Saturday, June 22, 2024

መንግሥት ሰላም በማስፈን አገር ማረጋጋት ግዴታው ነው!

የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ከሚወስኑ መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ የአገር ህልውናም ሆነ የሕዝብ ደኅንነት የሚወሰነው በሰላም ነው፡፡ ሰላም ከሌለ መንግሥት አይኖርም፡፡ ይኖራል ተብሎ ቢታሰብ እንኳ የጉልበተኞች ስብስብ ነው የሚሆነው፡፡ ሰላም የህልውና ዋልታና ማገር ቢሆንም በቀላሉ የሚገኝ ግን አይደለም፡፡ ሰላም እንዲሰፍን በሕዝብ መካከል መተማመን ሊኖር ይገባል፡፡ ልሂቃን በአገር ጉዳይ በግልጽ መነጋገር መቻል አለባቸው፡፡ ልዩነቶች በእኩልነት ተስተናግደው የተሻለ ሐሳብ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ሰላም እንዴት ይስፈን የሚለው ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ አገርን እስከሚመሩ ሰዎች ድረስ ለሰላም ትልቅ ዋጋ መስጠት አለባቸው፡፡ መንግሥት ጥያቄዎች ቀርበውለት በሕጋዊ መንገድ መመለስ ሲኖርበት ዳተኛ ከሆነ፣ ጥያቄ አቅራቢዎች ሌላ አማራጭ ሲፈልጉ ግጭት ይፈጠራል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ጥያቄዎችን ማቅረብ ያለባቸው ኃይልን ተጨማሪ አማራጭ ሲያደርጉ፣ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ሲል የኃይል ዕርምጃ ውስጥ ይገባል፡፡ ግለሰቦች በማኅበራዊ ትስስሮችም ሆነ በተለያዩ ዘዴዎች ሐሰተኛ ወሬዎችን ሲያሠራጩ፣ በስሜት የሚጋልቡ ሰዎችን በማነሳሳት ጥፋት እንዲፈጸም ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ሲቻል ልዩነት ቢኖር እንኳ የጋራ አማካይ መፍጠር አያዳግትም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ከእጅ እያመለጠ ያለው ፀጋ ይህ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት አገር ሰላም እንዲሰፍን ጠንክሮ መሥራት ያለበት፡፡ ግዴታውም ነው፡፡

ከመንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ግለሰብ ድረስ ከብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በአገር ህልውና ላይ መቆመር የሚፈልጉ ግለሰቦችና ስብስቦች የብሽሽቅ ፖለቲካውን የሚያደሩት፣ ለገዛ ጥቅሞቻቸው ሲሉ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ለአገር አንዳችም አስተዋጽኦ አበርክተው የማያውቁ ወገኖች በሕዝብ ስም ሲነግዱ፣ ለሚፈጠረው ቀውስ ኃላፊነት አይወስዱም፡፡ ይልቁንም ከቀውሱ ለማትረፍ ይፈልጋሉ፡፡ እያደረጉ ያሉትም ይኼንን ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ይዘው ቀውስ ፈጣሪዎችን የሚፈሩ ወይም የሚታዘዙ አሉ፡፡ በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመተላለፍ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙም አሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን ለግልና ለቢጤዎች ጥቅም ማግበስበሻ የሚያደርጉም እንዲሁ፡፡ በዚህ መሀል ተገፍተናል የሚሉ ወገኖች ቅሬታ ሲያቀርቡ ወይም መብቶቻቸውን ሲጠይቁ፣ የብሽሽቅ ፖለቲካውም ይጀመራል፡፡ ብሔር፣ እምነት፣ የፖለቲካ አቋምና ቋንቋ ሳይቀሩ ለግብዓትነት ይውላሉ፡፡ ፖለቲካው መሠልጠን ሲገባው የመንደር ጨዋታ ይመስል በየጎራው መሰዳደቡ፣ ዛቻውና ማስፈራራቱ የበላይነት ይይዛል፡፡ እንኳንስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ለመጣል ለአገር ህልውና አደገኛ የሆኑ የቃላት ጦርነቶች ይጀመራሉ፡፡ የብሽሽቅ ፖለቲካው ማንነትንና እምነትን ማጥቂያ እየተደረገ፣ አገሪቱን ወደ እሳት ምድጃነት ለመለወጥ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ፡፡ ይህ በፍፁም ከዚህ ዘመን ሰዎች የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ ለአገርም አይበጅም፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርበትም፡፡ ከማንም በላይ ደግሞ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ሰላማዊ ሐዲዱን ስቶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሲነጉድ፣ በሴራ ትንተናዎች እየታጀበ ሁከት ቅስቀሳ ውስጥ ይሰማራል፡፡ ሁከቱ ያገኘውን እያዳረሰ ወደ ግጭት ሲቀየር፣ ሃይማኖትና ብሔር እያጣቀሰ ባገኘው አቅጣጫ ይፈሳል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ከምንም ነገር በላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ስምምነቱ የሚመነጨው ደግሞ ለልዩነት ዕውቅና በመስጠትና የጋራ አማካይ በመፈለግ ነው፡፡ ይህንን አማካይ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ካልተቻለ ግን ከመቀራረብ ይልቅ መለያየት፣ ከመነጋገር ይልቅ መተናነቅ፣ ከመተባበር ይልቅ ጠላትነትን ማጠናከር የዘወትር ተግባር ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች እያጋጠሙ ያሉ ሁከቶችና ግጭቶች፣ ለሰላማዊ ፖለቲካ ዕድል ለመስጠት ካለመፈለግ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር የግጭት ሰለባ እየሆኑ ተማሪዎች ተገድለዋል፡፡ የፖለቲካው ቁማር ሒሳብ የሚወራረደው በንፁኃን ደም ስለሆነ፣ አንዳች ችግር ሲያጋጥም ተቀምጦ በሥርዓት መነጋገር አይፈለግም፡፡ ማስፈራሪያው መንገዶችን መዝጋት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን መበጥበጥ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የጦር ቀጣና ማድረግ፣ የንፁኃንን ሕይወት መቅጠፍና የሕዝብና የአገር ንብረት ማውደም ነው፡፡ የሥልጣኔ ጮራ ያልፈነጠቀበት የአገሪቱ ፖለቲካ ለዴሞክራሲ ባህል ባዕድ በመሆኑ፣ ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ተስፋ እየደበዘዘ የቀውስ ሥጋት አገሩን ተቆጣጥሮታል፡፡ አገርን ማረጋጋት አለመቻል መዘዙ የከፋ ስለሆነ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሆኖ መላ ማበጀት ግዴታው ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና ዓላማቸውን እንደያዙ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ግን መስማማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ስምምነት በተወሰኑ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በመላ አገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማካተት አለበት፡፡ በተለይ የአገሪቱ ገጽታ በደም አፋሳሽ ግጭቶች ችግር ውስጥ በወደቀበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ ማስፈራሪያዎች በግልጽ ሲለፈፉና የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት እነዚህን አደገኛ ድርጊቶች ለማስቆም በአንድነት ካልተነሱ ፋይዳቸው ምንድነው? ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ሥርዓት በማስያዝ ከግጭት ቀስቃሽነትም ሆነ አስተጋቢነት ካልገቷቸው ምን ይጠቅማሉ? ሌላው ቀርቶ የአገር ህልውናና የሕዝብ ደኅንነት ካላሳሰባቸው ምን ይሠራሉ? ልዩነቶቻቸው ላይ ብቻ አተኩረው የአገር አንድነት አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ዝም የሚሉ ከሆነ ምን ይረባሉ? የአገር ሰላም፣ አንድነትና የሕዝብ ዘለቄታዊ ደኅንነት አሳስቧቸው በኅብረት ካልሠሩ እንደሌሉ ይቁጠሩት፡፡ አገር ካልተረጋጋች እነሱም ዋጋ የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል የብሔርና የእምነት ክፍፍል በመፍጠር ጥቃት የሚያስፈጽሙ ኃይሎች ዓላማቸው በሚፈልጉት ደረጃ ሳይሳካ ሲቀር፣ አንዱ ብሔር ወይም እምነት በሌላው ላይ ጥቃት እንደፈጸመ በማስመሰል ሌላ ዙር ቅስቀሳ ሲያደርጉ መታለል አይገባም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ዋናው የሚፈለገው ግጭቱን ማቀጣጠል ስለሆነ፣ በተለይ መንግሥት ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀው መገንዘብ አለበት፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት ሲኖርበት፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅነነት የማስጠበቅ ግዴታም አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን አለው፡፡ በዚህ ሥልጣኑ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ግዴታው ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ብልኃትና ጥበብ ቢያስፈልገውም፣ ሕግ የማስከበር ተግባሩ ግን ፈፅሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ የዜጎችን መብቶችና ነፃነት የማክበር ሥራው ሳይዘነጋ፣ ሕገወጥ ድርጊቶችን በሕግ አደብ ማስገዛት የግድ ነው፡፡ በተለይ የአገርን ሰላም የሚያናውፅ፣ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ድርጊት ሲያጋጥም ኃላፊነትን መዘንጋት ያስጠይቃል፡፡ በዚህ ጊዜ በርካቶች መንግሥት ለምን ሕግ አያስከብርም ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥት ሕግ ማስከበር ተስኖት ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ንፁኃን ሲገደሉ፣ ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ ሲፈናቀሉና ሲዘረፉ፣ እንዲሁም የአገር ንብረት ሲወድም በስፋት ተስተውሏል፡፡ ጥቃቶቹ አድማሳቸውን እያሰፉ ወደ አገር ወደ ማፍረስ እያመሩ ነው፡፡ የንፁኃን ሕይወት በከንቱ እየጠፋ አገር ችግር ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ችግሮች ከማጋጠማቸው በፊት የተበላሹ አሠራሮችን ማስተካከል፣ በወቅቱ መመለስ ያለባቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ማስተናገድና ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ድርጊቶችን ማስወገድ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ወጣቶች የአገርን አቅምና ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘቡ ጥያቄዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ፣ አገርን ችግር ውስጥ ከሚከቱ ድርጊቶች ለመቆጠብ በንቁ አዕምሮ ነገሮችን መመርመር አለባቸው፡፡ የአገር ሰላም ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ የመንግሥት ያለህ ሲባል ደግሞ፣ መንግሥት ሕግ አክብሮ በማስከበር መኖሩን ማሳየት አለበት፡፡ ከአገር ሰላምና ህልውና የሚቀድም የለም፡፡

የአገርን ሰላም በማደፍረስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ኃይሎች ስለመኖራቸው በተደጋጋሚ ብዙ ተብሎበታል፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሐሰተኛ መረጃዎችንና ምሥሎችን ከሚያሰራጩ ጀምሮ፣ እጃቸውን በማስረዘም ግጭቶችን በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች የሚያበረታቱ አሉ፡፡ እነዚህ የራሳቸው ጥቅም እንዳይጓደል ተግተው የሚሠሩ ኃይሎች፣ የእነሱ ዓላማ እንዲሳካ ማንኛውንም ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር ከፋፍለው ከማጋጨት አልፈው፣ ቤተ እምነቶችን እያቃጠሉ የሃይማኖት ጦርነት ለማስነሳት ሰይጣናዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበሩ መልካም እሴቶችን በመሸርሸር ጥርጣሬና አለመተማን እየፈጠሩ ነው፡፡ የብዙኃኑን ዝምታና ችላ ባይነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አጥፊ ቅስቀሳዎችን ያደርጋሉ፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ ይነዛሉ፡፡ ማመዛዘን የማይችሉ ግለሰቦችን እየተጠቀሙ ሁከት ያስነሳሉ፡፡ በስሜት እየኮረኮሩ ለውድመት ያሰማራሉ፡፡ ለዘመናት ተሳስሮ የኖረውን ሕዝብ ለማለያየት አስፀያፊ ስድቦችን ያሠራጫሉ፡፡ ቁጡዎችንና በስሜት የሚነዱትን ለአፀፋ እያዘጋጁ ግጭት ይቀሰቅሳሉ፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እነዚህ ኃይሎች ይታወቃሉ፡፡ ምን እንደሚፈልጉም ይታወቃል፡፡ አገርን ማረጋጋት ከተፈለገ ሕጋዊ መንገዶችን በሚገባ መጠቀም ይቻላል፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብም በየአቅጣጫው መንግሥትን እየጠየቀ ያለው ይህንን ነው፡፡

ኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ አሁን እንደሚታየው በሁከትና በውድመት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምትነግዱ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አፈንግጣችሁ የማንን ዓላማ ነው የምታሳኩት? ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ያለው ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አይደለም፡፡ ስለትናንቱ አይረቤ ጉዳይ ከመነታረክ ነገ የሚፈጠረውን የተሻለ ሥርዓት ማለም ነው የሚበጀው፡፡ ይህ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው በሕዝብ ድምፅ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ፀባይ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ዓይንና እጅን በሕገወጥ መንገድ የሚገኝ ሥልጣንና ገንዘብ ላይ አድርጎ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ሥልጣንና ገንዘብ አያማልላቸውም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ከአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በታች እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እያነሳሱ አያጋድሉም፡፡ የአገርን ሰላም እያደፈረሱ ቀውስ አይፈጥሩም፡፡ ከሴራና ከአሻጥር የፀዱ በመሆናቸው ተግባራቸው ግልጽ ነው፡፡ ጨለማ ውስጥ መሽገው አገር አይበጠብጡም፡፡ ከእንዲህ ዓይነት የማይረባ ድርጊት ነፃ ነን የምትሉ አገር አረጋጉ፡፡ ከአገር መረጋጋት በላይ የሚቀድም ነገር የለ፡፡ መንግሥት ደግሞ ከማንም በላይ ግዴታም ኃላፊነትም ስላለበት፣ ሰላም በማስፈን አገር ማረጋጋት ይኖርበታል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...