Monday, June 17, 2024

ጥቂቶች ብዙኃኑን ሕዝብ ድምፅ አልባ ማድረጋቸው ይብቃ!

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድምፃቸው በጣም ጎልቶ የሚሰማው በጣም ጥቂቶች ስለሆኑ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ ግን ድምፅ አልባ ሆኖ ተመልካች የለውም፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ በዚህ ዘመን በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች፣ ድምፅ አልባውን ብዙኃን ሕዝብ እየዘነጉ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ጥቂቶች እጅ ላይ ያለ ይመስል ከመጠን በላይ ያስተጋባሉ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ አመራሮቻቸው ጭምር ብዙኃኑን ድምፅ አልባ ሕዝብ እየናቁ፣ እነሱም የፖለቲካ ልፊያውን በእሱ ሕይወትና ንብረት መስዋዕትነት ላይ ለመመሥረት ይጣደፋሉ፡፡ መንግሥትም የብዙኃኑን ሕዝብ ፍላጎት በመዘንጋት መላ ትኩረቱ ጥቂቶች ላይ ነው፡፡ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የሚመሩ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው ቢበዙ ግን፣ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ብዙኃኑ ሕዝብ እንደሆነ ይረዱ ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ኖሮ ሕዝብ በነፃነት በሚሰጠው ድምፅ መሆን ሲገባው፣ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነቱ ተረስቶ እንደ መናኛ ዕቃ ወደ ጎን ተገፍቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመጣል ይልቅ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሥልጣን ለመያዝ ወይም የተያዘውን ሥልጣን ለማጠናከር መሰሪ ድርጊቶች ይከናወናሉ፡፡ ጥቂቶች እንደፈለጉ እየጮሁ ድምፃቸው ከጣራ በላይ ሲሰማ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ ግን ተንቆ ድምፅ አልባ ተደርጓል፡፡ በአገሩ ጉዳይ የመወሰን መብቱን ተነፍጎ ጥቂቶች በሚጭሩት እሳት ይለበለባል፡፡ የተሻለ ሥርዓት ተገንብቶ ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል መደላድል ከመፍጠር ይልቅ፣ ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ በማዝገም ብዙኃኑን ድምፅ አልባ ሕዝብ ተስፋ ማስቆረጥ የብዙዎች ፖለቲከኞችና ቢጤዎቻቸው የተለመደ ድርጊት እየሆነ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለማስገንዘብ እንደተሞከረው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች እየተራገፉበት አንዲት ጋት ወደ ፊት መራመድ ተስኖት ቆይቷል፡፡ ከማርክሲስቶች የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም እስከ አደናጋሪው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ድረስ፣ አገርን ወደኋላ የሚጎትቱ አስተሳሰቦች ገዥ እንዲሆኑ ተደርገው የትውልድ ዕልቂትና ከፍተኛ የአገር ሀብት ብክነት ደርሷል፡፡ በየዘመኑ የሚከሰቱ ጉልበተኞች ሕዝቡ ላይ እንዳሻቸው የፈለጉትን እየጫኑ አምባገነንነትን ጌጥ አድርገዋል፡፡ ልሂቃኑን በጥቅም እየደለሉና እያስፈራሩ አገሪቱን እንደ ላቦራቶሪ አይጥ ቀልደውባታል፡፡ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት የሚገዛ ሥርዓት በአገር በቀል ዕውቀቶች ጭምር በመታገዝ መገንባት እየተቻለ፣ ከውጭ በተቃረሙ ጥራዝ ነጠቅ መነባንቦች ምክንያት አገርን የሚበታትን አንቀጽ ሕገ መንግሥት ውስጥ በመሻጥ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያዊያንን የዘመናት አብሮ የመኖርና የጋራ አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶች የሚንዱ፣ ኅብረ ብሔራዊነትን የሚጋፉ፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ከማጉላት ይልቅ የሚከፋፍሉ፣ ማስረጃ የማይቀርብባቸው ሐሰተኛ የታሪክ ትንታኔዎችን በመፍጠርና ለአገረ መንግሥት ግንባታ የሚያግዙ አማራጮችን በመደፍጠጥ ሕዝቡን ማንገላታት ዋነኛ ሥራ ሆኗል፡፡ ለብዙኃኑ ሕዝብ ደንታ ባለመኖርና ከአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተሳትፎውን በመገደብ፣ ድምፅ አልባ ሆኖ የበርካታ ጉዳቶች ሰለባ እንዲሆን አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ አሁንም በብዙኃኑ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ንግግር የሚደረገው፣ በጣም ጥቂት በሚባሉ ልሂቃን መሆኑ አነጋጋሪ ነው፡፡ ብዙኃኑን ሕዝብ ወደ ጎን በመግፋት በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚደረጉ ውይይቶችም ሆኑ ክርክሮች ጉንጭ አልፋ የሚሆኑት፣ የሚነሱት ሐሳቦች በጣም ጠባብ ዕይታ ባላቸው ጥቂቶች ስለሚቃኙ ነው፡፡ እነዚህ ጥቂቶች ደግሞ ለሕዝብና ለአገር ክብርና ህልውና የሚሰጡት ክብደት በጣም አናሳ ነው፡፡

ፖለቲከኞችም ሆኑ ልሂቃን ብዙኃኑን እያገለሉ በእነሱ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመደራደርም ሆነ፣ ለመወሰን የሚያደርጉት አጉል ድርጊት መገታት አለበት፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚወሳው ዋነኛ ጉዳይ የጥቂቶች ከመጠን በላይ መግዘፍና የብዙኃኑ መኮሰስ ነው፡፡ ለምሳሌ ወጣቶች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ ተኮትኩተው መብቀል ሲገባቸው፣ የጥቂቶች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆነው በአጭር እንዲቀሩ ይደረጋሉ፡፡ ጥቂቶች ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በማያሳትፉበት ደም አፋሳሽ ትግል፣ የብዙኃኑ ልጆች ግን ደማቸውን ይገብራሉ፡፡ ጥቂቶች ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ውድ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ፣ የብዙኃኑ ልጆች ግን ጥራታቸው የተጓደለ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይታጎራሉ፡፡ ጥቂቶች በተለያዩ መንገዶች ከሚያጋብሷቸው ጥቅሞች ቤተሰቦቻቸውን አንደላቀው እያኖሩ፣ ለማገዶነት የሚጠቀሙባቸውን ወጣቶች ግን በማይረባ አበል ንፁኃንን እያስገደሉ አገር ያስወድማሉ፡፡ እነሱ በሚቀሰቅሱት ግጭት አንድም የቤተሰባቸው አባል ዝር ሳይል፣ የብዙኃኑን ልጆች ግን ወላፈኑ ውስጥ ይከቱዋቸዋል፡፡ ጥቂቶች የተንደላቀቀ ሕይወት መምራት አልበቃ ብሏቸው አገር ሲያተራምሱ የሚጎዱት ብዙኃን ናቸው፡፡ የሚገደሉት፣ የሚፈናቀሉትና ያለቻቸው ንብረት የምትወድምባቸው ብዙኃኑ እንጂ ጥቂቶች እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ነው የአመፅ ጥሪ ሲያቀርቡና አገር ለማፍረስ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ብዙኃኑ አይሆንም ማለት ያለባቸው፡፡ ጥቂቶች ሌላው ቀርቶ የውጭ ፓስፖርት ስላላቸው የከፋ ነገር ሲመጣ ይሸሻሉ፡፡ ብዙኃኑ ግን ከአገራቸው ውጪ የት ነው የሚሄዱት? ማንስ ነው የሚያስጠጋቸው? ጥቂቶች በብዙኃኑ ህልውና ላይ እንዲወስኑ ዕድሉ መሰጠት የለበትም፡፡ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችም ቢሆን ይህ አተያይ በፍጥነት መቀየር አለበት፡፡

ለበርካታ ዓመታት የተለመደው ብዙኃኑን ሕዝብ ድምፅ አልባ የማድረግ አባዜ እንዲገታ ከሚያስፈልግባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር የቂመኞችና የበቀለኞች መራኮቻ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመረውን ለውጥ ዳር በማድረስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንደርደሪያ ለማበጀት የተደረገው ሙከራ፣ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ በተሰገሰጉ ግለሰቦችና ስብስቦች ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ከአገር ውስጥም ከውጭም ተሰባስበው የፖለቲካ ምኅዳሩን ዴሞክራሲያዊ ፈር ያስይዙታል ሲባል፣ የቁጥራቸው መብዛት አልበቃ ብሎ በየቦታው ግጭት መቀስቀስና ሕዝቡን መከፋፈል መደበኛ ሥራቸው ሆነ፡፡ በተለይ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ኢትዮጵያዊነትን በመናቅና በመፀየፍ ጭምር አገር የሚያፈራርስ ተግባር ውስጥ ነው የተገኙት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች አገር ቤት ገብተው ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት ምኅዳር ቢጠብቁም፣ ከዚህ ቀደም ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ የብሔርና የሃይማኖት ግጭቶች በየቦታው ይከሰቱ ጀመር፡፡ በግጭቶቹ ንፁኃን ለዕልቂት ተዳረጉ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቀሉ፡፡ ከፍተኛ የአገር ሀብት ወደመ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የግጭቶቹ ጠንሳሾችም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ምንም አልሆኑም፡፡ ድሆች ግን ያለ ኃጢያታቸው መከራ ወረደባቸው፡፡ ላባቸውን ጠብ አድርገው ለዓመታት የለፉ ታታሪዎች ንብረቶቻቸው የእሳት እራት ሆኑ፡፡ ጥቂቶች በሕዝብና በአገር ላይ እንዲህ ነው የቀለዱት፡፡ ብዙኃኑ ተገፍተው ጥቂቶች የበላይነቱን ሲይዙ ውጤቱ ውድመት ነው፡፡ እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡

ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ ሥልጣን ተቆናጠው አገር ሲቦጠቡጡ የነበሩ ጥቂቶች በርካታ ወንጀሎች ፈጽመዋል፡፡ በጋብቻና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የተሳሰሩ ግለሰቦችና ስብስቦች፣ በሕዝብ ስም ከፍተኛ በደል አድርሰዋል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ከመግፈፍ ጀምሮ መቆሚያ መቀመጫ በማሳጣት፣ ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን አበልፅገዋል፡፡ መሬት እየወረሩ በመያዝ፣ የባንክ ብድሮችን በመቀራመት፣ የውጭ ምንዛሪን በቁጥጥር ሥር በማዋል፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድልን ከመጠን በላይ በመጠቀም፣ ግብር በማጭበርበር፣ በመሰወርና በመሳሰሉት ሕገወጥ ተግባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሚሊየነርነት ወደ ቢሊየነርነት ተመንጥቀዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንን በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ ኃጢያታቸው እንዲሸፋፈን አድርገዋል፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ግብረ በላ ሠራዊት በማደራጀት ራሳቸውን ለመከላከል፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ ከደሙ ንፁህ ለመምሰል ሞክረዋል፡፡ የንፁኃንን ስም እያስጠፉ ማደናገሪያ ፈጥረዋል፡፡ የጥቅም ሸሪኮቻቸውን የዘመቻቸው አካል በመሆን በአገኙት አጋጣሚ በሕዝብ ላይ በደል ፈጽመዋል፡፡ እነዚህ ሸሪኮቻቸው የመገናኛ ብዙኃንንና የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቆጣጠር ጭምር አደናጋሪ መረጃዎችን ከመልቀቅ አልፈው፣ የተጀመረው ለውጥ ፈር ይዞ እንዳይጓዝ የተለያዩ መሰናክሎችን ፈጥረዋል፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎችን ከመልቀቅና አሉባልታዎችን ከመንዛት በተጨማሪ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ጥቂቶች በ110 ሚሊዮን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲወስኑ የሚያስችሉ ተዘርዝረው የማያልቁ በደሎች ደርሰዋል፡፡ ልዩነትን ይዞ ለጋራ ብሔራዊ ጉዳይ አንድነት አስፈላጊ መሆኑ እስኪዘነጋ ድረስ፣ በሕዝቡ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲነግሥ መርዛማ ቅስቀሳዎች ተካሂደዋል፡፡ ለጥቂቶች ሥልጣንና ጥቅም ሲባል ብዙኃኑ ደማቸውን ገብረዋል፡፡ ይህ ነውረኛና አሳፋሪ ድርጊት መቆም አለበት፡፡

ኢትዮጵያውያን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚኖሩባት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊት አገር መገንባት እየተቻለ፣ በጥቂቶች ፍላጎት ምክንያት መንገዱ ሁሉ አባጣና ጎርባጣ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች እየተከላከሉ በደጉም በክፉም ጊዜ አብረው ያልኖሩ ይመስል፣ በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል ለማጋጨት የሚደረጉ ደባዎች ከባድ ኪሳራ እያስከተሉ ነው፡፡ ጥቂቶች ብቻ ፍላጎቶቻቸው በተለያዩ መንገዶች እየተስተጋቡ የብዙኃኑ ድምፅ ግን ታፍኗል፡፡ ልዩነቶቹን ጌጥ አድርጎ በበርካታ ማኅበራዊ እሴቶቹ ታጅቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረን ሕዝብ፣ ለራሳቸው ጠባብ ዓላማና ራዕይ ሲሉ አገር የሚያፈርስ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ ጥቂቶች አሁንም ሊታቀቡ የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩና ብዙኃኑን ሥጋት ውስጥ የሚከቱ ፕሮፓጋንዳዎችን እየነዙ፣ አገር ሰላም ከመንሳት አልፈው ለዕድገት የሚውል ጊዜና ሀብት እንዲባክን እያደረጉ ነው፡፡ የአገሪቱ ልሂቃን ለአገራቸው የሚያስቡ ከሆነ የጥቂቶችን ውሎና አዳር ከሚተነትኑና የቅዠት ፕሮፖዛላቸውን ከሚያስተጋቡ፣ የብዙኃኑን የታፈነ ድምፅ በማሰማት ውለታ ይሥሩ፡፡ ጥቂቶች አገር ለማፍረስና ሕዝቡን ለመበተን የሚያደርጉት መሯሯጥ ብቻ ትኩረት ሲሰጠውና ከመጠን በላይ ሲስተጋባ፣ የብዙኃኑ ድምፅና ፍላጎት ይታፈናል፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ነው ማለት፣ ከምንም ነገር በላይ ድምፁ መሰማት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ጥቂቶች ለብዙኃን መገዛት ሲኖርባቸው የተገላቢጦሽ መሆኑ ልሂቃንን ማስቆጨት አለበት፡፡ ብዙኃን መፈጠራቸው እየተዘነጋና እየተናቁ ነው ጥቂቶች አገሪቱን መጫወቻ ያደረጓት፡፡ ጥቂቶች በተለይ ወጣቱን የብሔር ፖለቲካ ውስጥ እየደፈቁት አውዳሚ እያደረጉት ነው፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ልሂቃን ወጣቱን በመታደግ ወደ ትምህርትና ምርምር እንዲያተኩር ያግዙት፡፡ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በህዋ ሳይንስ፣ በሕክምና፣ በምህንድስና፣ በኢኮኖሚክስና በሌሎች ዕውቀቶች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ ይርዱት፡፡ በጥቂቶች ከሚመራ የግድያና የውድመት ድርጊት ታቅቦ አገሩን በፍቅር እንዲያገለግል ይደግፉት፡፡ ጥቂቶች የሚፈነጩበት ምዕራፍ በትብብር ይዘጋ፡፡ ለዚህም ነው ጥቂቶች ብዙኃንን ድምፅ አልባ ማድረጋቸው ይብቃ የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...