Thursday, June 20, 2024

ኢኮኖሚውን የሚታደገው ወሬ ሳይሆን ሥራ ነው!

የዓለም ኢኮኖሚ አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከማምረቻ እስከ ማከፋፈያና ችርቻሮ ንግድ ድረስ፣ ታይቶ የማይታወቅ ኪሳራ እያጋጠመ ነው፡፡ በቀጥታ ከሸማቾች ጋር ግንኙነት ያላቸው በርካታ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የንግድ መደብሮች፣ ሞሎች፣ የውበት ሳሎኖችና የመሳሰሉት ሥራ ፈተው ሠራተኞችን በትነዋል፡፡ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሟል፡፡ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ቀጥ በማለቱ የዓለም ኤርፖርቶች ኦና ሆነዋል፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ግዙፎቹ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቀጣዮቹ ተመቺዎች ይሆናሉ ተብሎ ፍራቻ አለ፡፡ አሜሪካውያን የመንግሥት ድጎማ ጠባቂ ከሆኑ ሰነባበቱ፡፡ አውሮፓውያንም ከዚያ በማይሻል ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ መላው ዓለም በኮሮና ምክንያት እንዲህ የመሰለ ጭንቅ ውስጥ ሆኖ፣ ወረርሽኙ እየተስፋፋ በርካቶች አሁንም እየሞቱ ነው፡፡ የወረርሽኙ ጫና እስከ መቼ እንደሚቆይ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ከዚህ የከፋ ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል እየተባለ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ስናማትር የወረርሽኙ ተጠቂዎችና ሰለባዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የምርመራ አቅም ሲጨምር ጫናው እየታየ ስለሆነ ብርቱ ጥንቃቄና ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ ራስን ከመቻል ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ለዚህም ነው ዝግጁ መሆን የሚያስፈልገው፡፡

ከዝግጅቱ ዋነኛውና አንደኛው ኢኮኖሚያዊ አቅምን መገንባት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅምን መገንባት የሚቻለው እጅ ላይ ያለ ሀብትን በሚገባ በመጠቀም ነው፡፡ ከ80 በመቶ ያላነሰ ሕዝብ በእርሻና በከብት አርቢነት በሚተዳደርባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት ያለበት ለግብርናው ዘርፍ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ አመቺ የአየር ፀባዮች፣ ከሁሉም በላይ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የወጣት ኃይል ይዛ ስንዴ ከውጭ ትገዛለች፣ ባስ ሲልም ትመፀወታለች፡፡ በአገር ውስጥ መመረት የሚገባቸው መሠረታዊ ሸቀጦች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ከውጭ ይገዛሉ፡፡ ከአፍሪካ በእንስሳት ሀብት አንደኛ ሆና ሥጋ፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ዓሳ፣ ወዘተ ብርቅ ናቸው፡፡ ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በከተማ ግብርናም ሆነ ሰፊ የሰው ኃይል ባለበት በገጠር ግብርና አማካይነት ቢያንስ ገበያዎችን ማጥገብ ይቻላል፡፡ ለመሆኑ ክልሎች በመስኖም ሆነ በዝናብ ሊታረሱ ከሚችሉ መሬቶች ምን ያህሉን እየሠሩባቸው ነው? ወጣቶች መሥራት በሚችሉበት ዕድሜያቸው የወላጅ ተጧሪ ከሚሆኑ ለምን በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ሥራ አይዘጋጅላቸውም? በከተማም እንዲሁ በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩና አምራች እንዲሆኑ ማድረግ ለምን ያዳግታል? ይህ በዋዛ የሚያይ ሳይሆን ሊተኮርበት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለማመን በሚያስቸግር ደረጃ ከሥራ ይልቅ ለወሬ የተሰጠው ሥፍራ ያስደነግጣል፡፡ ከወሬው በመቀነስ ሥራው ላይ መበርታት ከተቻለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕምቅ ሀብትና የወጣት ኃይል ተዓምር ማሠራት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያን የበደሏት ወደ ተግባር መመንዘር የማይችሉ አተካራዎችና ወንዝ የማያሻግሩ ወሬዎች ናቸው፡፡ ከበፊት ጀምሮ የሚሠሩ ሰዎች ቢከበሩ፣ ከሚያስገኙት ውጤት በተጨማሪ ለሰብዕናቸው ዋጋ ቢሰጥና የሥራ ክቡርነት ታላቅ ወግና ማዕረግ ቢያገኝ ኖሮ፣ ከሚሠሩ ይልቅ የማይሠሩ አድርባዮችና አስመሳዮች ልቀው አይገኙም ነበር፡፡ የሥራ ክቡርነትን የተረዱ ሰዎችን ገንዘብ ሲያሳድዱ እንደሚውሉ ቀበኞች የማየት ልማድ፣ በኢትዮጵያ ምድር ከሚሠሩ ይልቅ ለሚያወሩ የተመቻቸ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ውጤቱ ግን ድህነት፣ ኋላቀርነትና ልመና ብቻ ነው፡፡ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ታታሪ ሰዎችን ማግኘት ባለመቻሉ፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅቶች የተሰማሩ ሰዎች ውጤት ከሚጠበቀው በታች የወረደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጎጂ ልማድ በማስወገድ በዚህ ከባድ ጊዜ ለሥራ ታጥቆ መነሳት የግድ ይላል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ለሥራ የሚሰጠው ትኩረት ከቃላት ጋጋታ ባሻገር በተግባር ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ከፍተኛ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር አናቷ ላይ የሚያናጥርባት አገር፣ ሁሉም ነገር በተቆላለፈባት ዓለም ትከሻ ላይ መተማመን አትችልም፡፡

ኢትዮጵያውያን ከከተማ እስከ ገጠር በዕቅድ፣ በጠንካራ ክትትልና አፈጻጻም ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጠንካራ ተቋማትና በዕውቀታቸውም ሆነ በልምዳቸው በተመሰከረላቸው ባለሙያዎችና አመራሮች የሚታገዝ ሥርዓት ሲኖር፣ ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለአፍሪካ ጭምር የሚተርፉ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ይቻላል፡፡ ከሌብነት፣ ከሸፍጥና ከክፋት በፀዳ ክህሎትና ሰብዕና የሚመራ አገር ሀብቱ ይትረፈረፋል፡፡ ከራሱ አልፎም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያገኛል፡፡ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ግን በዓባይ ውኃ የበቀሉ ብርቱካንና ሽንኩርት በውጭ ምንዛሪ ከግብፅና ከሱዳን ማስገባት ነው፡፡ አትክልት ተራና የሸቀጣ ሸቀጥ ግሮሰሪዎችን ያጣበቡት የሱዳንና የግብፅ ምርቶች እንደሆኑ ለማረጋገጥ ትንሽ ዞር ዞር ማለት በቂ ነው፡፡ የስንዴ፣ የዘይት፣ የስኳር፣ የወተትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ምርቶች የውጭ ግዥ አልበቃ ብሎ፣ የዓባይ ውኃ ውጤት የሆኑትን የጎረቤት አገር ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት ያማል፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህል አብዮት አካሂዳ ወጣቱን ሥራ ላይ ማሰማራት እንዴት ያቅታታል ሊባል ይገባል፡፡ ጠንካራ ተቋማት እንዲኖሩ ከመሥራት ጎን ለጎን እያፈጠጠ ከመጣው መከራ ለመትረፍ፣ በተቻለ መጠን በእጅ ላይ ያለውን ሀብት ሥራ ላይ ለማዋል መጣደፍ የወቅቱ ዓብይ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ከራስ በስተቀር በማንም ላይ መተማመን አይቻልም፡፡

እንደሚታወቀው የመሥራት ባህል አለመዳበር የሚጎዳው አገርን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዕለት ዕርዳታ ጥገኛ የሆኑ ሰዎች ቁጥር በጣም አሻቅቧል፡፡ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚሹ የድርቅ ተጠቂዎች፣ ከተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ፣ በኮሮና ምክንያት ሥራቸውን ያጡ፣ ወዘተ በርካታ ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ በቀን አንድ ጊዜ የረባ ምግብ የማያገኙ ሰዎች ቁጥር ከዕርዳታ ፈላጊዎቹ ይልቃል፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፡፡ ሥራ አጥነቱ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው፡፡ በከተሞች ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት መጠኑ በጣም እየጨመረ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ብዙዎቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአቅም በታች ነው የሚያመርቱት፡፡ የአገሪቱ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዙ ጊዜ ይቀረዋል፡፡ የሕዝብ ቁጥር ከመጠን በላይ እየጨመረ ከመሆኑም በላይ፣ ከተሞች ሥራ በሌላቸው ዜጎች እየተጥለቀለቁ ነው፡፡ ሌሎች ተቆጥረው የማያልቁ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት ይገባል፡፡ ምርታማነትን በብዙ እጥፍ ማሳደግ የግድ ይላል፡፡ አገር የምታድገውና የምትበለፅገው በወሬ ሳይሆን በሥራ ብቻ ነው፡፡ ለሥራ ቅድሚያ ካልተሰጠ ከባድ ችግር አለ፡፡ ኢትዮጵያ የሚሠሩ እንጂ ወሬ ላይ የተጣዱ አስመሳዮች ምንም አይፈይዱላትም፡፡

ኢትዮጵያ ከተሠራባት እንኳን ለራሷ ለአፍሪካም ትተርፋለች ሲባል ቀልድ አይደለም፡፡ በሁሉም መስክ የሚሠሩ ከተከበሩ ሥራ ፈጣሪዎች ይበዛሉ፣ ሀብት ይትረፈረፋል፣ ድህነት በእርግጥም ታሪክ ይሆናል፡፡ የሚሠሩ ካልተከበሩ ግን ከምኞት የዘለለ ውጤት አይገኝም፡፡ ከአጉል ምኞት በመውጣት ተስፋ መሰነቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ተስፋ እንዲለመልም ግን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመላቀቅ ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዘዴ ያለው በሥራ ውስጥ ነው፡፡ ሥራ ክቡር ነው፣ የሚሠራም ምሥጉን ነው መባል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የጎደላት ከፍተኛ የሆነ የሥራ ባህል ነው፡፡ የሥራ ባህል ሲኖር ፖለቲካውም፣ ኢኮኖሚውም ሆነ ማኅበራዊው ጉዳይ በሙሉ በቀና መንገድ ይጓዛል፡፡ አብሮ ከመብላት በተጨማሪ አብሮ መሥራት ይለመዳል፡፡ አብሮ መሥራት ሲቻል የተባበረ ኃይል ይፈጠራል፡፡ ይህ የተባበረ ኃይል ውጤቱ ከፍተኛ ስለሚሆን ከፍተኛ ትርፍ ይገኛል፡፡ የአፈጻጸም ድክመት እየተባለ ሰበብ አይደረደርም፡፡ መለገም አይታሰብም፡፡ አድርባይነትና አስመሳይነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ወሬ፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ጭፍን ጥላቻና ድጋፍ፣ ቂም በቀል፣ ክፋት፣ ሴራ፣ አሻጥር፣ ወዘተ ከሥራቸው ተመንግለው ይወድቃሉ፡፡ መሥራት ሲቻል ለአገር የማይጠቅሙ የፖለቲካ መጓተቶች ትኩረት ያጣሉ፡፡ ‹‹ድመቷ ጥቁር ወይም ነጭ መሆኗ ሳይሆን ቁምነገሩ ዓይጥ መያዝ መቻሏ ነው›› እንደሚባለው የአገሪቱ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ቁምነገር መሥራት ያለባቸው፣ ኢትዮጵያን ከችግር አረንቋ ውስጥ እንዴት ማውጣት እንደሚቻል መፍትሔ ለማፍለቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚታደገው ወሬ ሳይሆን ሥራ ብቻ ስለሆነ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...