Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዒድ አል-አድሃ ክብረ በዓል

የዒድ አል-አድሃ ክብረ በዓል

ቀን:

በእስልምና ሃይማኖት ከተቀደሱ ወሮች አንዱ በሆነው፣ ዙልሂጃህ ወር አሥረኛ ቀን ላይ የሚውለው ዒድ አል-አድሃ፣ “የመስዋዕት ክብረ በዓል” ከነገ በስቲያ ዓርብ ሐምሌ 24 ቀን 2012 ዓም (ዓመት) ይከበራል፡፡ በዓለም ሙስሊሞች ከሚከበሩት ሁለት ዒዶች ሁለተኛው ነው፡፡ ሌላኛው ዒድ-አል-ፈጥር ወይም ከአንድ ወር ጾም በኋላ የሚከበረው የረመዳን ዒድ ነው፡፡

በኢስላሚክ ካላንደር አሥራ ሁለተኛና የመጨረሻ ወር የሚከበረው ዒድ አል-አድሃ ወደ መካ የሐጅ ጉዞ ይደረግበታል፡፡ የወሩ መጠርያ “ዙልሂጃህ” ጥሬ ትርጉሙ “የሐጅ ወር” ነው፡፡ በዚህ ወር በዓለም ዙርያ የሚገኙ ሙስሊሞች ወደ መካ ካባ ይዘልቃሉ፡፡

ዒድ አልአድሃ መነሻው ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን ለመሰዋትአላህ ያሳዩት ታዛዥነትና ታማኝነት ነው፡፡ ኢብራሂም ልጃቸውን ለመስዋዕት ሲያዘጋጁ በምትኩ በግ ለመስዋዕትነት የቀረበበት ነው፡፡ ይህንኑ ድርጊት ተከትሎ ለአረፋ ሕዝበ ሙስሊሙ በግ አርዶ ማዕዱን ይቋደሳል፡፡ የተዘጋጀውን ምግብ ከፊሉን ለደሃና ለሚያስፈልጋቸው፣ ሌላውን ለቤተሰብና ቀሪውን ለቤተዘመድ እንዲከፋፈል ይደረጋል፡፡

የአረፋ አከባበር ሌላ ታሪካዊ ዳራ እንዳለው ይወሳል፡፡ አደምና ሃዋ የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ በማጉደላቸው የተነሳ ከገነት ወደ ምድራዊ ዓለም ተባረው ተለያይተው ከኖሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙትአርዱል አረፋ” ተብሎ በሚጠራው የአረፋ ኮረብታ ላይ በመሆኑ ረፍኪኒ፣ አረፍቲኒ መባባላቸው ይታሰብበታል፡፡

ዘንድሮ በዓሉ እንደቀድሞው በአደባባይ እንዳይከበር የኮሮና ቫይረስ ሥጋት ሆኗል፡፡ ሁሉም በያለበት ሆኖ እንዲያከብር ማሳሰቢያ የሰጡት በተለይ የጉራጌና ስልጤ ዞኖች ናቸው፡፡ የአካባቢዎቹ ተወላጆች እንደሁሌው ወደ ዞኖቹ መጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዓሉን ማክበር እንደሌለባቸው አስተዳደሮቹ ባለፈው ሳምንት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቀረበውን ጥሪ ተላልፈው በዓሉን ለማክበር ወደ ዞኑ የሚመጡ ካሉ ግን 14 ቀን የለይቶ ማቆያ ቆይታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ኅብረተሰቡ እንደማይቀላቀሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የአረፋ ነባር አከባበር

የአረፋ በዓል ከሚከበርባቸው አካባቢዎች በደቡብ ክልል የሚገኙት የጉራጌና ስልጤ ዞኖች ይጠቀሳሉ፡፡ ስለ ዒድ አል-አድሃ አከባበር ከየዞኖቹ ያገኘናቸው መረጃዎች እንዲህ አቀናብረናቸዋል፡፡

“ጉራጌና የባህል እሴቶቹ” በሚል ርዕስ በዞኑ የባህል ጥናትና ልማት የሥራ ሒደት በተዘጋጀው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸውበጉራጌ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል የአረፋ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሆኑት የብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ደምቆ ይከበራል፡፡

 ለአረፋ በዓል የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በዚህም እናቶች ለበዓሉ የሚሆን መጪ (ምርጥ) ቆጮ፣ ቅቤ፣ ሚጥሚጣ …ወዘተ ሲያዘጋጁ ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳትና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡

ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከወን ይሆናል፡፡

አረፋ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው የጉራጌ ተወላጅ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ከየሚኖርበት የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ የትውልድ ቀዬው የሚመለስበትና በዓሉን ከወላጆች፣ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ከአብሮ አደግ ጓደኛ …ወዘተ ጋር በመሆን የሚያከብርበት ታላቅ በዓል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የአረፋ በዓል በሥራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውንም ሙስሊም የጉራጌ ተወላጅ ከያለበት አሰባስቦ የሚያገናኝም በዓል ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ደግሞ በቀጣዩ ሦስት ጉልቻ ለመመሥረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሠረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑን የብሔረሰቡ ተወላጆች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የአረፋ በዓል ያለው ማኅበራዊ ፋይዳ በተጣሉ ሰዎች መሀል እርቀ – ሰላም እንዲወርድ የማስቻል ብቃቱ ይሆናል፡፡ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጅ፣ ጎረቤታሞች …ወዘተ በአረፋ ሰሞን “ይቅር” ተባብለው ሰላምን ያወርዳሉ፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀውን አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉም፡፡

የአረፋ በዓል ሌላው ማኅበራዊው ፋይዳው ከአራቱም ማዕዘናት በዓሉን ለማክበር ወደ ትውልድ አካባቢው የመጣው ሙስሊሙ የጉራጌ ተወላጅ በቤተሰባዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔዎችን የሚሻበት መሆኑ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ ሕይወት እንዲሻሻል “ምን ይደረግ?” በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋ “ምን እንሥራ?” ብለው ለበዓሉ እትብታቸው ወደ ተቀበረበት ምድር የተመለሱት በአንድነት ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ይመክራሉ፡፡ መፍትሔዎችንም ያበጃሉ፡፡

በአጠቃላይ የአረፋ በዓል ሙስሊም በሆነው የጉራጌ ተወላጅ ዘንድ ሁሉ ከፍተኛ ግምት ሰጥቶት የሚከበር በዓል ሲሆን ከመብላትና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች ብዛት ያላቸው ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎችም ጭምር ያሉት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ስልጤ

በስልጤ ዞን በከፍተኛ ድምቀት ስለሚከበረው ትልቁ በዓል አረፋ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ድርሳን ላይ የሚከተለውን አስፍሯል፡፡
አረፋ ገና ከመድረሱ ቀደም ብሎ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ከፍተኛ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ሴቶች ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና ቆጮ ያዘጋጃሉ፣ አባወራዎች ለእርድ የሚሆን ሠንጋና የማገዶ እንጨት ያቀርባሉ፡፡ ልጃገረዶች ቤቶቹን በተለያዩ የማስዋቢያ ቀለማት በመጠቀም ይቀባሉ፣ ግቢን ያፀዳሉ፡፡ በበዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደየአካባቢያቸው ይገባሉ፡፡

 የአረፋ በዓልን በስልጤ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው በበዓሉ ሰሞን የሚጀመረው የልጃገረዶች ጭፈራ ነው፡፡ በየመንገዱ ያሉ ልጃገረዶች ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በመሄድ በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚጨፍሩበት ወንዶች ወጣቶችም በመሄድ አብረው ሲጫወቱ ለወደፊት የምትሆን የትዳር አጋራቸውን የሚያጩበት ወቅት ነው፡፡ በበዓሉ ዋዜማ የሚከበረው የሴቶች አረፋ ሲሆን የወንዶች ደግሞ የበዓሉ ስግደት በሚከናወንበት ዕለት ነው፡፡ በሴቶች አረፋ ክልፋን (የተከተፈ ጐመን) አተካና (ቡላ፣ አይብና ቅቤ) የተለመዱ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ እርዱ የሚከናወነው በበዓሉ ዕለት በሽማግሌ ከተመረቀ በኋላ ነው፡፡ የአረፋ በዓል ብሔረሰቡ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ዝግጅት የሚያደርግበት የተለያዩ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበት ስጦታ የሚለዋወጡበት ትዳር ያልያዘ የሚተጫጭበት ትዳር የሚመሠርቱበት በዓል በመሆኑ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...