Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በርካታ የግል የሕክምና ተቋማት በኢኮኖሚ ችግር እየተመቱ ነው›› አቶ ዳዊት ሞገስ፣ የኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን አስተባባሪ

በኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ሥር ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ የሕክምና ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ የግል ሕክምና ተቋማት ማኅበርን ያካተተው ፌደሬሽንን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት አቶ ዳዊት ሞገስ፣ የኢትዮጵያ የጤና ክብካቤ ፌደሬሽንን ከአጋሮቻቸው ጋር በመመሥረት በሥሩም የሆስፒታል ማኅበራት፣ የክሊኒኮች ማኅበራት፣ የላቦራቶሪዎችና የመድኃኒት አስመጪዎች ማኅበርና በሕክምናው መስክ የሚንቀሳቀሱ የሙያ ማኅበራት የሚካተቱበትን ይህንን ፌዴሬሽን እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሌሎች የአሠሪዎች ፌደሬሽኖች ሁሉ በጤናው መስክም የፌደሬሽኑ ሥራ እየተስፋፋ ነው፡፡ አቶ ዳዊት በዚህ መስክ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ፣ በኢኮኖሚክስና በኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ሁለት የማስትሬት ዲግሪዎች ያገኙና የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም እየሠሩ ናቸው፡፡ የሔማ አድቫንስድ ዲያግኖስቲክስና ላቦራቶሪ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የሲስተር አቅሌሲያ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዳዊት ከጤናው መስክ ባሻገር በልዩ ልዩ የምርትና አገልግሎት መስክ የተሰማሩ የቤተሰብ ድርጅቶችን ያስተዳድራሉ፡፡ በአቶ ዳዊት ቤተሰብ ከሚተዳደሩ ኩባንያዎች መካከል ቴርሞ ፕላስቲክስ፣ ዩኒቨርሳል ጋዝ፣ ዩኒቲ ፕሪንቲንግ ፕሬስ፣ ፋልከን ፎርዋርዲንግ የተባሉና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የአሠሪዎች ፌደሬሽንን ከጤናው ዘርፍ ተወክለው በመምራት ላይ የሚገኙት አቶ ዳዊት፣ በዚሁ ዘርፍ የግል ጤና ተቋማት በኮሮና ምክንያት የደረሰባቸውን ጫና በተመለከተ ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- በሰሞኑ የፖለቲካ ትኩሳት እንዲሁም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሥራ ዕድል የፈጠሩ ኩባንያዎች ወይም አሠሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በፖለቲካው አለመረጋጋትና በበሽታው ምክንያት የደረሱ ተፅዕኖዎችን በተመለከተ መንግሥት የሚያወጣቸው አኃዛዊ መረጃዎች አሉ፡፡ በእናንተ በኩል የተደረጉ ምልከታዎችን በአኃዝ አስደግፈው ቢነግሩን? 

አቶ ዳዊት፡- በአኃዝ የተደገፈ መረጃ ለማቅረብ ትንሽ ይቸግረኛል፡፡ ነገር ግን የተሠራው ሥራ ምንድነው ካልከኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ልክ በጣሊያን፣ በስፔን፣ አሁን ደግሞ በብራዚል እየሆነ ያለው ዓይነት የወረርሽኙ ተፅዕኖ ሊከሰት ይችላል የሚል ትልቅ ፍርኃት ነበረን፡፡ በዚህ ምክንያት አሠሪዎች ራሳቸውን የሚፈትሹበትና ለኮሮና ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ የሚያዩበት የሥራ ማኑዋል አጋጅተናል፡፡ በፋይናንስ፣ በምርትና በምርታማነት ረገድ ምን ማደረግ እንደሚገባቸው የሚያመላክቱ ከዓለም ሥራ ድርጅት  (አይኤልኦ) ማኑዋሎችን በማምጣት፣ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም የሠራናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት ትልቁ ትኩረት የነበረውና የመከላከል ሥራዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና የተሰጠው፣ በአብዛኛው በጤና ዘርፍ ለሚሳተፉ አካላት ነው፡፡ አሠሪዎችን የተመለከቱ ሥልጠናዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ሥልጠና ለኩባንያዎች እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ በሥራ ቦታ ላይ ለአሠሪዎች በሽታው እንዳይስፋፋ ምን ማድረግ እንደሚገባ፣ መከላከል ላይ ምን መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ ወዘተ. ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ስብሰባዎች በዲጂታል እንዲሆኑ ማድረግም ወሳኝ ነገር ነበር፡፡ አንድ መጥፎ ነገር ሲከሰት አብሮት የሚያመጣው ጥሩ ነገርም አይታጣም፡፡ በርካታ በየወሩ የሚካሄዱ የቦርድና የክልል ስብሰባዎች ነበሩ፡፡ የቦርድ ስብሰባዎችን ከክልሎች ጋር ስናደርግ ወጪው ብዙ ነበር፡፡ ለአውሮፕላን፣ ለሆቴል፣ ለአበል፣ ወዘተ. ተከፍሎ የሚካሄደው ስብሰባ አሁን በ‹‹ዙም›› አማካይነት ለሦስት ሰዓታት ከቢሮ መውጣት ሳያስፈልግ፣ ቶሎ ቶሎ እንደ ልብ መነጋርና መሰብሰብ ችለናል፡፡ የስብሰባ ወጪ ቀርቶልናል፡፡ በፊት ቶሎ ቶሎ የማንሰበሰበው ወጪ ፍራቻ ነበር፡፡ የአሠሪዎች ፌደሬሽን አባላት ወደ ታች ወርደው ለማኅበር አባላት እንዲያስተዋውቁና እንዲተገብሩት እያደርግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከአራት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአሠሪዎች ላይ ያሳደረው ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ጫና ምን ይመስላል?

አቶ ዳዊት፡- እኔ ራሴ አሠሪ ነኝ፡፡ እስከ አምስት ድርጅቶች እመራለሁ፡፡ ጫናው እውነቱን ለመናገር ከባድ ነው፡፡ በብዛት በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ድርጀቶችን ነው የምመራው፡፡ በጤናው አካባቢ በጣም አስገራሚ ነገር እየታየ ነው፡፡ በሽታ ሲከሰት ሥራ እንደሚበዛባቸው የሚጠበቀው የጤና ተቋማት ሲሆኑ፣ በበሽታ ምክንያት አገልግሎቶቻቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደሚፈለግና እንደሚጨምር ሁሉም ይገምታል፡፡ ከጤና ተቋማት በተጨማሪ ይቅርታ ይደረግልኝና የበሽታ ወረርሽኝ ሲንሰራፋና በርካቶች ለሕልፈት ሲዳረጉ፣ የአስከሬን ሳጥን የሚሸጡ አካላት ተፈላጊነታቸው መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የጤና ተቋማት ልክ እንደ ሆቴሎችና ቱሪዝም ዘርፍ ዜሮ የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የሥራ እንቅስቃሴያቸው ቆሟል፡፡ ሰው ስኳሩን ወይም ደም ግፊቱን ለመለካት ወደ ክሊኒክና ሆስፒታል መሄድ እያቆመ ነው፡፡ ምክንያቱም ኮሮና ይዞት ሊመለስ እንደሚችል ሥጋት ስላደረበት አልግሎት ማግኘቱን እያቆመ ነው፡፡ በፊት ኮሌስቶሮሌ ከፍ ሳይል አልቀረም ሄጄ ልታይ የሚለው ሰው ሁሉ አሁን ጠፍቷል፡፡ ትልልቅ ሆስፒታሎችን ገንብተን፣ በቀን ሁለት ቢበዛ ሦስት ነፍሰ ጡሮችን ብቻ ለማስተናገድ የተገደድንበት ወቅት ነው፡፡ ወላዶች ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ወይም ደግሞ በአደጋ ምክንያት ጉዳት ያጋጠመው ታማሚ ካልሆነ በቀር፣ አብዛኛው ለጤናው ክትትል የሚያደርግ ተመላላሽ ታካሚ ቤቱ ቀርቷል፡፡ ይህንን ጉዳይ ለክብርት ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሳስረዳቸው ሊያምኑ አልቻሉም፡፡

በአዲስ አበባ ሁለት የግል ሆስፒታሎች መጥተው ሠራተኛ አትቀንሱ አላችሁን፣ ሥራ በሌለበት፣ በኪራይ ሕንፃ በምንሠራበት ወቅት ምንም ገቢ ሳይሆን ከየት አምጥተን ደመወዝ እንክፈል? በማለት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ኑና ተረኩቡን፣ ከፈለጋችሁ ራሳችሁ አስተዳድሩት በማለት ለፌዴሬሽኑ ተማፅኖ አሰምተዋል፡፡ በሽታ በበዛበት ጊዜ እንዲያውም ከጤና ተቋማት የበለጠ ማን ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል በማለት ልናነጋግራቸው ሞክረናል፡፡ በመሆኑም እንኳንና ሌላው ዓይነት መደበኛ የንግድ ሥራ ቀርቶ፣ በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡ በርካታ የግል የሕክምና ተቋማት በኢኮኖሚ ችግር እየተመቱ ነው፡፡ በተለይ ሆስፒታሎች ትልቁ ወጪያቸው ለሠራተኞች ወይም ለሐኪሞች የሚከፈለው ደመወዝ ነው፡፡ አንድ ኢንተርኒስት ሐኪም ከ100 ሺሕ ብር በላይ ይከፈለዋል፡፡ ከ75 እስከ 80 ሺሕ ብር  የተጣራ እጁ ላይ እንዲደርሰው ይደራደራል፡፡ ሥራው በቆመበት ወቅት ሰርጂኑ፣ ጋይኖኮሎጂስቱ፣ ፔዲትሪሽያኑ፣ ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣ ወዘተ. ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ናቸው፡፡ እኔ የምመራው ሆስፒታል በወር ለደመወዝ ብቻ ከ1.6 ሚሊዮን ብር በላይ በአማካይ ይከፍላል፡፡ አሁን ገቢያችን ወርዶ በወር ከ200 እስከ 300 ሺሕ ብር ብቻ በሆነበት ወቅት ከየት አምጥተን ይህን ያህል ደመወዝ እንክፈል? እንዳናሰናብት በሕግ ተከልክሏል፡፡ የባንክ ዕዳውን ትተን፣ በሠራተኛ ደመወዝ ብቻ መግቢያ መውጪያ ያጡ የጤና ተቋማት በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ያልታሰበና ያልታየ አጋጣሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ለእናንተ ወይም ለማኅበራቸው ያመለከቱ የሕክምና ተቋማት ብዛታቸው ምን ያህል ነው?

አቶ ዳዊት፡- በአብዛኛው ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የጤና ዘርፍ ላይ የሚሠሩና በማኅበራት የተደራጁ አባላት ሥቃይ ውስጥ ናቸው፡፡ የትም ሆስፒታል ሄዶ መመልከትና ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ታካሚው በሌለበት ወቅት የሕክምና ባለሙያዎች፣ በተለይም ዶክተሮች የጤና አገልግሎት መስጫዎች አካባቢ መሆን አይፈልጉም፡፡ ታካሚ ሲመጣ ጥሩን ይላሉ፡፡ በቀን አንድ ታካሚ ሲመጣ አየት አድርገው ወዲያው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ እነሱም ሥጋት ስላለባቸው ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ገጥሞታል፡፡ አገልግሎት ፈላጊውን ጨምሮ፣ አሠሪውም ሠራተኛውም የማይደሰቱበት፣ ባለሀብቱ ችግር ላይ የወደቀበት አስከፊ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ማንም ያልጠበቀው ጉዳይ እየታየ ነው፡፡ በአሜሪካ የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት፣ ከፍተኛውን ተጠቃሚነት ያገኙት የግል ጤና ተቋማት ናቸው፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ተቋማት ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ በእያንዳንዱ ታካሚ ልክ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚከፍላቸው በማስታወቁ፣ የግል ሕክምና ተቋማት የኮሮና በሽታ ተጎጂዎችን እየተቀበሉ እያስተናግዱ ነው፡፡

በእኛ አገር ሁኔታ የግል ጤና ተቋማት የኮሮና በሽታን እንዳይመረምሩ ተከልክለዋል፡፡ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ክሊኒኮች ምን ሠርተን እንብላ እያሉ ነው፡፡ የግል ሕክምና ተቋማት አቅም ስለሌላቸው አይደለም እንዳይመረምሩ የተደረጉት፡፡ ፈቃደኞችም ናቸው፡፡ ከምንዘጋ እንሥራ እያሉ ጥያቄ እያረቡ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተወሰኑ የታች የመንግሥት ኃላፊዎች በፈጠሩት ጫና ነው የግል ሕክምና ተቋማት እንዳይመረምሩ የተደረገው፡፡ በሌላ በኩል ከግል ተቋማት ጋር በአጋርነት እየሠራን ነው ሲባል እንሰማለን፡፡ እያሳተፍን ነው ይባላል፡፡ እርግጥ የተወሰኑ የግል ሕክምና ተቋማት ተመርጠው የደም ናሙና እንዲሰበስቡ እየተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ እግሩን ተሰብሮ ለሕክምና ወደ ግል ሆስፒታል የሚሄድ ታካሚ፣ ደሙ ለአስፈላጊ የሕክምና አገልግሎት ሲወሰድ እግረ መንገዱን አጠራጣሪ ሁኔታዎች ከታዩበት፣ ማለትም ትኩሳትና መሰል ነገሮች ከታዩበት፣ የኮሮና በሽታ ሊኖርበት ስለሚችል ለናሙና የሚፈለገው ደም እንዴት እንደሚቀዳና ታሽጎ እንዴት ወደ ፓስተር መላክ እንደሚያስፈልገው ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውጪ ምርመራ ማድረጉ አልተፈቀደም፡፡ ይህ ሊታይ ይገባዋል፡፡ በጠቅላላው በደረሰባቸው ጫና ምክንያት የግል ሕክምና ተቋማት ሥጋት ላይ ወድቀዋል፡፡

በተለይ ሠራተኛን ያለ ምንም ሥራ ደመወዝ እየከፈሉ ማቆየቱ ትልቅ ጫና ሆኖባቸዋል፡፡ አቅም አጥተናል፣ ከስረን እየዘጋን ነው እያሉ ነው፡፡ ሠራተኛ ቤቱ እንዲቆይ የሚደረግበት፣ ደመወዙን በብድር ማግኘት የሚችልበት አንቀጽ በአሠሪዎች ፕሮቶኮል ውስጥ ተካቷል፡፡ ደመወዝ በብድር መክፈል እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ድርጅቴ መሥራት ከማይችልበት ደረጃ ቢደርስ፣ ሠራተኞቼን ቤታችሁ ተቀመጡ እላቸዋለሁ፡፡ የሥራ ውላቸውን ግን አላቋርጥም፣ አላባርራቸውም፡፡ ነገር ግን ደመወዝ መክፈል ስለማልችል፣ ደመወዛቸውን በብድር መልክ እሰጣቸዋለሁ፡፡ ይህንን ፕሮቶኮሉ አሥፍሯል፡፡ ግን እኔ ማን ነኝ ገንዘብ የማበድረው? ብድር ለመስጠት የተቋቋምኩ ድርጅት አይደለሁም፡፡ ብድር የሚሰጠው ባንክ ነው፡፡ መንግሥት ካዘነና ጉዳዩ የእኔም ነው ብሎ ካሰበ፣ ከባንክ እንዲበደሩ ማመቻቸት ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ ከባንክ በ17 በመቶ ወለድ ከፍዬ ያገኘሁትን ገንዘብ፣ ሠራተኛውን በሥራው ላይ ለማቆየት ሲባል ብቻ በነፃ አበድር ማለቱ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ባይሆን መንግሥት ከባንኮች ጋር ተነጋግሮ በነፃ የሥራ ማስኬጃ ብድር አበድሩት ብሎ ቢያመቻችልኝ አንድ ነገር ነበር፡፡ ወይም ደግሞ ባንኮች ለሠራተኞች እንዲያበድሩ ቢያደርግና እኛ ዋስትና እንድንሰጥ ቢደረግ ሌላ አማራጭ ነበር፡፡ ሥራው ሲመጣ ከደመወዛቸው እየቆረጥን ለባንኩ ዕዳቸውን መክፈሉ አይቸግረንም ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ደመወዛቸውን እንደ ሁኔታው የሦስት ወይም የስድስት ወራት ቀድመው በመክፈል በብድር የሚያስናግዱበት የተመለደ አሠራር አላቸው፡፡ ይህንን በማድረግ እንዲያግዙ ነው መሰል የተፈለገው?

አቶ ዳዊት፡- ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ በፕሮቶኮሉ የተቀመጠ ገደብ ግን የለም፡፡ መጨረሻው አልተቀመጠም፡፡ ሠራተኛውን አታሰናብተው፣ በቤቱ እንዲቀመጥ አድርገው የሚለው ለአሠሪውም ጥሩ የሚሆነው ብዙ ሥልጠናና ልምድ እንዲያገኝ ያደረገው ሠራተኛውን ማጣት ስለሌበት ጭምር ያግዘዋል፡፡ ነገር ግን ላለፉት አራትና አምስት ወራት ድርጅቶች አቅማቸው በቻለው ሁሉ ሠራተኞቻቸውን ይዘው ቢቆዩም፣ ከዚህ በላይ መሸከም ካልቻሉ ግን ሠራተኞቻቸውም ያለ ሥራ አሠሪዎች እንደያዟቸው ተገንዘብው በቤታቸው እንዲቆዩ፣ የሥራ ዋስትናቸው ግን እንደተጠበቀ ሆኖ ሥራው ሲመጣ መቀጠል የሚችሉበት ስምምነት ማድረግ አንድ መልካም አማራጭ ሐሳብ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ሒደት ግን ደመወዙን በብድር እንዲሰጠው በአንቀጽ ተካቶ ሲቀመጥ፣ የስንት ወር ደመወዙ በብድር እንደሚሰጠው አልተቀመጠም፡፡ እግዚአብሔር አያድርግብን እንጂ በሽታው ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ጭምር እየባሰበት እንደሚሄድ ሥጋቶች አሉ፡፡ ይህ ከሆነ የስድስት ወራት ደመወዝ ከየት መጥቶ ነው ለሠራተኞች በብድር የሚሰጣቸው? ከባንኮች በ17 ወይም በ18 በመቶ ወለድ የተገኘውን ብድር በነፃ ለሠራተኞች አበድሩ ማለቱ ትንሽ አግባብ አይደለም፡፡ ይልቁንም መንግሥት ለሠራተኞች ደመወዛቸው በብድር እንዲሰጣቸው ከፈለገ፣ እኛ አሠሪዎች ዋስትና ሰጥተን፣ ከደመወዛቸው ላይ እየቆረጥን ለባንኩ እንደምንሰጥ ማረጋገጫ የምንገባበትን አሠራር ያስፍን፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት ከዚህ ቀደም ለአበባ፣ ለሆቴልና ለቱሪዝም ዘርፎች የሥራ ማስኬጃ ብድር ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡ እናንተስ ይህንን ለማግኘት ጠይቃችኋል? ከጠየቃችሁስ ምን ምላሽ አገኛችሁ?

አቶ ዳዊት፡- በእኛ ዘንድ ይህ ነገር አልታሰበም፡፡ ተስፋ ስለነበረን ጭምር ነው፡፡ በሽታው በጀመረ በመጀመርያዎቹ ወራት ሰሞን ትልቅ ተስፋ የደረገው በመንግሥትና በግል አጋርነት መሠረት በጤናው መስክም እንዲተገበር የገንዘብ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ነበር፡፡ እኛም ይህ አጋርነት እንዲፈጠር፣ መንግሥትን ብቻም ሳይሆን ራሳችንንም ለማገዝ የሚረዳን በመሆኑ ጥያቄ ስናቀርብ ነበር፡፡ ላቀረብናቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባናገኝም፣ በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት የነበራቸው ምልከታ እንደ ኤችአይቪ/ኤድስ መንግሥት ነገሮችን በሚገባ አጥንቶና አገናዝቦ የግሉ ዘርፍ በተለይ በከተሞች አካባቢ ሰፊ ኔትወርክ ስላለው፣ ለኮሮና ወረርሽኝም ያሳትፈናል የሚል ግምት ነበረን፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የግል የሕክምና ተቋማት ተሳታፊ ሆነው ገቢ ማግኘት የሚችሉበት እንቅስቃሴ ከተፈጠረላቸው ድርጅቶቻቸውን ሳይዘጉ፣ ሠራተኞቻቸውን ሳይበትኑ መዝለቅ ይችላሉ የሚል ግምት ነበረን፡፡ መንግሥት የግሉ ሕክምና ተቋማት በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በምን አግባብ ይሳተፉ በሚለው ላይ እየመከረበት እንደሆነ ሲገለጽልን የመጀመርያው ወር አለፈ፡፡ ሁለተኛውም ወር እንዲሁ አለፈ፡፡ ሦስተኛው ወር ሲመጣ ግን ይኼ ነገር ምን ይሻላል ብለን ሁላችንም ጥያቄ ማቅረብ ጀመርን፡፡

ይሁን እንጂ ለአንድ የግል ተቋም ብቻ የምርመራ ሥራ ከመፈቀዱ በቀር በግል ተቋማት ደረጃ የኮሮና ቫይረስን የመርመር ሥራ ያልተፈቀደበት ምክንያት፣ በላይኞቹ አመራሮች ዘንድ በተገቢው መንገድ የሚታወቅ አይመስለንም፡፡ በሽታ ሲከሰት ያውም ወረርሽኝ ያስከተለ በሽታ ሲፈጠር፣ ከጤና ተቋማት በላይ ማን ነው ሊንቀሳቀስና ሊሳተፍ የሚችለው? አገልግሎቱን በሚገባ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ይገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ በሽታ በመከሰቱ እኛም አገልግሎት እየሰጠንና ከአገልግሎታችንም ተጠቃሚ እንደሆንን ሁሉም ያስባል፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ተጠቃሚ የሆንን እየመሳለቸው ነው መሰለኝ ማናቸውም ጆሮ ሰጥተው አልሰሙንም፡፡ እውነትም በሽታው በተስፋፋበት ወቅት የጤና ተቋማት ሥራ አጥተው ሊዘጉ ነው ቢባል ማንም አያምንም፡፡ እውነታው ግን ለመዘጋት የተገደዱ በርካቶች መሆናቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ይህን ያህል ጉዳት አጋጥሞኛል በማለት በአኃዝ የተደገፈ መረጃ አቅርቦ ድጋፍም ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የግል ጤና ተቋማት የጉዳት መጠን ምን ያህል ነው?

አቶ ዳዊት፡- የጉዳቱ መጠን ይህን ያህል ነው ብሎ በአኃዝ መናገሩ ለጊዜው ይከብደኛል፡፡ ነገር ግን ከሆቴሎች የበለጠ ጉዳት እንደደረሰ ግን መናገር እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት እንግዲህ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አጋጥሟችኋል ማለት ነው?

አቶ ዳዊት፡- ጉዳቱ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በጥናት ይደረስበታል፡፡ ዋናው ግን የሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ አይተመንበትም፡፡ አንድ ታማሚን ማከም ባለመቻል ሕይወቱ አደጋ ውስጥ ሲወድቅና ለማለፍ ሲገደድ ማየት የሚያደርሰው ጉዳት ከኪሳራ በላይ ነው፡፡ ተመንም የለውም፡፡ አንድ የስኳር በሽተኛ በተገቢው ክትትል በሽታውን መቆጣጠር የሚችልበት አገልግሎት አጥቶ፣ የስኳር ሕመሙ የኩላሊት በሽታ መንስዔ ሲሆንበት እየታየ ምንም ማድረግ አለመቻል በአገር ደረጃ ትልቅ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል አደጋ ነው፡፡ ይህ በገንዘብ አይተመንም፡፡ የወባ ሕመምተኛ፣ የኤችአይቪና መሰል በሽታዎች ታማሚ በተገቢው መንገድ ሕክምና ሊያገኝ የሚችልባቸው የግል ተቋማት ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ፣ ሌሎች በሽታዎች የሚዛመቱበት አስፈሪ ሁኔታ እየመጣ ነው፡፡ በድኅረ ኮሮና የሚመጡ አደጋዎችን እንደ አገር ስናስባቸው ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉበት ሥጋት ከወዲሁ ተደቅኗል፡፡ እነዚህ ነገሮች ያሳስቡናል፡፡ አቅም ያለው፣ ገንዘብ ያለውና ድጋፍ ያገኘ የግል ሕክምና ተቋም በሥራው ላይ የመቆየት ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡ ሌሎቹ የግል የሕክምና ተቋማት ግን የመዘጋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ስኳር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአገር ደረጃ በገዳይነታቸው አብላጫውን ድርሻ ይዘዋል፡፡ አራቱ ዋና ዋና የሚባሉትን ጨምሮ የተሽከርካሪ አደጋ ሲታከልበት ከፍተኛ የሞት ቁጥር እየተመዘገበ እንደሆነ ከኮሮና በፊት የነበሩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በኮሮና ወቅት እነዚህ በሽታዎች ተገቢውን ሕክምናና ክትትል የማግኘታቸው ነገር አሳሳቢ እየሆነ ከመጣ፣ የበለጠ አስከፊ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል እየተባለ ነው፡፡

አቶ ዳዊት፡- ይህንን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ አንደኛ ሥርጭቱን የሚያባብሰው የአገልግሎቱ መስተጓጎል ነው፡፡ ሁለተኛ የመከላከል ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀዛቀዙ በመምጣታቸው ነው፡፡ በፊት አስተማሪ የጤና ፕሮግራሞች፣ ዘመቻዎች፣ በየቀበሌው እስከ ገጠር ድረስ እየሄዱ የሚያስተምሩ፣ ክትባት የሚሰጡ፣ የጤና ምክርና ክትትል የሚሰጡ አካላት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ አገልግሎታቸው ቀንሷል፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም የተከሰተ ችግር ነው፡፡ አሁን ተላላፊም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም በኮሮና ምክንያት የሚደረግባቸው ክትትልና ቁጥጥር ቀንሷል፡፡ ይህ አደገኛ ነው፡፡ በድኅረ ኮሮና የሚፈራው ብዙ ተለፍቶና ብዙ ሥራ ተሠርቶ የቀነሱ በሽታዎች እንዳያንሰራሩ ነው፡፡ ይታይህ ትበላለህ፣ ትጠጣለህ፡፡ ነገር ግን እንደ ልብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አትችልም፡፡ የስፖርት እንቅስቃሴ የሚሠራባቸው ማዘውተሪያዎች ወይም ጂም ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ኮሮናው ከክረምቱ ጋር ተዳምሮ እንቅስቃሴያችንን እየገደበው ነው፡፡ የምንመገበው ቅባትና ሌላውም ምግብ ኮሌስተሮላችንን ይጨምረዋል፡፡ ይህ ሥጋት ሆኖበት ሄዶ የሚመረመር ሰው ጥቂት ነው፡፡ ኮሮና እንዳይዘኝ እያለ ሰው ወደ ጤና ተቋም አይመጣም፡፡ የሕክምና ተቋማት ውስጥ ኮሮና እንዳይዘው የሚሠጋ ብዙ ሰው አለ፡፡ አብዛኛው ሰው ኮሮና መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ እየጠበቀ ይመስላል፡፡ ሌሎች በሽታዎችን በጊዜ ታክሞና ተከታትሎ በመቆጣጠር ራሱን መዳን የሚችልበትን ዕድል እያጠበበ ነው፡፡ የስኳር ሕመሙ ጣሪያ ሊነካ ይችላል፡፡ በርካታ ሰዎች ሳያስቡት ለችግር እየተጋለጡ ነው፡፡ መንገድ ላይ እየሄዱ ለተወሳሰበና ለከፍተኛ የጤና ችግር የሚጋለጡ ሰዎችን ማየት እየተበራከተ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ የጤና ጫናው በዚህ መንገድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ተጋላጭነት ከመዳረጉ በፊት ነገሮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የእኔ ሥጋትና ፍርኃት በኮሮና ምክንያት የተባባሰ የጤና ቀውስ እንዳይፈጠር ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...