የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የኮረናን ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ ግማሽ ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞቹን ለማሰራት አቅዶ፣ ከ300 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞች በማሰማራት ከስምንት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተደራሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
በክልሉ የአፍና ፊት መሸፈኛ አጠቃቀም ዝቅተኛ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ የእጅ መታጠብም ቢሆን ከባንኮች፣ ከአንዳንድ ትልልቅ ተቋማትና ሕንፃዎች ውጪ የሚታይ እንዳልሆነ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ትምህርት የሚሰጥ ምንም አካል እንደማይታይ የትራንስፖርት አጠቃቀም የተሻለ ቢሆንም ለመግባት ግን ተጋፍቶ መሆኑ፣ የገበያ ማዕከላትና መዝናኛ ቦታዎች ልቅ መሆናቸው በክልሉ የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ከምንጊዜውም በላይ ተጋላጭነታቸው እንዲሰፋ ማድረጋቸውን የቅርንጫፉ ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ ገልጸዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ የሚገኘው ጦና ሆስፒታልን ጨምሮ በሐዋሳ ከተማም ሦስት መንደሮች መዘጋታቸው፣ የመዘጋት ዕድል በለይቶ ማቆያ፣ በሆስፒታሎችና በእስር ቤቶች ከፍተኛ የበሽታው ቅድመ መከላከያ ግብዓቶች እጥረት እንዳለም ታውቋል፡፡
አቶ ተሾመ እንደሚሉት፣ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በክልሉ በቀን ከ6,000 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር ማምረቻ ከመገንባት ጀምሮ በ25 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በመንግሥት፣ በጤና ተቋማት በሙሉ የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎችን አከፋፍለዋል፡፡ በለይቶ ማቆያዎች ደግሞ ፍራሾችን፣ ብርድ ልብሶችንና የውኃ ማጠራቀሚያዎችን ገዝቶ በእነዚሁ ተቋማቶች ሁሉ የርጭት ሥራ እንደሚከናወን ገልጸው፣ በቅርቡም በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ዞን ለክልሉ የሚበቃ ሳኒታይዘር ማምረቻ ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቻውን አክለዋል፡፡
በደቡብ ቅርንጫፍ ኃላፊ የሚመራ ቡድን፣ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሳምንት አንድ ቀን በቪዲዮ ኮንፈረንስ የመረጃ ልውውጥ በማካሄድ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር እየሠራ ሲሆን፣ ይህን አካሄድ ሌሎችም ክልሎች እንደ መልካም ልምድ በመውሰድ ቢተገብሩት መልካም ነው ብለዋል፡፡