Thursday, June 20, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስልክ ተደወለላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አቤት፡፡
 • እሺ ምን እናድርግ?
 • ማን ልበል?
 • ባለፈው ደውዬልዎት ነበር፡፡
 • ይቅርታ ብዙ ሰዎች ስለሚደውሉልኝ ነው፡፡
 • ከእኔ ጋር ረዥም ሰዓት ነበር ያወራነው፡፡
 • ስለምን ጉዳይ?
 • ስለሰሞኑ ሁከትና ብጥብጥ ነዋ፡፡
 • እሺ፡፡
 • በሁከቱ ከፍተኛ ውድመት ደርሶብኝ ነበር፡፡
 • አሁን አስታወስኩህ፡፡
 • ምን እየተደረገ ነው ግን ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ተደረገ?
 • ያ ሁሉ በደል መድረሱ ሳያንስ ድጋሚ ምን አጠፋን?
 • ድጋሚ ጥቃት ደረሰባችሁ እንዴ?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡
 • ሆነ እያልኩዎት እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በድጋሚ ቤታችሁ ተቃጠለ?
 • ምን ቤት ኖሮን ያቃጥላሉ?
 • ታዲያ የሥራ ቦታችሁን በድጋሚ አቃጠሉት?
 • ከመጀመርያው ቃጠሎ ምን የተረፈ ነገር አለ ብለው ነው?
 • ምን ዓይነት ጥቃት ነው የደረሰባችሁ ታዲያ?
 • ክቡር ሚኒስትር ባለፈው የመከሩኝ ትዝ ይልዎታል አይደል?
 • ምን ነበር?
 • በሚዲያ እንድቀርብና ሕዝቡ ከታሪኬ እንዲማር ተስማምተን ነበር፡፡
 • በትክክል አስታውሳለሁ፡፡
 • እኔም እርስዎ እንዳሉኝ አደረግኩ፡፡
 • በጣም ጥሩ፡፡
 • ምን በጣም ጥሩ በጣም መጥፎ ነው እንጂ፡፡
 • ለምን?
 • ይኸው የስልክ መዓት ነው የሚደወልልኝ፡፡
 • ሊረዱህ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው?
 • ኧረ በፍፁም፡፡
 • በታሪክህ ያዘኑ ሰዎች ናቸው ታዲያ?
 • ኧረ እንዲያውም፡፡
 • ታዲያ ማን ናቸው የሚደውሉልህ?
 • የአካባቢው ባለሥልጣናት፡፡
 • እንረዳሃለን ብለው ነው?
 • ምን በወጣቸው?
 • ታዲያ ለምንድነው የሚደውሉልህ?
 • ሊያስፈራሩኝ ነዋ፡፡
 • ምን ብለው?
 • አርፈህ ተቀመጥ፡፡
 • ለምን?
 • ሥራቸው እንዳይጋለጥ ነዋ፡፡
 • የምን ሥራ?
 • ሴራቸው ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንደዚህማ አይቀለድም፡፡
 • ይኸው እየነገርኩዎት እኮ ነው፡፡
 • እኔ ጠፋሁ፡፡
 • አሁን ለሕይወቴም እየፈራሁ ነው፡፡
 • ፈጽሞ እንዳታስብ፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስነግርህ ስልካቸውን ላክልኝ፡፡
 • ምን ሊያደርጓቸው?
 • አስገባቸዋለሁ፡፡
 • የት?
 • ዘብጥያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ባለሥልጣን ስልክ ደወሉ]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ትንሽ አታፍርም?
 • ምን አጠፋሁ?
 • ምነው እንዲህ አናት ላይ እንውጣ አላችሁ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰውን ባትፈሩ እግዚአብሔርን አትፈሩም እንዴ?
 • እ. . .
 • ለነገሩ እሱንማ ብትፈሩ እንዲህ አታደርጉም ነበር፡፡
 • ሰባኪ ሆኑ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን?
 • ያው ስለእግዚአብሔር ወሬ አበዙብኝ ብዬ ነው፡፡
 • አርፋችሁ ብትቀመጡ ጥሩ ነው፡፡
 • ምን አደረግን?
 • ሰውን እያሸበራችሁት እንደሆነ ሰምተናል፡፡
 • ምን አድርገን?
 • ለምን ሚዲያ ላይ ቀረባችሁ እያላችሁ ነዋ፡፡
 • አሁን እኮ አካባቢያችን እየተረጋጋ ነው፡፡
 • ታዲያ ቢረጋጋስ?
 • ያው ሰው በሚዲያ ወጥቶ ሲናገር ሌላ ሁከት እንዳይነሳ አስበን ነው፡፡
 • ሌላ ሁከትም ለመቀስቀስ ታስባላችሁ?
 • ኧረ በፍፁም፡፡
 • ታዲያ ስለምን ሁከት ነው የምታወራው?
 • ማለቴ የተጎዱ ሰዎች ቀርበው ሲያወሩ ሌላ ጥላቻ ይፈጠራል ብለን ነው፡፡
 • እኮ እናንተ ለሕዝቡ አስባችሁ?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ካሰባችሁ ታዲያ ያ ሁሉ ጥፋት ሲደርስ የት የነበራችሁ?
 • እ. . .
 • መልስልኝ እንጂ?
 • ያው ከአቅማችን በላይ ነበር እኮ፡፡
 • አልመሰለኝም፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የእናንተም እጅ እንደነበረበት እየተወራ ነው፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተን ምን ነክቶሃል ብዬ ልጠይቅህ እንጂ፡፡
 • ስሜን እኮ እያጠፉት ነው?
 • እናንተ የሰው ሕይወትና ንብረት ስታጠፉ እንዴት አልተሰማህም?
 • እ. . .
 • አሁን ያለ እናንተ ዕርዳታ ያ ሁሉ ሊፈጸም ይችላል?
 • እኔ እንጃ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለማንኛውም እየተጣራ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • ሁሉም ነገር ነዋ፡፡
 • እኔ ምንም አላደረግኩም፡፡
 • ነገርኩህ እኮ መረጃ እየተሰበሰበ ነው፡፡
 • እኛም እኮ ለዚያ ነው በየሚዲያው አትቅረቡ የምንለው፡፡
 • መረጃ እንዳይሰጡባችሁ?
 • እ. . .
 • ለማንኛውም ተዘጋጅ፡፡
 • ለምኑ?
 • ያው በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርማ፡፡
 • ምን ልታደርጉን ነው?
 • የሚገባችሁ ቦታ ትገባላችሁ፡፡
 • የት?
 • እስር ቤት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሽማግሌ ስልክ ደወሉላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነዎት አባት?
 • በጣም ሰላም ነኝ እርስዎስ?
 • እኔም ሰላም ነኝ፡፡
 • እንዴት ሆነች ያቺ ጉዳይ?
 • የቷ ጉዳይ?
 • ባለፈው ሽምግልና የመጣንባት ናታ፡፡
 • ከዚህ በኋላ ሽምግልና እኮ አይሠራም፡፡
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • ሽምግልና እኮ ባህላችን ነው፡፡
 • አውቃለሁ አባቴ፡፡
 • ታዲያ ሽምግልና እንዴት እምቢ ይባላል?
 • ጥያቄው ከማን ጋር ነው ሽምግልናው ነው የሚለው ነዋ፡፡
 • ያው ከበፊቶቹ ባለሥልጣናት ጋር ነዋ፡፡
 • እኛ መቼ ተጣላን?
 • ምን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ይኸው አገሪቱ እየታመሰች ያለችው በእናንተ ጥል ምክንያት አይደል እንዴ?
 • አዩ እርስዎ ራስዎ የሁከቱ መነሻ እነሱ እንደሆኑ ያውቃሉ?
 • ያው እኔ እንኳን ሲወራ ሰምቼ ነው፡፡
 • ለነገሩ አልተሳሳቱም፡፡
 • ለማንኛውም እኔ እንደ ሽማግሌ ማስታረቅ እንጂ እሱ አይመለከተኝም፡፡
 • አባቴ የእርስዎ ጥረትና ፍላጎት ይገኛባል፡፡
 • ታዲያ ምላሻችሁ ምንድነው?
 • አሁን  ጉዳዩ የሚፈታው በሕግ እንጂ በሽምግልና አይደለም፡፡
 • እንዴት?
 • ሰዎች ወንጀል ሠርተው ሽምግልና አይሠራም፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ስለዚህ ይኼ አካሄድ አያዋጣም፡፡
 • የትኛው ክቡር ሚኒስትር?
 • የሽምግልናው ነዋ፡፡
 • ለምን?
 • ወንጀል ሠርቶ አሸማግሉኝ ማለት አያስኬድማ፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለ?
 • እኛ ጉዳዩን በሕግ እየሄድንበት ነው፡፡
 • እኛ እኮ ሥጋታችን ሕዝብ እንዳይጎዳ ነው፡፡
 • የእኛም ትዕግሥት እኮ ሕዝቡ እንዳይጎዳ ከሚል የመነጨ ነበር፡፡
 • ጥሩ አድርጋችኋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን  ግን በቃ ብለናል፡፡
 • ምኑን?
 • ትዕግሥቱን ነዋ፡፡
 • እና ምን ልታደርጉ?
 • ልንወስድ ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ዕርምጃ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምንድነው የምሰማው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሰማህ?
 • የሰላም ሰዎች ነን ስትሉ አልነበር እንዴ?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • እንዲያውም የሰላም ሚኒስቴር አቋቁማችኋል፡፡
 • በትክክል፡፡
 • ታዲያ ምነው ሰላም ማምጣት አቃታችሁ?
 • እናንተ እያላችሁ ምን ሰላም አለ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • በየቦታው ሁከትና ብጥብጥ እየለኮሳችሁ ሰላም ከየት ይምጣ?
 • እንዲህማ ሊሉን አይችሉም፡፡
 • ለምን?
 • እምቢ ያላችሁት እኮ እናንተ ናችሁ፡፡
 • ምኑን?
 • ሽምግልናውን ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ሽምግልና ነው?
 • እንታረቅ አልን እኮ፡፡
 • ከዚያ አራት ኪሎ ልትገቡ?
 • ምን አለበት?
 • እሱ መቼም አይፈጸምም፡፡
 • ስለዚህ ሰላም አንፈልግም ያላችሁት እኮ እናንተ ናችሁ፡፡
 • ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አሉ፡፡
 • ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የሰላሙን መፍትሔማ አላገጣችሁበት እኮ፡፡
 • እንዴት?
 • ትዕግሥታችንን ተሳለቃችሁበት፡፡
 • እኛ?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ገብቶናል እባካችሁ፡፡
 • ምን?
 • እናንተ አለመዳችሁም፡፡
 • ምንድነው ያለመድነው?
 • ሰላማዊ መንገድን መከተል ነዋ፡፡
 • እ. . .
 • ከዚህ በኋላ ጉዳዩ የሚያልቀው በአንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡
 • በምን?
 • በሕግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...