Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየኢትዮጵያ የብር ኖቶችና የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓተ ልማድ ከአካል ጉዳተኞች መብት አንፃር

የኢትዮጵያ የብር ኖቶችና የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓተ ልማድ ከአካል ጉዳተኞች መብት አንፃር

ቀን:

በፋንታሁን መንግሥቴ

በአገራችን ከ20 ሚሊዮን  በላይ የአካል ጉዳት ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደማንኛውም ሰው በአገራችን የተለያዩ የመንግሥትና የግል ባንኮችን አገልግሎቶች ለመጠቀም አካላዊ ኢተደራሽነት (Physical Inaccessibility), የመረጃ ኢተደራሽነት (Information Inaccessibility), የአገልግሎት ኢተደራሽነት (Service Inaccessibility) ይገጥማቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ የብር ኖቶች አጠቃቀምና በባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ከሕግና ከአሠራር አንፃር እንዳስሳለን፡፡

ባንኮች ከሕዝብ የአክሲዮን መዋጮ ሰብስበው አገሪቱ ባወጣቻቸው የባንክ ሥራ አዋጅ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ፣ የንግድ ሕግና ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣቸው የማስፈጸሚያና የመቆጣጠሪያ መመርያዎች የሚቋቋሙና የሚተዳደሩ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የንግድ ማኅበራት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከወረቀት የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት በስፋት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን  ለመከላከል  የዲጂታል ባንክ  አገልግሎት አካላዊ ንክኪን ስለሚቀንስ  ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባንኮች ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚሰጡበት አሠራርና ተግዳሮቶቹ

የመጀመርያው ተግዳሮት በተለይ ዓይነ ሥውራን ግብይት ለማድረግ የገንዘብ ኖቶችን አንብቦ ለመለየት የሚያስችል ምልክት (Currency Identification) አለመኖሩ ነው፡፡ ችግሩ የማየትና የመስማት ድርብ ጉዳት ባለባቸው ሰዎች ላይ ይበልጥ የከፋ ነው፡፡ ይህ ችግር ባንኮች ብቻ የፈጠሩት ሳይሆን የገንዘብ ኅትመት ሥርዓቱ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብር የቀለም ጽሑፍና የምስል መለያ እንጂ በእጅ የሚለይ ምልክት (Tactile Markings) የለውም፡፡ በሌሎች አገሮች በብሬል፣ በእጅ በሚያዙ የገንዘብ መለያ መሣሪያዎችንና ሶፍትዌሮችን ይጠቀማሉ፡፡ በተጨማሪም መስማት የተሳናቸው የባንክ ደንበኞች  የባንክ ጉዳዮቻቸውን ለመፈጸም የሚያስችላቸው በባንኮች የተዘጋጀ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖሩ ነው፡፡

ባንኮች በብዛት ለዓይነ ሥውራን የሚሰጡት የቁጠባ ሒሳብ ደብተር  አገልግሎት (ፓስቡክ አካውንት) ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለማግኘትና ገንዘብ ገቢ ለማድረግ የሚጠበቀው መሥፈርት እንደማንኛውም ደንበኛ የተለመደ ነው፡፡ ችግሩ የሚጀምረው ሒሳባቸውን ሲያንቀሳቅሱ ነው፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች ዓይነ ሥውራን ደንበኞቻቸው ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ ምስክር ካላቀረቡ ሒሳባቸውን ወጪ ማድረግ አይችሉም፡፡ ባንኮች ለዚህ አሠራራቸው መነሻ የሚያደርጉት የ1952ቱን  የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1728ን ነው፡፡ እንደ ሕጉ አነጋገር ከማህይማንና ከእውራን ጋር የሚደረግ የውል ፊርማ በውል አዋዋይ ሹም ወይም በፍርድ ጸሐፊ ወይም ዳኛ በሥራቸው ላይ ሆነው ያረጋገጧቸው ካልሆነ አያስገድዳቸውም በማለት ይደነግጋል፡፡ በዚህ መነሻነት በዳበረው ልማዳዊ  አሠራር መሠረት የደንበኛውንና የምስክሩን/ሯን መታወቂያ ኮፒ በማድረግ ደንበኛው ይህን ያህል ብር ሲያወጣ አይቻለሁ በማለት እንዲፈርሙ በማድረግ የምስክሩ  ማንነት፣ የሥራ ቦታና ሁኔታ፣ የደንበኞቹ ቤተሰብ ይሁን የሥራ ባልደረባ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ አንዳንዶቹ በዚህ አሠራር ገንዘብ ለማውጣት፣ ለማስተላለፍና ቀሪ ሒሳባቸውን ለማወቅ ደብተራቸውን ለሦስተኛ ወገን ማስነበብ የግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አንዱ የሆነውንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 የተረጋገጠውን የግላዊነት ሕይወት መብትን ይጋፋል፡፡ በሕግ መሠረት ካልሆነ በስተቀር የግል ሕይወት መብት ሊገደብ አይችልም፡፡ ሚስጥራዊነታቸውንም በማጋለጥ ደንበኞችን ለዘረፋና ለጥቃት ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡

ሌላው አካል ጉዳተኞች ፈተና የሚሆንባቸው በፊርማ ምክንያት የባንክ ብድር አገልግሎት ለማግኘት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የኮንዶሚኒየም ዕድል ባለ ዕጣ የሆነ አንድ አካል ጉዳተኛ የ20/80 የባንክ ብድር ለመፈረም ወደ ባንኩ ሲሄድ፣ በባንኩ አሠራር መሠረት የብድር አገልግሎቱን የምታገኘው በአንተ ፊርማ ሳይሆን የምትወክለው ሦስተኛ ወገን ካለህ ብቻ ነው በማለት ይነግረዋል፡፡ ባለ ዕድሉም እኔ የምወክለው ሰው የለኝም በራሴ ፊርማ ይሁንልኝ ብሎ ሲጠይቅ፣ እንደዚያ ከሆነ ብድሩን መስጠት አንችልም በመባሉ በወቅቱ የውልና ማስረጃ ቀርቦ ውክልና በሰጠው ሦስተኛ ወገን አማካይነት የብድር ውሉን ተዋውሎ ብድሩ ተፈቅዶለታል፡፡

ከንግድ ወረቀቶች አንዱ የሆነውን የቼክ አካውንት ወይም ተንቀሳቃሽ የባንክ ሒሳብ ለመጠቀም ጸሐፊው እስካለው መረጃ ድረስ ለዓይነ ሥውራን ደንበኞች አገልግሎቱን የሰጠ ባንክ የለም፡፡ ምክንያታቸው ወጥ የጣት አሻራ ፊርማ ናሙና ለመስጠት ያስቸግራል የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 733 ማናቸውም በውል ለመገደድ ችሎታ ያለው ሰው በንግድ ወረቀትም ለመገድድ ይችላል፡፡ የዚሁ ሕግ አንቀጽ 734(1) በንግድ ወረቀት የተደረጉ ማስታወቂያዎች (ዴክላራሲዮን) እነዚሁ ማስታወቂያዎች የሰጠው ሰው የእጅ ጽሑፍ ፊርማ ሊኖራቸው ይገባል ቢልም፣ በእጅ ወይም በመኪና አሠራር ምልክት በሚያደርግ ዘዴ ማኅተምን በመሰለ ፊርማ ወይም ለመፈረም የአካል ችሎታ የሌለው እንደሆነ መፍቀዱ በሰነዱ ላይ በባለሥልጣኑ ፊት በተደረገ ማስታወቂያ መረጋገጥ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ የባንክ ደንበኛው የሁለቱም እጅ ጉዳተኛ ወይም ዓይነ ሥውር ቢሆን የዓይነ ሥውሩን የእጅ ጣት አሻራ ወይም ከጣት አሻራው በሚወሰድ የአሻራ ፊርማ ናሙና ማኅተም በመጠቀም፣ ወይም ደንበኛው በሁለቱም እጆቹ ጉዳት ምክንያት ለመፈረም የማይችል ከሆነ መፍቀዱ በሰነዱ ላይ በባለሥልጣኑ ፊት በተደረገ ማስታወቂያ መረጋገጥ ይችላል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የውል አዋዋይ ሲባል የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ባንኮች የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሲጠሩ በስብሰባው ላይ መገኘት የማይችሉ ባላክሲዮኖች በስብሰባው ላይ  የሚገኙላቸውን  ወኪሎች ውክልና የሚሰጡት ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቀርበው ሳይሆን፣ ራሳቸው ባንኮች ናቸው ውክልናውን የሚያዋዋሉት፡፡ ስለዚህ በጠባቡም ቢሆን ባንኮችም የማዋዋል ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን በፍትሐ ብሔር ሕጉ፣ በንግድ ሕጉና በባንክ ሥራ አዋጁ መሠረት ያለውን የአፈጻጸም ክፍተት የሚደፍን አሠራር መዘርጋት ቢኖርባቸውም፣ ብሔራዊ ባንክም በዚህ አግላይ አሠራራቸው አልጠየቃቸውም፡፡ ባንኩ በሚያወጣቸው መመርያዎችም ጉዳዩ መፍትሔ እንዲኖረው አላደረገም፡፡ አካታች የባንክ አገልግሎት ለዓይነ ሥውራን በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ አቶ ዮሐንስ ታከለ በ2011 ለድኅረ ምረቃ ማመዋያ ጥናታቸው ባደረጉት ጥናት፣ ዓይነ ሥውራን የድርጅቶቻቸውን የባንክ ሒሳብ ለመክፈትና በነፃነት ለማንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ስለማያገኙ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሁለት በመቶ የሚሆኑት ዓይነ ሥውራን፣ የከፍተኛ ሥራ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ወይም ለኃላፊነት መደብ ላለመወዳደር ተገደዋል፡፡

የወረቀት ባንክ አገልግሎት በተለይ ዓይነ ሥውራን በሦስተኛ ወገን ዕገዛ የሚጠቀሙት አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት የዓይነ ሥውራን ደንበኞችን የግል ሕይወትና ሚስጥራዊነት የመከበርና የመጠበቅ መብት የሚጋፋ ሲሆን፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ሒሳብ ለማንቀሳቀስ ወደ ባንኮች በአካል ለመሄድ ስለሚያስገድድ፣ ፊርማ ለመፈረምና  ገንዘብ ለመቀበል አካላዊ ንክኪን ስለሚፈልግ ነው፡፡

ሌላው ቴክኖሎጂ የወለደው የኢባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች በተለይም ለዓይነ ሥውራን የባንክ ደንበኞች ከወረቀት የባንክ አገልግሎት አንፃር ከአካላዊ ተደራሽነቱ በተጨማሪ በዓይነቱ እጅግ የተሻለ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ ባንኮች አገልግሎቱን ሲሰጡ አብዛኞቹ ግን ዓይነ ሥውራን ኢባንክ አገልግሎት እንዴት እንደሚጠቀሙ ግልጽ መመርያ ስለሌለን አገልግሎቱን አንሰጥም ይላሉ፡፡ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት አንዱ የሆነውን ኤትኤም ለመጠቀም የሚያስችል የኤቲኤም ስክሪን ማንበቢያ ሶፍትዌር ባንኮች የሚተክሏቸው ማሽኖች ላይ የላቸውም ወይም ይህን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስተካከያ አያደርጉባቸውም፡፡ የሞባይል ባንክ አገልግሎት ግን ዓይነ ሥውራን ስክሪን ማንበቢያ ሶፍትዌር ያላቸውን ስልኮች የሚጠቀሙ ከሆነ አገልግሎቱን እንደማንኛውም ደንበኛ መጠቀም ይችላሉ፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች ግን ይህ እንደሚቻል ስለማያውቁ አገልግሎቱን ይከለክላሉ፡፡ ችግሩ በግል ባንኮች ላይ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ በአንዳንድ ባንኮች ክልከላው ከባንኮች ኮርፖሬት/ተቋማዊ ፖሊሲ የሚመነጭ ሲሆን፣ በአንዳንድ ባንኮች ደግሞ እንደተቋም የተያዘ አቋም ሳይሆን  ከግለሰባዊ የአመለካከት ችግር የሚመነጭ ነው፡፡

ጉዳዩን በተጨባጭ ምሳሌ ይበልጥ ለማስረዳት አንድ ዓይነ ሥውር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለሥራውና ለመኖሪያ አካባቢው ቅርብ ወደሆነ ቀደምት የአገራችን የግል ባንክ ቅርንጫፍ በማምራት የቁጠባ ሒሳብ ከፍቶ የቁጠባ ሒሳብ ደብተርና የኤቲኤም ካርድ ተሰጠው፡፡ የሞባይል ባንክ አገልግሎቱስ ብሎ ሲጠይቅ የከፈትከው ሒሳብ ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ደንበኞች የተዘጋጀነው ይባላል፡፡ የዚህ ዓይነት የሒሳብ ቁጥር ደግሞ ከሞባይል ባንክ አገልግሎት ሲስተም ጋር መገናኘት አይችልም በማለት መለሰለት፡፡ ማንበብና መጻፍ መቻል  ማለት የግድ የቀለም ጽሑፍ ብቻ ነውን? ሌላው እዚህ ላይ መመለስ ያለበት ጥያቄ ዓይነ ሥውራን የሞባይል ባንክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ስልክንና ኮምፒውተርን ለመጠቀም የሚያስችሏቸው የስክሪን ማንበቢያና መጻፊያ መተግበሪያ ሶፍትዌሮች አማካይነት ያነባሉ፡፡ ይጽፋሉ፡፡ ስለዚህ ባንኮች እንደማንኛውም ደንበኛ  የሞባይል ባንክ አገልግሎት ለዓይነ ሥውራን ለመስጠት   አገልግሎቱን ከመልቀቅ የተለየ ሥነ ሥርዓት አያስፈልጋቸውም፡፡ በተለይም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መራራቅን የሚያበረታታ፣ ንክኪን የሚቀንስ፣ የሦስተኛ ወገን ጥገኝነትን የሚያስቀር፣ ግላዊ ሕይወትን፣ ግለሰባዊ ልዕልናን፣ ነፃነትን፣ የሚያስጠብቅና  አካላዊ ንክኪን የሚቀንስ በመሆኑ ይበልጥ ተደራሽና ተመራጭ ነው፡፡ ይልቅስ የኤቲኤም ማሽኖቻቸውን ሲገዙና ሲተክሉ የስክሪን ማንበቢያ ሶፍትዌሮች የተገጠሙላቸውና የተስተካከሉ መሆናቸውን ቢያረጋግጡ ጥሩ ነው፡፡ ባንኮች አሉታዊ  አሠራራቸውን በተመለከተ የሕጋዊነት ጥያቄ ሲነሳላቸው ሕጉ እንደማይፈቅድ  እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡ የሕግ አማካሪዎቻቸው ክልከላውን ብቻ ነው እንዴ የሚያማክሯቸው?

ስለ አካል ጉዳተኞች መብቶች በአጭሩ

የአካል ጉዳተኞች መብት ከሰብዓዊ መብቶች የሚመነጭ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚጎናጸፏቸው መብቶች ናቸው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ባለቤት ለመሆን የግለሰቦች ወይም የመንግሥት ፈቃድ አያስፈልግም፡፡ አካል ጉዳተኞች ሰው ከመሆናቸው በተጨማሪ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በመሆናቸው በጠቅላላው የሰብዓዊ መብቶች ከሚደረግላቸው ጥበቃ በተጨማሪ፣ በልዩ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ዕውቅና የሚሰጡ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነቶችና ሕጎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋነኛው የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት ነው፡፡

ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ካላቸው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና የኮንቬንሽኑ መርሆችና ትርጓሜዎች መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከተደነገጉት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች መካከል በሕግ ፊት እኩል ዋስትናና ጥበቃ የማግኘት፣ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ፣ የግለሰባዊ ነፃነትና ልዕልና መጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የሕግና የሕገ መንግሥቱን የበላይነት በሚደነግገው አንቀጽ 9 (2) እና አንቀጽ 13 (1) ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት አካል፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል እንዲሁም ባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በአንቀጽ 9 (1) ላይ ተደንግጓል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 676/2002 የፀደቀውና በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (4) መሠረት የአገሪቱ ሕግ አካል የሆነው የተባበሩት መንግሥት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መብቶችን እንዲሁም በአስቸኳይ ሁኔታና በጦርነት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነውን የሰብዓዊነት ሕግን (Humanitarian Law) በተሟላ ሁኔታ አካቶ ይገኛል፡፡

በስምምነቱ አንቀጽ 2 በተደነገገው መሠረት ‹‹ሁሉን አቀፍ ንድፍ›› (Universal Design) ማለት ተጨማሪ የማስማማት ዕርምጃ ወይም የተለየ ዲዛይን ሳያስፈልገው የተቻለውን ያህል አጣጥሞ ለማንኛውም ሰው እኩል ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች፣ አካባቢዎች፣ መርሐ ግብሮችና አገልግሎቶች ማሳያ ንድፍ ነው፡፡ ይኸው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሁሉ አቀፍ ንድፍ የተለየ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የአካል ጉዳተኛ ወገኖች የሚያገለግሉ የመርጃ መሣሪያዎችን ከግምት ላለማስገባት አይችልም፡፡

በአንቀጽ 3 (ሀ) በግል ምርጫ የመወሰን ነፃነትና ራስን ችሎ የመኖር መብትን ጨምሮ ለተፈጥሯዊ ክብርና ለግለሰብዓዊ ልዕልና ዋጋ የመስጠት ግዴታ ተደንግጓል፡፡ ሌላው በስምምነቱ አንቀጽ 2 (ሐ) የተደነገገው መሠረታዊ መርህ አካል ጉዳተኝነትን መሠረት ያደረገ መድልኦ አልባነት (Non-Discrimination Based on Disability) ነው፡፡ በዚህ ንዑስ  አንቀጽ መሠረት ‹‹በአካል ጉዳት ላይ የተመሠረተ መድልኦ›› ማለት በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ በባህላዊ፣ በሲቪል ነክ ወይም በሌላ በማናቸውም መስክ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን ሁሉ ከሌሎች ጋር በእኩልነት ደረጃ ከመጠቀም ወይም ተግባራዊ ከማድረግ ወይም ለነዚሁ መብቶችና ነፃነቶች ዕውቅና ከመስጠት የመገደብ ዓላማ ወይም ይህንኑ ዓይነት ውጤት የሚያስከትል ማናቸውም ልዩነት፣ አገልግሎት ወይም ተፅዕኖ ነው፡፡ አድራጎቱ ምክንያታዊ ተቀባይነት ያለው ማስተካከያ አለማቅረብን ወይም ይህንኑ መንፈግን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የመድልኦ ተግባራት ያካትታል፡፡

አካል ጉዳተኞች በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የመሰማራት፣   የፋይናንስና የኢኮኖሚ ጉዳዮቻቸውን የመቆጣጠርና የማንቀሳቀስ መብት አላቸው፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 12(5)፡፡ እንደተመለከተው አካል ጉዳተኞች የንብረት ባለቤት የመሆን፣ ንብረትን የመውረስ፣ ፋይናንስ ነክ ጉዳዮቻቸውን በገዛ ራሳቸው የመቆጣጠርና የባንክ ብድር፣ የወለድ አገድና ሌሎች የዱቤ አገልግሎቶችን የማግኘት እኩል መብትና ዕድል ያላቸውና ንብረታቸውን በዘፈቀደ የማያጡ ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡

ሌላው መሠረታዊ ነጥብ የተደራሽነት መርህ  ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ምቹና ቅርብ በሆነ መንገድ ማቅረብን ያካትታል፡፡ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያጋጥሙ የአካላዊ፣ የመረጃና የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት በአንቀጽ 9 ሥር የተደነገገ ሲሆን፣ ባንኮች የሚሰጡትን የወረቀትና የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ባንኮች በሚሰጧቸው አገልግሎቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አካል ጉዳትን መሠረት ያደረገ አግላይና አድሏዊ አሠራር እየተገበሩ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች

ሕግ አውጪው አካታች ሕጎችን የማውጣት፣ ተግባራዊነታቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡

አስፈጻሚው አካል በተለይ የዘርፉ ተቆጣጣሪ አካል የሆነው ብሔራዊ ባንክ አካታች የባንክ መመርያዎችንና አሠራሮችን በማውጣት አካል ጉዳተኞች ተደራሽ የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አጋዥ ሕጎች እንደ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 እና ሌሎች ሕጎችን፣ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መቅሰምና ጥናቶችን ማድረግ አለበት፡፡ በጉዳዩ ላይ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራትን በማሳተፍ  የባንኮችን  ግንዛቤ ማሳደግ አለበት፡፡ ማኅበራቱም እስኪጠሩ ሳይጠብቁ ከመንግሥት ጋር በቅርበት መነጋገርና መሥራት  ይኖርባቸዋል፡፡

ባንኮችና ማኅበራቸው ሕጋዊ ግዴታዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውንም መወጣት አለባቸው፡፡ አገልግሎቶቻቸውን በሥርዓተ ልማድ ሳይሆን በሕግ መሠረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ በባንክ ሥራ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1159/2012 አንቀጽ 56 መሠረት ባንኮች የሚሰጧቸውን የባንክ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በመሆኑም ኤቲኤሞቻቸውንና ሌሎች አሠራሮቻቸውን በሕጉ መሠረት ምቹና ተደራሽ ማድረግ አለባቸው፡፡ ዓመቱን ሙሉ በሚዲያ  ማስታወቂያ በማስነገር ብቻ ሳይሆን የአገልግሎቶቻቸው ተጠቃሚ ያልሆኑ አካል ጉዳተኞችን በማካተት የውድድራቸው አካል አድርገው ቢሠሩ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትርፋማነታቸው አሁን ካላቸው ዓመታዊ ትርፍ የበለጠ ይሆናል፡፡  

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ከባንክ ሥርዓት ውጪ የሆነ ወደ 113 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ወደ ባንክ ሥርዓቱ ለማስገባት ሲባል በብር ኖቶች ላይ ለውጥ እንዲደረግ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አስገብቷል፡፡ የማኅበሩ ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ በእነዚህ የገንዘብ ኖቶች ላይ በዳሰሳ የሚለይ ምልክት ወይም የብሬል  ቁጥሮችን አካቶ በማተም ለዓይነ ሥውራን፣ የማየትና የመስማት ድርብ ጉዳት ላለባቸው ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ስለሆነ የገንዘብ ኅትመት ከመደረጉ በፊት የአካል ጉዳተኛ ማኅበራትና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስቀድመው ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fameng2@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...