በኢትዮጵያ ቴኳንዶ ስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ አኑረዋለው፡፡ በሥራ አጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ኮሪያዎች ልምምድ ሲያደርጉ ሲመለከቱ ዕድል በማግኘታቸው በአርቱ ውስጥ ከ30 ዓመት በላይ እንዲቆዮ አስችሏችዋል፡፡ ከዚያም ወደ ደቡብ ኮርያ በማምራት በዩኒቨርስቲ የአሠልጣኝነት ትምህርት መውሰድ ችለዋል፡፡ ስፖርቱን በኢትዮጵያ ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ በአሠልጣኘነት ጉዞም 300 አሠልጣኞችን አፍርተው፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ቴኮንዶ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ማስተር ኪሮስ ገብረ መስቀል የሰባት ዳን ድግሪን ተጎናጽፈዋል፡፡ እንደ ክለብ ሲታይ የነበረው የቴኳንዶ ስፖርት በመላ አገሪቷ እንዲለመድና ወጣቱ በሥነ ሥርዓት እንዲታነጽ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በቅርቡም በመስቀል አደባባይ በማስ ስፖርት እየተዘወተረ የመጣውን እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ የሪፖርተሩ ዳዊት ቶሎሳ ስፖርቱ አሁን ያለበትን ሁኔታና በቀጣይ ሊሠሩ የታቀዱ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ቴኳንዶ ስፖርት በመላ አገሪቷ በወጣቶች የተወደደና የተለመደ መሆን ችሏል፡፡ አጀማመሩና አሁን ያለበት ሆኔታ ምን ይመስላል?
ማሰተር ኪሮስ፡- በኢትዮጵያ ማሠልጠን ከጀመርኩበት ጊዜ ማለትም በ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር። ሆኖም በሲቪል ደረጃ አሠልጣኝ ስላልነበር አርቱ በማኅበረሰባችን አይታወቅም ነበርና በዚያ ወቅት ስንጀምር በአገራችን ሦስት አሠልጣኞች ብቻ ነበርን። እውነት ለመናገር ብዙ ውጣ ውረድ አልፈን አርቱ ለዚህ በማድረሳችን ትልቅ ኩራት ይሰማኛል። ያው ኅብረተሰቡ አርቱ የመደባደቢያ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር የአርቱ ዓላማ ለኅብረተሰባችን ማስረዳት ከባድ ነበር። በተለይ የመንግሥት አካላት እንደ ስፓርት አይመለከቱትም ነበርና ብዙ ውጣ ውረድ እንድናልፍ ተገደናል። አሁን ግን በርካታ ባለሙያዎችን አፍርተን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበትን መንገድ ከፍተናል፡፡ ስፖርቱም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰርፆና ተለምዶ ለመቆየት ችሏል፡፡ አሆን ላይ ጥሩ ተቀባይነት ኖሮት በመላ አገሪቷ በስፋት የበርካታ ወጣቶች ስፖርት መሆን ችሏል፡፡ በዚህም እኔ በግሌ 28,000 በላይ የቴኳንዶ ሠልጣኞችን ማፍራት ችያለው፡፡ ስለእዚህ ስፖርቱ አሁን ያለበት ሆኔታ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ አሠልጣኞች የአንተ ተማሪዎች ናቸው። ስፖርቱ ከተነሳበት ጊዜ አኳያ አሁን ያለበትን ሁኔታ ስትመለከትና በርካታ አሠልጣኞችን ማፍራት መቻሉ የነበረው ጉዞ እንዴት ይገመገማል?
ማሰተር ኪሮስ፡- እንደ አገር ስናስበው ይህን ያህል አሠልጣኝ አሠልጥኖ ለራሱ ሥራ ፈጥሮ ኅብረተሰቡ ጤናማ እንዲያደርግ ማድረግና በሥነ ምግባር የታነጹ ወጣቶች ማፍራት ትልቅ ተግባር ነው። ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ወጣቶች በራሳቸው እንዲተማመኑ ጤናማና በሥነ ምግባር የታነጹ፣ ኅብረተስቡን የሚደግፉ ማድረግ ተችሏል፡፡ አንድም መንግሥት ለመድሐኒት የሚያወጣውን ወጪ መቀነስ ነው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ወጣቶችን ግብረ ገብ አድርጎ ወንጀል እንዲቀንስ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለ ስፖርት ነው። በማኅበራዊ ጉዳይም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር በርካታ ተወዳዳሪዎችን በማፍራት በተለያዩ አገር አቀፍና አኅጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠር ተችሏል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ሰዓት በመላው አገሪቱ በአንተ ሥር ስንት የቴካንዶ አሠልጣኞችና ሠልጣኞች እንዲሁም የኅብረተስብ ክፍል አለ?
ማሰተር ኪሮስ፡- በክለብ ደረጃ 276 ክለቦች ሲኖሩ እነዚህ ክለቦች ዋና አሠልጣኝና አንድ ምክትል አላቸው፡፡ በድምሩ 552 አሠልጣኞች ማለት ነው። በእነዚህ ክለቦች ውስጥ የሠለጠኑና በእኔ አማካኝነት ተፈትነው እንግሊዝ ከሚገኝ ከዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ዳን ዲግሪ እንዲያገኙ ያደረኩዋቸው ይገኛሉ፡፡ ከ1-7 ዳን ዲግሪ ድረስ የሆኑና የጥቁር ቀበቶ ባለቤት መሆን የቻሉ አሉ፡፡ በአፍሪካ በቀዳሚነት ነው የተቀመጡት፡፡ በከለር ቀበቶ ደረጃ 25,000 ስፖርተኞች አሉ፡፡ የእነዚህ እህት ወንድም እናት አባት ከጀመርን እስከ አንድ ሚሊዮን ኅብረተስብ በእኛ አካባቢ አሉ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስፖርቱ ከሕጻናት ጀምሮ በአዋቂዎች ዘንድ እንደሚዘወተር ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበረሰቡ በተለያዩ አካባቢዎች ሥልጠናውን ሲከታተሉ ይስተዋላል፡፡ መንግሥት ለስፖርቱ የሚያደርገው ድጋፍ ምን ይመስላል?
ማሰተር ኪሮስ፡- ስፖርቱ በኅብረተሰብ ውስጥ በተለይ ደግሞ በወጣቱ ዘንድ ሰርጾ መግባት ችሏል፡፡ ይኼንንም ለመገንዘብ በአገሪቷ ያሉትን ስፖርት ቤቶች መመልከት ይቻላል፡፡ ወላጆችም ለልጆቻቸው ገንዘብ ከፍለው ሲያስተምሩ ይስተዋላል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ስፖርቱ ምን ያክል በኅብረተሰቡ ውስጥ ምን ያክል ተወዳጅ እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ ሆኖም መንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ አያደርግም ማለት ይቻላል። እንዳውም አብዛኛው አሠልጣኝ የሚያሠለጥንበት አዳራሽ የመንግሥት ስለሆነ አላግባብ ኪራይ በማስከፈል ስፖርቱን የሚወደው ማኅበረሰብ እንዲማረር ያደርጉታል። ስለእዚህ ስፖርቱ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እየተደረገለት ነው ለማለት ያዳግታል፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ በሚድያ መንግሥት ለስፖርቱ ዕድገት ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ስትሰጥ ይደመጣል፡፡ አሁን ላይ ስፖርቱን እየመራ ያለው የመንግሥት አካልስ ለስፖርቱ እየሰጠ ያለው ትኩረት እንዴት ትመለከተዋለህ?
ማሰተር ኪሮስ፡- በተደጋጋሚ በተገኙ ሙድረኮች ላይ በግሌ ስለሁኔታው ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ የስፖርት ፖሊሲው መሻሻል እንዳለበት፣ ጤናማ ኅብረተሰብ ለመንገንባት ሆስፒታል መሥራት በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንስ የስፓርት ማዘውተሪያ በብዛትና በጥራት መሠራት አለበት። ስፓርቱን እየመሩ ያሉት የስፓርት ሚኒስትሮችና ፓለቲከኞች ስለሆኑ ስፖርት እንዴት ማደግ እንዳለበት በቂ ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችላል። ለዚህም ነው ለዘመናት የአገሪቷ ስፖርት ለውጥ ማምጣት የማይችለው። እነዘህ አካላት ባለሙያዎችን በማማከር ወጣቱን መጥቀምና አገር መጥቀም አለባቸው፡፡ ወጣቱን ደግሞ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እኛ ባለሙያዎቹ መንገዱን ማሳየት ወይም ለመደገፍ በራችን ሁሌም ክፍት ነው፡፡ ግን እኛን መስማት ፍላጎት የላቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- ስፖርቱ በኅበረተሰቡ ውስጥ ተወዳጅ እንደመሆኑ መጠን ስፖርቱን የሚመሩት አካለት ድጋፍ ያለማድረጋቸው ሚስጢር ምንድነው? እናንተንሰ መስማት ያልፈለገበት ምክንያት ቢያብራሩልን?
ማሰተር ኪሮስ፡- መንግሥት ለዜጎች ታማኝ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ዜጎች ደግሞ ጤናማ እንዲሁም ሥራ ፈጣሪ ሆነው በአገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ መሆን ይፈልጋሉ። ስለሆነም ቢሰማን ጥሩ ነው፡፡ ያው ለአገር የሚጠቅም ሐሳብ ነው እያቀረብን ያለነው። ኢትዮጵያ ብዙ አቅም ያላቸው፣ ባለሙያዎች ያላት አገር ናት፡፡ ከተጋገዝንና ከተደማመጥን የአገራችን ስፖርት መቀየር ይቻላል። መንግሥትም ወጣቱን ማዕከል ያደረገ ሥራ ቢሠራ መልካም ነው፡፡ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫው በብዛት በወጣቱና በስፖርት አካባቢ ነው ያለው። በተለይ ማርሻል አርት ዙርያ በርካታ ወጣቶች የሚገኙበትና በዚያው መንገድ ማነጽም የሚቻልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ቡድን ይዘው በስፔን፣ በህንድና በደቡብ ኮርያ ላስገኙት ውጤት ሽልማት ተበርክቶሎታል። አጋጣሚውንና ማበረታቻው ምን ይመስል ነበር?
ማሰተር ኪሮስ፡- በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ይዘን መጓዝ ችለናል፡፡ በዚህም በተለያዩ አገሮች መልካም ውጤቶችን ማምጣት ችለናል፡፡ ከዚያም በላይ የተለያዩ ልምዶችን ቀስመን በኢትዮጵያ ያለውን የቴኳንዶ ስፖርት የበለጠ እንዲሻሻልና በርካታ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የምንችልበትን አጋጣሚ መፍጠር ችለናል ማለት ይቻላል፡፡ ይኼ በቀጣይም የበለጠ ጠንክረን የምንሄድበት መንገድ ነው፡፡ በግል ለተደረገልኝ ዕውቅና አመስግኜያለሁ፡፡ ደስተኛም ነኝ።
ሪፖርተር፡- ቀደም ብሎ በእንግሊዝ፣ በህንድ፣ በፓላንድና በአሜሪካ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠትም እንዲሁም መውሰድ መቻልህ ይታወሳል። የብዙ አገሮችን የስፖርት ፓሊሲና አሠራር ልምድ ቀስመሀል። ከዚህ በመነሳት አሁን ስፖርቱን ለሚመራው የመንግሥት አካል ልታቀርብ የምትችለው ምክረ ሐሳብ ካለ?
ማሰተር ኪሮስ፡- ብዙ ሰነዶች በእጄ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በስፖርት ፖሊሲ ሐሳብን በተመለከተ እንዲሁም በታዳጊዎች ሥልጠናና ውጤታማነት ዙርያ በርካታ ዕቅዶች አሉኝ። የአንድ አገር የስፖርት ዕድገት መነሻ የሆኑ ፓሊሲዎችና ደንቦች ማንዋሎች እንዲሁ አሉኝ፡፡ እነዚህን ለአገሬ ማበርከት እፈልጋለሁ፡፡ አገር በሁሉም ድጋፍና ትብብር ነው የምትለወጠው እንዲሁም የምታድገው። ሆኖም የአገራችን የስፖርት አሠራርና ፓሊሲ አያስኬድም። ይህን ምክረ ሐሳብ የመንግሥት አካል ተመልክቶትና ለስፖርቱ ዕድገት የበኩላችንን እንድናበረክት በሩን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ ከባለሙያው ጋር ተቀራርቦ መሥራት ካልተቻለ ግን ስፖርቱን ወደ ኋላ እየጎተትነው ነው የምንሄደው፡፡