Saturday, June 22, 2024

ለኢትዮጵያ የሚበጀው መተናነቅ ሳይሆን መመካከር ነው!

በአሁኑ ጊዜ የአገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ምክራቸውን እያካፈሉ ነው፡፡ በቅንነት መንፈስ ተነሳስተው በጎ መንገዶችን የሚያመላክቱ ወገኖችን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ከሚተላለፉ ቅን ሐሳቦች መካከል የሥራ ማጣት፣ የኮሮና ወረርሽኝ፣ የኑሮ ውድነት፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ የማይታወቁ ሥጋቶች፣ ፍርኃቶችና የመሳሰሉት ቢያስጨንቁም፣ ነገር ግን ቅን በመሆንና ራስን በመጠበቅ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ይታለፋሉ የሚለው ይገኝበታል፡፡ በእርግጥም ቅንነትና በአገር ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በጎ ፈቃድ ሲኖር፣ የማይታለፍ ችግርና መከራ እንደሌለ ከባድ ጊዜዎችን አሳልፈው የሥልጣኔ ማማ ላይ ከደረሱ አገሮች መማር ይቻላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መሆን ግን በጦርነት ወድመው ሕዝባቸውን ለዕልቂትና ለስደት እንደዳረጉት የፈራረሱ አገሮች መሆን ይከተላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ለሰላም፣ ለሕግ የበላይነትና ለአገር ህልውና ትልቅ ክብደት እንደሚሰጡ የታወቀ ነው፡፡ ይህ በቅንነት የታጀበ ፍላጎት ግን በጥቂት ነውጠኞች ምክንያት በተደጋጋሚ ችግር እየገጠመው፣ ሕዝብ ለበርካታ ችግሮች ከመጋለጡም በላይ አላስፈላጊ የሕይወት መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በልምድ፣ በተፈጥሮ ስጦታና በራስ ጥረት ለአገር ትልቅ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚችሉ ከአዛውንት እስከ ወጣት በርካታ አገር ወዳድ ዜጎች አሏት፡፡ እነዚህ ወገኖች ዕድሉ ቢመቻችላቸውና በቅንነት ተደማጭነት ቢያገኙ፣ እንኳንስ ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ የሚተርፍ የመፍትሔ ሐሳብ ማመንጨት የሚችሉ ናቸው፡፡ አገር በቀል ዕውቀቶችን ከዘመናዊው ጋር በማዋሀድ ጭምር ትልቅ ውጤት ማስገኘት የሚያስችሉ ስለሆኑ፣ ጊዜው ሳይረፍድ መጠቀም የሕዝብም የመንግሥትም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ብዙዎቹ የአገር ችግሮች አገራዊ መፍትሔ እንዳላቸው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የጥንቶቹ ኢትዮጵያዊያን በሥነ ጽሑፍ፣ በሒሳብ፣ በሥነ ፈለክ፣ በሕክምና፣ በዕፅዋት፣ በአዝርዕት፣ ወዘተ ለዓለም ያበረከቷቸው የዕውቀት ትሩፋቶች በብራና ጽሑፎች ጭምር የተሰነዱ ቢሆንም ብዙዎቹ የሚገኙት በውጭ አገር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ቢገኙም ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን የዓለም ቁንጮ በሚያደርጓቸው ዘርፈ ብዙ ዕውቀቶች የታደሉ ቢሆኑም፣ መለስ ብሎ እነዚህን በረከቶች ለመመርመር የሚደረገው ጥረት በጣም አናሳ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በጣም በርካታ ቅርሶች በውጭ ኃይሎች ከተዘረፉባቸው አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ኢትዮጵያዊያንን ከድህነት ማጥ ውስጥ ሊያወጡ የሚችሉ፣ እንዲሁም ከሐሰተኛ የታሪክ ትርክቶች የሚገላግሉ ይገኙበታል፡፡ በታሪካዊ ጠላቶች ተፈብርከው ዛሬ እርስ በርስ የሚያባሉ ከፋፋይ አጀንዳዎችን ማምከን የሚያስችሉ የሥነ ጽሑፍም ሆኑ ሌሎች ቅርሶች አሉ፡፡ በተለይ ይህ ትውልድ ከገባበት አደገኛ የግጭት አዙሪት ውስጥ በማውጣት፣ በአንድነት ተሠልፎ አገሩን የሚያሳድግባቸው በርካታ አገር በቀል ዕውቀቶችን የሚጨብጥባቸው ቅርሶች አሉት፡፡ ለዚህም ነው አገሪቱ አሉኝ የምትላቸው ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም አካባቢዎች ተፈልገው መገኘት ያለባቸው፡፡ ከዘመናዊው ትምህርት ጎን ለጎን ወጣቶች በእነዚህ ዕውቀቶች እንዲታነፁ ስለሚያስፈልግ በተለይ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንና ሌሎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ በማንም ሳይጎተጎቱ ቀድመው ሊተጉ ይገባል፡፡ አገር ሰላም የምትሆነው፣ በሥልጣኔ የምትገሰግሰውና ከአስመራሪው ድህነት የምትገላገለው ትውልዱ በሁለገብ ዕውቀት ሲታነፅ ነው፡፡ ዕውቀት በሌለበት ድንቁርና ስለሚንሰራፋ ነው መግደልና ማውደም የበዛው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ከፍተኛ ምክክርና መፍትሔ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መደረሱን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለዕውቀት የተሰጠው ግምት በጣም አናሳ ስለሆነ ምክንያት አልባ ጥላቻዎች ተንሰራፍተዋል፡፡ ለትውልድ አርዓያ የሚሆን ተግባር አከናውነው ስኬት ላይ በደረሱ ግለሰቦች ላይ የጥላቻ ንግግሮች ይሰማሉ፡፡ ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ ኢንቨስትመንት ላይ አውለው ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ስስታም ተብለው ይወረፋሉ፡፡ ሥራ ላይ የዋለ ገንዘብ ለምን ሜዳ ላይ ተበትኖ አይታደልም የሚል ጥላቻ ያስገርማል፡፡ አንገታቸውን ደፍተው አገራቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ታታሪዎች ለምን ዘርፈው አያዘርፉም እየተባሉ ይወገዛሉ፡፡ ቀናውን መንገድ እያመላከቱ ለመምራት የሚተጉ ግለሰቦች ያለ ኃጢያታቸው ይዘለፋሉ፡፡ ኅብረ ብሔራዊት አገር በጋራ እንገንባ ብለው የሚደክሙ ምሥጉኖች አገርን እንደ ቅርጫ ለመቃረጥ በሚሹ ኃይሎች የስድብ ናዳ ይወርድባቸዋል፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ በራስ ቋንቋ መነጋገርና መዳኘት፣ በገዛ ባህል መጠቀምና የመሳሰሉት መብቶች ሥራ ላይ ውለው የጋራ የሆነችውን ኢትዮጵያን እናሳድግ የሚሉ እንደ ደመኛ ጠላት ይታያሉ፡፡ ጥላቸው መረን ከመለቀቁ የተነሳ ለዘመናት አንድ ላይ የሚኖር ሕዝብ፣ ማንነቱና እምነቱ እየተለየ እንዲገደልና እንዲፈናቀል ይቀሰቀሳል፡፡ በጥላቻ ያበዱ ጥቂቶች በሚቀሰቅሱት ግጭት ንፁኃን እየተገደሉና እየተፈናቀሉ፣ አገር ከዚህ ቀደም አይታቸው የማታውቃቸው ቀውሶች በላይ በላይ ይደራረባሉ፡፡ ጥላቻን በማስፋፋት ነውረኛ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ቡድኖች ግን፣ አንድም ቀን ስለዕውቀት አስፈላጊነትና ስለአገር ዕድገት ጠቃሚነት ሲናገሩ አይታወቁም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ወጣቱ ትውልድ በዕውቀት እየታነፀ የግንዛቤ አድማሱ ሲሰፋ፣ የእነሱ ከንቱ መፈክር አስተጋቢና አጀንዳ ማራገፊያ ስለማይሆን ነው፡፡ አገራቸውን የሚያፈቅሩና ለዘለቄታ ዕድገቷ የሚጨነቁ ኢትዮጵያዊያን፣ ለወጣቱ ትውልድ ተስፋና መከታ ሊሆኑት ይገባል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ዕውቀት እንዲገበይ፣ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆንና ለአገሪቱ አለኝታነቱ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲገነባ ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ለመዘጋጀት መመካከር ይኖርባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ብሔር ይወለዱ፣ የትኛውንም እምነት ይከተሉ፣ በየትኛውም ቋንቋ ይነጋገሩ፣ የትኛውንም ዓይነት ባህል ይከተሉ፣ ወዘተ ከከፋፋዮችና ከበታኞች አደገኛ አጀንዳ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉት ማስተዋል በታከለበት ዕውቀት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በውጭ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር በተደጋጋሚ ድምፃቸው የሚሰማ ግለሰቦች፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአመቻቸው መንገድ ለመከፋፈል ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ክርስቲያኑ በእስላሙ ላይ፣ እስላሙ በክርስቲያኑ ላይ፣ አማራው በኦሮሞው ወይም በትግሬው ላይ፣ ኦሮሞው በአማራው ወይም በትግሬው ላይ፣ ትግሬው በአማራው ወይም በኦሮሞው ላይ፣ ወዘተ እንደተነሱ በማስመሰል ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ለማፋጀት ለጅምላ ጭፍጨፋ እየቀሰቀሱ ነው፡፡ እነዚህን አደገኛ ግለሰቦችና ስብስቦች በብልኃትና በጥበብ ማለፍ የሚቻለው፣ በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ዕውቀት ለወጣቶች በማቋደስ ነው፡፡ በብሔርተኝነት ጃንጥላ ሥር ተጠልለው ነውጠኞችን በማንቀሳቀስ ሕዝብ ሲያስፈጁ የነበሩ ነውረኞች፣ አሁን ደግሞ ወደ ሃይማኖቶች ሠፈር ጎራ በማለት ያንኑ አስነዋሪ ድርጊታቸውን ለመድገም ሲጣጣሩ መንቃት የግድ ይሆናል፡፡ ለዚህ ተንኮል የሚጠቀሙባቸው ያልበሰሉ ወጣቶችን ስለሆነ፣ በተለይ የእምነት መሪዎችና በሳል ምዕመናን በጊዜ መላ መፈለግ አለባቸው፡፡ እነዚህ አደገኛ ስብስቦች የተነሱበት ዋነኛ ዓላማ አገር መበታተን በመሆኑ፣ ከአሁን በኋላ በእነሱ መቀደም አይገባም፡፡ ከዚህ በፊት ያስፈጸሙዋቸው ነውረኛ ድርጊቶች እንዲደገሙ መፍቀድ በአገር ህልውና ላይ አደጋ መጋረጥ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በእምነቶች ውስጥ ክፍተት በመፈለግ እየተዶለተ ያለው ሴራ በፍጥነት መክሸፍ አለበት፡፡ ለወጣቶች ይህንን አደገኛ ሴራ በጥብቅ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች ግንዛቤያቸው ከፍ ሲል ሴራው ይመክናል፡፡ ለዚህም ብርቱ ምክክር የግድ ይላል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በተቻለ መጠን ለሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ቀደም ሲል በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው እነዚህ እሴቶች ተሸርሽረዋል፡፡ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ ክፋት፣ ጭካኔ፣ አሉባልታ፣ ስንፍና፣ ምቀኝነት፣ ይሉኝታ ቢስነት፣ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት፣ ወዘተ የተንሰራፉት የኢትዮጵያውያን የዘመናት ማኅበራዊ እሴቶች ሆን ተብለው እንዲናዱ በመደረጋቸው ነው፡፡ ትውልዱ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ውስጥ እንዲገባና የዘራፊዎችና የውሸታሞች ደቀ መዝሙር እንዲሆን የተገደደው፣ ሆን ተብሎ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በተሸረበ ሴራ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ቀደም ባሉት ዓመታት ችግሮች ሲያጋጥሙ ያጠፋን በመገሰፅ፣ የተበደለን ደግሞ እንዲካስ በማድረግ የሚጠቀሙባቸው ተምሳሌታዊ ልማዶች ወደ ጎን እየተገፉ ከባድ ችግር ደርሷል፡፡ ከሚሠራ ይልቅ የሚያወራ፣ ከታታሪው ይልቅ አስመሳዩና አድርባዩ ለኃላፊነት እየታጩ አገር ከስራለች፡፡ ለወገኖቻቸው ሌት ተቀን ሳይታክቱ የሚደክሙ እየተገፉ፣ አሉባልተኞች በመከበራቸው ትውልዱ ተጣሞ እንዲያድግ ተፈርዶበታል፡፡ ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትውልዱን ለማዳን መረባረብ አለባቸው፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ መደማመጥ እንዳይኖር ሆን ተብሎ የክፋት ድርጊት በመፈጸሙ፣ የደረሰውን ኪሳራ በአንክሮ በማጤን ለመመካከር መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች እንዲያብቡ ለምክክር ሰፊ ጊዜ መስጠት የኢትዮጵያዊያን የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያና ሕዝቧ ከማንም ሥልጣንና ፍላጎት በላይ ናቸው፡፡ የአገር ክብርና ህልውና ከማንም ፖለቲከኛ በላይ ነው፡፡ ራሳቸውን ከአገርና ከሕዝብ በላይ ለመመልከት የሚዳዳቸው ካሉ ራሳቸውን ቆም ብለው ይመልከቱ፡፡ የማንም ፖለቲካ ፓርቲ ዓርማ ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በታች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት በሞቱላትና በደሙላት ልጆቿ ደምና አጥንት የተገነባች አገር እንጂ፣ ጥራዝ ነጠቅ ፖለቲከኞች እንደሚሉት የአንድ ወገን የእጅ ሥራ ውጤት አይደለችም፡፡ ለሥልጣን ሲያቆበቁቡ አገሬ እያሉ የሚያሞካሹዋት፣ የሚፈልጉትን ሲያጡ ደግሞ የሚያተራምሷትም አይደለችም፡፡ የባዕዳንን ፈንድና አጀንዳ ተንተርሰው የሚያመሰቃቅሏት መንደር ሳትሆን፣ በጣም በርካታ ሚሊዮኖች ለህልውናዋ ዘብ የሚቆሙላት ታሪካዊት አገር ናት፡፡ በብሔር ከፋፍሎ ማፋጀት ያልተሳካላቸው ወፈፌዎች፣ እስላም ክርስቲያኑ በአንድ ጣራ ሥር በሚያድሩባት አገር ውስጥ በታኝና ከፋፋይ ቅስቀሳ ሲጀምሩ ኢትዮጵያዊያን በቃችሁ ብለው በኅብረት መነሳት አለባቸው፡፡ ለዚህም የአገራቸውን ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ፣ ከፍተኛ የምክክር አጀንዳዎችን የማዘጋጀት ሥራ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ፣ በሲቪል ማኅበረሰቦች፣ በቤተ እምነቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ አካባቢዎችና በመሳሰሉት ብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ልዩነት የሚፈታው በሰከነና በሠለጠነ መንገድ እንጂ፣ የንፁኃንን ደም በማፍሰስና የደሃ አገር ንብረት በማውደም እንዳልሆነ በግልጽ መነጋገር ይገባል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በብሔርና በእምነት እያሳበቡ አገር ማተራመስ የኋላቀሮች የረከሰ ተግባር እንደሆነ መተማመን ተገቢ ነው፡፡ አሜሪካና አውሮፓ መሽገው ሕዝብ ለማባላት ያሰፈሰፉ አረመኔዎችን ማሳፈር የሚቻለው፣ በበርካታ ጉዳዮች ከእነሱ ተሽሎ በመገኘት ስለሆነ ለሕዝባዊ ምክክሮች ትልቅ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጀው መተናነቅ ሳይሆን መመካከር እንደሆነ በተግባር ይረጋገጥ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...