መስመር ላይ ትገኛለች፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰባሰቡ ስድስት ነፍሶች ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ገብተው የጉዞውን መጀመር እየጠበቁ ነው፡፡ ጥበቃ ሁሉም ቦታ መሆኑ አዲስ አይደለምና!

ሾፌርና ወያላ ገብተው ጉዞ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡ ጎዳናው በካፊያ መርጠብ ጀምሯል። የበቆሎ እሸት ጥብስ ይዞ የተሳፈረ ብቻውን መኖርና መብላት ያለመደበት አንድ ጎልማሳ፣  ‹‹እንብላ…›› እያለ ሊያስፈለፍል ይጋብዛል። ‹‹ወዳጄ እናመሠግናለን! በዘመነ ኮሮና ግን አታስበው…›› ሲለው አንድ ወጣት፣ ‹‹ለብቻ ተሠርቶ ለብቻ መክበር የኑሮ ዘዬ በሆነበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለው ደግ መገኘቱ መልካም ቢሆንም፣ ጊዜው አብሮ ለመብላት ጥሩ አይደለምና ወጣቱ ያለው ትክክል ነው…›› እያለ ሌላው ያክላል ‹‹ደግ መቼ ይበረክታል?›› እያለ አንዱ ከፊቱ ከተቀመጠ ሰው ጋር ወሬ ይጠርቃል። ‹‹ተወኝ እስኪ!›› ይላል የወዲያኛው። ወያላው ክርኗ ተቀዳ የተጣፈች ሹራቡን እየደረበ፣ ‹‹የሚለብሰው የሌለው የሚከናነበውን እየሸመተ ባለባት አገር፣ እኔ ሳልቫጅ መቀየር ያቅተኝ? ወይኔ የሰውዬው ልጅ!›› እያለ ብሶቱን ለሾፌሩ ያካፍላል። ‹‹ሰው አይንሳህ አቦ! ልብስ ቢደረብ ያለ ሰው መቼ ይሞቃል?›› ይለዋል ሾፌራችን። ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹ተወኝ እባክህ! ዘንድሮ የሰውን ነገር ተከድኖ ይብሰል…›› ብሎ ይመልስለታል፡፡ የታክሲ ነገር ሲጀመር ቀስ እያለ ነው!

ጋቢና የተሰየመ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹እውነቱን ነው! የዘመኑን ሰው እኮ ገንዘብ ይዞት ጠፋ…›› እያለ የገዛ ሕይወቱን ውጣ ውረድ ሳይጠይቀው ለሾፌሩ ይነግረዋል። ሾፌሩ ራሱን እየነቀነቀ አንዴ መንገዱን አንዴ የተራኪውን ዓይኖች እያየ ይዘውራል።ደግ አይበረክትምባዩ ጎልማሳ ወዳጁን ዘወር ብሎ፣ ‹‹ኧረ ለመሆኑ ማነው ስሙ ደህና ነው?›› ሲል የተረሳ ወዳጁን ያነሳል። ‹‹ምን ይሆናል እሱ? ፖለቲከኛ ሆኖ ፀባዩ ከተለወጠ እኮ ቆየ፡፡ አሁንም የሚያገኙት ሁሉ ሲነግሩኝ የሚናገረው ራሱ አይገባም አሉ፡፡ ሁልጊዜም ብሔሬ፣ ማንነቴ፣ ባህሌ… እያለ እንደ ሰው ቆጥሮ ማነጋገር ትቶናል ሲሉ ነበር…›› የሚል መልስ ያደርሰዋል። ‹‹ወይ ድፍረት? እንኳንም ኢየሱስ ክርስቶስ 21ኛው ክፍለ ዘመን አልመጣ…›› ይላል።እንዴት?” ይጠይቀዋል ግርምት በተቀላቀለበት የድምፅ ቃና። ‹‹እህ ያኔ አንድ ሰው ነው አሳልፎ የሰጠው። አሁን ቢሆን ኖሮ አሥራ ሁለቱም አሳልፈው አይሰጡትም ብለህ ነው?›› ይላል ያኛው። ገጻችን በፈገግታ ተሳስቦ ቢወጠርም ውስጣችን በጭንቀት ተንጧል። ስለሰብዓዊ ፍጡር ዋጋ የለሽነትና ከንቱ የኑሮ ልማድ እንዲህ በአደባባይ ዕውቅና እየሰጡ እንደ መጨዋወት ምን የሚያም ነገር ይኖራል? ምንም!

‹‹ማን ስለሆነ? ምኑ ይሰረቃል ደግሞ እሱ? ቢል ጌትስ ወይስ ዋረን ቡፌት ነው?›› ድንገት የአንዲት ወጣት ድምፅ በጥያቄ አስገመገመ። ‹‹ኧረ ዝም በይውማ እሠራለታለሁ…›› ትላለች አብራት የተሳፈረች ወዳጇ። ‹‹እንዴ ሌላው ፍጡር በቃ ምንም የለውም? እንዲህ የዓለማችንን ታላላቅ ቱጃሮች እየጠራችሁ በሞራላችን የምትረማመዱት?›› አላት ወጣት ተንጠራርቶ። ሴቶቹ ፊትና ኋላ ሆነው እርስ በርሳቸው ተያይተው ሲያበቁ፣ ‹‹ሌላው ማለትም የእኛውማ ጉራ ወይም ባዶ ቦርሳ ነው ያለው…›› አለችው አንደኛዋ። ታክሲያችን በሆታ ሳቅ ተናጋች። ‹‹አንቺ? ያውም ወጣት ሚሊየነሮች በበዙበት ዘመን እንዲህ ይባላል?›› አላት ወጣቱ መልሶ። ‹‹ሀብታቸው በዓለም እንዳያሳውቃቸው አመጣጡ አይታወቅም እባክህ።ፓስወርዱየማይታወቅ ሀብት አይሠራ…›› አለች ደግሞ ሌላኛዋ። ‹‹ወይ ታክሲ ስንቱን ያሰማናል?›› ትላለች ጠና ያለች ወይዘሮ ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹ሲያዩሽ የኑሮፓስወርድየገባሽ ይመስላል። ለመሆኑ ይህ ያንቺ የሚስጥር ቁጥር በሙስናና በሽብር የሚያስጠረጥር ነው ወይስ ሰላማዊ ነው?›› አንድ አንድ መባባሉ ሩቅ የሚያስኬደው የመሰለው ወጣት ጥያቄውን አላቆመም። ‹‹ሌላውንም ነገር እንዳለ ከመሰልቀጥ እንዲህ ቢጠይቅ ይሻለው ነበር፡፡ መጠየቅና መጎትጎት አናውቅበት ብለን የሰጡንን ሳናላምጥ እንውጣለን፡፡ ከዚያም በሐሜትና በአሉባልታ፣ ባስ ሲልም በእሳት አገር እንለበልባለን…›› ይላል አንድ ዝምተኛ ለራሱ፡፡ የሰማው ስለሌለ መልስ የሰጠው የለም፡፡ ለነገሩ እሱ ብቻ ሳይሆን ብዝኃንስ ማን አዳማጭ አላቸው!

ሴቶቹ ቆንጅዬዎች ናቸው። ዘመኑ በቆንጆዎች የተወረሰ ነው የሚመስለው እኮ፡፡ ‹‹አንተፋራ› ነህ መሰል? በዲጂታል ዘመን ተወልደህ ያደግክ መስሎኝ? የግለሰብፓስወርድይጠየቃል እንዴ?›› ስትለው አንደኛዋ፣ ‹‹ምን ችግር አለው? ኃያላን መንግሥታትና የመረጃ ቀበኞች ሳያንኳኩ ሰብረው ይገቡ የለ። እንዲያውም እኔ በፀባይ ነውጠየቅኩሽ…›› አላት። ወጣቶቹ መድረኩን እንደ ተቆጣጠሩት ዘለቁ። ልጁ ያሻውን የኑሮ ሚስጥር ቁጥር ግን እንዳሰበው አላገኘውም። ‹‹ለአንዱ የቀናው መንገድ ለሌላው ይቀና መሰለው እንዴ ይኼ? አቦ ተፋታቸው…›› መጨረሻ ወንበር ከአንዲት ወይዘሮ ጋር የተቀመጠ ጎረምሳ ነው። ከቆንጆዎቹ ጋር ወግ የያዘው ወጣት የሰማው አይመስልም። ቢሰማውም የያዘውን የተፋፋመ ወሬ አሳልፎ መስጠት የፈለገ አይመስልም፡፡ እውነቱን ነው፡፡ የዘንድሮ ሰው በማያገባው ዘው እያለ በሰው ቁስል እንጨት ሲሰድ፣ በሰው ገበታ ጣቶቹን ሲያሾል፣ የሰው ድስት እያማሰለ ሲያሳርር የምን ዕድል መስጠት ነው ያሰኛል፡፡ ፖለቲካው የማንም መጫወቻ የሆነው መንገደኛው ሁሉ ሰተት ብሎ አይገባ አይደል!

ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት ስልካቸው ደጋግሞ ሲጮህ አነሱት፡፡ ‹‹አንተ ለመሆኑ በጤናህ ነው?›› ብለው ላነሱት ጥያቄ ምላሹን ከሰሙ በኋላ፣ ‹‹ተው! ተው! ሲፈታተንህ ነው…›› ሲሉ የሁላችንም ጆሮ ነቃ አለ፡፡ የምን መፈታተን ይሆን? አዛውንቱ ቀጠሉ፡፡ ‹‹ይኸውልህ እኔ አንተን አልመክርም፣ ነገር ግን ማሳሰቢያ ነው የምሰጥህ…›› ማለት ሲጀምሩ ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ወደ እሳቸው ሲያንጋጥጡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ቀርበው በአገር ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ የሚሰጡ ይመስል ነበር፡፡ ‹‹ስማ ኢትዮጵያን እኮ ከአንተና ከቢጤዎችህ በላይ አውቃታለሁ…›› ሲሉማ ሾፌሩ ሳይቀር የታክሲዋን ፍጥነት ቀነሰ፡፡ ‹‹እኔ አገሬን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በክብር አገልግዬ ጡረታ ላይ ብሆንም፣ የከፋው ከመጣ ግን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል የማላንገራግር መሆኑን እንድታውቅ እፈልጋለሁ…›› ሲሉ ዓይናችንን ፈጠጠ፡፡ ‹‹ሰማህ ማን ፈትቶ እንደ ለቀቃቸው ከማይታወቁ ጋጠወጦችና ሥርዓተ አልበኞች ጋር ገጥመህ ምን እንደምትሠራ የማላውቅ እንዳይመስልህ…›› ሲሉማ የታክሲዋ ፀጥታ የእሳቸውን ድምፅ ከሞንታርቦ የሚያወጣው አስመስሎታል፡፡ ድምፃችን ታፍኖ እንጂ እኛስ መቼ ሰነፍን ያሰኛል አነጋገራቸው!

‹‹ይኸውልህ ማሳሰቢያዬን ስማ፡፡ ካልመሰለህም እንደ ማስጠንቀቂያ መቁጠር ትችላለህ…›› ያሉት አዛውንቱ በዚያ ጎርናና ድምፃቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ አገሬ የተለወድኩባት፣ የተማርኩባት፣ የሠራሁባት፣ የምጦርባትና በመጨረሻም በክብር የምቀበርባት ናት፡፡ ይህችን አገሬን ያስረከቡን አያት ቅድመ አያቶቼ ብቻ ሳይሆኑ፣ አባትና እናቴ ጭምር ምን ያህል መስዋዕትነት ከፍለው እዚህ እንዳደረሱዋት የማውቀው አንተ ሳትሆን እኔ ነኝ፡፡ አንተ ዛሬ ጊዜው ተመቸኝ ብለህ በሠለጠነ አገር እየኖርክ መሠልጠን አቅቶህ፣ አገሬን የሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተህ አገሬን ስታራክስ መስማት ያመኛል፡፡ ከአሁን በኋላ የጀመርከውን አደገኛ ነገር ካላቆምክ ከአንተ ጋር ዝምድና ሳይሆን ጠላትነት እንዳለኝ እንድታውቀው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ከእኔ ጋር የመነጋገር ሞራል እንደሌለህ ማወቅ ይኖርብሃል…›› ሲሉ የግንባራቸው ሥሮች ተገታትረው ነበር፡፡ ለአንድ ደቂቃ ያህል ከወዲያ በኩል የሚነገራቸውን ካዳመጡ በኋላ፣ ‹‹ሰማህ! ከቻልክ የምነግርህን ስማ፣ ካልሆነልህ ግን ከቢጤዎችህ ጋር ሆነህ ዘመን ያለፈበት እንጉርጉሮህን አስነካው…›› ብለው ሰሜን ሆቴል ላይ ‹‹ወራጅ!›› አሉ፡፡ ጉድ እኮ ነው!

አዛውንቱ ታክሲው ሲቆምላቸው፣ ‹‹ምን ዓይነት ልክፍት ነው?››  እያሉ ሲወርዱ ወያላው፣ ‹‹ፋዘር ምን ሆነው ነው?›› ብሎ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ አዛውንቱ ከወረዱ በኋላ ወያላውን ለአፍታ ትክ ብለው ዓይተውት፣ ‹‹ልጄ የዘመኑ የጽንፈኛ ብሔርተኞች ዕብደት ነው እኔንም ወፈፍ ያስደረገኝ…›› ብለውት መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ወያላው በንግግራቸው እየተገረመ፣ ‹‹እሳቸውን እንዲህ ያሳበዳቸው ሌሎችን እንዴት እያደረጋቸው ይሆን?›› ከማለቱ ከቆንጆዎቹ አንደኛዋ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ይህ ቀፋፊ ዘመን የማያሳየን የለም፡፡ ድሮ ወጣቱ አንድ ሆኖ የተነሳው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት፣ እኩልነትና መብቶች መከበር ነበር፡፡ ዛሬ አንድ ላይ የኖረን ሕዝብ በመከፋፈል አገር የሚያፈረሱ ኋላቀሮችን ማን እንደለቀቀብን እንጃ…›› አለች፡፡ ጎልማሳው ጉሮሮውን እየጠራረገ፣ ‹‹ችግሩ እኮ ለአገርም ሆነ ለማንነት መታገሉ ላይ አልነበረም፡፡ የከፋው ነገር ሁሉም ሥልጣን ፈላጊ ሆኖ በሕዝብ ስም ዕልቂትና ፍጅት መደገሱ ነው…›› በማለት የበኩሉን ሲናገር ወጣቱ፣ ‹‹ከሥልጣን ፍላጎት በላይ የጠላት ተላላኪነት በመብለጡ ይመስለኛል ግድባችን ውኃ ሊሞላበት ሲል ያ ሁሉ መዓት የወረደው…›› ከማለቱ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ጉዞአችን ማለቁን አበሰረን፡፡ በአዛውንቱ የንዴት ንግግር የተነሳ ዘመኑንና ዘመነኞችን እያማን ወደ ጉዳያችን አመራን፡፡  መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት