Wednesday, June 7, 2023

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ መሞላት በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትላቸው ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎችና የመውጫ መንገዶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ፣ በግንባታው አምስተኛ ዓመት ላይ መሞላት የነበረበትን የመጀመርያ ዙር ውኃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠራቀም መቻሉ ይፋ ተደርጓል፡፡ ግድቡ እየተሞላ መሆኑን መንግሥት ይፋ ከማድረጉ በፊት የተለያዩ የሳተላይት ምሥሎችን በመመልከት ከግድቡ ጀርባ የሚተኛው የውኃ መጠን እየጨመረ እንደሆነ፣ የተለያዩ ግለሰቦችና የዜና አውታሮች ያስታወቁ ሲሆን፣ ግድቡ የመጀመርያውን ዙር 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መያዙንና ይኼም በተከሰተው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ሳቢያ በፍጥነት መከናወኑን የውኃ@ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የግድቡን የውኃ ሙሌትና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረገውን ድርድር በማስመልከት መግለጫ ያወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአካባቢው የታየው በርከት ያለ የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ ግድቡን ውኃ ለመሙላት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ሙሌትና ዓመታዊ ሥራን (First Filling and Annual Operation) በሚመለከት በሚደረገው ድርድር፣ ኢትዮጵያ ሁሉም ወገን የሚያሸንፍበት ሚዛናዊና የዓባይ ወንዝ ሦስቱንም አገሮች የሚጠቅም እንደሆነ የሚያረጋግጥ እንዲሆን ቁርጠኛ ነች፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ዝናባማ ወቅት የግድቡ የመጀመርያ ዓመት ውኃ ሙሌት የተጠናቀቀ በመሆኑ ከግንባታው በላይ እየፈሰሰ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

የግድቡ የውኃ ሙሌትን፣ በተደራዳሪ አገሮች መካከል ስለሚኖር የግድብ የውኃ መጠንና ልቀት መረጃ ልውውጥን፣ ዓመታዊ የህዳሴ ግድብ ውኃ አለቃቀቅን፣ እንዲሁም ግጭቶች ቢነሱ ለመፍታት የሚያስችሉ ማዕቀፎችን በተመለከተ ለዓመታት ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች መቋጫ ሳይበጅላቸው የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2020 መጀመርያ ላይ የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በድርድሩ በታዛቢነት በተገኙበት ከተካሄዱ ድርድሮች በኋላ፣ ኢትዮጵያ ከስምምነት ሳይደረስና ውል ሳይያዝ የግድቡን ውኃ ሙሌት እንዳትጀምር በርካታ ግፊቶች ሲደረጉ ነበር፡፡

የአሜሪካ መንግሥት በግምጃ ቤት ኃላፊው ስቲቨን ምኑሽን ውክልና እንዲሁም የዓለም ባንክ በፕሬዚዳንቱ ዴቪድ ማልፓስ ሲያቀላጥፉ የነበረው ድርድር ከስምምነት ሊደርስ ባለመቻሉ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በግብፅ አርቃቂነት የቀረበውን ስምምነት አልፈርምም ማለቷን ተከትሎ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በሦስቱ አገሮች መካከል የሚደረገው ድርድር መቋጫ ሳይበጅለትና ከስምምነት ሳይደረስ፣ ኢትዮጵያ ግድቡን በፍፁም በውኃ መሙላት የለባትም የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይኼም መግለጫ ከጅምሩ እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) ሆኖ ሳለ ድርድሩ የሚካሄደው ለምን በግምጃ ቤትና በዓለም ባንክ ሆነ በማለት አግባብነት የሌለው ተፅዕኖ ኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር በማለም እንደሆነ፣ በጥርጣሬ ሲናገሩ የነበሩ ታዛቢዎች ዕይታ እውነትነት እንዳለው የተመላከተ ነበር፡፡

በአሜሪካና በዓለም ባንክ አቀላጣፊነት ሲደረግ ከነበረው ድርድር በመጨረሻው ስብሰባ ላይ ሳትሳተፍ የቀረችው ኢትዮጵያ፣ በአገር ውስጥ የማደረገውን ውይይት አልጨረስኩምና ይራዘምልኝ ብትልምና ይኼ ጥሪዋ ሰሚ ሳያገኝ ቢቀርም፣ አሜሪካና የዓለም ባንክ ከተሰጣቸው ሚና ያለፈና ለግብፅ ያደላ አቋም እንደያዙ በመግለጽ ትችት ስትሰነዝር ነበር፡፡

ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይኼንን ጉዳይ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ አሜሪካ በተካሄደው ድርድር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ረገድ ምንም ተቀባይነት እንደሌለውና ግምጃ ቤቱም ይኼንን መሰል መግለጫ ለማውጣት ሥልጣኑ እንደሌለው በመግለጽ የተቹ ሲሆን፣ ‹‹በመግለጫው የተጠቀሰው በተለይ ግድቡን ከስምምነት ሳትደርሱ አትሞሉም የሚለው አገላለጽ ግብፆች እንኳን ያልጠየቁት ነው፡፡ እናም ኢፍትሐዊና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጋፋ አቋም ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የአሜሪካና የዓለም ባንክ መሩ ስብሰባ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2020 ያለ መቋጫ ቢጠናቀቅም፣ ግብፅና ሱዳን በተለዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ከስምምነት ሳይደረስ ውኃ መሙላት እንዳትጀምር ሲሉ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ማስገንዘቢያ የላኩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በበኩሏ ከስምምነት መድረስ ቢቻል ምርጫዋ እንደሆነ በመግለጽ፣ ከስምምነት ባይደረስም ግን ግድቡ ውኃ መያዝ ሲችል ውኃ መሙላት እንደምትጀምር አስታውቃለች፡፡ ይኼ እንዳይሆን በማሰብ ግብፅ የጦርነት አዋጅ የሚመስሉ ማስፈራሪያዎችን ስታስተጋባ የተደመጠ ቢሆንም፣ ጊዜው ደረሰና እነሆ ኢትዮጵያ ግድቡን ውኃ ለመሙላት በቃች፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ግድብ ውኃ መሙላቷ በራሱ ትልቅ ድል እንደሆነ የሚያትቱ ቢኖሩም፣ ትርጉሙ ግን ከዚህ የላቀ እንደሆነ በህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ሰሞኑን የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገዱ በንግግራቸው፣ ‹‹በብዙ አገሮች ባሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚፈሩት የላይኞቹ አገሮች ናቸው፡፡ የላይኞቹ አገሮች በብዛት እንዳይጠቀሙና ለታችኞቹ አገሮች እንዳታስቀሩብን ተብሎ ነው ስምምነትና ድርድር የሚካሄደው፡፡ የእኛ የተገለበጠ ነው፡፡ በተፋሰሱ በታችኛው ያለ አገር የላይኛው አገር ውኃ እንዳይጠቀም ለዘመናት የበላይነት ይዞ የቆየና ያንን ለማስቀጠል ጥረት የሚያደርግበትን አቅጣጫ ይዞ ነው የሚሠራው፡፡ ይኼ ልምድ በዓለም ላይ የለም፡፡ ኢትዮጵያ እየሠራች ያለው ሥራ ይኼንን ሁኔታ የሚገለብጥ፣ ይኼንን ታሪክ የሚቀይር ነው ግድቡ፡፡ ከኃይል ማመንጨትና ከኃይል ከምናገኘው ጥቅምና ሌሎች ጥቅሞች ብቻ ሳይሆን የጂኦ ፖለቲካዊ አካሄዱና ፍትሐዊ አቅጣጫ እንዲያመራ የሚደረግ ውጤት ያለው ፕሮጀክት ነው፤›› በማለት፣ ግድቡ የሚኖረውን ከሚታይ በላይ የሆነ አንድምታ አስረድተዋል፡፡

ይሁንና ኢትዮጵያ በሦስቱ አገሮች መካከል ከስምምነት ሳይደረስ ግድቡን በመሙላቷ፣ እንዲሁም አሜሪካ ካሳየችው መንገድ ውጪ በራሷ ዕቅድ ግድቡን ውኃ መሙላት በመቻሏ ቅሬታ የገባው የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሊሰጠው ያሰበውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ለማቆም እያሰበ እንዳለ ፎሬን ፖሊሲ የተሰኘው የአሜሪካ የባለሙያዎች ስብስብ የሆነው የዕሳቤ ቋት (Think Tank) ከበርካታ ምንጮቼ ሰምቻለው ሲል ሰሞኑን ያስነበበ ሲሆን፣ ግድቡን በተመለከተ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በግልጽ ግብፅን ለማገዝ ሲል ሚዛናዊነቱን እየሳተ ነው ብሏል፡፡

የህዳሴ ግድቡን መሞላት ተከትሎ ቅሬታ ከተሰማው የአሜሪካ መንግሥት በተጨማሪ ከግድቡ መሞላት በኋላ ምንም ዓይነት አስተያየት ያልሰጠው የግብፅ መንግሥት፣ እስከ ዛሬ ሲያደርጋቸው ከነበሩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በተጨማሪ በቀጣይም ተመሳሳይ ጫና ለማሳደር መንቀሳቀሱ የማይቀር እንደሆነ ዕሙን እንደሚሆን በርካቶች ይስማማሉ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን የሚመራው የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባሪያ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረገው ስብሰባ የህዳሴ ግድቡን ቀጣይ ፈተናዎችና ኢትዮጵያ ስለምትከተለው ስትራቴጂ ተወያይቷል፡፡ በዚህ ስብሰባ፣ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የምክር ቤቱ አባል አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ ‹‹እነ ግብፅ የሚኖሩት በዓባይ ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ውኃቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙበትና ምናልባትም የእነሱን ይሁንታ ሳናረጋግጥ ውኃችንን መጠቀም የማንችል ዓይነት ዕሳቤ ይዘው እየሠሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የዓባይ ግድብ ከእነሱ አልፎ የዓረብ አገሮችና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አጀንዳ እንዲሆን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ጉዳዩን እየወሰዱ መወያያ ሊያደርጉት እንደሚፈልጉ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የዲፕሎማሲ ሥራዎቻችን ጠንከር ብለው እንዲሄዱ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና የጂኦ ፖለቲካ ምሁሩ ተስፋዬ ታፈሰ (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ እስካሁን ከተመጣበትና በግልጽ ከሚታየው ፍላጎታቸው በተቃራኒ ግድቡን ውኃ በመሙላቷ፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ደስተኛ ላይሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ይላሉ ተስፋዬ (ፕሮፌሰር)፣ አሜሪካ አራት ጊዜ በታዛቢነት ያካሄደችው ስብሰባ ውጤት የሆነውን ስምምነት ኢትዮጵያ አልፈርምም በማለቷ የከፋት አሜሪካ፣ የተናቀች ሊመስላት እንደሚችልና ‹እኛ ብለን እንዴት አንዲት አፍሪካዊት አገር እንቢ ትላለች?› እንደምትል ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቋርጣለሁ ብትልም ግን ታደርገዋለች ብዬ አላስብም፤›› ይላሉ፡፡

ለዚህ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ደግሞ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በተለይ አልሸባብ የጥፋት ተልዕኮውን ማስፈጸም እንዳይችል ማድረግ የጋለ የወታደራዊ ተሳትፎ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ አሜሪካ ልታጣት የማትችለው አጋር እንደሆነች ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጦር ለማስወጣት ብትወስን ውጤቱ እጅግ አስከፊ ይሆናል ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ብትጀምር የዓባይ ውኃ ፍሰት ይቀንሳል በማለት ያለ ስምምነት እንዳይሞላ ሲያቀርቡ የነበረው የመፍትሔ ሐሳብ፣ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ያለ ምንም ተፅዕኖ መሞላቱ፣ የግድቡ መሞላት በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ተፅዕኖው የጎላ ይሆናል፣ የውኃ መጠንም ይቀንሳል የሚሉት የመከራከሪያ ሐሳቦች ከንቱ እንዲሆኑ ያደረገ ነው በማለትም የቀደመው የግብፅ ደጋፊዎች አቋማቸውን የሚያስመረኩዙበትን ሐሳብ አሁን ተቀባይነቱ እምብዛም እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ተስፋዬ (ፕሮፌሰር) ምልከታ፣ የግድቡን ጉዳይ አያያዝና የድርድር ተሳትፎ በተመለከተ በአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ውስጥም ክፍፍል እንዳለ፣ በውጭ ጉዳይ መያዝ የሚገባው ጉዳይ በግምጃ ቤት ኃላፊው መያዙ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስቴት ዲፓርትመንት) በኩል ቅሬታ ማስተናገዱ አይቀርም፡፡

‹‹ሥራው ለውጭ ጉዳይ ነበር መሰጠት የነበረበት፡፡ ስቴት ዲፓርትመንት ልክ አይደለም ይላል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያን ጠቀሜታና የቀጣናውን ሁኔታ ተንትኖና ተረድቶ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችሉ ባለሙያዎች ያሉት በዚህ ክፍል በመሆኑ፡፡ መጀመርያውኑ ለበጅሮንዱ መሰጠቱ ግራ የሚያጋባ ነው ከዚህ አንፃር፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በዘለለም ዕርዳታ ለማቆም ወደ ኮንግረስ መሄዱ የግድ ስለሚሆን፣ በዚያ የምክር ቤት አባላት ይደግፉታል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን የአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ዕርዳታ ቢቋረጥ እምብዛም የሚያሳስብ እንደማይሆን፣ ይልቁንም ለኢትዮጵያ የልማት አጋር በመሆን በመሠረተ ልማት ረገድ ትልቅ ድጋፍ የሚያደርጉት የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይና፣ ጃፓንና ኮሪያ የመሳሰሉ አገሮች ከዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ እንደሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡

ከአውሮፓና ከእስያ ለኢትዮጵያ የልማት አጋር ሊሆኑ የሚችሉት እንደ አውሮፓ ኅብረትና ጃፓን የመሳሰሉ አገሮች በንግድና በወታደራዊ ትስስር ከአሜሪካ ጋር ባላቸው ጥብቅ ግንኙነት ሳቢያ፣ አሜሪካ የምትወስደውን ዕርምጃ ሊደግፉ ይችሉ እንደሆን በሚለው ሐሳብ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ተስፋዬ (ፕሮፌሰር)፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ስለሆነ በዚህ መንገድ ይተባበራሉ ብሎ ማሰብ አይሆንም ይላሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የአሜሪካ ተፅዕኖና ተቀባይነት እየተቀዛቀዘ መምጣቱን በማስገንዘብ፣ በተለይ የአውሮፓ ኅብረት በግድቡ ላይ ጠንከር ያለ አቋም ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያን የልማት ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል በማለት፣ ‹‹ሁሉም ልዩነቶቻችሁን በውይይት ፍቱ እያሉ ስለሆነ፣ ከአሜሪካ የሚመጣውን የማያሳምን ዕርምጃ ይከተላሉ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የአሜሪካ ውሳኔ ምክንያታዊነት እያጣ ስለሚገኝ ነው፤›› በማለት ይደመድማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት ተቋም የጂኦ ፖለቲካ መምህሩና የአገር ልማት ባለሙያና ተመራማሪ የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ግድቡን ውኃ እንዳትሞላ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግፊቶች ቢኖሩምና ግድቡ መሞላቱ ራሱን የቻለ አዎንታዊ ምልከታዎችን የያዘ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከፍተኛ የሆኑ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ሊያስከትል የሚችል ዕርምጃ ነው ይላሉ፡፡

የግድቡ መሞላት ግብፅ እ.ኤ.አ. ከ1929 ጀምሮ በበላይነት የያዘችውን የዓባይ ወንዝ ውኃ ተጠቃሚነትን የቀየረ እንደሆነና ያለ ግብፅ ፈቃድ ምንም ዓይነት ልማት በዓባይ ግድብ ላይ እንዳይከናወን ስታደርግ የነበረው የረዥም ዓመታት ተፅዕኖ ዕልባት ያበጀለት ዕርምጃ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በራሷ ፈቃድ ለመጠቀም በመወሰኗ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችበት መሆኑ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተምሳሌት የሆነ በራስ አቅም ሊሠራ ታስቦ የማያውቅ ፕሮጀክት በመሆኑ፣ ለብድርና ለድጋፍ ወደ አሜሪካና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማማተርን የሰበረ እንደሆነ በመጠቆም፣ ይኼ የሚኖረው አንድምታ አሜሪካና ዓለም አቀፍ የፋይናስ ተቋማት ተፅዕኖ ለመውጣት በር ከፋች በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንዲኖር የሚያደርግ ምክንያት ነው ይላሉ የሺጥላ (ዶ/ር)፡፡ ስለዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት ካላቸው የዓረብ አገሮች በተለይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር ጋር ቀጥታ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች እንደሚኖሩ መጠበቅ ያስፈልጋል በማለት አንዱን የተፅዕኖ አቅጣጫ ያመላክታሉ፡፡ በሌላ ወገን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ይላሉ፡፡ ‹‹እስካሁን ምን ዕርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ያልሰማነው ከዓረቡ ዓለም ነው፤›› በማለት፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ከአሜሪካና ከፋይናንስ ተቋማት የሚመጣው ተፅዕኖ ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል በማመላከት፣ ኢትዮጵያ ለበጀት ጉድለት መሙያና ለተለያዩ የልማትና የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ኅብረትና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በምታገኘው ገንዘብ ላይ የተመረኮዘች በመሆኗ ተፅዕኖው ከባድ ሊሆን ይችላል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ፈተና ለገጠመው ኢኮኖሚ ድጋፍ የሚገኘውም ከእነዚሁ አካላት እንደሚሆንም መታሰብ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ እነዚህን ጫናዎች በመፍራት ለሌሎች ፍላጎት ተንበርክካ መሙላት አልነበረባት ወይ ከተባለ፣ መሙላቷ ትክክል እንደሆነና የድርጊቱ አንድምታ ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ግብፅ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ ተቃውሞ ስታቀርብ የነበረው ግድቡ በሚኖረው ተፅዕኖ ሥጋት ሳይሆን፣ እኔ ሳልፈቅድ አይሆንም ከሚል ፍላጎት እንደሆነ ግልጽ ነው የሚሉት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ግድቡ ውኃ መሞላቱ የእነሱን የውኃ መጠን ይጎዳል ብለው ሳይሆን ይኼ ግድብ በመሠራቱና ውኃ መያዙ የሚፈጥረውን አንድምታ (Precedence) በመፍራት ይቃወሙታል ይላሉ፡፡ አሜሪካና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በበኩላቸው፣ አገሮች ከእነሱ የተፅዕኖ ማዕቀፍ እንዳይወጡ ስለሚሹ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ሥር ሊያደርጓቸው ይሻሉ ሲሉም ያክላሉ፡፡

እነዚህን ጫናዎች ለመቋቋም ደግሞ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት ጥንቃቄዎችና ዕርምጃዎች መኖር አለባቸው በማለት ምከረ ሐሳብ ይለግሳሉ የሺጥላ (ዶ/ር)፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የመጀመርያው ሲሆን፣ ይኼንን በማጠናከር ዓለም ስለኢትዮጵያ በሚገባ እንዲያውቅ ማድረግና በውጭ የሚገኙ የተለያዩ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኢትዮጵያ የወሰደችው ዕርምጃ ያልተለመደ ቢሆንም፣ ያላት ምክንያት ግን አሳማኝ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅባታል በማለትም ያስገነዝባሉ፡፡ በዚህ ድርጊት ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት ያለባቸው የተማረው ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሚዲያው እንደሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዲጂታል ዲፕሎማሲ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ በማመልከት፣ ይኼ በተቀናጀ መንገድ እንዲከናወን የማስተባበር ሚና መጫወት ያለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የመደበኛ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀምም ስለኢትዮጵያ እንዲታወቅ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከእነዚህ ዕርምጃዎች በዘለለም ጫናዎች እየጎለበቱ ሲመጡ ምን እናድርግ ለሚለው አማራጭ መታየት እንዳለበትና በተለይ አገሪቱ ለሚያስፈልጋት ፋይናንስ ሌላ ምንጮችን መማተር የግድ ይላል ይላሉ፡፡ በተለይ አሁን ከኮሮና ቫይረስና ከፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ፋይናንስ ስለሚያስፈልግ ኢኮኖሚያዊ መቃወስ ስለሚኖር፣ አማራጭ ማየትና ምዕራባውያን በራቸውን ቢዘጉ ምን ማድረግ እንችላን የሚለው ሊታሰብበት ይገባል ባይ ናቸው የሺጥላ (ዶ/ር)፡፡ ነገር ግን ይኼም በደርግ ጊዜ እንደታየው ዓይነት ከምዕራቡ ራስን የማግለል መልዕክት እንዳይኖረው ጥንቃቄ በማድረግ፣ ለምዕራቡ አጋርነትን እያሳዩ ግንኙነቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ማድረግ የግድ ይላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከሁሉ በላይ ግን በነዳጅና በንግድ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው የዓረቡ አገሮች ተፅዕኖ በቅርቡ ሊታይ የሚችል እንደሚሆን የሚተነብዩት ምሁሩ፣ በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ማግባባትና ወዳጅነትን ማሳየት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ግብፅ ኢትዮጵያ እስልምናን ለማጥፋት እየሠራች እንዳለች አድርጋ ስለምታቀርብ፣ አሁን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚያደርጉትን ዕገዛ በማጠናከር ኢትዮጵያ ይኼን መሰል ዓላማ እንደሌላት ማስረዳት ያስፈልጋል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

በተጨማሪም በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ካሉ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፉ ስለሚገኙ፣ እነሱንና ሌሎች የአሜሪካ የነጩ ቤተ መንግሥት ባለሥልጣናትንና የምክር ቤት አባላት ድጋፍ እንዲሰጡ ማግባባት (Lobby) ማድረግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡

ከግብፅ ወገን ደግሞ፣ እስካሁን ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ለማድረግ ብትሞክርም እምብዛም ያልተሳካላት በመሆኑና በአገር ውስጥም ብጥብጥና አለመረጋጋት ለማምጣት እየሠራች እንደምትገኝ በመጠቆም፣ ይኼ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችልና ቀጣዩ ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ጋር ቅራኔ እንዲፈጠር ማድረግ እንደሚሆንና በጥንቃቄ ሊቃኝ የሚገባው ተፅዕኖ ከግብፅ ወገን እንደሚመጣ ይናገራሉ፡፡ የአገር ውስጥ ኃይሎችም ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው የፖለቲካ ውጥረት እንዲፈጠርም ለማድረግ እንደምትሞክር በማስገንዘብ፣ እነዚህን ተፅዕኖዎች በጥንቃቄና በጠንካራ ዲፕሎማሲ ማለፍና ማሸነፍ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካልተመረጡ ግን በርካታ ነገሮች ሊቀየሩ እንደሚችሉ የሺጥላ (ዶ/ር) ይገምታሉ፡፡ በተመሳሳይ ግብፆች የትኛውንም ቀዳዳ ካገኙ ሊጠቀሙበት እንደሚሹና በተለያዩ አቅጣጫዎች ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙት ተስፋዬ (ፕሮፌሰር)፣ ግብፆች የግድቡ የመጀመርያው ዙር ውኃ ከተሞላ በኋላ ዝም ቢሉም ዝም ብለው ይቀራሉ ተብሎ መገመት የለበትም ይላሉ፡፡ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ በአገር ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖርና በዓለም መድረክ ደግሞ የትራምፕን ዓይነት መሪዎችን በመጠቀም ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚታትሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ስለዚህ በዲፕሎማሲው መድረክ በደንብ መሥራት ያስፈልጋል፤›› በማለት፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ ምክንያት ስላላት ልታሸንፍ እንደምትችል ይጠቁማሉ፡፡

በደኅንነት ረገድም ግድቡን፣ አካባቢውንና አገሪቱን መጠበቅ የሚችል የመከላከያ አቅም በመገንባትና ዝግጁ በማድረግ ተዘጋጅቶ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ መንግሥትም እነዚህን ተፅዕኖዎች በመገንዘብ እየተዘጋጀ ያለ በሚመስል ሁኔታ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኰንን፣ ‹‹ይኼ ብርቅዬ ፕሮጀክታችን የአገራዊ መግባባት አንድ ማሳያ ዕንቁ ፕሮጀክት ነውና የአብሮነትና የብሔራዊ መግባባት ንቅናቄያችንን በእንዲህ ዓይነት ፋና ወጊ ዓለምን ባስደመመ ሥራችን አጠናክረን የምንቀጥልበት፣ የተለያዩ አካላት እኛ ለእውነትና ለመብታችን በቆምንበት መንገድ የተለያየ ስም እየሰጡን በዓለም አደባባይ እየከሰሱን በተሠለፉበት ጎራ ጠንካራ የዲፕሎማሲና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራችንን አጠናክረን የምንቀጥልበት፣ በእውነት መንገድ ቆመን ይኼንን የተፈጥሮ ሀብታችንና ፀጋችንን የመጠቀም መብታችንን ማንም ሊዳስሰው የማይችል መሆኑን በተግባር ያሳየንበትና ይኼው ተጠናክሮ የሚሄድበት አካሄድ ነው ሊኖር የሚገባው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -