Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኮሮና 40 በመቶ የአፍሪካ የኃይል ፍጆታ ለጤና ለትምህርትና ለንግድ ዘርፎች እንዲውል አስገድዷል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ፣ በርካታ አገልግሎቶች የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን መሠረት ልማቶችን ከወትሮው በበለጠ እንዲጠቀሙ እያስገደደ ይገኛል፡፡ የሰዎችን አካላዊ መስተጋብር የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች እንዲቀንሱ ያስገደደው ይህ በሽታ፣ በበርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ እየተባባሰ መጥቷል፡፡

የሰዎችን እንቅስቃሴና ግንኙነት የሚጠይቁ መስኮች በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች እየተተኩ በመምጣታቸው ሳቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ ሳቢያ በተለይ የጤና፣ የትምህርት እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴዎች በአይሲቲ ቴክኖሎጂዎች ላይ ጥገኛ ለመሆን በመገደዳቸው ይህን አገልግሎትም በስፋት ለማቅረብ ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ የገለጹት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በአፍሪካ የታዳሽ ኃይሎች ላይ በማተኮር ሰሞኑን በተካሄደው የኢንተርኔት ኮንፈረንስ ላይ ሶንግዌ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ ሦስቱ የአገልግሎት ዘርፎች ብቻቸውን የአፍሪካን የ40 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የአይሲቲ ዘርፉ እነዚህንና ወደፊትም የሚስፋፋውን የአፍሪካን የመሠረተ ልማት ፍላጎት በሚገባ ለማቀላጠፍ እንዲያስችል ካስፈለገ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በአፍሪካ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

ሶንግዌ (ዶ/ር) ይህን የተናገሩት ‹‹ሬስ ፎር አፍሪካ- Res4Africa›› በተሰኘው የውይይት መድረክ ላይ ሲሆን፣ አፍሪካንም እያጥለቀለቀ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ የኃይል ፍጆታ ጫና ማስከተሉ፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ከሌላውም ጊዜ ይበልጥ ተፈላጊ እንዲሆኑ አስገድዷል፡፡ ድኅረ ኮሮናም ቢሆን ይኸው የታዳሽ ኃይሎች ምንጭ ወሳኝ እንደሆነ ሲገለጽ፣ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ኢኮኖሚስቷ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኃላፊ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በአፍሪካ ለዘመናት ጥቅም ላይ የዋለውንና በነዳጅ ላይ የተመሠረተውን የኃይል አቅርቦት ምንጭ በታዳሽ ኃይሎች መተካት እንደሚገባ፣ ይህም ሲደረግ የአየር ንብረት ለውጥንና የአካባቢ ጉዳትን ለመከላከል በማሰብ ጭምር ከሚሰጠው ጠቀሜታ አኳያ እንደሆነ፣ ከዋጋ አኳያም ከተለመደው የኃይል አማራጭ አኳያ ታዳሽ ኃይሎች አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው መንግሥታትና ኩባንያዎች በታዳሽ ኃይሎች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል፡፡

የአፍሪካ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጪዎች በድኅረ ኮሮና አፍሪካ በሁለት እግሯ እንድትቆም ለማገዝ ከፈለጉ፣ የጨዋታውን መዘውር ሊወጡት ይገባል በማለት በአቅርቦትና በኃይል አማራጮች ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በአፍሪካ ኡጋንዳና ሲሼልስ ብቻ አዋጭና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ እንደፈጠሩ ይነገርላቸዋል፡፡ 19 አገሮች ወጪያቸውን ብቻ እንደምንም በመሸፈን የኃይል አቅርቦት እንደሚሰጡ ሲጠቀስ፣ የተቀሩት ግን በኪሳራ ይንቀሳቀሳሉ ሲል የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

‹‹በአፍሪካ ያለው የኃይል አቅርቦት ታሪፍ ወጪ ቆጣቢ ከመሆን ይልቅ ወጪ አመላካች ሆኗል፤›› የሚሉት ሶንግዌ፣ አፍሪካ የምታወጣቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፎች ወጪ ቆጣቢ ሊሆኑ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ለዚህ አንዱ አማራጭ አኅጉራዊ የኃይል ምንጮችን ማበራከት እንደሆነ ይመክራሉ፡፡

የታሪፍ ጉዳይ ሲነሳ በኢትዮጵያ ከዓምና ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ታሪፍ የወጪ ጫና ነፀብራቅ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለታሪፍ ለውጡ መነሻ የተደረገው ምክንያት ታሪፉ ሳይለወጥ ለ12 ዓመታት ያህል መቆየቱ፣ የግብዓትና የመለዋወጫ፣ የዋጋ ንረት፣ የምንዛሪ ለውጥና በርካታ ዋጋ ተኮር ምክንያቶች ተያይዘው ሲጠቀሱ ይታወሳል፡፡ ይህ በመሆኑም የተደረገው የታሪፍ ለውጥ ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ ማስከተሉ እየታየ ነው፡፡ በአራት ዓመት ዑደት መቶ በመቶ ለውጥ የሚደረግበት የኤሌክትሪክ ታሪፍ ለውጥ ጥራትን፣ አቅርቦትን፣ ተደራሽነትና ወጪ ቆጣቢነትን ለማምጣት ረዥም መንገድ የሚቀረው ሆኖ ይገኛል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን የሚመሩ ሹማምንትም የታሪፍ ለውጡ ከአገልግሎት ጥራትና ብቃት ጋር መያያዝ እንደሌለበት፣ ይልቁንም ለዓመታት ሲተገበር የቆየው ታሪፍ ‹‹ዘመን ያለፈበት›› የወቅቱን የኑሮና የዋጋ ለውጦችን የማይወክል በመሆኑ ለውጥ ማድረግ እንዳስፈለገ ይከራከራሉ እንጂ ለተጠቃሚው ከሚቀርበው የኃይል አቅርቦት ጥራትና አስተማማኝነት አኳያ የሰማይን ያህል ብዙ እንደሚቀረው አይክዱም፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦች እንዲመጡ ታዳሽ ኃይሎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ይመክራል፡፡ ይህም ይባል እንጂ የታዳሽ ኃይል አማራጮችና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ የሚታየው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖም ለአፍሪካ ራስ ምታት መሆኑ እየታየ ነው፡፡

እንደ ውኃ ባሉ መስኮች ላይ ልምዱም የተፈጥሮ ሀብቱም ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የገዛ ሀብታቸውን ተጠቅመው ኃይል ለማልማት እየገጠማቸው ያለው ፈተና በዓባይ ወንዝና በህዳሴው ግድብ ላይ የሚታይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያመነጨች ካለችውም ሆነ በሥራ ላይ ካዋለችው የኃይል አቅርቦት ውስጥ አብዛኛው ከውኃ ምንጮች የተገኘ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ የሚያመነጨውን 6000 ሜጋ ዋት ኃይል ጨምሮ በአገሪቱ እንደሚመረት የሚገለጸው 4000 ሜጋ ዋት ኃይል ቢሆንም፣ ግማሽ የሚደርሰው በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሳይውል እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ቆይቷል፡፡ የህዳሴው ግድብ የቱንም ያህል አማራጭና አዋጭ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ቢሆንም በግብፅ ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት የውጭ የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት እንዳይችል ተደርጓል፡፡

እንዲህ ያሉ ዕውነታዎችን ወደ ጎን ያለው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ አገሮች በታዳሽ ኃይሎቻቸው ላይ እንዲሠሩ፣ ኩባንያዎቻቸውን እንዲያሠሩና እንደ ኮሮና ያሉ ሞገደኛ ወረርሽኞች የሚፈጥሩትን ያልተጠበቀ ጫና መቋቋም የሚችሉ የኃይል አማራጮችን እንዲገነቡ አበክረው ይወተውታሉ፡፡

ኮሚሽኑ እየተሳፈበት የሚገኘውና ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት አገሮችን በመነሻነት ያካተተ የ10 ሺሕ ሜጋ ዋት የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን በግል ኩባንያዎች አማካይንት በመነሻ የ10 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ለማልማት በማሰብ ይፋ ያደረገው ዕቅድ ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ባሻገር፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል በቅርቡ ለግንባታ ያዘጋጀቻቸው ሁለት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን ጭምሮ የአሉቶ ላንጋኖ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ከሚጠቀሱት የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በመቀሌ አቅራቢያ የተገነባውን የአሼጎዳ ነፋስ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ  በአዳማ የተገነቡት የነፋስ ኃይል ማመንጫዎችም ኢትዮጵያን በአማራጭ የኃይል ምንጮች አምራችነት እንድትካተት ያበቋት መሆናቸው ብቻም ሳይሆኑ፣ የአገሪቱን ዕምቅ አቅም ያመላከቱም ናቸው፡፡ ከ10 ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት ኃይል ከጂኦተርማል ወይም ከእንፋሎት ለማምረት የሚያስችል አቅም በኢትዮጵያ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች