Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአገር ጉዳይ ሲሆን ከልብ ያሟግታል!

ሰላም! ሰላም! በቀደም ዕለት እንዲያው ግራ ግብት ብሎኝ የሆድ የሆዴን የማጫውተው ሰው ብፈልግ አጣሁ። የባሻዬ ልጅ ሥር ሥር እያለ ቀልቡ ከእሱ የለም። ባሻዬ የተጣላ ሲያስታርቁ ቀብር ሲደርሱ ዕድሩን ሲያመሩ ጊዜ አጡ። ነገሩ ዙሪያን ባስስ ባስስ ሆነብኝ። እናንተ ሆናችሁብኝ እንጂ ሰው በሞላበት አገር ሰው አጣሁ ብሎ ማውራትም እኮ ያሳፍራል። ኋላ ዘወር ስል አንድ መጽሐፍ አዟሪ መጽሐፍ ብሎ አንድ ‹‹ወዳጄ ልቤ›› የሚል ርዕስ አስነበበኝ። ባሻዬ እግዜር የሚናገርለት ሰው ቢያጣ ድንጋይ ያናግራል የሚሉት ነገር ትዝ ብሎኝ፣ መዥረጥ አድርጌ ከኪሴ ብር አወጣሁና መጽሐፉን ገዛሁት። ግን እውነቴን ነው የምነግራችሁ እስካሁን አላነበብኩትም። በቆምኩበት ለአንድ ዘመናዊ ሲኖትራክ ገልባጭ መኪና ግብይት የቀጠርኳቸውን ሰዎች እየጠበቅኩ ከልቤ ጋር ጨዋታ ያዝኩ። ‹እሳትስ ይነዳል እንጨት ካልገደዱ፣ ሰው ከርሞ ይርቃል ልብ ነው ዘመዱ› ተብሎ አይደል። ታዲያ ለንባብ ግድ የሌለው ትውልድ አባል ሆኜ መቆጠሬ እያንገበገበኝ መንገዴን ስቀጥል፣ ማንበብ ለምን ብርቅ ሆኖ ያነጋግረናል የሚለው ሐሳብ ውልብ ይልብኛል፡፡ ከማንበብ ይልቅ ከአፍ ወደ አፍ እንደ ሰደድ እሳት የሚግለበለበው ወሬ ጆሮ ጠገብ ሲሆን፣ የብዙዎች ከንቱ ሆኖ መቅረት ምክንያቱ ይገባኛል፡፡ የደላላ ጭንቅላቴ እንዳይፈነዳ እየተጨነቅኩ ሳዘግም ለካ ከገዛ ልቤ ጋር ወግ ይዣለሁ፡፡ በአገር ጉዳይ ሲሆን ደግሞ ከራስ ጋር መነጋገር መልካም ነው!

ታዲያ ብቸኝነቴ ሳላውቀው ጨምድዶ ይዞኝ ከልቤ ጋር ጨዋታ መያዜ የበለጠ ብቸኛ አደረገኝ። ወጭ ወራጁን ስታዩት የገዛ ራሱን ልብ እየረሳ ልብ የሚልም ጠፍቷል። እንዲያውም ካነሳነው አይቀር ሰው ልቡ የሚመክረውን ከመስማት የሰው ምክር እየሰማ መስሎኝ መከራ እየመከረ ያስቸገረው። እውነቴን እኮ ነው። ልብ ይስጠን ነው መቼም። ታዲያ አጫውተኝ ያልኩት ልቤ በጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ እያስከተለ ሕመሜን አባሰው። ‘ምነው ሰው ሁሉ ነፍሴ እርቃኑዋን ቀረች ይለኛል?’ ይለኛል። ‘እባክህ ተወኝ’ ስለው ‘ምነው ፍቅር ቀዘቀዘች?’ ይለኛል። ‘እኔ ምን አውቄ’ ስለው ‘ምነው እንዲህ እነ አቶ ውሸት፣ እነ እሜቴ ምቀኝነት፣ እነ ፍቅረ ንዋይና ከራስ በላይ ንፋስ ናኙ?’ ይለኛል። ‘ጉድ ነው’ እላለሁ አፍ አውጥቼ። ታዲያ ከልቤ አስጥሉኝ ብዬ አልጮህ። ለነገሩ ብንጮህም የሚጥለን እንጂ የሚያስጥለን ጠፍቷል። ወይ ልቤና እኔ፡፡ የልቤን ሙግት ችዬው በአንክሮ ሳዳምጠው ለካ ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ ለምሳሌ ልቤ አባትና እናቴን አስታወሰኝ፡፡ ‹አንበርብር አደራህን ክፉ ነገር ሠርተህ በዕድር ስማችንን እንዳታስነሳው…› የሚሉኝን በለሆሳስ ሲነግረኝ፣ የዛሬን አያድርገውና የዕድሜ እኩዮቼና የታላላቆቻችን ወላጆች የጋራ አደራ እንደሆነ ሳስብ ሆድ ባሰኝ፡፡ ይኼኔ አገራችን እኮ፣ ‹አደራ ልጆቼ እንዳታዋርዱኝ› ትለን ይሆናል፡፡ እኔም አደራ ልብ በሉ ልበል እንጂ!

መኖር መቼም ደግ ነው። በመቆየት ብዙ አየን። ያደላቸው ደግሞ ላላዩት ጭምር ያሳያሉ። እሱን ‘ፀጋ’ ብሎ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም። የምር ግን እያዩ የማያዩ፣ እየሰሙ የማይሰሙ ሰዎች ቁጥር አልበዛባችሁም? ባልኖርንበት ዘመን ታሪክ የምንደባደብ ዘመነኛ ሰዎች መንገዱን ሞልተነው ምነው የሚል መጥፋቱስ አይገርምም? በቀደም አንድ ወዳጄን እንዲህ ብለው ቁም ነገሩን ስቶ፣ “ተው እንጂ አንበርብር የታክሲው አንሶ አንተ ደግሞ መንገዱን አትሙላው እንጂ፣ የት ልንሠለፍ ነው?” ብሎ አፌዘብኝ። እንዲህ እየተጠማዘዝን ነው ታሪክ እያጣመምን የምንነጃሰው፡፡ ዘመን መቼም ብዙ ብዙ ምዕራፍ እንዳለው አውቃለሁ። ግን እንዲህ እያነሳን እየጣልን ነገር ሁሉ በፌዝ የሚታጀብበት ምዕራፍ እንዳለው አልጠረጥርም ነበር። ብዙ ጊዜ እኮ ቁም ነገሩን የምንስተው ፌዝ እየደባለቅን ሆኗል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ይኼንን ትችት ሰምቶ፣ ‹‹አሁንስ አበዛኸው!›› አለኝ። ‹‹ምን ብዬ አበዛሁት? ስንት ያበዙት እያሉ አንተስ እኔን ለመገሰፅ ለምን አበዛኸው?›› ስለው፣ ‹‹ቆይ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? የትውልዱ እጥር ምጥን ያለች የኑሮ ዘይቤ መፈክር ምንድናት?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹ፎካሪዎቹ እንጂ እኔ ምን አውቄ…›› ስለው ‹‹አታካብድ ትባላለች…›› ብሎ ወደ ትንታኔው ገባ። ‹‹እንግዲህ ይኼ ትውልድ የከበደ ነገር ላይቀበልና ላይደራደር ወደ እዚህ የዓለም ታሪክ ምዕራፍ የመጣ እስኪመስል ማካበድ አይወድም። ሌላው ቀርቶ የተቆለለ ተራራ፣ እግዚኦ የሚያስብል ደመና ሲያይ አይወድም። ዘመኑም ይኼን አውቆ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሲበሉት ቀላል፣ ሲለብሱት ቀላል፣ ሲነካኩት በቀላሉ፣ ሲያላምጡት በቀላሉ፣ እንዲሁም በቀላሉ የሚዋጡ ነገሮችን የሚያመርት አዕምሮ አስነስቷል…›› አለኝ። ሳስበው ተዋጠልኝም አልተዋጠልኝ ያለው እውነት አለው። እያዩ ያለ ማያት እየሰሙ ያለ መስማት ጉዳይም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ታየኝ። አቃለን አቃለን ይኼው ቀለን የምኖረውን ቤት ይቁጠረን። እውነቴን እኮ ነው። ብቻ የዚህ ዓለም የቅሌት መዝገብ የተከፈተ ቀን እንደ ለመደብን ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆነን እንዳንገኝ ፀልዩ አደራ፡፡ ለፀሎት ጊዜ መስጠት ያስፈልገናል!

የዚህ አቃሎ የመቅለለ የዘመኑ ፎርሙላ ነገር ትዝ ብሎ ልቤን ‹ሳይለንት› አድርጌ ሳስብ ሳለሁ ውዷ ማንጠግቦሽ ደወለች። ‹‹ወዬ የእኔ ፍቅር!›› ስላት፣ ‹‹ውዴ አንበርብር ሆይ ኮሮና ስለበረታ በጊዜ ተሰብሰብ ለማለት ነው የደወልኩልህ…›› ስትለኝ ልቤ በድንጋጤ ብርክ የያዘው መሰኝ፡፡ ግን ልቤ በድፍረት ጀመረኝ፡፡ ‹አንበርብር ተጠንቀቅ ሲባል ለምን ይሆን የምትንጰረጰረው?› ሲለኝ፣ ‹ኮሮና ሰው እየፈጀ ነው› ማለት፡፡ ‹ተው እንጂ በዘመናዊ የሥልጣኔ መንገድ ተመራ ስትባል እንቢ እያልክ ቁጥሩ ሲያሻቅብ መሸሽ መፍትሔ ነው?› ሲለኝ አንገቴን ደፍቼ ዕርምጃዬን ሳጣድፍ፣ ‹አንበርብር ፈሪን እንኳን ሰው ፈጣሪም አይወደውም› ብሎ ነገር ሲጀምረኝ እንደገና ብልጭ ብሎብኝ፣ ‹እንዴት?› አልኩት፡፡ ‹ፈሪን ማን ያከብራል? ጀግና ሲሆን ግን ሁሉም ከመቀመጫው ተነስቶ ኖር ይለዋል፡፡ ፈጣሪም እኔ አምላኩ እያለሁለት የሚፈራ እምነተ ቢስ ነው ብሎ ይፀየፈዋል…› ሲለኝ ልቤ አስገረመኝ፡፡ እውነት እኮ ነው፡፡ እኔም ከመፍራት መጠንቀቅ ብያለሁ፡፡ ‹ፈሪ አይፀድቅም› የተባለው ለካ እውነት ነው!

ልብን ማዳመጥ ትልቅ ነገር መሆኑን አዛውንቱ ባሻዬ ሁሌም የሚነገሩኝን አልረሳውም፡፡ ጊዜው ራቅ ቢልም እንዲህ ብለውኝ ነበር፡፡ ‹‹አንድ ሰው አንድ ጉዳይ ገጥሞት መወሰን የሚያቅተው ከልቡ ጋር ስለማይመካከር ነው፡፡ ከልቡ ጋር የመከረ ሰው የተማረ ወይም ዕድሜ ያስተማረው ሰው ዘንድ ሄዶ ተጨማሪ ምክር ይጠይቃል፡፡ የልቡን ሐሳብ አደርጅቶ ምክር ሲጠይቅ የሚያዋጣውና የማያዋጣው፣ ደካማና ጠንካራ ጎን፣ እንዲሁም ጥቅምና ጉዳቱ ሲነገረው ከልቡ ምክር ጋር አመዛዝኖ ይወስናል፡፡ በውሳኔውም ተጠቃሚ ይሆናል…›› ማለታቸው አይረሳኝም፡፡ አገር የሚመሩ ሰዎችም ከልባቸው ጋር ተማክረው የደረሱበትን ሐሳብ ይዘው አማካሪዎቻቸውን ሲያማክሩ፣ በተጨማሪም ሕዝቡ ውስጥ ያለውን ፍላጎት በማከል ነው ሲሉም እንደነገሩኝ አልዘነጋውም፡፡ ምሁሩ ልጃቸውም፣ ‹‹ልብን ማዳመጥ ማለት ከራስህ ሐሳብ ጋር ተፋልመህ የምታገኘው ውጤት ነው…›› የሚለው ረቀቅ ያለ ፍልስፍና አለው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚነግረኝ በሕግና በሥርዓት መኖርን ነው፡፡ ‹‹መንግሥት የበርካታ ምክሮች ድምር ውጤትን ፖሊሲ በማድረግ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ይወጣል፡፡ ሕዝብ ደግሞ የወጡ ሕጎችን በማክበር ይተዳደራል፡፡ ጥያቄ ያለው በሥርዓት ያቀርባል፡፡ ምላሽ መስጠት ያለበት መንግሥታዊ አካል ደግሞ በአግባቡ ያስተናግዳል፡፡ ይህ ማለት መንግሥትና ሕዝብ በልባቸው እየተመካከሩና በአንደበታቸው እየተነጋገሩ፣ ለአገር ዕድገት በጋራ ይማስናሉ ማለት ነው…›› እያለ ሲያስረዳኝ የነበረው ትዝ ይለኛል፡፡ ትዝታ ደግሞ ብዙ ሰበዞች አሉት!

ደላላ ሥራውን በትጋትና በታማኝነት ሲያከናውን እንጂ ሲፈላሰፍ ስለማያምርበት፣ እጄ በድንገት የገባውን ሲኖትራክ ለማሻሻጥ እየባተልኩ ነው፡፡ በዚህም በዚያ ተብሎ ዕድሜው 30 ሊሆን የተቃረበ ገዥ ተገኘ፡፡ ሻጭ የገዥን ወጣትነት ተመልክቶ ቅር አለው፡፡ ‹‹ምነው ወንድሜ ቅር አለህ?›› ብዬ በትህትና ጥያቄ ሳቀርብለት፣ ‹‹ይኼ ወጠጤ በዚህ ዕድሜው ከየት አምጥቶ ነው መኪናዬን የሚገዛው?›› ከማለቱ አንዱ ቀዥቃዣ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ሰሞኑን በወረራ ከያዛቸው መሬቶች አንዱን ጆሮ ግንዱን ብሎት ነዋ…›› ብሎ አመዴን ቡን አደረገው፡፡ እኔም ነገሩ ከንክኖኝ፣ ‹‹አንተስ ይህንን ወሬ ከየት አመጣኸው?›› ብዬ ላፋጥጠው ስፍጨረጨር ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ሳቁ አስገርሞኝ በአግራሞት ሳየው፣ ‹‹ሰማህ አንበርብር! ይኼ ጎረምሳ እኮ ከአሁን በፊት ሦስት ዶልፊኖች ገዝቶ ለወንድሞቹ ታክሲ እንዲሠሩበት አድሏል፡፡ አሁን ደግሞ ሁለተኛ ሲኖትራክ እየገዛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሥራው ምንድነው ብዬ ሳጣራ ምንም ታሪክ የለውም፡፡ ቢጤዎቹን አስተባብሮ መሬት ወሮ ይይዛል፣ የእሱ ቢጤ የበላዮች ደግሞ ካርታ እየሰጡት ሀብት እየሰበሰበ ነው…›› ሲለኝ በቁሜ የምቃዥ መሰለኝ፡፡ ሻጭ በንዴት፣ ‹‹እስቲ ይሁና! እኛ ሰላሳና አርባ ዓመት ለፍተን አያልፍልንም፣ በየተራ እየመጡ ያበግኑናል…›› ሲል ልቤ መምታት ጀመረ፡፡ ልቤ ሲመታ ነገር አለ!

በንዴት ውስጥ ሆኜ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ስሄድ አንገቴን አቀርቅሬ ነበር፡፡ አንዱ የድለላ ሥራ ወዳጄ አስቁሞኝ፣ ‹‹በጠፋ ሥራ ኮሚሽን አግኝተህ የምን አንገት መድፋት ነው?›› እያለ ሲያነቃኝ አንደበቴ ተዘግቶ በምልክት ሰላምታ ሰጥቼው መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ አንዳንዴ ወሬ መስማት የማልፈልገው እንዲህ ዓይነት አውጣነት በመብዛቱ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከልጅነት እስከ እርጅና ለፍተው ያፈሩት የበርካታ ዓመታት የልፋት ውጤት፣ ያልበሰለ አዕምሮ ባላቸው አፍለኞች በደቂቃ ውስጥ አመድ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የፈሰሰ ውኃ የማያቀኑ ሥራ ጠሎች ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ በተገኘ ዕድል ሚሊዮኖችን ይቆጥራሉ፡፡ ልቤ በዚህ መሀል ከች አለ፡፡ ‹ድፍረትን ከማስተዋል ጋር አዳብለህ በሥርዓት ከተነሳህ እኮ እንዲህ ዓይነቱን ኃፍረተ ቢስ ድርጊት ማስቆም ይቻላል› ሲለኝ ነቃሁ፡፡ ዕርምጃዬን አፍጥኜ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ዘንድ ስደርስ አልታወቀኝም ነበር፡፡ የገጠመኝንና የልቤን ሐሳብ ነገርኩት፡፡ እሱ እንኳን ይህንን አግኝቶ እንዲሁም እንዲያ ነው ጀመረልኝ፡፡ እሱ ሲጀምር እኔ ማዳመጥ ተግባሬ ነው፡፡ መደማመጥ ከሌለ የጭልፊቶች መጫወቻ መሆናችን እንደማይቀር አሳስባለሁ!

‹‹ሰማህ! ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የትግሉ ውጤት ግን ማኅበራዊ ፍትሕ ለማምጣት እንጂ፣ በተረኝነት ስሜት አገር ለመዝረፍ አይደለም፡፡ ከፖለቲከኞች መሀል በጣም በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹ የሚጮሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?›› ሲለኝ አንገቴን በአሉታ ነቀነቅኩ፡፡ ‹‹በእነሱ ወሬ በፍፁም እንዳትታለል፡፡ እነሱ ወይ በብሔር ወይም በአገርና በጠቅላላው ሕዝብ ስም ለግላዊና ቡድናዊ ጥቅም ነው እሪታቸውን የሚያቀልጡት፡፡ የሥልጣኑን እርካብ ሲረግጡ መሬቱን፣ የባንክ ብድሩን፣ የውጭ ምንዛሪውን፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድሉንና ጥቅም የሚያስገኘውን ሁሉ ይቀራመታሉ፡፡ ለዚህ ነው በንቃት ለማኅበራዊ ፍትሕና ለእኩልነት እንዲሠሩ ማስገደድ ያለብን…›› እያለ ሲነግረኝ ጭው ብሎብኝ ነበር፡፡ ልቤ ግን በለሆሳስ እየደለቀ ‹እውነቱን ነው!› ሲለኝ ይሰማኛል፡፡ የምሁሩ ንግግርና የልቤ ሐሳብ ገጥመው እንደ መመራመር እየቃጣኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው ለካ በአገራችን ጉዳይ እውነቱና እርግጡ ሲነገረን የምናጨበጭበው፣ በሐሴት የምንረካው፣ በደስታ ጮቤ የምንረግጠው፣ እርስ በርስ የምንመራረቀው፡፡ ለካ የአገር ጉዳይ እንዲህ ሰቅዞ ይይዛል? ልብን ፋታ እያሳጣ ያሟግታል? ከቁጥጥር ውጪ አድርጎ አደባባይ ያስወጣል? አንድ ላይ አስተቃቅፎ በደስታ ያስነባል? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት