Sunday, June 4, 2023

የግብፅና የሶማሌላንድ የጦር ሠፈር ወሬ ኢትዮጵያን ምን ያህል ያሠጋታል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ግድቡ እንዳይጠናቀቅና ውኃ እንዳይሞላ የተለያዩ ጫናዎችን ግብፅ ስታደርግ የቆየች ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በመጀመርያው ዙር በግድቡ ለመያዝ ያቀደችውን 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሞላች ሐምሌ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታውቃለች፡፡

የግድቡን መሞላት ተከትሎ የደረሰባት ጉዳት እንደሌለ ግብፅ ያስታወቀች ቢሆንም ቅሉ፣ በተለያዩ መንገዶች የግድቡን ግንባታ ተከትለው ሲደረጉ ዓመታትን ያስቆጠሩት ድርድሮች ግባቸው፣ ግድቡንና በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ሳይሆን የናይል ውኃ ክፍፍል ላይ እንዲያተኩሩ ተደርጎ በመቅረቡ፣ አሁንም መቋጫቸው መቼ እንደሆነ ለመተንበይ አዳጋች እንዲሆን አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን ያለ ስምምነት እንዳትሞላ ለማስረገጥ ግብፅ የዓባይ ውኃ ለሕዝቦቿ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው በማለት ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ስታሳድር የቆየች ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ላይ የጦር ሥጋት በመደቀን ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ የሚኖራትን የመጠቀም መብት አጥብቃ እንዳትይዝና የወደፊት የልማት ዕቅዶችም ቢኖሩ ዕውን መሆን እንዳይችሉ ለማድረግ ግፊቶችን ማድረጓ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡

የግድቡ ግንባታ በተጀመረ በሦስተኛው ዓመት ግድቡ ላይ አደጋ ሊደቅኑ የሚችሉ የግብፅን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ሥጋት የገባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በበኩላቸው ግብፅ ለኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ለሚከናወን የግድብ ግንባታ ዕርዳታም ሆነ ብድር እንዳይሰጥ ከማድረግና በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከመጣር ባለፈ፣ ሦስተኛ ስትራቴጂዋ አድርጋ የምትጠቀመው ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል በመፍጠር ሌሎች አገሮች አደጋውን ፈርተው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹ይኼንን በተመለከተ ልንከተል የሚገባው ፖሊሲ አለመፍራት ነው የሚሆነው ማለት ነው፤›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ እስከ ዛሬ የዘለቀውን የግብፅን በጦር የማስፈራራት አባዜ በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጦር የማዝመት ፍላጎት ያዋጣታልና ግብፃውያንም ይኼንን ያስባሉ ብለው እንደማያምኑ በመግለጽ፣ ይኼ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ጦርነት ለማምራት የሚፈልጉ ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ሚሊዮኖችን ልታሠልፍ እንደምትችል ተናግረው ነበር፡፡ ይሁንና ለሁለቱም ወገኖች የሚያዋጣው  ሰላማዊ ድርድር በማድረግ ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት መጣር እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

የግብፅን የጦር ሥጋትነት በተመለከተ የተለያዩ ትንታኔዎችንና ማብራሪያዎችን የሚያቀርቡ አስተያየት ሰጪዎች፣ የግብፅ ወታደራዊ ማስፈራሪያም ሆነ ዝግጅት ዕውን ሊሆን የማይችልባቸው ምክንያቶችን ሲዘረዝሩ በመጀመርያ የሚያቀርቡት፣ ግብፅ የምድር ጦር በማስፈር ኢትዮጵያን ለመውረርና ጦርነት ለማካሔድ የሚያስችላትን ገዥ መሬት ለማግኘት አትችልም የሚል ነው፡፡ በአየር ብቻ ወይም በሚሳይል የሚፈጸሙ ጥቃቶች በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማነታቸው አነስተኛ እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡ ግብፅ የእግረኛ ጦር አስገብታ ኢትዮጵያን መውጋት ስለማትችልም የጦርነት ነጋሪት ጉሰማዋ ዋጋ ቢስ ነው በማለት፣ ይልቁንስ እስከ ዛሬ እየተሳካላት ያለውና ለወደፊትም ሊሳካላት የሚችለው ስትራቴጂ በአገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ኃይሎችን በመደገፍ ትርምስ መፍጠር እንደሚሆን ያክላሉ፡፡

ይሁንና የመጀመርያው ኢትዮጵያን በእግረኛ ጦር የመውረር ፍላጎትን ዕውን ለማድረግ በእጅጉ ስትታትር የቆየችው ግብፅ፣ በቅርቡ ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር ባደረገችው ውይይት በሶማሌላንድ ደቡብ ምሥራቅ ቀጣና ለኢትዮጵያ ቅርብ በሆነ ሥፍራ የጦር ሠፈር ለመገንባት ፍላጎት እንዳሳየች ተዘግቧል፡፡

ከሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ጋር በቅርቡ ውይይት ያካሄደው የግብፅ መንግሥት ልዑክ በሶማሌላንድ የጦር ሠፈር ለማቋቋም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወያይ ልዩ ልዑክ ካይሮና በሃርጌሳ ተመላልሶ እንዲወያይ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተነግሯል፡፡

ይኼንን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለተለያዩ ሚዲያዎች የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ግብፅ እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ አገር በቀጣናው ካሉ ሌሎች አገሮች ጋር ግንኙነት የመመሥረት መብት ያላት ቢሆንም፣ የግብፅ ግንኙነት ግን ሌላውን አገር በሚጎዳ መንገድ መከናወን የለበትም ብለዋል፡፡

‹‹የግብፅ በቀጣናው መኖር ለሌላው አገር ሥጋት የሚደቅን ከሆነ አግባብ አይሆንም፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ይኼንን ክስተት በተመለከተ ግን ግልጽ መረጃዎችን ማየትና መገምገም እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ በየትኛውም የቀጣናው አገርም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ የደኅንነት አደጋ የሚደቅንና ሥጋት የሚሆን ከሆነ፣ ከሕግ ውጭ የሆነና ከዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር የሚጣረስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የዚህን ዜና መሰማት ተከትሎ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በሶማሌላንድ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ አንዳንዶች ይኼ ጉዞ ከሁኔታው ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ቢኖራቸውም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ጉዳዩ ከተለመዱና በዕቅድ ከተያዙ የሁለቱ አገሮች የግንኙነት ተርታ የሚሠለፍ ነው ሲል አስተባብሏል፡፡

የግብፅ ፍላጎት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደርና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አለመረጋጋት እንዲንሰራፋ ለማድረግ እንደሆነ ግምታቸውን የሚያስረዱ አንዳንድ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት፣ ግብፅ የህዳሴ ግድቡንና የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሊቢያ ቀውስ ጋር በማስተሳሰር ዓለም በተመሳሳይ ክብደት ተመልክቶ ጫናውን እንዲያጠነክርም ያለመ ነው ሲሉ ምልከታቸውን ያጋራሉ፡፡

በተጨማሪም በዓረብ ሊግ ስብሰባ ወቅት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በመቃወም በልዩነት የወጣችውን ሶማሊያን ለመበቀል በማቀድ፣ ግብፅ ሶማሊያ እንደ አንድ የግዛቷ አካል ከምትቆጥራት ሶማሌላንድ ጋር ግንኙነት እየመሠረተች እንደሆነም ይነገራል፡፡

ይሁንናና ሶማሌላንድ ለግብፅ የጦር ሠፈር መገንቢያ ሥፍራን በመስጠት የራሷን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ትጥላለች ብሎ ማሰብ እንደሚያዳግት የሚናገሩ የተለያዩ ታዛቢዎች፣ እንኳን ሶማሌላንድ ይ     ቅርና ትልቋና ከግብፅ ጋር ታሪካዊም ሆነ ሥነ ምድራዊ ትስስር ያላት ሱዳን እንኳን ይኼንን መሰል ድርጊት ታደርጋለች ማለት ከባድ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ የምትጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ከሃርጌሳ ወገን እምነት በመኖሩ ሲሆን፣ ሁለቱ ሶማሌዎች በቅርበት በመሥራት ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ጂቡቲ የምታደርገው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ የኢትዮጵያ ሚና አሌ የማይባል መሆኑን ሶማሌላንድ ስለምትረዳ ነው ይላሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት ስታደርግ የቆየችው የአሥርት ዓመታት ጥረት በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ የጣለ ቢሆንም፣ አሁን ግን ኢትዮጵያ የሁለቱን ሶማሌዎች ልዩነት ለመፍታት የሄደችበት መንገድ ለሶማሊያ ያደላ ነው የሚል እምነት ከሶማሌላንድ በኩል በመኖሩ፣ ለዕውቅና ይሆናት ዘንድ ወደ ግብፅና የዓረቡ ዓለም ዓይኗን ለመማተር ልትገደድ ትችላለች በማለት የሚያምኑም አልጠፉም፡፡ ለዚህም ሲባል ሶማሌላንድ ግቧን ለማሳካት ስትል በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ዕውቅናዋን በአፋጣኝ ለማግኘት መትጋትን ዓላማ በማድረግ እንዲህ ያሉ ፍላጎቶችን ባትቀበልም፣ ጥያቄዎቹ የሚቀርቡባቸውን ዕድሎች ልትፈጥር ወይም ለጥያቄዎቹ በር ልትከፍት ትችላለች በማለት የሚያመላክቱም አሉ፡፡

የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሊበን ዩሱፍ ኦስማን ግብፅ በአፍሪካም ሆነ በዓረቡ ዓለም ትልቅ አገር በመሆኗ ለአገራቸው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማሰጠት ሚና እንደሚኖራት በመናገር፣ ይኼም ትልቅነቷ በአፍሪካ ኅብረትና በዓረቡ ዓለም ዕውቅናን ለማስገኘት ይረዳል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጦር ሠፈር ለመገንባት ግብፅ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ብትሆንም፣ ቀጣናው የተለያዩ የዓለም ኃያል አገሮች የጦር ሠፈሮችን ያስተናገደ ነው፡፡ በጂቡቲ ብቻ ዘጠኝ የጦር ሠፈሮች ይገኛሉ፡፡ ሌሎቹም አገሮች ቁጥሩ ይለያይ እንጂ የሌሎች አገሮችን የጦር ሠፈሮችን ያስተናገዱ ሲሆን፣ ግብፅ ይኼንን መሰል የጦር ሠፈር በቀጣናው አይኑራት እንጂ በቀይ ባህር ዳርቻ ባሏት የባህር ኃይል ሠፈሮች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ እንደምትገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳን የግብፅ ፍላጎት ይኼንን ያህል የተለጠጠና በተደጋጋሚም ከግብፅ የሚወጡ መግለጫዎች የጦርነት አማራጮችን የያዙ ቢሆንም፣ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለጦርነት ትጋበዛለች የሚለው ሐሳብ ብዙዎችን የሚያሳምን አይደለም፡፡ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለጦርነት ብትጋበዝ ኪሳራው እንደሚያይልባትና በቀጣይም በዓባይ ውኃ ክፍፍልም ሆነ በግድቡ ላይ ለሚኖሩ ከእውነተኛ ሥጋቶች ለሚመነጩ የውይይት ፍላጎቶች በር የሚዘጋ እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡

ይሁንና በግድቡ ጉዳይ አሁን በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ወደ ጦርነት የሚያመራ ጉዳይ ሊከሰት አይችልም ሲሉ በርካቶች ያምናሉ፡፡ ስለዚህም የጦር ሠፈር ወሬው ከማስፈራሪያ ያለፈ ሚናም አይኖረውም ባይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንዳሉት፣ ለሁኔታው በቂ ዝግጅት እያደረጉ አለመፍራት እንደሆነም ያክላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -