Saturday, June 22, 2024

የዓባይ ውኃን እያቆረ ያለው ትውልድ የጽንፈኞች መቀለጃ አይሆንም!

ኢትዮጵያዊያን ዳግማዊ ዓድዋ ሊባል የሚችል ታላቅ ገድል በማከናወናቸው በጣም ሊደሰቱ ይገባል፡፡ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግንባታ እስከ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት እንዲሳካ ያደረጉ ወገኖች በሙሉ፣ ታላቅ ክብርና ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ የዘመናት የቁጭትና የብሶት ምንጭ የነበረው ዓባይ ወንዝ ተገርቶ፣ ለአገር የድል ብሥራት ሲሰማ ይህ ትውልድ ሊኮራ ይገባል፡፡ ከመኩራት ባሻገርም ኢትዮጵያን ከድህነት ወደ ባለፀጋነት ለሚያሸጋግሩ የወደፊት ታላላቅ ፕሮጀክት ዕቅድና አፈጻጸም መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው በአንድነት ቆመው አገራቸውን ሲያበለፅጉ እንጂ፣ ድህነት ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ሲተናነቁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት መንጥቆ የማያወጣ የፖለቲካ አጀንዳም ሆነ ሌላ ትርክት መቆም አለበት፡፡ ልዩነት ለጋራ ዕድገት የሚበጁ የተሻሉ ሐሳቦች የሚፈልቁበት እንጂ፣ ንፁኃን ለዕልቂት የሚዳረጉበትና የደሃ አገር አንጡራ ሀብት የሚወድምበት የመሰሪዎች መሣሪያ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአስመራሪው ድህነት ውስጥ መንጥቆ የሚያወጣቸው፣ በእኩልነትና በነፃነት የሚያኖራቸው ሥርዓት ግንባታ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ አንድ ላይ የኖረን ሕዝብ በተልካሻ ብሔርተኝነት በማለያየት ማፋጀት ዘመን ያለፈበት የፖለቲካ ቁማር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ማን እንደሚጠቅማቸውና ማን ደግሞ አገራቸውን ለማፍረስ ታጥቆ እንደተነሳ ነጋሪ አያሻቸውም፡፡ ለዘመኑ ትውልድ በማይመጥን የዛገ አስተሳሰብ አዲሱን ትውልድ ካሁን በኋላ ማታለል አይቻልም፡፡ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር አድርሶ አገሩን በኩራት አንገቷን ቀና ለማድረግ የተነሳው ትውልድ፣ የጽንፈኞች መቀለጃ እንደማይሆን በአገር ውስጥም በውጭም ሆኖ በግልጽ መልዕክቱን እያስተላለፈ ነው፡፡ አዲሱን ትውልድ በአረጀ አስተሳሰብ ማታለል አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ራሳቸውን በተደጋጋሚ የሚጠይቁበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከመጠየቅ ባለፈም ራሳቸውን በመገምገም ጠበቅ ያለ ወቀሳ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጣም ጥቂት ከሚባሉ የፖለቲካ ሰዎችና ድርጅቶች በስተቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ፣ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን ላይ በመስቀል በርካታ አሳዛኝ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡ ለአቅመ ፖለቲካ ሳይበቁና ለአገር ራዕይ ሳይኖራቸው ራሳቸውን በከንቱ አግዝፈው፣ በሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ላይ አሻጥረዋል፡፡ የአገር ህልውናን ከራሳቸው ሽራፊ ጥቅም በታች በማድረግ በታሪክ የሚያስጠይቃቸው ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ ለአገር ዕድገትና ለሕዝብ ኑሮ መመንደግ አንዳችም አስተዋፅኦ ሳይኖራቸው፣ አገር ለሚያፈራርሱና ሕዝቡን ለስደት ለሚዳርጉ የግጭት ቅስቀሳዎች እሳት አቀብለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ጽንፈኛ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች የውጭ ጠላት ተላላኪ በመሆን ጭምር ግፍ ፈጽመዋል፡፡ የግፋቸው ውጤትም በንፁኃን ሕይወትና በደሃ አገር ንብረት ውድመት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖርም አንዱ ገንቢ አንዱ አፍራሽ ሆኖ መገኘት ወንጀል ነው፡፡ በሕዝብ ፅኑ ፍላጎት የተቀጣጠለውን ለውጥ ለመቀልበስ የተነሱ ጀብደኞች የፈጸሙት ወንጀል መቼም ቢሆን አይረሳም፡፡ ለውጡ የመጣላቸውና ተስፋ የሰነቁ ብዙኃን እንዳሉ ሁሉ፣ የመጣባቸውና ጥቅማቸውን ያሳጣቸው ውስን ኃይሎች ፈተና ሆነዋል፡፡ ለሰላማዊ ፖለቲካ የተዘረጋው እጅ እንዲታጠፍና የጠመንጃ ፖለቲካ እንዲጀመርም ምክንያት በመሆን፣ አገርን የሚያፈርሱና ሕዝብን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ግጭቶችን በተደጋጋሚ ቀስቅሰዋል፡፡ ለውጡ በተጀመረበት ፍጥነት እንዳይጓዝ መሰናክሎችን በመፍጠር በርካታ ትርምሶች ፈጥረዋል፡፡ ዓባይን እየገራ ያለው ትውልድ ካሁን በኋላ እንዲፈነጩ እንደማይፈቅድላቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ካመረሩ መልሱ ከባድ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር በሰፊው እንዲከፈት ትግል የተደረገው በኢትዮጵያ ምድር ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር ኖሮ ሕዝብ አማርጦ የፈለገውን እንዲመርጥ ነው፡፡ ይህ በጣም መሠረታዊ የሆነ መርህ ነው፡፡ የፖለቲካው ተዋንያን ራሳቸውን ሳያጠሩ ሕዝብ ፊት አይቅረቡ፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚፎካከሩት ብቻ ሳይሆኑ፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይኛው የመንግሥት መዋቅር አመራሮች ድረስ በሕዝብ ፊት የሚያስከብራቸው ተግባር ያከናውኑ፡፡ ሕዝቡን ታች ድረስ ወርደው ፍላጎቱን ይወቁ፡፡ በማይረቡ ድርጊቶቻቸው ምክንያት ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ አያድርጉ፡፡ ከብሔር እስከ መንደር ድረስ እየተቧደኑ አገር ከመዝረፍ ጀምሮ እስከ ሕዝብ ማስመረር ድረስ ከተሰማሩበት አሳፋሪ ድርጊት ይፅዱ፡፡ አገር ከሚያፈርሱ ኃይሎች ጋር በግልጽና በሥውር እየተባበሩ ሕዝብ ላይ አይዝመቱ፡፡ በቅርቡ በተቀሰቀሰው አውዳሚ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩና ተባባሪዎች ጭምር በግልጽ ታይተዋል፡፡ በዚህም ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ውስጡ የተሰገሰጉ አገር አጥፊዎችን መንጥሮ ያውጣ፡፡ በርካታ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ውስጥ እንዲህ ዓይነት ፖለቲከኞችና ምስለኔዎቻቸው አሉ፡፡ በመኖራቸውም ሳቢያ በሕዝብ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ እንዲደነቃቀፍ ተረባርበዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በለውጡ ሥልጣናቸውን የተነጠቁ አምባገነኖች ትንፋሻቸውን ሰብስበው፣ አገሪቱን እንደ ሶሪያና የመን ለማፍረስ መኩራ እንዲያደርጉ ዕድል ሰጥተዋቸዋል፡፡ ፖለቲከኞች ይህንን አደገኛ ባህሪያቸውን ካላሻሻሉ፣ አገሪቱ ያጋጠማትን መልካም ዕድል በማበላሸት ወዳልሆነ አቅጣጫ ይነዷታል፡፡ ካለፈው ስህተታቸው ለመማር አሁንም ጠባብ ቢሆን ጊዜ ስላለ ያስቡበት፡፡ ካልሆነ ግን ሕግና ሥርዓት ሲከበር ዕብሪታቸውም ሆነ ጥጋባቸው ይተነፍሳል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ግፊት እያደረገ ነው፡፡ ትውልዱም ትዕግሥቱ አልቋል፡፡

በመንግሥት በተለይም በገዥው ፓርቲ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች በሕዝብ ውስጥ አሁንም እየተነሱ ነው፡፡ በሰሞኑ ከፍተኛ ግድያና ውድመት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በአመራር ላይ ያሉ ውስን ግለሰቦች፣ የጥቃቱን ሰለባዎች እያስፈራሩ መሆናቸው ይሰማል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በፓርቲ መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸውን ግለሰቦች መቆጣጠር ካልተቻለ፣ ሌላ ፈተና እንደሚኖር መገንዘብ አያቅትም፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅሮችን በመጠቀም ለአገር አፍራሾች መረጃ ከማቀበልና በንፁኃን ሕይወትና ንብረት ላይ ከመቆመር ባለፈ፣ ለብሔራዊ ደኅንነት ትልቅ ሥጋት እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ፈጣንና ቆፍጣና ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በቅጡ ሳይገሩ፣ ሥልጣን ላይ ጉብ ለማለት ብቻ ከተንቀሳቀሱ አደጋ እንዳለ መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሕዝብ ፊት በብቃትና በኩራት ሊያቀርብ የማይችል አጀንዳና ሥነ ምግባር ሳይኖራቸው፣ ከአሁን በኋላ እየቀለዱ መቀጠል እንደማይቻልና አዲሱ ትውልድም እንደማይቀበላቸው ቢረዱ ይመረጣል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ለሕዝብ ሥጋት መሆኑ አብቅቶ ለመጪው ምርጫ ሕዝብ ፊት መቅረብ የሚቻለው በተለመደው የለቅሶና የማጉረምረም ፖለቲካና ጊዜ ያለፈበት ብልጣ ብልጥነት ሳይሆን፣ ለአገርና ለሕዝብ ወደ ተግባር ሊተረጎምና ውጤት ሊገኝበት የሚችል አማራጭ ይዞ በመቅረብ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተለ ስለሆነ፣ እንደተለመደው በማጭበርበርም ሆነ በማደናገር ለማታለል መሞከር ትርፉ ውርደት ነው፡፡ ባረጀና በዛገ አስተሳሰብ ወጣቱን ትውልድም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ለመቅረብ መሞከር መሳቂያ ያደርጋል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚረባ ራዕይ የሌላቸው ራሳቸውን ቢያገሉ ይመረጣል፡፡ ይህ ትውልድ በቃ እያለ ነው፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋና ሕዝብ ደግሞ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ የመምረጥ ዕድል እንዲያገኝ፣ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በሕዝቡ ፍላጎት ቁመና ልክ መገኘት አለባቸው፡፡ በምርጫ የሕዝቡን ውክልና ያላገኙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች አገር የመበጥበጥ መብት እንደሌላቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መደላድል እንዲፈጠር ዕገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው የፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥም መገኘት የለባቸውም፡፡ ከዚህ በፊት ሕዝብ ሲያሰቃዩና አገርን መጫወቻ ሲያደርጉ የነበሩ አምባገነኖችም፣ ካባቸውን ገልብጠው በአገርና በሕዝብ ላይ እንዲያላግጡ ሊፈቀድ አይገባም፡፡ የአገርን መፍረስና መበተን ቀንና ሌሊት የሚያውጁ ኃይሎችም፣ የተለመደ ድርጊታቸውን ለማከናወን ዕድል ማግኘት አይኖርባቸውም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ማስተናገድ ያለበት ሰላማዊና ሕጋዊ የሆኑትን ብቻ ነው፡፡ ይህ የማይስማማቸው ካሉ የራሳቸውን አማራጭ አሳውቀው ወደሚሄዱበት መቀጠል ይችላሉ፡፡ ሕዝብ ውስጥ ተሸሽጎ የሕዝብ ደም ማፍሰስና የአገር ሀብት ማውደም አይቻልም መባል አለበት፡፡ አገር የሥርዓተ አልበኞች መቀለጃ የምትሆነው ጥጋበኞችና ዕብሪተኞች፣ በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ያለ ከልካይ እንዳሻቸው ሲሆኑ ነው፡፡ በተለይ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ በማፋጀት አገር ለማፍረስ ያሴሩት፣ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን በአግባቡ ባለመወጣቱ እንደሆነ ብዙ ተብሎበታል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ሕዝብ በነፃነት የተሻለውን ካልተሻሉት የሚያማርጠው፣ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ በሥርዓት መምራትና መመራት ሲለመድ ብቻ ነው፡፡ ጽንፈኞች ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት አንድ ላይ ያልኖሩ ይመስል፣ ‹‹ዲቃላ፣ ነፍጠኛ፣ ሰፋሪ፣ ወዘተ›› የሚባሉ ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርዱ አግላይና ለጅምላ ጭፍጨፋ የሚያመቻቹ ቃላትን በመጠቀም፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን በደም ለማጨቅየት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አፀያፊ ድርጊት ኢትዮጵያን መቀመቅ የሚከት እንጂ አንድ ጋት ወደፊት አያራምዳትም፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በመከፋፈልና በማጋጨት የተጠመዱ የፖለቲካ ሰዎችም ሆኑ ስብስቦች፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን አያቆሽሹት፡፡ በሰላማዊነት ሽፋን ማታለላቸውን ያቁሙ፡፡ ዓባይን እየገራ ያለው ትውልድ አይታገሳቸውም፡፡

 ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች፣ ‹‹አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት፣ ይህች አገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት›› ብለው በታላቅ መስዋዕትነት ያስከበሩዋትን አገር፣ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ለጠላት ያጎበደዱ ምንደኛ ፖለቲከኞች እንዲቀልዱባት መፍቀድ አይገባም፡፡ በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚፈልግ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ከሕገወጥነት ይፁም፡፡ ለፖለቲካ ምኅዳሩ ማበብና መጎምራት አስተዋፅኦ ሳያበረክት፣ ከማንም ምንም ዓይነት ውጤት አይጠብቅ፡፡ የበኩልን አስተዋፅኦ ሳያበረክቱ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፊና አሳታፊ እንዲሆን መጠበቅ ጊዜው ያለፈበት ፋሽን ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት የሚያፎካክረው፣ ሁሉም የሚፈለግባቸውን ሲያበረክቱ ብቻ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ መብት ከመጠየቅ በፊት ግዴታን መወጣት መቅደም አለበት፡፡ ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡትን ዳር ሆኖ በማሽሟጠጥና በአሉባልታ አላሠራ ማለት ነውር ስለሆነ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሕዝብን ማጭበርበር አይቻልም፡፡ ራዕይ አልባ የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች በሕዝብ ስም መነገድ ያቁሙ፡፡ አገር በማመስና ሕዝብን በማተራመስ ሥልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ፣ በሕዝብ ዕይታ ውስጥ ስለሆነ ከአውዳሚ ተግባራት ይቆጠቡ፡፡ ዓባይን እየገራ ያለውና የህዳሴ ግደቡን እያቆረ ያለው ትውልድ የጽንፈኞች መቀለጃ አልሆንም እያለ ነው!  

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...