Monday, June 17, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተው ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ወፍረዋል እኮ፡፡
 • ምን ላድርግ ብለህ ነው?
 • በዚያ ላይ ፀጉርዎት አድጓል፡፡
 • ፈርቼ ነዋ፡፡
 • እታሰራለሁ ብለው ነው?
 • ምን ይላል ይኼ?
 • ታዲያ ምኑን ነው የፈሩት?
 • ኮሮናውን ነዋ፡፡
 • እኔማ ያው ተነካክተዋል ብዬ ነው?
 • በሙስና ነው?
 • መቼም ንፁህ ነኝ አይሉኝም?
 • ለዚያውም እንደ በረዶ የነፃሁ ነኝ፡፡
 • ለነገሩም በሚገባ አውቃለሁ፡፡
 • ምኑን?
 • ውሸታምም እንደሆኑ ነዋ፡፡
 • አልተደፋፈርንም ትንሽ?
 • ክቡር ሚኒስትር ምን አጠፋሁ?
 • እየሰደብከኝ እኮ ነው፡፡
 • ምን ብዬ?
 • ሌባና ውሸታም ነዋ፡፡
 • እኔ እኮ የሰማሁትን ነው፡፡
 • ከማን ነው የሰማኸው?
 • ከሠራተኛው ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ያው አላዘዙኝም እንዴ?
 • ምን ብዬ?
 • እኔ ሳልኖር ሳልኖር ወሬ አነፍንፍ ብለው ነዋ፡፡
 • እሱማ ብዬሃለሁ፡፡
 • ስለዚህ እርስዎ በኮሮና ቤትዎ ተደብቀው ሲኖሩ እኔ እዚህ ባዘዙኝ መሠረት ሁሉን ወሬ በየቀኑ ነው የምቃርመው፡፡
 • እኔ እኮ ቤቴ ተደብቄ ሳይሆን ትልቅ ሥራ እየሠራሁ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔን እንኳን አይዋሹኝ፡፡
 • ምን?
 • ያው ወሬ ሲያወሩ እንደሚውሉ አውቃለሁ፡፡
 • እኔ ጠፋሁ?
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ያዘዙኝን በሚገባ ፈጽሜያለሁ፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው ሁሉንም ኃላፊዎች እርስ በርሳቸው ሳባላቸው ነበር፡፡
 • አትቀልድ?
 • ፋይናንሱን ከግምጃ ቤት ኃላፊው፣ የመሠረተ ልማት ኃላፊውን ከዋና የሥራ ሒደት ኃላፊው ጋር ሳባላቸው ነበር፡፡
 • በነገራችን ላይ የመሠረተ ልማት ኃላፊው እንዴት ነው?
 • ይኸው ቀን ተሌት ነው ሥራውን የሚሠራው፡፡
 • ለነገሩ እኔ ዋና የሥራ ሒደት ኃላፊው ነው የማይመቸኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እሱም እርስዎን በጣም ነው የሚንቅዎት፡፡
 • እ…
 • ሳይሠሩ ቁጭ ብለው ነው የሚበሉት ይላል፡፡
 • ግድ የለም ይህቺ ኮሮና ይዛኝ ነው፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • ዕርምጃ እወስድበታለሁ፡፡
 • ግን ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ሳይኖሩ ቢሮውን ቀጥ አድርጎ የያዘልዎት እኮ እሱ ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ለማንኛውም ምንድነው ሽልማቴ?
 • ለአንተ?
 • እህሳ፡፡
 • ከዚህ በኋላ አዲስ ሹመት እሾምሃለሁ፡፡
 • ምን አድርገው ሊሾሙኝ?
 • ክቡር ወሬኛ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር ተገናኙ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • እንዴት ይዞዎታል ኮሮና?
 • ይኸው ቤቴ ተቆልፌ ነው የምውለው፡፡
 • ቢሮ እኮ ብመላለስ ላገኝዎት አልቻልኩም፡፡
 • ምን ላድርግ ይኼ ኮሮና ሕይወቴን አመሰቃቀለው፡፡
 • ምን የእርስዎ ብቻ የእኛም ተመሰቃቅሏል፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው ግን?
 • በዚህ ጊዜ ምን ሥራ አለ ብለው ነው?
 • እንዴት?
 • ሁሉ ነገር ተቀዛቅዟል አይደል እንዴ?
 • ለነገሩ አሁን ክረምትም ስለሆነ ይቀዘቅዛል፡፡
 • በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር…
 • እ…
 • የዘንድሮ ክረምት ግን እንዴት ነው?
 • ምን ሆነ?
 • ቅዝቃዜው አይጣል ነው እኮ፡፡
 • የእኛ ውጤት ነዋ፡፡
 • ማለት?
 • የችግኛችን ውጤት ነዋ፡፡
 • እንደዚህ በአንድ ጊዜ?
 • ባለፈው ዓመት የተከልናቸው ችግኞች እኮ በቅለው ነው እንደዚህ ዝናብ በዝናብ ያደረጉን፡፡
 • እኔ እኮ ዓምና ጠይቄ ነበር፡፡
 • ምን?
 • መሬት ነዋ፡፡
 • የምን መሬት?
 • ችግኝ የምተክልበት ነዋ፡፡
 • ግቢህ ላይ አትተክልም እንዴ?
 • በአጋጣሚው ልጠቀም ብዬ ነዋ፡፡
 • በምኑ አጋጣሚ?
 • ማለቴ በችግኝ እተክላለሁ ሰበብ መሬት ለመውረር ነዋ፡፡
 • የምትገርም ሰው ነህ እኮ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ባገኘኸው አጋጣሚ መጠቀም ነው የምትፈልገው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንደዚያ ካላደረጉ መቼ ኑሮ ይቻላል?
 • ለማንኛውም መሰሪ ብዬሃሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መሰሪ ካልሆኑ መኖር አይቻልም፡፡
 • እ…
 • እዚህ እንዴት የደረስኩ ይመስልዎታል?
 • እንዴት ነው የደረስከው?
 • አንዱን  ከአንዱ እያጋጨሁ ነዋ፡፡
 • እ…
 • አዩ በአካባቢዎ ያሉ ሰዎችን እርስ በርስ በማጋጨት እርስዎ በጎን የድርሻዎን ይወስዳሉ፡፡
 • ይኼ አካሄድ ግን ያዋጣል?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • እንዴት?
 • አዋጥቶኝ አይደል እንዴ ባለሀብት ያደረገኝ፡፡
 • ሀብት እኮ ባዳ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • በአንዴ ሊከዳ ይችላል፡፡
 • እ…
 • ምነው?
 • ለማንኛውም እኔን ከፍታ ላይ አስቀምጦኛል፡፡
 • መፍራት ያለብህ ነገር አለ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ጉድጓድ እንዳትገባ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ስልክ ደወለላቸው]

 • ኧረ ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ?
 • አየሩ ነዋ፡፡
 • ምን ሆነ?
 • ቅዝቃዜው ሊያሳብደኝ ነው፡፡
 • የችግኝ ተከላችን ውጤት ነዋ፡፡
 • እኔም እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
 • ገና በግንቦት እንዲዘንብ እናደርገዋለን፡፡
 • ምንም አልጠራጠርም፡፡
 • እንዴት ነህ ታዲያ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ተጧጡፏል፡፡
 • ምኑ?
 • የመሬት ወረራው፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ በየሄድኩበት ይታጠራል፡፡
 • ለልማት ነዋ፡፡
 • ታዲያ እኛ እኮ ዋና የልማት አርበኞች ነን፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ በየቦታው እያጠርን መሬት እንይዛለና፡፡
 • ከዚያስ?
 • ከዚያማ እንቸበችበዋለን፡፡
 • ለልማት የያዝነውን መሬት?
 • ምን ችግር አለው?
 • ልማቱ የት አለ ብዬ ነዋ?
 • እኛ ሸጠነው ከከበርን ከዚያ በላይ ልማት አለ እንዴ?
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ስለዚህ ሳንቀደም እንቅደም፡፡
 • ምኑን?
 • ማጠሩን ነዋ፡፡
 • በኋላ እኮ ተጠያቂነት ያመጣል፡፡
 • ለዚያ አይደል እንዴ እርስዎ የሚፈለጉት፡፡
 • ለምን?
 • ከለላ እንዲሰጡ ነዋ፡፡
 • እኔንስ ማን ይከልለኛል?
 • እ…
 • መልስልኛ?
 • ገንዘባችን ነዋ፡፡
 • ተው እንጂ፡፡
 • ምነው?
 • ገንዘብማ እንደማያስጥል እያየነው ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው የቀድሞ ጓደኞቻችንን መቼ አስጣላቸው?
 • እነሱ ግራ ተጋብተዋል፡፡
 • እኔ ደግሞ ይኼን ፈጽሜ እንዲገባኝ አልፈልግም፡፡
 • ምን?
 • ሥጋት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • አሁን ቆርጠናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ተስፋ ነው?
 • ነገርኩዎት ቆርጠናል አልኩዎት፡፡
 • ትኬት ነው?
 • የምን ትኬት?
 • አዲስ አበባ ለመምጣት ነዋ፡፡
 • ምን በወጣን?
 • ለነገሩ ከተማዋም አትቀበላችሁም፡፡
 • ለምን?
 • እንደ ስሟ አዲስ አስተሳሰብ ያለውን ነዋ የምትቀበለው፡፡
 • እኛ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው ያለን?
 • ያረጀ ያፈጀ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ምን ለመሆን ነው?
 • ምኑ?
 • የሰሞኑ ፉከራና ቀረርቶ፡፡
 • ልናሳያችሁ ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ለሁሉ ነገር ዝግጁ መሆናችንን ነዋ፡፡
 • እንደዚህ በወጣት መቀለድ ቀረ እኮ፡፡
 • እንዴት?
 • እናንተ የራሳችሁን ልጆች አውሮፓና አሜሪካ ልካችሁ ወጣቱን እዚህ ልታስጨርሱት?
 • እ…
 • ማንም አይሰማችሁም፡፡
 • እኛ እኮ የምንዋጋው ኮሮናን ነው፡፡
 • እኛ ደግሞ የምንዋጋው እናንተን ነው፡፡
 • ምን አደረግን?
 • አገሪቱ ዘርፋችሁ ባዶ ካስቀራችሁ በኋላ የጦር አውድማ ለማድረግ እየሠራችሁ ነዋ፡፡
 • ስማችንን አያጥፉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ስም አላችሁና፡፡
 • እና ምንድነው ያለን?
 • ሴራ፡፡
 • እሱማ ያደግንበት ነው፡፡
 • አሳድጎ የት እንደሚከታችሁ ታውቃለህ?
 • የት ይከተናል?
 • መቀመቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን ቅሬታውንም አልሰማሁም። እንዴት? አልሰማሁማ? የምን ቅሬታ ቀርቦባቸው ነው? ሰሞኑን ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ውድና ቅንጡ አውሮፕላን ተከራይተዋል የሚል ቅሬታ...