የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለረዥም ጊዜ የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጋር በትብብር ለመሥራት ፈቃደኛ አይደሉም በማለት አገዳቸው፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው በዚህ ሳምንት ሲሆን፣ ሊቀመንበሩ በበኩላቸው ከቀናት በፊት ምክትል የፓርቲ ሊቀመንበሩን አቶ አራርሶ ቢቂላ፣ የሥራ አስፈጻሚው አባሉን አቶ ቶሌራ አዳባንና አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ ስድስት አመራሮችን ከፓርቲው አግደው ነበር፡፡
ፓርቲው ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ክፍፍልና የአመራሮች መተጋገድ የመጣው ከሳምንታት በፊት የኦነግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያለ ሊቀመንበሩ ተሳታፊነት ያደረገው ስብሰባ ነው፡፡ በወቅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለአቶ ዳውድ አስቀድሞ አሳውቆ እሳቸውም ስብሰባው እንዲካሔድ የተስማሙ ቢሆንም፣ በኋላ የስብሰባው ዋዜማ ምሽት ላይ አቶ ዳውድ ስብሰባውን ሕገወጥ እንዳሉትና ስብሰባው እንደሚካሔድም እንደማያውቁ መናገራቸውን አቶ ቶሌራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ቶሌራ ገለጻ የፓርቲው ዋና ሊቀመንበር በማይኖሩበት ጊዜ ምክትል ሊቀመንበሩ በመተካት ስብሰባዎችን እንደሚመሩ በሕገ ደንባቸው የተደነገገ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት የተደረገው ስብሰባ ሊቀመንበር የማንሳትም ሆነ ተመሳሳይ አጀንዳ ያልያዘ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ በሊቀመንበሩ የተላለፈው መልዕክት ግን የፓርቲውን ሊቀመንበር ለመገልበጥ ተደርጎ የቀረበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳውድ በወቅቱ በሥራ አስፈጻሚ አባላቱ ላይ ካስተላለፉት ውሳኔ ጋር አክለው አባላቱ በሒልተን ሆቴል የሰጡትንም መግለጫ ሕገወጥ ነው ሲሉ ኮንነውት ነበር፡፡ ‹‹ሊቀመንበሩ ስብሰባውን አላውቀውም ማለታቸው ግራ አጋብቶናል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ወጥቶ ፓርቲውን እንዲጠብቅም ሁሉ ጥሪ አስተላልፈው ነበር፤›› ሲሉ አቶ ቶሌራ ተናግረዋል፡፡
ይኼ በእንዲህ እንዳለ እሁድ ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ለስብሰባ ወደ ፓርቲው ጽሕፈት ቤት ሲሔዱ በጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የማይታወቁ ሰዎች እንደነበሩና በእሑድ ቀን የሚመጣ ሰው ባለመኖሩ ሁኔታው ግራ እንዳጋባቸው አቶ ቶሌራ ተናግረው፣ ሰዎቹ ረብሻ ለማስነሳት ፍላጎት ስለነበራቸው ፖሊስ መጥራታቸውንና በፖሊስ ጥበቃ ሥር ሆነው የሁለት ቀን ስብሰባ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ስብሰባው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እንደተካሔደ በማንሳት የሚከራከሩት አቶ ቶሌራ፣ አቶ ዳውድ የጠሩት ስብሰባ ያለ ሥራ አስፈጻሚው ዕውቅና የተጠራ በመሆኑና የስድስቱ አባላት ዕገዳ በምክር ቤቱ ሁለት ሦስተኛ ድምፅ መፅደቅ ሲኖርበት ይኼ ባለመደረጉም ሕገወጥ ነውም ይላሉ፡፡
ስለዚህም ለአቶ ዳውድና ቡድናቸው (አቶ ቶሌራ ከአምስት አይበልጡም ይላሉ) ዕርምጃ ምላሽ ይሆን ዘንድም የሥራ አሥፈጻሚ አባላቱ አቶ ዳውድን እስከ ቀጣዩ የፓርቲው ጉባዔ ድረስ ከሊቀመንበርነት አግደዋቸዋል፡፡ ይኼ ውሳኔ በሥነ ምግባርና ቁጥጥር ኮሚቴ ተጣርቶ የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላላ ጉባዔው ይቀርባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና አቶ ቶሌራ፣ ከአቶ ዳውድ ጋር ያሉት አምስት ናቸው ካሏቸው አባላት መካከል ውሳኔ የተላለፈበት ሌላ አባል እንደሌለና የእነርሱ ጉዳይ በፓርቲው የውስጥ አሠራር ይፈታል ብለው እንደሚያምኑም አክለዋል፡፡
አቶ ዳውድ ያልተገኙበት ስብሰባ ሊቀመንበሩ በቤት ውስጥ እስር ላይ ናቸው የሚል መረጃ ይናፈስ በነበረበት ወቅት የተከናወነ ሲሆን፣ መንግሥት አቶ ዳውድን በወቅቱ ለደኅንነትዎ ነው በሚል በቤታቸው እንዲቆዩ አድርጓቸው እንደነበር አቶ ቶሌራ አረጋግጠዋል፡፡
ነገር ግን የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሊቀመንበሩ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ የሚተቹ ወገኖች የብልፅግና ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ያመጣው ነው በማለት ውሳኔውን ያስተላለፉትን የሥራ አስፈጻሚ አባላት እየተቹ ሲሆን፣ አቶ ቶሌራ ግን ይኼንን ክስና ወቀሳ ያጣጥላሉ፡፡
ለዚህ ክስ እንደ አንድ ምክንያት የሚቀርበው በሐምሌ 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገው ስብሰባ የተሰጣቸው የፖሊስ ጥበቃ እንደሆነ በመግለጽ፣ ይኼንን ማድረግ ደግሞ በነበረው የፀጥታ ሥጋት ሳቢያ አስፈላጊና ረብሻውን ለማስወገድ ወሳኝ ዕርምጃ ነበር ይላሉ፡፡
‹‹ብልፅግና ፓርቲ በእኛ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ እንዲገባ አንፈቅድም፡፡ የድርጅቱንም ህልውና የመጠበቅ ግዴታ አለብን፤›› በማለትም አቶ ቶሌራ ተከራክረዋል፡፡ ትችቱም ፓርቲው በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለማጠልሸት የታለመ ነው በማለት ያጣጥሉታል፡፡