Monday, June 17, 2024

ፖለቲከኞች በእሳት ላይ ቤንዚን አታርከፍክፉ!

አሁንም የሕዝብን ሰላምና የአገርን ብሔራዊ ደኅንነት የሚፈታተኑ ድርጊቶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ የሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ዕልቂትና ውድመት እስካሁን ወላፈኑ እየተጋረፈ፣ ወላይታ ውስጥ እየደረሰ ያለው ሞትና የፀጥታ ሁኔታ በጣም ያሳስባል፡፡ በቅጡ ተቀምጠው ለመነጋገርና ለመደማመጥ የማይፈልጉ ፖለቲከኞች፣ ዛሬም በንፁኃን ደም ሒሳባቸውን ለማወራረድ ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት ከመፈጸም እንደማይመለሱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ አንድ ዓላማ ለማስፈጸም የተነሳ ማንኛውም ፖለቲከኛ፣ ከምንም ነገር በፊት የሰላማዊ ፖለቲካ ወጉ ሕዝብን ማክበር እንደሆነ ጠንቅቆ መረዳት ይገባዋል፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሁከትን የዓላማ ማስፈጸሚያ ለማድረግ መሞከር ውጤቱ አደጋ ነው፡፡ ይህ ችግር ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን ገዥው ብልፅግና ፓርቲን ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ሥልጣን ለመያዝ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችም ሆኑ፣ ሥልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሚፈጥሩ ተግባራት ውስጥ ሲሰማሩ ግድያና ውድመት የየዕለት ዜና ይሆናሉ፡፡ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች፣ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ባህል ባዕድ መሆንን አመላካች ናቸው፡፡ ለሰላም እጅን ከመዘርጋት ይልቅ እሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ እየቀለለ ነው፡፡

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ሦስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መታገዳቸውን ፓርቲው አካሄድኩት ካለው ግምገማ በኋላ አስታውቋል፡፡ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት፣ ሚስጥር በማባከንና በግጭት ተሳትፎ ስማቸው በመነሳቱና በመሳሰሉት የታገዱት ኃላፊዎች ጉዳይ ወደፊት በሕግ ጭምር የሚታይ ቢሆንም፣ ከፖለቲካ አሠላለፍ ጀምሮ በተለያዩ ክስተቶች የአገሪቱ ፖለቲካ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ አመላካች ነው፡፡ የንድፈ ሐሳብና የተግባር አንድነት የሌላቸው ሰዎች አንድ ፓርቲ ውስጥ ታጭቀው እርስ በርስ የሚነካከሱ ከሆነ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚፎካከሩት ምን ሊደራረጉ እንደሚችሉ ለመገመት አያዳግትም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሥልጣኔ አልገባ ብሎ፣ ዛሬም ‹‹ለምሳ ያሰቡንን ቁርስ አደረግናቸው›› ዓይነት ትርክቶችን መስማት ያስደነግጣል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራው አባላትን በጥራት ከመመልመል፣ ሥልጠና ከመስጠትና ሕዝባዊነትን ከማላበስ መሠረታዊ ተልዕኮ አፈንግጦ፣ ሁሉም ነገር መነሻውና መድረሻው ሴራ ማጠንጠን ሲሆን ከመግረም አልፎ ያሳዝናል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ብልሹ የሴራ ፖለቲካ ንፁኃን ሕይወታቸውን ሲገብሩ ያንገበግባል፡፡ ለአገር ግንባታ የሚረዱ በርካታ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተዘንግተው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ብቻ ሲዘረጋና ሲታጠፍ ማየትም ያስተዛዝባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ናቸው በአገሪቱ ላይ እሳት እያበዙ ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ተቆጥረው የማያልቁ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ለማንም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ እነዚህን ችግሮች የሚረዳ ማንኛውም ቅን ዜጋ ባሉት ላይ ሌላ ከመጨመር ይልቅ፣ ችግሮቹ ደረጃ በደረጃ እንዴት ቢፈቱ ይሻላል በማለት ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ነው የሚያቀርበው፡፡ ይህ ኃላፊነት የሚሰማው ሰብዓዊ ፍጡር የሚያደርገው ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ከዚህ በተቃራኒ ባሉት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮችን እየቀፈቀፉ፣ አገርን ቁምስቅሏን የሚያበዙ በመበርከታቸው ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ አማራጮች የሌሉዋቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና አመራሮቻቸው፣ አሁንም ድረስ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን እያጦዙ አገር ያምሳሉ፡፡ በዚህ ጦስም ንፁኃን ሕይወታቸውን ይገብራሉ፡፡ የደሃ አገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁከት፣ ጥቃት፣ ግድያና ማፈናቀል የዘወትር ተግባር እየሆኑ ያሉት፣ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች የግጭት ነጋዴዎች ስለሆኑ ነው፡፡ እንወክለዋለን ለሚሉት ማኅበረሰብ የሚጠቅም ተግባር ከማከናወን ይልቅ፣ በስሙ እየነገዱ ሕይወቱን ያመሰቃቅላሉ፡፡ ወጣቶችን ራዕይ አልባ በማድረግ ወንጀል ያስፈጽሙዋቸዋል፡፡ ሕዝብ ሲናቅ ትውልዱ እሳት አንዳጅ እንዲሆን ይፈረድበታል፡፡

ቂም ባረገዘ ውዝግብ ምክንያት ምርጫንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማስታከክ በብልፅግና ፓርቲና በሕወሓት አመራሮች መካከል የሚስተዋለው አደገኛ ፍጥጫ፣ በኦሮሚያ ክልል የበላይ ለመሆን የሚደረገው አስደንጋጭ የፖለቲካ ሽኩቻ፣ በደቡብ በክልልነት ጥያቄ ሳቢያ በተደጋጋሚ የሚታዩ ደም አፋሳሽ ግጭቶች፣ በወሰንና በማንነት ጉዳዮች መቋጫ ማግኘት ያልቻሉ ችግሮችና የመሳሰሉት ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ እየገፉዋት ነው፡፡ በዚህ ላይ በተለያዩ መንገዶች እየሾለኩ የሚወጡ አደገኛ መረጃዎች ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ እየሆኑ ነው፡፡ ለአገር ደንታ ከሌላቸው እስከ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፖለቲከኞች የተሰገሰጉበት የፖለቲካ ምኅዳር፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈሪ እየሆነ ነው፡፡ ለአገር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ነገር ግን በውጤታቸው አገር ከማፍረስ የማይመለሱ ድርጊቶች መብዛታቸው፣ ከተስፋ ብርሃን ይልቅ ድቅድቅ ጨለማ የበለጠ ብርታት እንዲያገኝ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፡፡ በሐሳብ ተሟግቶ በሕዝብ ህሊና መዳኘትን የመሰለ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እያለ፣ የጦር መሣሪያን እንደ ጌጥ ማሳየት ነውር አልሆን ያለበት ጊዜ ላይ መደረሱ የፖለቲካውን መበላሸት ነው የሚያመላክተው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ነገር አለማፈር ያስገርማል፡፡ ሕዝብ ቢከበር ኖሮ ይህ አይሞከርም ነበር፡፡ ነገር ግን በእሳት መጫወት ባህል እየሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በስሙ ሲነገድበትና ሲቆመርበት ዘመናት ለመንጎዳቸው ዋነኛው ማሳያ፣ የፖለቲካ ልሂቃን አንድም ቀን በአንድነት ቆመው ለብሔራዊ ጉዳዮች በኅብረት ድምፃቸው አለመሰማቱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ዓርማ ለሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ አሁን በመጠኑ ተሻሻለ እንጂ የነበረው አመለካከት ተቃራኒ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ለጠላት ተላላኪ ሆነው የመጀመሪያውን ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ለማስተጓጎል ከሞከሩት ጀምሮ እስከ ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ አስተጋቢዎች ድረስ፣ በግድቡ አገራዊ ፕሮጀክትነት ላይ ሸውራራ አመለካከት ያላቸው አሉ፡፡ ወጣቱን ትውልድ በዕውቀት በመቅረፅ አገር ተረካቢ የማድረግ ታላቅ ዓላማ በመጥለፍ፣ የከሸፈና ዘመኑን የማይዋጅ ትርክት በማስታጠቅ አገርና ሕዝብ ላይ የሚያዘምቱ ፖለቲከኞች መኖር ሌላው ማሳያ ነው፡፡ ከአፍሪካውያን አልፋ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነ ታላቅ ተጋድሎ ከኮሎኒያሊስቶች ጋር ያደረገችን ታላቅ አገር፣ አስፀያፊና ነውረኛ በሆነ ዘረኝነት መቀመቅ ለመክተት የሚዳዱ ፖለቲከኞች መኖራቸው በይፋ የሚታወቅ ነው፡፡ ለሕዝብ ክብርና ለአገር ህልውና የማይጨነቁ ደንታቢስ ፖለቲከኞች እሳት ይዘው መዞራቸው የሚያመላክተው፣ ኢትዮጵያ በጣም ከባድ ጊዜ ውስጥ እንዳለች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ዘመን ነውጥ ሳይሆን ክብር ነበር የሚገባው፡፡ ይህ አገሩን ከራሱ አስበልጦ የሚወድ ሕዝብ ለአገር ደንታ በሌላቸው ፖለቲከኞች እየታመሰ ነው፡፡ ትዕግሥት፣ አስተዋይነት፣ ጨዋነትና ታጋሽነት የተፈጥሮ በረከቶቹ የሆነው ሕዝብ በፖለቲከኞች ተንቋል፣ ተዋርዷል፡፡ አገርን ከገባችበት የድህነት ማጥ ውስጥ ጎትተው ለማውጣት ራዕይ የሌላቸው ፖለቲከኞች፣ መሥራት የሚገባቸውን እጆች እሳት እያስያዙ አገር ያስወድማሉ፡፡ ወጣቶችን በወገኖቻቸው ላይ እያዘመቱ ዕልቂት ያውጃሉ፡፡ በሰላማዊ ሥልጡን የፖለቲካ የትግል ሥልት ሊፈቱ የሚችሉ መናኛ ችግሮችን ሰበብ እያደረጉ፣ ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም ሲሉ ብቻ አገርን የሲኦል ምድጃ ለማድረግ እየተቅበዘበዙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የፈሰሰው የንፁኃን ደምና የወደመው ንብረት አልበቃ ብሎ ዛሬም ሌላ ዙር ክተት የሚታወጀው፣ እሳቱ ከማይደርስበት ሥፍራ በብዙ ሺሕ ማይልስ ርቀት ላይ ባሉ አድሮ ቃሪያ ፖለቲከኞች ጭምር ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ለመንግሥት ሲያሸበሽቡ የነበሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ በቀቢፀ ተስፋ ሥልጣን ሲያልሙ የሰነበቱ መሆናቸው ነው የሚገርመው፡፡ እነዚህ ዋነኛ ግባቸው ሥልጣን ስለሆነ በሕዝብ ስም ሲምሉና ሲገዘቱ መስማት ያስደነግጣል፡፡ ለሕዝብ ክብር ቢኖራቸው ኖሮ ከእነ ነውራቸው አደባባይ አይታዩም ነበር፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ግን በዝምታ ሁሉንም ነገር እየታዘቡ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፖለቲከኞች እባካችሁ ሕዝብ አክብሩ ከመባል ታልፎ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን አታርከፍክፉ የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...