Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊገበታ ለአገር ለተባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሐ ግብር 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋመ

ገበታ ለአገር ለተባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሐ ግብር 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋመ

ቀን:

በአዲስ አበባ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ የሚገኘውን የአንድነት ፓርክ ጨምሮ ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ለሚገኘው የወንድማማቾች አደባባይና ለእንጦጦ ፓርክ ግንባታ ገንዘብ ለማዋጣት የተደረገው የገበታ ለሸገር መርሐ ግብር ቀጣይ አካል የሆነ ገበታ ለአገር ለሚባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክት ሀብት የሚያሰባስቡ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡

የኮሚቴው አባላትም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሀብታሙ ተገኝ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ወ/ሪት ሌሊሴ ነሜ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ እንዲሁም አሁን የሥራ ፈጠራ ኮሚሽነር በመሆን የተሾሙት አቶ ንጉሡ ጥላሁንን ያካተተ ነው፡፡

እሁድ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው ይኼ መርሐ ግብር በጠቅላላ ሦስት ቢሊዮን ብር፣ ወይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስሌት 100 ሺሕ ዶላር ለማሰባሰብ ያለመ ነው፡፡ የኮሚቴው አባላት ገንዘብ የማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን የተሰበሰበው ገንዘብ ምን ላይ እንደዋለም የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከሌላ ምንጮች ይኼንኑ መጠን ያክል ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደሚሠራ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሦስቱ ሥፍራዎች ማልሚያ የሚሆን ሁለት ቢሊዮን ብር ይመደባልም ብለዋል፡፡

የቦታ ማስዋብና የተለያዩ መሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲከናወንላቸው የተመረጡት ሦስት ሥፍራዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሥፍራዎች የሚገኙት በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ነው፡፡ በአማራ ክልል የሚለማው ሥፍራ ጎርጎራ ሲሆን፣ ጣና ሐይቅ አካባቢ የሚገኝና ጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች የሚጋሩት በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ደግሞ ለምለም የሆነው የወንጪ ሐይቅ ነው፡፡ ከደቡብ ክልል የተመረጠው ሥፍራ ኮይሻ የሚባል ቦታ ሲሆን፣ ይኼ በዳውሮ፣ ወላይታ፣ ጊቤ ሦስትና በኮንታ መካከል የሚገኝና የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ የሆነ ሥፍራም ነው፡፡

ገበታ ለሸገር ለተባለው መርሐ ግብር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ራት ለመመገብ ባለሀብቶች ያዋጡት ገንዘብ አምስት ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ለገበታ ለአገር ደግሞ የሚዋጣው የገንዘብ መጠን በሁለት ድርብ ተከፍሎ፣ ቪቪአይፒ አሥር ሚሊዮን ብር እንዲሁም ቪአይፒ አምስት ሚሊዮን ብር ያስከፍላሉ፡፡

ለዚህ መርሐ ግብር የገንዘብ መዋጮ የሚጠበቅባቸው የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች፣ ኩባንያዎች፣ ዳያስፖራው፣ እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱ ሲሆን፣ ገንዘቡ በሚከፈትለት የገንዘብ ማሰባሰቢያ የባንክ ቁጥር የሚጠራቀምና ከሁለት ወራት በኋላ በመስከረም መጨረሻ አልያም ጥቅምት አጋማሽ አካባቢ የታለመለት የእራት መርሐ ግብር ይከናወናል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለፕሮጀክቱ የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጭ መንገድ በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት እንደሚዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሠረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በ333 የአጭር መልዕክት መስመር ማንኛውም ማዋጣት የሚፈልግ ሰው በሚልከው የገንዘብ መጠን ተሳታፊ እንዲሆን አዘጋጅቷል፡፡

በአገሪቱ መልማት የሚችሉ 50 እና 60 ሥፍራዎች እንዳሉና ባለ ውስን ሀብትና አቅም ምክንያት ሦስቱ ቦታዎች መመረጣቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሦስቱ ሥፍራዎች የሚገኙባቸው ሦስቱ ክልሎች በመሪዎቹ የሚመሩ ንዑስ ኮሚቴዎች እንዳሏቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀብታሙ (ኢንጂነር) የኮይሻ፣ አብርሃም (ዶ/ር) የወንጪ እንዲሁም ፍሰሐ (ዶ/ር) የጎርጎራን ልማት ፕሮጀክቶች በኃላፊነት እንደሚመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ማሰባሰቡን ለማገዝም የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች እንደሚዘጋጁ እንዲሁም የተለያዩ ቲሸርቶች ታትመው በ500 ብርና በ1,000 ብር እየተሸጡ ወደ አዲሱ የእንጦጦ ፓርክ የእግር ጉዞ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ የሚያደርጉና በማስተባበር የሚሳተፉ ሰዎች ሥራ የሚመዘገብበትና መረጃ የሚያዝበት ድረ ገጽ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር መሠራቱና እያንዳንዱ ሥራም በዚህ ተመዝግቦ እንደሚቀመጥ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በትግራይ ተቋርጦ የነበረው የምግብ ዕርዳታ እንዲጀምር አቶ ጌታቸው ጥያቄ አቀረቡ

የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት...

ኢዜማ ከለቀቁ አባላት ግማሽ ያህሉ የዲሲፒሊን ችግር የነበረባቸው ናቸው አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በቅርቡ ከፓርቲው አባልነት ለቀናል...

የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ደመወዝና...

ኢሰመኮ በዩኒቨርሲቲዎች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጉዳይ የሚመራበት የጽሑፍ ፖሊሲ አለመኖሩን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች...