Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሮናን አስከፊ ገጽታ ያሳየው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምልከታ አሳሳቢ እውነታዎችን ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ዘንድሮ ከተፈጠሩ ሦስት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎች ከ330 ሺሕ በላይ ከስመዋል ይላል

ከኮሮና ወረርሽኝና ከህዳሴ ግድቡ ጋር የተያያዙ ዳጎስ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር አባላት፣ በወረርሽኙ ምክንያት በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ አሳሳቢና አስደንጋጭ እውነታዎችን ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተከሰቱ የሥራ አጥነት ችግሮችን ባሳዩበት አዲስ ትንታኔ፣ ከግንባታ እስከ ትራንስፖርትና መሰል በሆኑ ወሳኝ የአገልግሎት መስኮች ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግሮች መታየታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎቹ እንዳመለከቱት፣ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱ ይፋ ከተደረገበት ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት በነበረው ጊዜ ውስጥ ብቻ በጥናት ከተካተቱ 3,249 ቤተሰቦች መካከል 82.4 በመቶ የቤተሰብ አባላት ሥራ ለማጣት ተገደዋል፡፡ እነዚህ ቤተሰቦች በወረርሽኙ ምክንያት ለሥራ አጥነት የተዳረጉ መሆናቸው፣ የተቀሩት 17.4 በመቶ ከወረርሽኙ ጋር ባልተገናኙ ችግሮች ሳቢያ ሥራ ለማጣት የተገደዱ መሆናቸው ተመልክተዋል፡፡

ከእርሻ ሥራ ውጪ በሆኑ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ከተሰማሩ ቤተሰቦች መካከል 42 በመቶው በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ እንደነበሩ፣ ከተቀሩት ውስጥ 11 በመቶው በግብርና፣ 10.4 በመቶው በሕዝብ አስተዳደር ሥራዎች፣ በትራንስፖርት መስክ 8.4 በመቶና በሌሎችም በርካታ የሥራ መስኮች ውስጥ ተሰማርተው የሚተዳደሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ሥራቸውን ካጡት ከ82 በመቶዎቹ መካከል የሚተዳደሩት ገቢ ለማጣት የተገደዱትም 58 በመቶ እንደሆኑ፣ በተለይም ሥራቸውን ካጡ ወዲህ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው ያስታወቁ 28 በመቶ ያህል ቤሰተቦች መሆናቸውን አጥኚዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ በሚላክላቸው ገንዘብ ይተዳደሩ ከነበሩ ቤተሰቦች መካከል 39 በመቶ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የሚላክላቸው ገንዘብ እንደተቋረጠባቸው ተመልክቷል፡፡  

የዓለም ባንክን የጥናት መነሻዎችን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች የተሠራው ትንታኔ፣ ከ3,249 በላይ ቤሰተቦችን ያካተተ ነው፡፡ 70 በመቶ የከተማ፣ 30 በመቶው የገጠር ነዋሪዎች የሰጡትን ምላሽ የተንተራሰ ዕይታ የቀረበበት ነው፡፡ የባለሙያዎቹ ጥናት በኢኮኖሚ ዘርፍ ረገድ የግንባታ፣ የሆቴልና ሬስቶራንት፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የግል አገልግሎቶች ላይ የተሰማሩ ሰዎች በበሽታው ምክንያት ከሥራ ውጪ ለመሆን መገደዳቸውን አመላክተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በግንባታው መስክ 69 በመቶ የሥራ ዕድሎች መታጣታቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡ በሆቴልና ሬስቶራንት መስክ 66 በመቶ ሥራዎች ሲታጡ፣ በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ሥራ መስክ 62 በመቶ ሥራዎችና ሠራተኞች መለያየታቸውን አመላክተዋል፡፡ በኢንዱስትሪ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ መስክ 42 በመቶ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት 37 በመቶ፣ እንዲሁም የግል አገልግሎት የሚሰጥባቸው ልዩ ልዩ የሥራ መስኮች 31 በመቶ መክሰማቸው ተመልክቷል፡፡ 

ምንም እንኳ ጥናቱ የተካሄደው ቅድመ ክረምት ከመሆኑና ከበሽታው መከሰት ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር በነበረው ጊዜ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በሚያሳይ መንገድ ቢሆንም፣ ከዚህም የከፋ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል አጥኚዎቹ አመላክተዋል፡፡

መንግሥት በበኩሉ በዚህ ዓመት ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ አስታውቋል፡፡ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳው በ2012 በጀት ዓመት ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ ከዕቅድ በላይ የተሳካበትና መቶ በመቶ በላይ ውጤት የተገኘበት ወቅት ቢሆንም፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ግን በበጀት ዓመቱ ከተፈጠሩ ሥራዎች መካከል ከ330 ሺሕ በላይ ሥራዎች መክሰማቸውን የኮሚሽኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ፖለቲካዊ ቀውስ የፈጠረው አደጋ ሲታከልበት ከዚህም በላይ የሥራ ዕድል ሊታጣ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢኮኖሚክስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፣ ከማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ከግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያው ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) የተጣመሩበት፣ ደግዬ ጎሹና መንግሥቱ ከተማ የተባሉ የሙያ አጋሮቻቸው የተሳተፉበት ይህ ጥናት፣ በከተማም ሆነ በገጠሩ ነዋሪ ዘንድ መሠረታዊ የጤናና ንፅህና አጠባበቅ መመርያዎች ላይ ግንዛቤ መስረፁን የሚያመላክቱ አኃዞችም የተካተቱበት ነው፡፡

እጅን በሳሙና አዘውትሮ መታጠብ፣ ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች አለመገኘትና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን መቀነስን ጨምሮ ሌሎች ስምንት ያህል የመንግሥት ዕርምጃዎች ላይ የሕዝቡን ግንዛቤ ያመላከቱበት የጥናት ውጤት ላይ፣ መንግሥት እንዲያስተካክል በማለት የመፍትሔ ሐሳቦቻቸውንም አሥፍረዋል፡፡ የትምህርት መቋረጥና የተቋማቱ መዘጋት ያስከተለውን መቃወስ ያወሱት አጥኚዎቹ፣ ለመጪው ትምህርት ዘመን ተገቢው ቅድመ ዝግጅት የተደረገበትና ወላጆችም እንዲያውቁት የሚደረግበት የተቀናጀ አሠራር ታሳቢ እንዲደረግ ከጠየቋቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች