Friday, June 2, 2023

የወላይታው የሰሞኑ ክስተትና የክልልነት ጥያቄ ሒደት በወፍ በረር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(3) መሠረት በአገሪቱ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች የራሳቸውን የአስተዳደር ክልል ለመመሥረት በፈለጉ ጊዜ ክልል መመሥረት እንደሚችሉ የተደነገገውን ድንጋጌ በመንተራስ፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክልል እንሁን ጥያቄዎች 13 ከሚሆኑ የደቡብ ክልል ዞኖች ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች በርካታ የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ውድመትን ካስከተሉ በኋላ ምላሽ ያገኘው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ብቻ ሲሆን፣ ሌሎቹ ዞኖች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች የተለያዩ ውይይቶች እየተደረጉባቸውና አማራጭ መፍትሔዎች እየተፈለጉላቸው እነሆ ከዓመት በላይ ዘልቀዋል፡፡

እነዚህ ክልል ለመሆን በዞን ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀው ሕዝበ ውሳኔ ይደራጅላቸው ዘንድ በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት ጥያቄዎቻቸውን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቢያቀርቡም፣ እያንዳንዱ ዞን ክልል እንዲሆን መፍቀድ  እንደማያዋጣና አንድ አካባቢ ያሉ ዞኖች ተሰባስበው ክልል እንዲመሠርቱ መንግሥት ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በርካቶቹ ክልሎች በመልክዓ ምድርና በባህል ከሚጎራበቷቸው ዞኖች ጋር በጋራ ክልል ለመመሥረት የተስማሙ ቢሆንም፣ ራሳቸውን ችለው ክልል ለመመሥረት ፍላጎት ያላቸው ዞኖች ተስተውለዋል፡፡

ይኼንን በማስመልከት ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በደቡብ ክልል ለብቻቸው ክልል ለመሆን የጠየቁ ዞኖች እንዳሉ ሁሉ በርከት የሚሉት በቋንቋ፣ በባህልና በመልክዓ ምድር ከሚቀራረቧቸው ጋር በጋራ ክልል ለመመሥረት ፍላጎት አላቸው ብለው ነበር፡፡

ለብቻቸው ክልል ለመመሥረት ፍላጎት ካላቸውና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን ብቻ ተከትሎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ ዞኖች መካከል አንደኛው የወላይታ ዞን ሲሆን፣ የወላይታ ዞን ጥያቄን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ በተለይ የወላይታ ዞን ተወካዮች ጥያቄው የሕዝብ ነውና ምላሽ ይሰጠን በማለት የጠየቁ ሲሆን፣ በተለይ ተወካዮቹ የሚደረጉት ተደጋጋሚ ውይይቶችና ስብሰባዎች ለሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ምላሽ የሚሰጥባቸው ናቸው በሚል ተደጋጋሚ ትችቶች ያቀርቡ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ጊዜም ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተደረገው ስብሰባ በተመሳሳይ ለጥያቄው ይኼ ነው የሚባል መቋጫ ሳያበጅለት ወይም መግባባት ሳይደረስበት ተገባድዷል፡፡

ይኼ በእንዲህ እንዳለ የክልልነት ጥያቄው አንድ ዓመት ያለፈው በመሆኑና ጉዳዩ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በመቅረቡ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል በማለት ይመሠረታል ተብሎ ለሚጠበቀው አዲስ ክልል አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ተጀምሯል፡፡ በዚሁ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ላይ ለመወያየት በወላይታ ሶዶ ከተማ የወላይታ ጉታራ አዳራሽ ተሰባስበው የነበሩ የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ ከፍተኛ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) አመራሮች፣ የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) አመራሮች፣ ወትዋቾች እንዲሁም የወላይታ ክልል ምሥረታ ምክር ቤት አባላት እሑድ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በፌዴራልና በደቡብ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የእነዚህ ባለሥልጣናትና የተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች በድንገት በቁጥጥር ሥር መዋል ያስቆጣቸው የወላይታ ወጣቶች በተለይም በወላይታ ሶዶ፣ በቦዲቲና በአረካ ከተሞች ሠልፍ የወጡ ሲሆን፣ በእነዚህ ወጣቶችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት የአሥር ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና ከ20 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካባቢው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ይኼንን ክስተት በሚመለከት ወብን ባወጣው መግለጫ ‹‹የወላይታ ዞን አመራሮችና ከተለያየ አደረጃጀት የተውጣጡ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ አስተባባሪ ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላት በወላይታ ጉታራ ስብሰባ ላይ ባሉበት ወቅት ድንገት በመጣው የመከላከያ ኃይል ታፍነው ታስረዋል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹የፌዴራልና የደቡብ ክልል መንግሥታት የወላይታ ሕዝብ ሰላማዊ ጥያቄን ወደ ሁከት ለመቀየር የሚያደርጉትን ሕገወጥ ድርጊት እንዲያቆሙ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ የወላይታ ዞን አመራሮችና የወላይታ ክልል ምሥረታ ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላትን፣ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችንና በአጠቃላይ የሕዝቡ የትግል መሪዎችን በማሰር የሚቆም ትግል የለም፡፡ ፍትሐዊ፣ ሕገ መንግሥታዊና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም የወላይታ ሕዝብ ለሚጠይቀው ጥያቄ በሰላም ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አመራሮችንና ታጋዮችን የማሰር ዕርምጃ ፈጽሞ ሕገወጥና የመብት ጥሰት ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እስከሚሰጠውና በሰላም ስብሰባ እያካሔዱ ሳሉ በሕገወጥ መንገድ በወታደራዊ ከበባ የታሰሩ የወላይታ የሕዝብ የትግል መሪዎች እስኪፈቱ ድረስ ሁላችንም በአንድነት እስረኞች ነን፡፡ የታሰሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና የወላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) በሰጠው መግለጫ 28 የሚሆኑ ሰዎች ከአዳራሹ ተወስደው መታሰራቸውንና 21 ሰዎች ደግሞ በተከሰተው አመፅ ሳቢያ መሞታቸውን በመግለጽ፣ ‹‹ይኼ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሕግና ሥርዓትን በጠበቀ አካሄድ ያቀረበው በክልል ደረጃ የመደራጀት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዳያገኝ ለማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን እስከመጣስ የደረሰ ዕርምጃ ቢወስድም፣ ግፊቱን ተቋቁሞ ከሥርዓት ውጪ የሆነ እንቅስቃሴ ሳያሳይ በትዕግሥት የቆየ መሆኑ በማንም ዘንድ ይታወቃል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹በቁጥጥር ሥር የዋሉ የወላይታ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሥራ ባልደረቦቻቸው በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤›› በማለት ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሳቢያ በተፈጠረው ሁከት የሰው ሕይወት ያጠፉም በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግልን ሲል ጠይቋል፡፡

የደቡብ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ነቢዩ ኢሳያስ በበኩላቸው፣ እሑድ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት አሥር ሰዓት ገደማ 26 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በመግለጽ፣ አመራሮቹና ባለሙያዎቹ የተያዙት በዞኑ ሁከት ለመቀስቀስ በዝግጅት ላይ ስለመሆናቸው መረጃ በመገኘቱ ነው ብለዋል፡፡ ከደቡብ ቴሌቪዥን መግለጫ የሰጡት ሁለቱ ባለሥልጣናት አመራሮቹና ባለሙያዎቹ ኢ-መደበኛና ሕገወጥ ቡድኖችን በማደራጀት የጥፋት ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር ብለዋል፡፡

ባለሥልጣናቱ በሰጡት መግለጫ ‹‹አመራሮቹና ባለሙያዎቹ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ ለመክተት ከሚሠሩ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በመረጃ አረጋግጠናል፡፡ አመራሮቹ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም፣ ሊመለሱ ባለመቻላቸው በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ሥራ የተከናወነው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከአገር መከላከያ ሠራዊት የኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት ነው፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡

የወላይታ ዞን አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ወጣቶች በተደጋጋሚ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄያቸውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሠልፎችን ያደረጉ ሲሆን፣ የወላይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ የዞኑ አስተዳዳሪና ምክር ቤት ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫዎችን በማውጣት ጥያቄያቸውን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ በአንድ ወቅት በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የወላይታ የክልልነት ጥያቄ የመላው ወላይታ ሕዝብ መሆኑን እስካሁን በተገኘንበት በመንግሥትም ሆነ በድርጅት መድረኮች ሁሉ የሰፊው ሕዝብ ጥያቄን በታማኝነት ሳይሸራረፍ እየገለጽን እንገኛለን፡፡ ስለሆነም የወላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት ጥያቄ በቅርቡ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ዕውን እንደሚሆን ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጥያቄው በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃም እውነተኛ መሆኑ ተረጋግጧል፤›› ብለው ነበር፡፡

በተመሳሳይ የወላይታ ምሁራን ማኅበር በህዳር ወር 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ‹‹የወላይታ ዞን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ያቀረበው የብሔሩ የክልል ጥያቄ ሆን ተብሎ ታፍኖ መቆየቱ ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ ከመሆኑም በላይ፣ የወላይታን ሕዝብ ክብር የሚነካ መሆኑን በመገንዘብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ በሕዝባዊው ጉዳይ ላይ ዳግም ተወያይቶ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ፣ ምናልባትም ሕጋዊ ተገቢነት ካለው ለመብትና ነፃነት ጥያቄው የክልሉ ምክር ቤትና መንግሥት አፋጣኝ ሕጋዊ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ዳግም ጥያቄ እንዲያቀርብ ምክር ቤታችን አበክሮ ያሳስባል፤›› በማለት ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

በሌላ ወገን የወላይታ ዞን ምክር ቤት በአራተኛ ዙር ሰባተኛ ዓመት አንደኛ አስቸኳይ ጉባዔውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የወላይታ ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን ለነበሩ መንግሥታዊ መዋቅሮች ሕዝቡ በክልል የመደራጀት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እያቀረበ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ በወላይታ ዞን በሚገኙ በሁሉም ቀበሌያት የሕዝብ ምክር ቤቶች በመወያየት ጥያቄውን ለብሔሩ ምክር ቤት በታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. አቅርቦ በሙሉ ድምፅ ፀድቆ ለክልሉ ምክር ቤት መላኩ ይታወቃል፡፡ ሆኖም የክልሉ ምክር ቤት ወቅቱን ጠብቆ ጉባዔ ባለማካሄዱ የሕዝባችን ጥያቄ ለምክር ቤቱ እንዳይቀርብ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወቅቱን ያልጠበቁ ጉባዔዎችን ቢያካሄድም፣ የሕዝባችን ጥያቄ እንዳይቀርብ ከማድረግ ባሻገር የተከበረው የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በምክር ቤቱ አጀንዳ ተይዞ ውይይት እንዲደረግ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድል ሲጠይቁ ጭምር በመከልከል አፍኖ እንዳይቀርብ ተደርጓል፤›› በማለት ወቅሷል፡፡ ‹‹የደቡብ ክልል ምክር ቤት የወላይታ ብሔር ክልል የመመሥረት ጥያቄ ጉዳዩ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሳያስተላልፍ መቆየቱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ፣ የተከበረው የዞኑ ምክር ቤት ሁኔታውን ያወግዛል፤›› ብሏል፡፡

ምክር ቤቱ በተጨማሪ ‹‹የወላይታ ሕዝብ ፍጹም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ተከትሎ እየጠየቀ ያለውን ጥያቄ በመንግሥት በኩል ትኩረት ባለመስጠት የሕዝብን ድምፅ በሰላማዊ መንገድ ከመመለስ ይልቅ የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ የሚደረግ ዝግጅት ተቀባይነት የለውም፤›› ብሎ መውቀሱ የሚታወስ ነው፡፡

በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ መሆናቸውንና ጥያቄዎቹ እየቀረቡ ያሉትም ሕግን ተከትሎ መሆኑን በተደጋጋ የሚገልጹ ባለሙያዎች፣ ጥያቄዎቹ ምላሽ ሳያገኙ በመዘግየታቸው ሳቢያ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማስወገድ ይገባል ይላሉ፡፡ ይኼንን በማድረግም መንግሥት በሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ተከትለው የደረሱ ጥፋቶች በሌላ ሥፍራ እንዳይደገሙ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበት በማሳሰብ፣ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠትም የሚቻለውን ሰላማዊ መንገድ ብቻ በመከተል መሆኑን  ያስገነዝባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -