Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሞተር አልባ ትራንስፖርት ጅማሮዎች

የሞተር አልባ ትራንስፖርት ጅማሮዎች

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የከባቢ አየር ብክለትን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር፣ ፍጥነቱ አነስተኛ በመሆኑም የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር ጉልህ ሚና አለው፡፡  

ቻይና ህንድና ሌሎች አገሮችም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከአነስተኛ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ እስከ ባቡር ድረስ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ እየዋሉም ነው፡፡ ያደጉ አገሮች ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ከጀመሩ  ሰንበት ያሉ ሲሆን፣ የትራንስፖቱን ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ  ነዳጅ አልባ ለማድረግም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

በዚህም አገሮቹ ከመኪናዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ከማስቀረት ጎን ለጎን የድምፅ ብክለትን ቀንሰዋል፡፡ ዋጋው ተመጣጣኝ በመሆኑም ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ችለዋል፡፡

በተለይ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድና ሌሎች የእስያ እስያ አገሮች በዚህ እስትራጂ መመራት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አገሮቹ የሕግ ማዕቀፍ ከማስቀመጣቸው በተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ሲከናወኑ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ከግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገባ አድርገዋል፡፡

አገሮቹ በኤሌትክሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ደንበኞች መንግሥት ገሚሱን ወጪ እንዲሸፍንም አሠራር ዘርግተው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችለዋል፡፡ የሰሌዳ ቁጥር አወጣጥም ቀላልና ምቹ እንዲሆን እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር ስትራቴጂ ተነድፎ እንቅስቃሴ የተጀመረው በሰኔ 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማሻሻልና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማረጋገጥ ከምታተኩርባቸው አቅጣጫዎች አንዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. በሚኖረው ጊዜ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለማሻሻል የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋነኛው ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፣ ይህም ኅብረተሰቡ በቀላሉ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ ያስችላል ተብሎ ታስቧል፡፡

በኢትዮጵያ የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረትን ለመቀነስ የሞተር አለባ ትራንስፖርት ተመራጭ መደረጉ፣ አረንጓዴ አሻራን ከመደገፍ አንፃርም አመርቂ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ይነገራል፡፡  

በሞተር አልባ ትራንስፖርት ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል ቶም ኢባይክ አንዱ ነው፡፡ ቶም ኢባይክ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ግብዓቶችን ከቻይና በማስመጣት በአገር ውስጥ የሚገጣጥም ሲሆን፣ ከ40 ለሚበልጡ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በረከት ተስፋዬ እንደሚሉት፣ ተሽከርካሪዎቹ እዚህ በመገጣጠማቸው የእውቀት ሽግግር ለማድረግ አስችሏል፡፡

ድርጀቱ ቀላል የትራንስፖርት አገልግሉት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የትራፊክ አደጋን የሚቀንስና በቅናሽ ዋጋ ሁሉንም ያማከለ የትራንስፖርት ተጠቃሚ ማድረግን ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በድርጅቱ ከሚሠሩ ሠራተኞች ውስጥ ቻይና በመላክ አሠልጥኖ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን፣ ከንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ከሚመረቁ ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶውን ለሥራ እንደሚወስዱም አክለዋል፡፡

በድርጅቱ የሚገጣጠሙ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሞተር ሳይክሎች፣ የቆሻሻ መጣያዎች፣ እየተንቀሳቀሱ የመኪና እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖች፣ ለስድስት ሰው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ፣ ማረሻ፣ ማረሚያ፣ የቤት መኪና፣ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ኤፍኤስአርና ኮንዶሚኒየም ህንጻ ላይ 300 ኪሎ ግራም ክብደት ድረስ ይዞ የሚወጣ ተሽከርካሪ አምርቶ ለገበያ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ ስምንት ወራት ሲሆነው፣ በተለያዩ ክልል ከተሞች በወኪሎች አማካይነት ምርቱን እያቀረበ ይገኛል፡፡ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች እየቀረበ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ቀላልና ምቹ በመሆኑ አብዛኞቹ ደንበኞች አዎንታዊ ምላሽ እንዳላቸው፣ ፍጥነቱ የተገደበ በመሆኑም የአደጋ ሥጋት እንደማይኖረው ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ ሞተር አልባ ወይም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ያምርት እንጂ ዘርፉ ጅምር በመሆኑ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ክፍተቶች እንዳሉም ይነገራል፡፡

እንደ አቶ በረከት፣ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ በተለያዩ ሕንፃዎች ላይ የኤሌክትራክ ቻርጅ አገልግሎት፣ ለሞተር አልባ ትራንስፖርት የሚሆኑ መንገዶችና ሌሎችም ተያያዥ ሥራዎች እያሟሉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡

እንደ አገር የሕግ ማዕቀፎችና የኤሌክትሪክ ታሪፍ በማውጣት ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል የሚሉት አቶ በረከት፣ ሕንፃ ሲገነባ የኤሌክትሪክ ቻርጅ አገልግሎት እንዲሰጥም አድርጎ በመንደፍ ተጨማሪ ገቢ የሚገኝበትን መንገድ መክፈት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ለዚህ ዘርፍ የሚሆን ተቆጣጣሪና ፖሊሲ ቢያወጣ ለተጠቃሚዎች በብድር በመስጠት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል አቶ በረከት ይገልጻሉ፡፡ አሁን ላይ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ፣ ከባንኮች ጋር ለመሥራት አዳጋች መሆኑንና መመሪያና ደንብ ሲወጣ ግን ወደ ብድር አገልግሎቱ እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡

በድርጅቱ የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪያቸው እስከ ሁለት ዓመት የሚያገለግል ነው፡፡ መለዋወጫም በየወኪሎች ይገኛል፡፡ ነገር ግን የትራንስፖርት መመርያ ሲወጣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ ትልቅ ክፍተት ተገጥሯል፡፡

በዚህም ደንበኞች የገዙት ተሽከርካሪ ስለተያዘባቸው በዝናብ እየተበላሸ መሆኑንን የሚናገሩት አቶ በረከት፣ ቅሬታውን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም መፍትሔ እንዳላገኙ፣ በድርጅቱ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ፍጥነታቸው የተገደበ በመሆኑ ወንጀል ለመሥራት እንደማያመቹና ክልከላውም ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ባያካትት የሚል ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡

የዚህን ዘርፍ አስፈላጊነት መንግሥት ይደግፈዋል፣ ይህንንም ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን የተደረገበት አካሄድ፣ ሞተር  አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ይፋ መሆኑ ያሳያል ያሉት አቶ በረከት፣ ስለዘርፉ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤሌክትሪክ የሚሠራ፣ የካርቦን ልቀት የማያስከትለውንና  የሀዮንዳይ ኩባንያ አካል በሆነው ማራቶን ሞተርስ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተገጣጠመ መኪና ከሁለት ሳምንት በፊት በስጦታ ሲረከቡ፣ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለአረንጓዴ ልምላሜ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...