Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሥራ ፈጠራ ኮሚሽን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራዎች ሊታጡ እንደሚችሉ ሥጋቱን...

የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራዎች ሊታጡ እንደሚችሉ ሥጋቱን ገለጸ

ቀን:

የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከ330 ሺሕ በላይ ሥራዎችን እንዳሳጣ በመጪው ዓመትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎች አደጋ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ሥጋቱን አስታወቀ፡፡

የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤፍሬም ተክሌ (ዶ/ር) ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዕቅድ በላይ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ሥራዎች ሊፈጠሩ ችለው ነበር፡፡ ሆኖም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከ330 ሺሕ በላይ ሥራዎች መክሰማቸው እንደተረጋገጠ ኮሚሽነሩ ይፋ አድርገዋል፡፡

የከሰሙት ሥራዎች ከዚህም በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀደም ሲል በኮሚሽኑ የተደረጉ ቅድመ ትንበያዎች ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ኮሮና በኢትዮጵያ የሥራ ዕድልና የነፍስ ወከፍ ገቢ ላይ ሊያስከትል የሚችላቸው ተግዳሮቶችና መፍትሔ የፖሊሲ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ከወራት በፊት ባወጣው ትንበያ በመካከለኛ ደረጃ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚገመቱ የሥራ ዕድሎች ሊታጡ እንደሚችሉ፣ 1.9 ሚሊዮን ውሎ ገብና በራሳቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ በመሥራት የሚተዳደሩ ዜጎች እስከ 50 በመቶ ገቢያቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ትንበያ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኮሮና ለሦስት ወራት ቢቆይ በሚለው መነሻ ግምት መሠረት በከተሞች የሚገኙ 1.9 ሚሊዮን ውሎ ገብ ሥራ የሚሠሩ ዜጎች ከ265 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ ለስድስት ወራት ቢቆይ ከ543 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢያቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ የኮሚሽኑ ትንታኔ አመላክቶ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከመቀጠር በሚገኝ ገቢ የሚተዳደሩ ከ310 ሺሕ እስከ 476 ሺሕ የሚገመቱ ዜጎች፣ በሥራ ዋስትና ሥጋት ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር፡፡

በኮሚሽኑ ትንታኔ መሠረት ሲታይ ዜጎች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ በሚለው መመርያ መነሻነት በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽንና በአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ከሚሠሩ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ በሦስት ወራት ውስጥ ሊታጡ ወይም ሊከስሙ እንደሚችሉ ሥጋት ያሳደሩ 1.41 ሚሊዮን የሥራ መስኮች ነበሩ፡፡ በማኑፋክቸሪንግና በኮንስትራክሽን ዘርፎች ብቻ በስድስት ወራት በወረርሽኙ ተፅዕኖ እስከ 1.76 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ሊታጡ የሚችሉባቸው ሥጋቶች ይፋ ተደርገው ነበር፡፡

እንዲህ ያሉ ትንታኔዎች ሲቀርቡ ቢቆዩም፣ እስካሁን በተጨባጭ ማረጋገጥ የተቻለው ግን ከ330 ሺሕ በላይ ሥራዎች መጥፋታቸው ነው፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ እነዚህ የሥራ ዕድሎች ዘንድሮ ተፈጥረው ከሰባት ወራት ቆይታ በኋላ ለመክሰም የተገደዱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ 14 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመው ኮሚሽኑ፣ በአሁኑ ወቅት ለሥራ ብቁ ሆነው ሥራ በመፈለግ ላይ ለሚገኙ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች፣ ሥራ በመፈለግ ላይ ባይሆኑም ለሥራ ብቁ የሆኑ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች፣ በየዓመቱ ወደ ሥራ ገበያ የሚቀላቀሉ ሁለት ሚሊዮን ዜጎችን ጨምሮ በጠቅላላው እስከ 14 ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራ ፈላጊዎችን ለማዳረስ አቅዷል፡፡ በአሥር ዓመታት ውስጥም ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር ውጥን አለ፡፡

ይህ ይባል እንጂ እስካሁን የተፈጠሩት ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ምንም እንኳ የታሰበውን አፈጻጸም ለማሳካት ቢያስችሉም፣ ከሚያስገኙት ገቢ መጠንና  ከሚሰጡት የሥራ ዋስትና አኳያ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው የሥራ ፈጠራ ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

መንግሥት በሥጋት ቀለበት ውስጥ የሚገኙ የሥራ ዕድሎችን እንዳይከስሙ ለማድረግ ከአገር ውስጥና ከውጭ አጋሮቹ ጋር እየሠራ ነው ያሉት ኤፍሬም (ዶ/ር)፣ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ ሊውል የሚችል 384 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ካገኘው የ28 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ውስጥ በ12 ሴቶች ተመሥርተው ለሚተዳደሩ የሥራ ዘርፎች ድጋፍ በማድረግ ሠራተኞቻቸው ሳይበተኑ፣ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከል የሚያግዙ ምርቶችን በማምረት ለገበያ እንዲያቀርቡ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሠሩ 85 ሺሕ ሠራተኞች እንዳይበተኑ፣ የወጪ መጋራት ድጋፍ ለአምራች ኩባንያዎች በማቅረብ ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑም ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል፡፡

በድርቅና በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉትን ጨምሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ለገቡ 30 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ አቅርቦት ድጋፍ ለማድረግ፣ እንዲሁም የንግድ ተቋማት ከገጠማቸው ተፅዕኖ ተላቀው መደበኛ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለመደገፍ፣ መንግሥት 4.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲሰጡት ለዓለም መንግሥታት ጥሪ ማቅረቡ ተጠቁሟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...