Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጥጋብ ከመንገድ ያስቀራል!

ሰላም! ሰላም! ሰሞኑን እንደ ልማዴ ክው ክው ስል ድንገት፣ ‹‹እኛ ያልነው ካልተደረገ በስተቀር በተቃውሟችን ፀንተን እንገፋበታለን!›› የሚል ዘባራቂ በጆሮዬ ሰምቼ ባልሰማ ታጠፍኩ፡፡ ስሙን እዚህ የማልጠቅስላችሁ መቀለድ የማይታክተው ወዳጄ ደግሞ፣‹‹ ለነገሩ ለአገር ዕድገት ሐሳብ ማዋጣት የማይችል ወይም አንዳች ድጋፍ ማድረግ ያለመደበት ሁሉ፣ ከየጎራው እየተነሳ ሲፎክርና ሲሸልል ነው ነገራችን እንዳይሆን ሆኖ የቀረው…›› እያለ የግል የፖለቲካዊ ትንታኔውን ይሰጣል፡፡ ማንም የፈለገውን መብቱ ነው በሚል እንለፈው እንዳንል፣ ከማለት ታልፎ እኮ ነው ጉልበተኛ የበዛው፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም በድፍረታቸውና በሀቀኝነታቸው የማናውቃቸው አይደሉ እንዴ ዛሬ ደርሰው ያለ እኛ ማን ጀግና አለ ብለው ጉራቸውን የሚነሰንሱብን…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እሱ ከትምህርቱም ከልምዱም ገፋ ያደረገ ስለሆነ ብዙ ያውቃል፡፡ ማን ምን እንደ ነበረ፣ ከእነ ማን ጋር ተቧድኖ ምን ሲሠራ እንደከረመ፣ በወሳኙ ጊዜ አድፍጦ ሰላም ሲሰፍን ሰላም ለማደፍረስ ለምን እንደሚፈልግና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችን በሎጂክ አስደግፎ ሲያስረዳ ያረካል፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ደግሞ የሚነገረኝን እንደ ባዶ ገረወይና መሞላት ሳይሆን፣ ጥያቄዎቼን በፈርጅ በፈርጃቸው ሰድሬ የጎደለውን እየሞላሁ ያልተስካከለው እንዲታረም አግዛለሁ፡፡ ከፍ ያለው ትምህርት ቤት ገብቼ ምስክር ወረቀት ባልይዝም፣ አዕምሮዬ ተማርን ከሚሉት አንሶ እንዳይቀር እታገላለሁ፡፡ ዋናው ጉዳዬ ለዕውቀት መታገል ስለሆነ!

አንድ ቀን ከምሁሩ ወዳጄ ጋር ስናወራ፣ ‹‹እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ ተፀፀተ ሲባል እሰማለሁ፡፡ ከፈጠረን በኋላ ለምን ይሆን የተፀፀተው…›› እያልኩ ጥያቄ ማቅረብ፡፡ ‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል…› አይደል የሚባለው? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ፈገግ ብሎ እያየኝ፣ ‹‹የምድሩ አልበቃ ብሎህ ላይ ወጣህ?›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ወንድሜ አንበርብር! ፈጣሪ ምንም የሚሳነው ነገር የለም፡፡ ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ፀፀቱን ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ ሕግ መጣስ የሰው ልጅ አመል ሆኖ አይደል እንዴ እኔና አንተስ በዙሪያችን በሚፈጠሩ ግፎችና በደሎች ሳቢያ ሰው መሆናችን ለፀፀት የሚዳርገን?›› ሲለኝ የፈጣሪ ረቂቅነት ውልብ አለብኝ፡፡ ‹‹ሰብዓዊ ፍጡር የሚባለው ሰው ከአውሬ በታች ሆኖ አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጽም የሚገባህ፣ ፈጣሪ በራሱ አምሳል ፈጥሮትም እንኳን ለራሱ ቢጤ ሰው ለፈጣሪም የማይመለስ ሆኗል…›› እያለ ሲመለከተኝ፣ ውስጣችን ያለው እሳት ምን ያህል ሰይጣን እንደሚያደርገንና ርህራሔ የሚባል እንጥፍጣፊ እንደሚያሳጣን ብልጭ አለብኝ፡፡ እኔ ደግሞ ብልጭ ሲልብኝ ደሜ ይንተከተካል፡፡ ደሜ ሲንተከተክ መናገርም ሆነ ማዳመጥ ያስጠላኛል፡፡ በዚያን ሰሞን በወገኖቻችን ላይ ያ ሁሉ ውርጅብኝ ሲወርድ ልሳኔ ተዘግቶ ማዳመጫዬን ዘግቼው ነበር፡፡ ክብሪትና ነዳጅ ተሸክመው የሚዞሩ አፍለኛ ዕብዶች በበዙበት ጊዜ ለጊዜው ዝም ማለት ቢያስፈልግም፣ ለዘለቄታው ግን ዘራፍ ብሎ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ዘራፍ ለሰብዓዊነትና ለርህራሔ!

በቀደም ዕለት በድንጋይ መስተዋቶቹ በሙሉ ረግፈው ከቃጠሎ የተረፈ ቅጥቅጥ ለማሻሻጥ ገዥና ሻጭን ለማገናኘት ቀጠሮ ይዣለሁ፡፡ ሰዓቱ እንዳይረፍድ ጣደፍ ጣደፍ ስል አንዱ መንገድ ላይ አስቆመኝ፡፡ ‹‹አንበርብር ሰማህ እንዴ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ይላል ይኼ ምኑን ነው የምሰማው?›› አልኩት ጉዳዩን ሳይነግረኝ ዘሎ ድንጉር ሲል ብልጭ ብሎብኝ፡፡ ‹‹ጀግናው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መኪና እንደ ሸለማቸው ሰማህ አይደል…›› እያለ ወሬኛው መተርተር ከመቀጠሉ በፊት፣ ‹‹ለምን ብሎ?›› ስለው፣ ‹‹ዌል እንግዲህ አድናቂያቸው ስለሆነ ነዋ…›› ብሎ አረፈው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ይህ የሠፈር አውደልዳይ ወሬኛ ቀጥል ቢሉት፣ ‹‹እሱም ወደፊት ፖለቲከኛ መሆን ስለሚፈልግ ከወዲሁ ልምድ ሊቀስም ይሆናል ገፀ በረከት ይዞ ጠጋ ያለው…›› ብሎ ጭራና ቀንድ እያበቀለ ወሬውን ይዘረው ይሆናል፡፡ የቸገረን እኮ እንዲህ ዓይነት ምንጫቸው የማይታወቅ ወሬዎችን በየቦታው እንደ ፈንዲሻ የሚበትኑ በመብዛታቸው ነው፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የተገጣጠመች በኤሌክትሪክ የምትንቀሳቀስ መኪና ነው ያበረከተው እኮ…›› ብለው፣ ‹‹ወይ በኤሌክትሪክ መንቀሳቀስ ህዳሴ ግድቡ ሳያልቅ ኤሌክትሪክ ከየት ሊመጣ ነው… ብዙ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን…›› ብሎኝ ለተጨማሪ አሉባልታ ጥድፊያውን ተያያዘው፡፡  ልብ በሉ እንግዲህ የራሱን የፈጠራ ወሬ እንጂ፣ እውነት ሲነገረው መስማት አይፈልግም፡፡ አውደልዳይ!

እልፍ ስል ደግሞ አንዱ ሞባይል ስልኩን የያዘበትን ግራ እጁን ገትሮ አንዱ፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው እባክችሁ…›› እያለ ሲጮህ ምን ገጠመው ብዬ ጠጋ ማለት፡፡ አንገታቸውና አፋቸው ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ዓርማ ያለበት ስካርፍና ማስክ ያሰሩ ጎረምሶችና ኮረዶች አንዱን ነጭ መሬት ላይ ጥለው ይቀጠቅጡታል፡፡ እኔም ድርጊቱ አስደንግጦኝ፣ ‹‹ለመሆኑ ይህ ሁሉ ጉድ የት ነው?›› ስለው፣ ‹‹እዚህ ባሌ፣ አርሲ ወይም ሐረርጌ እንዳይመስልህ እዚያው ፈረንጁ አገር ነው…›› ሲለኝ ቅዤት ውስጥ ያለሁ ነበር የመሰለኝ፡፡ ሰውየው፣ ‹‹እነዚህ ዕብዶች እንኳን እዚህ ሰው አገር ውስጥም እየኖሩ ሕግ እንዳለ አያውቁም…›› እያለ በንዴት ሲንጨረጨር፣ ‹‹በሕግ አምላክ እየተባለ ፍትሕ የሚጠየቅበት ሥፍራ አጣን እኮ እናንተ…›› የሚል ወፈፍ ያደረገው የሚመስል ሰው ከፊት ለፊቴ ሲመጣ አየሁ፡፡ ይህ ደግሞ ምን ሆኖ ይሆን ብዬ ቆሜ ሳየው፣ ‹‹ኦ ፍትሕ በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ? በሴረኛ ፖለቲከኞችና በአሽከሮቻቸው የሕዝብ አስመሳይ ተቆርቋሪነት ስንትና ስንት ወንጀል ተፈጸመ? በገዛ አገራችን እንደ ጠላት እየተሳደድን ስንገደልና ስንዘረፍ አስተዳዳሪውና ፖሊሱ ቆመው አዩን፡፡ አቤት የሚባልበት ፍርድ ቤት ጭምር ሲቃጠል ነፍሳችንን ለማትረፍ እግሬ አውጪን ብለን ሜዳ ላይ ወድቀን ተመልካች አጥተናል፡፡ ፍትሕ የት ነው ያለሽው?›› እያለ ሲጮህ ዕንባዬን እያንጠባጠብኩ ወደ ጉዳዬ አመራሁ፡፡ ዕጣ ፈንታችን እንዲህ ሲሆን ያስለቅሳል!

አዛውንቱ ባሻዬ ዘወትር፣ ‹‹የትኛውም ዓይነት አለመግባባት ወደ ጠብ ከሚያመራ በሰላም ተፈትቶ፣ በሰላም ወጥተን መግባት የዘወትር ፀሎታችን መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ አንድም የጥይት ድምፅ በምድረ ኢትዮጵያ እንዳይሰማና በምትኩ የእልልታና የሆታ ድምፅ ብቻ እየሰማን መኖር የዘመናት ምኞታችን ነው፡፡ ጦርነት በተለይም የእርስ በርስ ጦርነት እንኳንስ ዓይነተ ብዙ የሆኑ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባት አገር ቀርቶ፣ ሩዋንዳ በምትባል አገር በሁለት ጎሳዎች መሀል ሆን ተብሎ በተለኮሰ እሳት ምን ያህል አሰቃቂ ዕልቂትና ውድመት እንደ ደረሰ በእኛ ዕድሜ ተመልክተናል፡፡ እኛ ከሌሎች መከራ መማር ሲገባን ጭራሽ አስበልጠን ለመፋጀት የሴረኞች ወጥመድ ውስጥ ለምን እንደምንወድቅ ይገርመኛል…›› የሚሉት ትዝ እያለኝ ነበር፡፡ እነዚያ የሠለጠነ አገር እየኖሩ ሰብዓዊ ፍጡርን ያለ ርህራሔ ካሜራ ፊት የሚቀጠቅጡ ወጣቶች በጣም ነው ያሳዘኑኝ፡፡ ለምን አትሉኝም? መልካም መካሪና ተቆጪ ቢኖራቸው ኖሮ እንዲህ ያለ ነውር በአደባባይ ይፈጽሙ ነበር? ዓርማውን ለብሰው እስር ቤት የሚያስገባ ወንጀል የሚፈጽሙ ወጣቶችን መገሰፅ ያልቻለ ዕድሜ ጠገብ ፓርቲስ ከእነሱ በምን ይሻላል? የማያፍር ሰው ያሳፍራል አትሉም ታዲያ!

ከዕለታት በአንዱ ቀን እግሬን ለማፍታት አውራ ጎዳናው ላይ ሳዘግም፣ አንድ ጡንቻው የፈረጠመ ፖሊስ ይገፈትረኛል፡፡ እኔም በትህትና፣ ‹‹ምነው ወንድም ምን ስህተት ሠራሁ?›› ማለት፡፡ ‹‹ለምንድነው ቀስ ብለህ እየሄድክ ግራና ቀኝ የምታየው?›› ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ እኔም ያ ብልጭታዬ ድንገት ደርሶ፣ ‹‹በየትኛው ሕግ ነው ቀስ ተብሎ መሄድ የተከለከለው? ግራና ቀኝ ማየትስ መቼ ነው ክልክል የሆነው?›› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹ቀጥል ከእኔ ጋር አፍ መካፈት አትችልም…›› እያለ ያልተጻፈ ሕግ መተንተን ሲጀምር አንድ ባልደረባው ደርሶ ገላገለኝ፡፡ ባልደረባው ባይደርስ ኖሮ ከእነ ሽበቴ በጥፊ ሊያላጋኝ እንደከጀለ ያስታውቅበት ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ እዚህ ግባ የማይባል የደላላ ምክሬን ለመንግሥት ባቀርብ ብዬ እመኛለሁ፡፡ ምን አትሉኝም? በሥርዓቱ ሳይሠለጥኑና በጥብቅ ዲሲፕሊን ሳይታነፁ ጠመንጃ አስታጥቆ አያሰማራብን፡፡ ምንም አታመጡም በሚል ስሜት  ጡንቻቸውን የወጠሩ ፖሊሶች እኮ ሕዝብ በየቦታው ሲጠቃ ድርሽ እንደማይሉ ከተጠቂዎች አንደበት ሰምተናል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የአጥቂዎች ከለላ ከመሆን አልፈው ሲዘርፉ የነበሩ እንዳሉም በግልጽ ነው የሰማነው፡፡ ብዙኃኑን የሚያሰድቡና የፖለቲከኞች ተላላኪ የሆኑትን ታቅፎ መቀጠል አይገባም፡፡ የከፋው ሲመጣ ግጭቱን በማስፋፋት አገር አሳር ያሳያሉ ለማለት ነው፡፡ ሰሚ ካለ ተናግረናል!

ዳሩ ምን ዋጋ አለው አንኳ አንድ ተራ ደላላ ቀርቶ የተማረ በማይከበርባት ምስኪን አገር ውስጥ፣  ወይም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደሚለው ጥራዝ ነጠቅ እንጂ በሳል በማይፈለግባት አገር ውስጥ የደላላ ምክር አዳማጭ ያገኛል ቢባል ሞኝነት ነው፡፡ አንድ ልባም ወዳጅ ነበረኝ፡፡ የዛሬን አያድርገውና በሕይወት ሳለ ሁልጊዜ ቁምነገር ከአፉ አይጠፋም፡፡ አንድ ጊዜ በዘመነ ኢሕአዴግ ጊዜ ያገነናቸው አንድ ቱባ ባለሥልጣን፣ ‹‹በቁጥጥር ሥር ያዋልናቸው በሙሉ አሸባሪዎች ናቸው፡፡ የማስረጃና የመረጃ ችግር የለብንም፡፡ እያንዳንዳቸው በፈጸሙት ወንጀል ተገቢውን ፍርድ ያገኛሉ…›› እያሉ ሲዝቱ ሰምቶ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተል ቆየ፡፡ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ዓቃቤ ሕግ እንደተባለው የመረጃና የማስረጃ ክምር ሳይሆን ይዞ የሚቀርበው፣ መንግሥትን ራሱን የሚያሳፍር ከላባ የቀለለ አርቲቡርቲ ስለነበር፣ ‹‹አይ ጊዜ እኚህም ሰው እኮ አንድ ቀን ሰው እጅ ላይ ወድቀው ፍትሕ ይጠይቁ ይሆናል…›› ያለው አይረሳኝም፡፡ በእርግጥም እሱ በሕይወት ባይኖርም እሳቸው ግን ተከሰው እስር ላይ ናቸው፡፡ ንፁኃንን አስረው ሲዛበቱ ኖረው ለእሳቸው የሚቆረቆር ጠፍቶ፣ ይኸው ከቤተሰብ ርቀው ያሳለፉትን ዘመን በፀፀት ያስባሉ፡፡ ምክር አልሰማ ብለው በሌሎች ላይ ሲያስፈርዱ አንድዬ በተራው መጣባቸው፡፡ እንዲህ ነው ነገሩ!

ከበፊት እስካሁን ፖለቲከኞች ሲባሉ ችግር አለባቸው፡፡ ሰሞኑን በተፈጠረው ደም አፋሳሽና አገር አውዳሚ ሁከት ተጠርጥረው ከተያዙት መሀል አንዱ፣ ከጥጋቡ የተነሳ ዓለምን የተቆጣጠረ ይመስለው ነበር ብላችሁ በማጋነን እንደማትከሱኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እሱ ደግሞ ማን ነው ካላችሁኝ ስድስተኛው ስሜታችሁ ይንገራችሁ እንጂ፣ እኔ በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር አላሳርፍም፡፡ የሆነ ሆኖ ጥጋብ ሲበዛ ረሃብ እንደሚያስረሳ የደረሰባቸው ያውቁታል፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ አንድ ጊዜ ይህንን ዕድሜ ጠገብ ተረት ነገሩኝ፡፡ ውሻና አህያ አርጅተው ከቤት ተባረው ስደት ሲጓዙ ቀኑን ሙሉ የሚበላ አጥተው አመሻሽ ላይ አንድ ለጥ ያለ ሜዳ ይደርሳሉ፡፡ መሰንበቻውን ዝናብ ጥሎ ጨሌ ሳር በቅሎ ያብረቀርቃል፡፡ አህያ ያንን ጨሌ ሳር መጋጥ ስትጀምር ውሻ የሚበላ ስላላገኘ ኩርምት ብሎ ይተኛል፡፡ አህያ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥጋብ ይዟት ማናፋት ትጀምራለች፡፡ ውሻ ደንግጦ፣ ‹‹በፈጠረሽ በጅብ መንጋ እንዳታስበይን…›› እያለ ቢለምናት እንቢ ብላ ሦስቴ በተከታታይ ማናፋቷን ትቀጥላለች፡፡ እባካችሁ አፍለኛ ፖለቲከኞች ሰከን በሉ ሲባል አልሰማ ብለው እንዳይሆኑ ሆነው የቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው ከማለት ውጪ ምን ይባላል፡፡

ምስኪኑ ውሻ ምክሩን የሚሰማው አጥቶ ቢጨንቀው፣ ‹‹አንደኛው መጥሪያ፣ ሁለተኛው ማቃረቢያ ሲሆን፣ ሦስተኛው ግን መበያ ነው…›› ከማለቱ አያ ጅቦ ከተፍ አለ፡፡ እንደ ደረሰም አህያዋ ላይ ጉብ ብሎ በቅጽበት ዘነጣጠላት፡፡ ከተለያዩ የሥጋዋ ክፍሎች ከጎራረሰ በኋላ ዞር ሲል ምስኪኑን ውሻ አየው፡፡ ‹‹አንተ ደግሞ ምንድነህ›?› ሲለው፣ ‹‹እኔማ የጌታዬ ሥጋ በላች ነኝ…›› ብሎ ሲመልስለት፣ ‹‹በል ከሽንጥና ከዳቢት አስተካክለህ አምጣልኝ…›› ብሎ ያዘዋል፡፡ ውሻም ርቦት ስለነበር ፊት ለፊት ያገኘውን ጉበትና ልብ ስልቅጥ አድርጎ ካጣጣመ በኋላ የታዘዘውን ያቀርባል፡፡ ጅብ የቀረበለትን ጎራርሶ ሲጨርስ፣ ‹‹አንተ ቶሎ ብለህ ልቧን አምጣልኝ…›› በማለት ሲያዘው፣ ‹‹ጌታዬ ይህች አህያ ልብ የላትም…›› ይለዋል፡፡ ጅብ ተናዶ፣ ‹‹አንተ አጭበርባሪ እንዴት ነው ልብ የሌላት እባክህ…›› ሲለው፣ ‹‹ጌታዬ ልብ ቢኖራት ኖሮ ተይ ስትባል እንቢ ብላ አናፍታ የእርስዎ እራት ትሆን ነበር…›› አለው ይባላል ነበር ያሉኝ ባሻዬ፡፡ እኔም እስቲ ልብ እንግዛ ብዬ ብሰናበታችሁ ትቆጡኛላችሁ? ወይስ ታኮርፉኛላችሁ? የቸገረ ነገር እኮ ነው የገጠመን፡፡ ጥጋብ ከመንገድ ያስቀራልና እስ እንስከን፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት