Thursday, June 20, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስልክ ተደወለላቸው]

 • ማን ልበል?
 • አያውቁኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ለምን ደወልክ?
 • ብሶቴን ላሰማ ነዋ፡፡
 • ጤነኛ ነህ ሰውዬ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ብዙ ሥራ ያለኝ ሰው ነኝ እኮ፡፡
 • ነው ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ማለት ነው?
 • ሥራ ላይ ብትሆኑማ አገር እንደዚህ አትሆንም ነበር፡፡
 • ምን አልክ?
 • የሕግ የበላይነት አስፍኑ ተብላችሁ ስትለመኑ ነበር፡፡
 • እኛ እኮ ሆነ ሰፊ እንሁን ብለን ነው፡፡
 • ታዲያ ሆደ ሰፊ ማለት ወንጀለኞችን ነፃ መተው አይደለም እኮ?
 • እኔ እኮ ግራ ነው የሚገባኝ፡፡
 • ምኑ ነው ግራ የገባዎት?
 • ዕርምጃ ሲወሰድ መንግሥት ጨቋኝ ነው ይባላል፡፡
 • እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ሕዝቡ እኮ እየጠየቀ ያለው መንግሥት አምባገነንና ጨቋኝ ይሁን ብሎ አይደለም፡፡
 • እ…
 • የሕዝቡ ጥያቄ የሕግ የበላይነት ይከበር የሚል ነው፡፡
 • እሱማ ገብቶኛል፡፡
 • ታዲያ ከገባዎት አገሪቱ ውስጥ ምንድነው የሚካሄደው?
 • ምን ተካሄደ?
 • እኔ ክፍለ ሀገር ነው የምኖረው፡፡
 • እሺ፡፡
 • የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ሰዎች ተደራጅተው ቤቴ ሊያጠቁኝ መጡ፡፡
 • እሺ፡፡
 • እኔም ወደ ላይ ስተኩስ ፈርተው ተበተኑ፡፡
 • ከዚያስ?
 • ከዚያማ ድጋሚ ተደራጅተው መጡብኝ፡፡
 • ድጋሚ?
 • እኔም ወደ ላይ ተኩሼ ድጋሚ በተንኳቸው፡፡
 • ፖሊሶች አትጠራም እንዴ?
 • የሚገርምዎት እሱ አይደል እንዴ?
 • ምኑ?
 • ለፖሊሶቹ ስነግራቸው የወሰዱት ዕርምጃ ነዋ፡፡
 • ምን አደረጉ?
 • እኛ እንጠብቅሃለን ብለው ከእነ መሣሪያዬ አሰሩኛ፡፡
 • ጭራሽ?
 • ምን እሱ ብቻ?
 • ምን ተፈጠረ?
 • ከእስር ቤት ስፈታ ያገኘሁት አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡
 • ምን አገኘህ?
 • ቤቴ ተቃጥሎ፡፡
 • የፈጣሪ ያለህ?
 • ታዲያ ይኼን ምን ይሉታል?
 • እ…
 • ተስፋ ቆርጫለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አይዞህ ወንድሜ፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አለ ብለው ነው?
 • ይገባኛል፡፡
 • ለማንኛውም እንደ ማኅበረሰብ አንድ ነገር ሆነናል፡፡
 • ምን?
 • ዘቅጠናል!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]

 • ወዴት እያመራን ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ይኼ አገር አስጠልቶኛል፡፡
 • ተው እንጂ ወዳጄ፡፡
 • ምንድነው ተስፋችን?
 • እንደዚህ አትሁን እንጂ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ባለሀብቱ የሚታማው ኢንቨስት አያደርግም ተብሎ ነበር፡፡
 • እሱማ ልክ ነህ፡፡
 • አሁን እኮ ኢንቨስት ያደረገው ሀብት ይኸው ወደመበት፡፡
 • ምን ይደረግ?
 • ይኼ ደግሞ በጣም ያሳምማል፡፡
 • ምኑ?
 • መንግሥት ለምን ሥራውን አይሠራም?
 • ምን ይሥራ?
 • የሕዝቡን ደኅንነት ይጠብቅ፡፡
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር የተፈጸመው ጥፋት እኮ የታቀደበት ነው፡፡
 • እኛም እየመረመርነው ነው፡፡
 • የእኔም ንብረት ሲቃጠል የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋ ደውዬ ነበር፡፡
 • ምን አሉህ?
 • ስብሰባ ላይ ነን፡፡
 • በጣም ያሳዝናል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይህች አገር እኮ ደሃ ናት፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • እኛ በአቅማችን የምንንቀሳቀሰው እኮ ድህነትን ለመቀነስ ነው፡፡
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • ታዲያ በሌለን ሀብት ይኼ ሁሉ ሲወድም ምን ይባላል?
 • በጣም ያሳዝናል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ግን መንግሥት መሆን አለበት፡፡
 • እንዴት?
 • የመንግሥት ዋና ሥራ የሚያጠፋን መቅጣትና የሚሠራን ማበረታታት ነው፡፡
 • እውነት ነው፡፡
 • ታዲያ መቼ ነው የምናየው?
 • ምን?
 • የሚያጠፉ ሲቀጡ ነዋ፡፡
 • ይኼው ጀምረናል እኮ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ተኳሾቹ ላይ ብቻ ሳይሆን አስተኳሾቹ ላይም መተኮር አለበት፡፡
 • እ. . .
 • አስተኳሾቹ ላይ ዕርምጃ ካልተወሰደ ተኳሽማ ይቀያየራል፡፡
 • እውነትህን ነው፡፡
 • አሁን እኮ ምንም መተማመኛ የለም፡፡
 • የምን መተማመኛ?
 • ድጋሚ ሁከት እንደማይኖር ነዋ፡፡
 • ከዚህ በኋላማ አይታሰብም፡፡
 • አስተኳሾቹ መቼ ተነኩ?
 • በቅርቡ ጠብቅ፡፡
 • ምን?
 • አስተኳሾቹ…
 • እ…
 • ይወረወራሉ፡፡
 • የት?
 • ዘብጥያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • በአገራችን እየሆነ ያለው ነገር ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ሰው ተጨካክኗል፡፡
 • አሁን ነው እንዴ ያወቅከው?
 • ዞር ዞር ብዬ አይቼ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑን ነው ያየኸው?
 • የደረሰውን ጉዳት ነዋ፡፡
 • መጀመርያ አታውቀውም ነበር፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው?
 • ሁሉን ነገር እናውቃለን እባክህ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛም ውስጥ ችግር አለ እኮ፡፡
 • የምን ችግር?
 • ከውስጣችን የሚያስተኩሱ ነበሩ፡፡
 • ከእኛ ውስጥ?
 • እህሳ፡፡
 • እንደዚህማ ሊቀለድብን አይገባም፡፡
 • ግን ተቀልዶብናል፡፡
 • እነዚያ ሰዎች ግን እጃቸው ረዥም ነው ማለት ነው?
 • እነ ማን?
 • ያኮረፉት ናቸዋ፡፡
 • እጃቸው የረዘመው እኮ እዚህ የሚተባበሯቸው ስላሉ ነው፡፡
 • እነሱ የሚያስወሩት ወሬ እንዳይሆን ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ ሁሉ ጥፋት ሲደርስ መንግሥት የት ነበር?
 • እኔ እንጃ፡፡
 • ራስህን ጠይቀሃል?
 • እኔማ ቤቴ ነበርኩ፡፡
 • ምን እያደረግክ?
 • ምነው ጥያቄ አበዙብኝ?
 • ምነው ፈራህ አንተ?
 • ጠረጠሩኝ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ያልጠረጠረ ተመነጠረ ሲባል አልሰማህም?
 • እኔ እንኳን ንፁህ ሰው ነኝ፡፡
 • እሱ በኋላ የሚጣራ ነገር ነው፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው?
 • ብዙ ማስረጃ እጃችን ላይ አለ፡፡
 • የምን ማስረጃ?
 • እሱን በኋላ ታውቀዋለህ፡፡
 • እየተመረመርኩ ነው እንዴ?
 • ንፁህ ከሆንክ ምን አስፈራህ?
 • ምንም፣ ግን ለምን ተጠረርኩ ብዬ ነው?
 • ነገርኩህ እኮ ከውስጣችንም ሆነው የሚያስተኩሱ አሉ፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ ሁሉም ነገር በቅርቡ ይጣራል፡፡
 • እኔ ንፁህ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አልመሰለኝም፡፡
 • ምን?
 • ለማንኛውም እየመጡልህ ነው፡፡
 • እነ ማን?
 • ፖሊሶች!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምን እያደረጋችሁ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ልታፈርሱት የነበረውን አገር እያረጋጋን፡፡
 • ከእኛ ላይ መቼ ነው የምትወርዱት?
 • ከእናንተ ውጪ ማን ይኼን ሴራ ያስባል ብዬ ነዋ፡፡
 • ራሳችሁን መቼ አጠራችሁ?
 • እሱ ላይ እየሠራን ነው፡፡
 • ታዲያ እሱን ሳታጠሩ ለምን እጃችሁን ወደ እኛ ትጠቁማላችሁ?
 • አስተኳሾቹ እናንተ ናችኋ፡፡
 • ኧረ እኛ በራሳችን ሥራ ላይ ተጠምደናል፡፡
 • የምን ሥራ?
 • ምርጫው ላይ ነዋ፡፡
 • ጤነኞች ናችሁ ግን አይደል?
 • ምነው ይጠራጠራሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝቡ እኮ ሰልችቶታል፡፡
 • ምኑ?
 • የእናንተ ውሸትና ፕሮፓጋንዳ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡማ ከእኛ ጋር እንደሆነ እንዳይረሱት፡፡
 • ሕዝቡ ዝም ያላችሁ እኮ ቢቃወማችሁ ስለምትፈጁት ነው፡፡
 • እኛ እዚህ ተደማጭና ተመራጭ ነን፡፡
 • ለማንኛውም በቅርቡ ጠብቁ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እንመጣላችኋለን፡፡
 • ልትጠይቁን ነው?
 • አታስቀኝ እስቲ፡፡
 • የምፈራው መጥታችሁ እዚሁ እንዳትቀሩ ነው፡፡
 • ለማንኛውም የምንመጣው ለአንድ ነገር ነው፡፡
 • ለምን?
 • ልንለቃቅማችሁ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...