Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየክረምት ጎርፍን በሼጣን ማዱአ

የክረምት ጎርፍን በሼጣን ማዱአ

ቀን:

የክረምት ወቅት ሲመጣ ለጎርፍ ለደራሽ ውኃ የሚጋለጡ አካባቢዎች የአደጋ ሥጋት መሆናቸው አይቀርም፡፡ የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች አኗኗራቸው ዕለት ተዕለት ከሥጋት ያልተፋታ ነው፡፡ ከበልግ ጊዜ ጀምሮ የሚኖረው የክረምት ጉዞ ኅብረተሰቡ አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲደርግ መንግሥታዊ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች አካላት በየጊዜው ማሳሰቢያ እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች ከነባር ትውፊታቸው ከልማደ ባህላቸው የሚመነጭ በክረምት ወቅት ከሚከሰት የጎርፍ አደጋ ራሳቸውን የሚጠብቁበት አሠራር አላቸው፡፡ ከነዚህም መካከል በትግራይ ሰሜናዊ ምሥራቅ የሚገኙ የኢሮብ ማኅበረሰቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 928 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ድውሃን ከተማ ማዕከሉ የሆነው የኢሮብ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ እጅግ ተራራማና ገደላማ ነው፡፡ አካባቢው በአሲምባ፣ እንዳልገዳና ሌሎች በርካታ ተራሮች የተከበበ ነው፡፡ ኢሮቦች በተራሮች መካከል በሚገኝ ሸለቆ ውስጥ አስደናቂ የእርከን ሥራ በማከናወን በክረምት ወቅት ከሚከሰት ጎርፍ አካባቢያቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ይህንን የጥበቃ ተግባራቸውን በተመለከተ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከሌሎች የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጋር ጥናታዊ ኢንቬንቶሪና  ምዝገባ በማድረግ ለኅትመት አብቅቷል፡፡

- Advertisement -

የቅርስ ባለሙያዎቹ እነ ቀለሟ መኰንን፣ ብርሃኔ የሺዋስ ባዘጋጁት መድበል እንደተገለጸው፣ ኢሮቦች በሚያከናውኑት የእርከን ሥራ ክረምቱ ከሚያስከትለው ጎርፍ አካባቢያቸውን በመጠበቅ የተለያዩ አትክልትን ለማብቀል ምቹ የሚሆን ከደላል የተገኘ መሬትም ያገኛሉ፡፡ በኢሮቦች ዘንድ በሸለቆ ውስጥ እርከን የሚሠራው ከዝቅተኛ ቦታ ወደ ከፍተኛ ቦታ ነው፡፡ መጀመርያ በሸለቆው ግርጌ አንድ እርከን ይሠራና እሱ ሲፀና ከፍ ብሎ ሌላ ይሠራል፡፡ በየዓመቱም ይህ ሥራ ይቀጥላል፡፡ እርከኑ የሚሠራው ከድንጋይ ሲሆን የታወቁ ሁለት ዓይነት የእርከን አሠራሮችን ይጠቀማሉ፡፡

የመጀመርያው ቀላል የእርከን ዓይነት ሲሆን ጠፍጣፋ ድንጋዮችን አንዱን በአንዱ ላይ በመደራረብ የሚሠራ ነው፡፡ ይኸኛው የእርከን ዓይነት ቀላል የጎርፍ መጠን በሚኖርባቸው ቦታዎች ላይ የሚማዘወተር ነው፡፡ ሁለተኛው የእርከን ዓይነት ሼጣን ማዱአ (የሰይጣን ማሰሪያ) ይባላል፡፡ ይኸኛው ሹልና ረዣዥም ድንጋዮችን በቁም እርስ በርሱ በማጎራረስ የሚሠራ የድንጋይ ካብ ሲሆን እጅግ ጠንካራና ከፍተኛ የጎርፍ መጠን ቢመጣ የማይናድ የእርከን ዓይነት ነው፡፡ ሁለቱንም ዓይነት እርከን ሲሠሩ ድንጋዮቹን እርስ በርሱ ለማያያዝ ምንም ዓይነት ማጣበቂያ አይገለገሉም፡፡

የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራ በኢሮብ ብሔረሰብ ዘንድ ረዥም ታሪክ ያለውና ከኅብረተሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋርም የተዋሃደ ነው፡፡ በአካባቢው ምንም ዓይነት ወንዝ ስለሌለ ዶራ ደራኡ (የውኃ ማቆሪያ ጉድጓድ) በማዘጋጀት በክረምት ወቅት የሚገኘው የዝናብ ውኃ ይታቆራል፡፡ ቀጣዩ ክረምት እስኪመጣም ለከብቶችና ፍየሎች በመጠጥ ውኃነት ያገለግላል፡፡ በደራኡ አካባቢ ቆሻሻ የጣለ ወይም በደራኡ ላይ ማንኛውንም ዓይነት አላግባብ የሆነ ተግባር የፈጸመ፣ አንድ ፍየል ይቀጣና ፍየሉ ታርዶ የተበላሸውን ደራኡ በማስተካከል  ላይ ለሚሠሩ ሰዎች እንዲቀርብ የሚያደርጉበት ማኅበራዊ ሥርዓት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በደራኡ ወይም በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርስን ሰው ሽማግሌዎች ተሰብስበው ያወግዙታል/ይረግሙታል፡፡ ውግዘት በኅብረተሰቡ ዘንድ እጅግ ስለሚከበርና ስለሚፈራ ሁሉም ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡

ዳልዳል በክረምት ከሚከሰት ጎርፍ አካባቢያቸውን የሚጠብቅ በመሆኑ ቅርሱ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አለው፡፡ በዳልዳሉ ራስ ላይ የተለያዩ አትክልትን ለማብቀል የሚሆን ከል የተሠራ መሬትም ለማግኘት ያስችላል፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የሚመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የእርከን ሥራ ከድሮው በበለጠ በስፋት በመከወን ላይ እንደሚገኝ አስረጂዎች ገልጸዋል፡፡

የማይዳሰሱ ቅርሶች ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፊያ ዋነኛ ክዋኔ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የዳልዳል አሠራርን እንዲከውኑ በማበረታታት፣ ወጣቶችም በዕድሜ ከፍ ያሉ የብሔረሰቡ አባላት የዳልዳል አሠራርን ይበልጥ እንዲያውቁት በማድረግ የቅርሱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አሪ አበት – ባህላዊ ቤት

የኢሮቦች ቤት አሠራር የኅብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤና የአካባቢውን ሥነ ተፈጥሮ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ በተለይ ሦስት ዓይነት የቤት አሠራሮች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡

የመጀመርያውና አብዛኛው ሰው የሚያዘወትረው የቤት ዓይነት ዓረ ይባላል፡፡ ዓረን ለመሥራት መጀመርያ መሬቱ ተጠርጎ ይፀዳል፡፡ ከዚያም የቤቱ ስፋት በገመድ ተለክቶ መሠረቱ ይቆፈርና በድንጋይ ይገነባል፡፡ ለግንባታው ምንም ዓይነት ሲሚንቶም ሆነ ጭቃን የመሳሰሉ ማጣበቂያዎች ጥቅም ላይ አይውሉም፡፡ ድንጋዮቹን እርስ በርስ በማስተሳሰር ብቻ ይገነባል፡፡ በመቀጠል በቤቱ መሀል መሀል ላይ አሚዳዎች (ቋሚ ተሸካሚ እንጨቶች) ይተከላሉ፡፡ በግድግዳውና በአሚዳዎቹ ራስ ላይ ጥቂት መረባቶዎች (ወፈር ያለ አግዳሚ እንጨት) እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡ በመረባቶዎች ላይ ደግሞ ከመረባቶ ቀጠን ያሉ ሳርወ (ርብራብ) ተጠጋግቶ ይደረደራል፡፡ ከሳርወ ላይ ደግሞ ከሳርወ ቀጠን ያሉ ሞሒፅ (ቀጫጭን ርብራቦች) ይረበረባል፡፡ ከሞሒፆቹ ላይ ደረሰ (ሳርና ቅጠሎች) ይጎዘጎዛል፡፡ በመጨረሻም ቡልጉዓ (አፈር) ይደረግበታል፡፡ ለቤቱም ከፊትና ኋላ እፈይ (በር) ይበጅለታል፡፡

የቤቱ የውስጥ ገጽታ ለሰውና ለክብት በሚል ሁለት ቦታ ይከፈላል፡፡ ለከብቶችና ፍየሎች ማደሪያ የሚሆነው ቦታ ዳጌ ይባላል፡፡ ሕድሞ ደግሞ የሰው መኝታ የሚሆንበት ቦታ ሆኖ  የሚተኙበትም ሴቶችና ልጆች ናቸው፡፡ ውድና ጠቃሚ የሚባሉ ዕቃዎች ይቀመጡበታል፡፡ እንግዳም ሲመጣ የሚተኛው ሕድሞ ውስጥ ነው፡፡ የቤቱ አባወራ የሚያርፍበትና የሚተኛበት ጋበላ ወይም ከእንጨት ርብራቦች በተሠራ ኮርኒስ መሰል ጣሪያ የተከለለ ቦታ ውስጥ በሚገኝ መደብ ላይ ነው፡፡ ከቤቱ የውስጥ ግድግዳ ጋር ተያይዞ ለሰዎች መቀመጫነት ዳንደስ (መደብ) ይሠራል፡፡ ከዓረ ጎን አነስ አነስ ያሉ ዳጌ (የከብት ቤት) እና ዲለላ ዳጌ ዲምባ (የንብ ቀፎ ማስቀመጫ) ቤቶችም አንድ ላይ ይሠራሉ፡፡

ሁለተኛው የቤት ዓይነት ደግሞ አዶጎይታ ይባላል፡፡ ይህ ሙሉ በሙሉ ከእንጨት የሚሠራ የቤት ዓይነት ነው፡፡ ሦስት አሚዳዎች (ባለባላ እንጨቶች) ይዘጋጁና ሦስት ቦታ በመትከል የአሚዳዎቹን ራስ አንድ ላይ በማገናኘት ይታሰራል፡፡ በሦስቱ አሚዳዎች መካከል ያሉት ክፍት ቦታዎች በሁጋዮ (ቋሚ ርብራብ እንጨቶች) ይሸፈናል፡፡ በመጨረሻም አንድ እፈይ (በር) ይበጅለታል፡፡

ደረባ ደግሞ ሦስተኛው የቤት ዓይነት ነው፡፡ ሁለቱ ባለ ባላ ቋሚ እንጨቶች ይተከሉና በባላዎቹ ላይ አንድ አግዳሚ እንጨት እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡ በመቀጠልም ከጎንና ጎን ሌሎች እንጨቶችን አግዳሚውን አስደግፎ በመደርደር (በመረብረብ) የቤት ቅርፅ እንዲይዝ ይደረጋል፡፡

በቅርሳዊው ምዝገባ እንደተገለጸው፣ የባህላዊ ቤት ዋና ዋና መገለጫ ቁሳቁሶች ድንጋይና እንጨት፣ ሳርና አፈር ሲሆኑ ውስጠኛው ክፍል ደግሞ በተለያዩ የኢሮቦች ባህላዊ የቤት ዕቃዎች ያጌጠ ነው፡፡ ባህላዊ ቤቶች ኅብረተሰቡ ለብዙ ዘመናት በመኖርያነት ሲጠቀምበት ከመኖሩም ባለፈ የአካባውን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ የሚያሳይ ቋሚ የታሪክ ማስረጃ መሆኑ ይወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ባህላዊ ቤቶች አሁንም እያገለገሉ ቢሆንም ዘመኑን ተከትለው የመጡ የቤት አሠራሮች ጥላቸውን ማሳረፋቸው አልቀረም፡፡ ጣሪያቸው በቆርቆሮ የተሸፈኑ ዘመናዊ ቤቶች ነባሩን አሠራር በመተካት ላይ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...