Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ መሥፈርቶችን አሟልተው የተመዘገቡ አዳዲስ ድርጀቶች 829 ብቻ መሆናቸው ተገለጸ

የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ መሥፈርቶችን አሟልተው የተመዘገቡ አዳዲስ ድርጀቶች 829 ብቻ መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

ሲቪል ማኅበራቱ ያቀረቡት የታክስ ቅነሳ ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም

በሔለን ተስፋዬ

ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሥፈርቶችን በማሟላት የተመዘገቡ አዳዲስ ድርጅቶች 829 ብቻ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ አዋጁ በሥራ ላይ ከዋሉበት ከመጋቢት ወር 2011 እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 1,043 አዳዲስ ድርጅቶች አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ በአዋጁ የተቀመጡ መሥፈርቶችን አሟልተው የተገኙት ግን 829 ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

ቀደም ብሎ በነበረው አዋጅ ቁጥር 621/2011 ተመዝግበው የነበሩ ድርጅቶች ቁጥር 3,512 እንደነበሩ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ክልከላዎችና ዕገዳዎች የበዛበትን የቀድሞ አዋጅ በማሻሻል በፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ድንጋጌ መሠረት በተደረገ ዳግም የነባር ድርጅቶች ምዝገባ ግን የተመዘገቡት 1,789 መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡  ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ 1,464 የአገር ውስጥ ሲሆኑ፣ 325 ደግሞ የውጭ ድርጀቶች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

በአዲሱ አዋጅ መሠረት ነባር ድርጅቶች በድጋሚ ካልተመዘገቡ እንደፈረሱ እንደሚቆጠሩ፣ ንብረቶቻቸው ተቆጥረውና ተጣርተው ተመሳሳይ ፕሮጀክት ላላቸው ማኅበራት እንደሚተላለፉ ገልጸዋል፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም አዲስ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለማጸደቅ ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መመራቱን፣ በዚህም ነባር ድርጅቶች በቅጣት እንደ አዲስ እንዲመዘገቡ የሚል አማራጭ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አዋጅ 1113/2011 በሰጣቸው መብት መሠረት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ በመሳተፍ ፕሮጀክቶቻቸውን ብቻ መደገፍ እንደሚችሉ መደንገጉን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

አዋጁ ሲቪል ማኅበራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአስመጪና ላኪ ሥራዎች ላይ መሳተፍ እንደሚችሉና በእነዚህ ገቢ ማስገኛ ዘርፎች ሲሰማሩም፣ ለተሰማሩባቸው ዘርፎች ሕግና መመርያ ይገዛሉ፡፡

የገቢ ማስገኛ ሥራው ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ብቻ የሚውል መሆኑን በመጥቀስ፣ ሲቪል ማኅበራት የሚያነሱት የታክስ ቅነሳና ሌሎች ጥያቄዎች እስካሁን ባለው አካሄድ እንዳልተፈቀደ አቶ ጂማ ተናግረዋል፡፡

ከገቢ ማስገኛ ሥራዎች የሚገኝ ትርፍ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለአባላቱ ጥቅም መዋል እንደሌለበትና ይህን የሚያደርጉ ድርጅቶች በሕግ እንደሚጠየቁም አስታውቀዋል፡፡

በንግድና ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ድርጅቶች ሁለት ተቆጣጣሪ እንደሚኖርባቸው፣ ታክስና ሌሎች የንግድ ሕጎችን በተመለከተ የተሰማሩበት ዘርፍ፣ እንዲሁም የሚያገኙትን ትርፍ ለፕሮጀክት ማዋላቸውን ደግሞ ኤጀንሲው እንደሚቆጣጠር አስረድተዋል፡፡

ድርጅቶቹ ለገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች የተለየ የባንክ ሒሳብ መክፈት፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ሥራውም የተለየ የሒሳብ መዝገብ መያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በንግድ ፈቃድና የምዝገባ ሕጎች መሠረትም አዲስ የንግድ ድርጅትና ኩባንያዎችን  ማቋቋም፣ ከነባር የንግድ ድርጅቶች ላይ አክሲዮን መግዛትና የንግድ ሥራን በብቸኛ ባለቤትነት በመያዝ ገቢ በማግኘት ለፕሮጀክት ዓላማ ብቻ ማዋል እንደሚችሉ አቶ ጂማ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...