የሲዳማ ክልል በዘጠኝ ክልል የተዋቀረው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተ ወዲህ የመጀመርያው አዲስ ክልል ሆኖ፣ አሥረኛው የፌዴሬሽኑ አባል በመሆን በቅርቡ በይፋ ተመሥርቷል፡፡ የሲዳማ ጥያቄ በተለይ በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ የሕግና የፌዴራዝም ጥናት በርካታ ጽሑፎች እንዲጻፉ፣ ምርምሮች እንዲሠሩና ውይይቶች እንዲደረጉ ያስገደደ ነው፡፡ ጥያቄውን ባነገቡ ወጣቶችና በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም በፀጥታ አካላት መካከል በነበሩ ግጭቶች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈና ቤት ንብረት እንዲወድም ያደረገ ሲሆን፣ ረዥም ዓመታት ባስቆጠረው ትግል ውስጥም ይኼን መሰል ክስተት ጎልቶ የታየበት የሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጥቃትና ውድመት ጎልቶ ይነሳል፡፡ የሲዳማ ክልል በዞን ደረጃ በደቡብ ክልል ሥር ይተዳደር በነበረበት ወቅት የክልልነት ጥያቄው መልስ ይሰጠው ዘንድ በዞን ምክር ቤቱ አፅድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ካቀረበ አንድ ዓመት ቆጥሮ የተከሰተው ይኼ አመፅና ብጥብጥ በርካታ ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት የነበረ ሲሆን፣ ቤት ንብረት እንዲወድም አድርጓል፡፡ በዚህና በመሳሰሉ በደቡብ ክልል በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ፣ የደቡብ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲሆንም ተደርጎ ነበር፡፡ የሲዳማ ጥያቄ በደቡብ ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲከናወን ከተመራበት ጊዜ አንስቶ 13 ያህል የተለያዩ የደቡብ ክልል ዞኖች ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ እስካሁን ምላሽ አግኝቶ በክልልነት የተዋቀረው የሲዳማ ብሔር ብቻ ነው፡፡ በሲዳማ ጥያቄ መሠረት ክልል ይመሠረት ዘንድ በተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ከ98 በመቶ በላይ መራጮች የሲዳማ ዞን ከደቡብ ክልል ተለይቶ ለብቻው ክልል እንዲሆን መደገፋቸውን ተከትሎ፣ ሲጠበቅ የነበረው የሥልጣን ርክክብ ከደቡብ ክልል ጋር በመደረጉ የሲዳማ ዞን ክልል ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ የሕግ አውጪ፣ የሕግ ተርጓሚና የሕግ አስፈጻሚ አካላትም ተዋቅረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው አዲስና አሥረኛው ክልል የሆነው ሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙት በቀድሞው አደረጃጀት የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ደስታ ሌዳሞ ካቢኔ ያዋቀሩ ሲሆን፣ የሲዳማ ክልል ቀጣይ ዕጣ ፈናታዎችን የሚወስኑ የተለያዩ ዓውዶችንና ፖሊሲዎችን በመተለም ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በ1989 ዓ.ም. በዲግሪ ተመርቀው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ደስታ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንም በምርጫ 97 ፓርላማውን ተቀላቅለው ነበር፡፡ በፓርላማ ቆይታቸውም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ አባልና የትምህርት ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በመቀጠልም በደቡብ ክልል በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ በቀድሞው የሲዳማ ዞን ደግሞ የመምርያ ኃላፊ፣ የድርጅት ኃላፊ እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የሲዳማ አዲሱ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙት አቶ ደስታ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ፣ እንዲሁም የወደፊት የክልሉን ዕጣ ፈንታና የወጣቶችን አደረጃጀት በተመለከተ ከብሩክ አብዱ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከተቀሩት የደቡብ ሕዝቦች ዞኖች አንፃር ሲታይ ሲዳማ ያደገና በፖለቲካም ረገድ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ ነው ይኼ ሆኖ ሳለ ሲዳማ ክልል ለመሆን የፈለገበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ደስታ፡- ምክንያቶች ሥነ ልቦናዊም ናቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊም ናቸው፡፡ ሥነ ልቦናዊ ናቸው ስንል ሲዳማ ኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግሥት ከመሰብሰቧ በፊት የራሱ አስተዳደር የነበረው ሕዝብና አካባቢ ነው፡፡ ኋላ ላይ የራሱ የነበረው አስተዳደር በማዕከላዊ መንግሥት ተፅዕኖ ሲፈርስበት፣ በቦታው የተተካው ሥርዓት የተመቸው አልነበረም፡፡ ከቀዬው ያፈናቀለው፣ መሬቱን የቀማውና በአስተዳደሩም ከራሱ አብራክ የወጡ ልጆች ሲያስተዳድሩት አልነበረም፡፡ ከሌላ አካባቢ የመጡና በዚህ አካባቢ ሲያስተዳድሩ ነበር የቆዩት፡፡ ስለዚህ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዕድሉን ጭምር የተነፈገ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሲፈጸምበት የነበረው በደል ብሶትን የወለደ ነበር ለማለትም ይቻላል፡፡ መሬቱ ሲነጠቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ነፃ ሆኖ ጉልበቱን በማይጠቀምበት ሁኔታ ነበር የጭሰኛ ሥርዓት የነበረው፡፡ በሳምንት ስድስት ቀን ለሚያስተዳድረው ነው የሚያርሰው፡፡ ለራሱ የእረፍ ቀን ተብሎ የተሰጠው እሑድ ቀን ብቻ ነበር፡፡ ይበዘበዝ ነበር፡፡ በቋንቋውም መጠቀም አይችልም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት እንዲያውም የነበረውን እምነት በአግባቡ መፈጸም እንዳይችል ተደርጎ ሌላ ሃይማኖት እንዲቀበል፣ አንድ ወጥ ሃይማኖት እንዲተገበር በፈቃድ ሳይሆን በኃይል የታወጀበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ በዕምነቱ የሚያከውናቸውንና ጥሩ ናቸው የሚላቸውን ተግባራት እንዳይተገብር ተገዶ ነበር፡፡ በባህሉም እንዲሸማቀቅ የተደረገበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ከዚያን ጊዜ ጀምረው ነፃ የመውጣት ስሜትን የወለዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ይኼ ሁኔታ ሄዶ ሄዶ የአፄዎቹን ሥርዓት በተደራጀም ባልተደራጀም መንገድ እየታገለ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተነሳበት ትግል ሥርዓቱ ሊወድቅ ችሏል፡፡ ከዚያ በኋላ የመጣው የደርግ ሥርዓት በራሱ መጀመርያ ላይ መሬት ላራሹ አውጆ ነበርና የሲዳማ ሕዝብ ተነጥቆ የነበረውን መሬት መለሰለት፡፡ በዚያም ምክንያት የደርግ ሥርዓትን ደገፈ፡፡ ይሁንና ቀደም ብሎ ያነሳኋቸው በቋንቋው እንደ ልቡ የመጠቀም፣ ባህሉን የመግለጽ፣ በማንነቱ የመኩራትና ራሱን በራሱ የማስተዳደር የመሳሰሉ ቀደም ብዬ ሥነ ልቦናዊ ያልኩት አስተሳሰብ አብሮ ይጓዛል፡፡ ሰውም በየጊዜው ጥያቄ ያነሳል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ሲመዝን አሁንም ያልተመቸው ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት በ1966 ዓ.ም. የካቲት ላይ ነበር ለውጡ የመጣው፡፡ ሁለት ዓመት ካየ በኋላ ትግል ጀመረ፡፡ ይኼ ትግል ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ የተደራጀ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) የሚባል ድርጅት መሥርቶና 50 እና 60 ቀናት በእግሩ ተጉዞ ሶማሊያ ሠልጥኖና ታጥቆ ይመለስ ነበር፡፡ ጠንካራ ትግል ነበር ሲደረግ የነበረው፡፡ ከፍተኛ ዋጋም አስከፍሎታል፡፡ በወቅቱ የደርግ ሥርዓት በስምንት ወረዳ አደራጅቶ ከነበሩት አካባቢዎች አራቱን ወረዳዎች ከደርግ አገዛዝ ነፃ በማውጣት፣ ራስ ገዝ አስተዳደር መሥርቶ ራሱን በራሱ ያስተዳድር ነበር፡፡ በኋላ ላይ በሲዳማ አካባቢ በድርጅት ውስጥ በተፈጠረ የአያያዝ ጉድለት መድከምና ደርግም የተለያየ ሥልት ተጠቅሞ ታጋዮቹን እንዲያፈገፍጉ ያደረገበት ጊዜ ቢኖርም፣ ከውጭ አገር ሆነው ይቀሰቅሱ ነበር፡፡ ነገር ግን ትግሉ አልመታም፣ ድርጅቱም አልጠፋም፡፡ በዚህ ሥነ ልቦና እስካሁን ተደረሰ፡፡ ሆኖም ከግራም ከቀኝም በነበረው ትግል የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢሕአዴግ መጣ፡፡
ኢሕአዴግን አሁንም ጥያቄ ይመልስልኛል ብሉ መጠበቅ ያዘ፡፡ የተወዳዳሪነት ጥያቄ ነው፡፡ በሌላ በኩል አገራዊ ተሳትፎም ላይ ጎልቶ የመታየት፣ ብቁ ተወዳዳሪ የመሆን፣ የመሳተፍ፣ ወዘተ ጥያቄ ነው እንግዲህ፡፡ ራሱን በራስ ማስተዳደር ሲባል እዚሁ አካባቢውን አስተዳድሮ መቅረት ሳይሆን፣ እንደ አገር አካባቢውን በሚገባ መወከልም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ይፈጸማሉ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ መጀመርያ ኢሕአዴግ ክልል ብሎ አደራጀው፡፡ ጌዴኦ፣ ቡርጂንና አማሮን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ይኼንን ግን የሲዳማ ሕዝብም ሆነ ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎታል ማለት አይቻልም፡፡ ያልተቀበለ የሲዳማ ኃይል ነበር፡፡ ከሕወሓት ጋርም ይታገል ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1984 ዓ.ም. ክረምት ላይ እዚህ ሐዋሳ ጦርነት ነበር፡፡ ይኼ ሁሉ ትግል እየተደረገ በኋላ ላይ በፖለቲካ ሴራ ይኼንን ክልል ስምንት ጨምሮ አምስት ክልሎች አንድ ደቡብ በሚል ክልል እንዲዋቀሩ ታስቦ በተሠራበት የፖለቲካ አሻጥር፣ ሲዳማ በደቡብ ክልል ሥር እንዲወድቅ ሆነ፡፡ ከዚያ ጀምሮ በአስተዳደር ደረጃ የሲዳማ ሰዎች እንዲያስተዳድሩ ይደረጋል፡፡ በአብዛኛው ነገር ግን ሕዝቡ ያም ሲሆን በደቦ የሚሠራውን የአስተዳደር ሁኔታ አልተቀበለም ነበር፡፡ በመሆኑም በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ያነሳል፡፡ የራሴ ክልል ይሰጠኝ፣ ራሴን በራሴ ማስተዳደር እፈልጋለሁ እያለ፡፡ በዚህ ምክንያት ሐዋሳ ከተማን ጨምሮ አካባቢውን ራሱ እየተቆጣጠረና እየወሰነ፣ በአገሩ ሁኔታ በአግባቡ እየተሳተፈ መኖር ስለሚፈልግና ምክንያቱ ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ሥነ ልቦናዊ እርካታን አላገኘም፡፡ የደቡብ ክልልን ማስተዳደር ለሲዳማ የፊት መሪነት ቢሰጠውም በስሙ የሚጠራ ክልል፣ በአገር ደረጃ ደቡብ ሳይሆን ሲዳማ ተብሎ የሚጠራበት፣ በውስጥ ጉዳዮችም ቢሆን ራሱ የሚወስንበት አደረጃጀት ነው ይፈልግ የነበረው፡፡ እነዚህ ግፊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ግጭቶችን እየወለዱ በፖለቲካው ዓለም የተለያዩ ድርጅቶችን እየፈጠረ የመጣበትና ብዙ ዋጋም የተከፈለበት ነው፡፡
መንግሥት ወደ ለውጥ ሲሸጋገር ሲዳማ ውስጥ የለውጥ ፍላጎት ስለነበር፣ በፊት የነበረው አደረጃጀትም አሠራርም ከልብ የደገፈው ባለመሆኑ ፈጥኖ ኦሮሚያና አማራ አካባቢ የነበረውን ለውጥ ተከትሎ ለውጥ ውስጥ የገባ አካባቢ ነው፡፡ ለውጡ ግን እዚህ አካባቢ መሠረት የሚያደርገው ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው፣ ያልተመለሰና ራሴን በራሴ ላስተዳድር የሚል ጥያቄ ነው የነበረው፡፡ ይኼ ጥያቄ መነሻው ከአፄዎቹ ጊዜ አንስቶ መሬቱን ተነጥቆ ስለነበረና መሬቱን የማልማት መብቱን ተነጥቆ ነበር፡፡ ከሌሎች የማንነት ጉዳዮችም ጋር ተያይዞ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄው መነሻ ቢሆንም ራሱን በራሱ የማስተዳደርና በነፃነት መንፈስ አካባቢውን የመምራት ስሜቱ ቀደም ብሎ ስለነበረም ያንን በማሰብ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ እኮ አራተኛ ትውልድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን ትግሉ ቀጥሏል፡፡ የሚመጣው ትውልድ ሁሉ ይኼንን ጥያቄ ስለሚደግፍ በፖለቲካ ለማለዘብ ብንሞክር እንኳን ትንሽ ጊዜ ይሆናል እንጂ መልሶ ያገረሽበታል፡፡ ይኼ አስተሳሰብ ላይ ያለ ስለሆነ ሥነ ልቦናዊ ምክንያት ነው ያለው፡፡ ሲዳማ የራሱን ክልል መሥርቶና በፌዴራል መንግሥትም እኩል ተሳታፊ ሆኖ መኖር ይፈልጋልና ዝም ብሎ ገንዘብ ቢሰጠውም የሚተው አይመስለኝም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ያንን የሚመግቡና በየጊዜው አንተ ክልል ብትሆን ኖሮ ትጠቀም ነበር የሚያስብሉ ነባር አደረጃጀቶች ስለነበሩ፣ ያገኛቸውም ያጣቸውም ነገሮች ቢኖሩም ያጣቸውን ነገሮች አጉልቶ የሚያይበት ሁኔታ ነበር፡፡
እነዚህን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያየን እንደሆነ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አይደርሰኝም ብሎ ያስባል ሲዳማ፡፡ ይኼ ሲባል ቀመሮቹ በምን እንደሚሰሉ ይታወቃል፡፡ ቀመሮቹ በምን እንደሚሠሩ ታሳቢ በማድረግ ሲዳማን የሚመለከቱ መረጃዎች ገብተው ቢሰሉ፣ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይደርሰው የነበረው ግን ከዚያ ያነሰ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሌሎች በድርድር የሚገኙ የፖለቲካ ተሳትፎዎችን ጭምር በተገቢው ድርሻዬን እያገኘሁ አይደለም የሚል አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሲዳማ በደቡብ ክልል በነበረበት ጊዜ በድርሻው የደረሰውን በጀት ጭምር በቂ በጀት የማይደርሳቸውን የክልሉ ዞኖችን በጋራ እንደግፍ በሚል፣ ከሲዳማ ከራሱ ቀንሶ የሚሰጥበት ሁኔታ ነበር በበጀት ክፍፍል ወቅት፡፡ ለምሳሌ ደመወዝ መክፈል የማይችሉ ትንንሽ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው አካባቢዎች በበጀት ክፍፍል ወቅት የሚደርሳቸው ትንሽ ይሆናል፡፡ ያ ሲሆን ደግሞ እንደ ዞን ለመቀጠል የማይችሉበት ሁኔታም ይኖራል፡፡ ይኼ እንዳይሆን በተመጣጣኝ ዕድገት መርህ አብረን እንደግ ተብሎ መሪዎች በፖለቲካ ተወያይተው የዚያ ዓይነት ድጋፍ ይሰጡ ነበር፡፡ ሲዳማ በትንሹ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ያጣል በዚህ ምክንያት፡፡ ይኼ እንግዲህ በደቡብ ውስጥ ሆኖ ከሚያገኘው ድርሻ ነው፡፡ ይኼንን ያስለቀቀው አብሮ መኖሩ ነው፡፡ እናም በዓመት ይኼንን ያህል ከለቀቀ በ10 እና በ20 ዓመት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለቀቀ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይፈልግም፡፡
ሁለተኛ ከአገሪቱ ለራሱ የሚሰጠው ድርሻ በፍትሐዊነት እየደረሰኝ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ሦስተኛ በራሱ አካባቢም ቢሆን በአግባቡ ዕድገትን በሚያፋጥን መንገድ የመምራት ሁኔታም አለ ብሎ አያስብም፡፡ ይኼንን ስንል ለምሳሌ ደቡብ ክልል ሰፊ ነው፡፡ የአካባቢውም አግሮ ኢኮሎጂም እጅግ ብዝኃነት የሚታይበት ነው፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ሁኔታዎች ለሚታዩባቸው አካባቢዎች የሚዘጋጁ ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ሲዳማ ያለውን ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ላይመስሉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሲዳማ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚመስሉ ፖሊሲዎችንና ዕቅዶችን አዘጋጅቶ ለመሄድ አይችልም ነበር፡፡ ሲዳማ ያለው አደረጃጀት በዞን ደረጃ ነው፡፡ ዞን ደግሞ ፖሊሲ አያወጣም፡፡ ሕግ መተግበር እንጂ ሕግ ማውጣት አይችልም፡፡ ስለዚህ ሥልጣን አልነበረውም የተመቹትን ጉዳዮች ለይቶና አርሞ ለመሄድ፡፡ ይኼንን ለማድረግ የማያስችሉ ውሳኔዎችን ለመስጠት ሕጋዊ ሥልጣን የለውም አደረጃጀቱ፡፡ ይኼ በራሱ ጥያቄን ይፈጥራል፡፡ ሲዳማ በብዛት የሚያመርተው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን (Cash Crop) ነው፡፡ ደቡብ ላይ ደግሞ በአብዛኛው የሚተኮረው በቆሎ ነው፣ ደቡብ በጠቅላላው ሲታይ፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥና በመጠኑ ደግሞ የተቀሩትን የዘነጋ ዕቅድ ለሲዳማ አዋጭ አይደለም፡፡ እንደ ሲዳማ ነባራዊ ሁኔታ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን አድርጎ፣ ውሳኔ ወስኖ፣ ፖሊሲና ዕቅዶችን አውጥቶ ለመሄድ የሚያስችል ሥልጣንም ስለሌለው፣ ይኼንን ማግኘት ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግ ኢኮኖሚያዊ አንድምታም ያላቸው ናቸው፡፡ በድምሩ እነዚህ ነገሮች ሲዳማ ሁልጊዜ እንዲታገል ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ100 ዓመታት በላይ በትግል ሕይወት ውስጥ ከባድ ዋጋዎችንም ከፍሏል፡፡ የምንሰማቸው ታሪኮች እንደሚሳዩት የሰው አንገት ተቆርጦ በገበያ ሥፍራ በእንጨት ተሰቅሎ ገበያተኛው እያየ እንዲፈራ፣ እንዲሸማቀቅና መሰል ትግሎችን እንዳያደርግ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በርካታ ነበሩ፡፡
ሪፖርተር፡- የሲዳማ ጥያቄ ለዓመታት የዘለቀና በርካታ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይኼም ራሴን በራሴ ላስተዳድር የሚል መሠረት እንዳለውም አመላክተዋል፡፡ አሁን ሲዳማ አሥረኛው የኢትዮጵያ ክልል በመሆን በይፋ ተመሥርቷል፡፡ ክልል መሆን እንዴት ነው እነዚህን ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችለው?
አቶ ደስታ፡– የመጀመርያው ክልል መሆኑ የሚመልሰው ሥነ ልቦናዊ ጥያቄን ነው፡፡ ሲዳማ ክልል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ትርጉም ባለው ደረጃ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ደግሞ በክልል ደረጃ ተደራጅተው እያየን ነው የቆየነው፡፡ ሲዳማም ከእነዚያ ውስጥ አንዱ ነኝ ብሎ ያስባል፡፡ እውነትም ከኦሮሞና ከአማራ ቀጥሎ ሶማሌና ትግራይንም በሚገዳደር ደረጃ ነው የሲዳማ ማኅበረሰብ ብሎ መውሰድ ይቻላል፣ ከሕዝብ ቁጥር አንፃር፡፡ ለሲዳማ በምርጫ ጊዜ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው ቁጥር 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ በማንኛውም ምርጫ እንደሚታወቀው ደግሞ ከጠቅላላ ሕዝብ 50 በመቶ ያህል እንኳን አይመዘገብም፡፡ አርባ በመቶ ነው ሕጋዊው፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሊሳተፍ የሚችለው የሚል ሥነ ሕዝባዊ ጥናቶች የሚያመላክቱት፡፡ ከዚህ ዕሳቤ እንኳን ተነስተን ከጠቅላላው ሕዝብ 40 በመቶ እንኳን ተመዝግቧል ብንል 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳተፈ ማለት፣ ጠቅላላ ሕዝቡ ከአምስት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ማንም ሰው ሊያምን የሚችለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥሩ በዚህ ደረጃ ያለ ሕዝብ ያለው ማኅበረሰብ ትንሽ ነው፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቦች ግን አደረጃጀታቸው በክልል ደረጃ ነው፡፡ ሲዳማም እንደዚያ ያለ አደረጃጀት ያስፈልገኛል ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ ይኼ ሥነ ልቦናዊ ጥያቄ ክልል ሲሆን ተመለሰ፡፡
ቀጥሎ የሚመጣው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን መመለስ ነው፡፡ ፖለቲካዊ የምንላቸው የተሳትፎና የእኩል ተጠቃሚነት ነው በውስጡ ያለው፡፡ ተሳትፎን በሚመለከት አደረጃጀቱ ይኼ እስከሆነ ድረስ አደረጃጀቱን ተከትሎ የሚኖሩ አገራዊ ተሳትፎዎች ሌሎችን ሕዝቦች እንደሚያሳትፍ ሁሉ፣ ሲዳማንም ያገናዝባል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፖለቲካዊ ተሳትፎዎቹ እንደ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ፣ ወዘተ ከመሳሰሉ ዘላቂ ጥያቄዎች በስተቀር በፌዴራል መንግሥት አሠራርና አደረጃጀት ሥርዓት መሠረት እኩል የመወከል፣ የመሳተፍ፣ የመወከልና በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በብቃት የመሳተፍና የመወሰን ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱ በራሱ ይኼንን ይፈቅዳል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በአደረጃጀት የሚመለሱ ነበሩ፣ አሁን ተመልሰዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀሩት ኢኮኖሚያዊ ባህርይ ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከድህነት መውጣት፣ ባለው ዕድል እኩል ተሳታፊ መሆን፣ በተሳተፈው ልክ እኩል ተጠቃሚ መሆን፣ እንዲሁም የገቢና የኑሮ ሁኔታ እየተሻሻሉ የመሄድ ሁኔታዎች ክልል በሆንን ማግሥት የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ክልል ግን እነዚህንም ለመፍታት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ እንዴት ብትለኝ ክልል አደረጃጀት ነው፡፡ አደረጃጀት ደግሞ ነባራዊ ሁኔታን በማገናዘብ ፈጣን ዕድገት የሚያመጡ ሥራዎችን ለመሥራት አንደኛው ትልቁ አቅም ሕዝብ ነው ብለን ብናምንም፣ እንደ ጨው ማጣቀሻ በመሆን የሚያገለግለው በጀት ነው፡፡ በጀትም፣ ዕውቀትም ሕዝብ ውስጥ ያለው እንዳለ ሆኖ በጋራ አምርተን በአገር ደረጃ የፈጠርነው ሀብት የሚከፋፈለው መጠንም ቢሆን በድርሻ ነው የሚገኘው፡፡ አሁን ሲዳማ በዚህ ዓመት ከፌዴራል መንግሥት በጀት አላገኘም፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን እኮ 6.9 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ ተበጅቶለታል፡፡
አቶ ደስታ፡– ድርሻውን ማለት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አላገኘም ለማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አነሰ ማለትዎ ነው ታዲያ?
አቶ ደስታ፡– ትንሽም ትልቅም ሆነ ለማለት ሳይሆን፣ ያገኘበት መንገድ የሚገባው ነው የሚያስብል አይደለም፡፡ በጀት የተከፋፈለበት ቀመር ለሲዳማ ለብቻው አልተሠራም፡፡ ያኔ ቀመር ሲሠራ ለክልል ነው የተሠራው፡፡ ሲዳማ ደግሞ ክልል አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት በእነዚህ ቀመሮች ሲሰላ ሲዳማን በሚመለከት ለብቻው ከአገር እንደ አገር ለክልሎች ሲሠራ አልተሠራለትም፡፡ ስለዚህ ሲዳማ በደቡብ ክልል ሳለ በዚያ የነበረው መረጃ ነው የተላለፈው፡፡ በመሆኑም ጥቅሉ ለደቡብ ክልል የመጣው ያሉ ሁኔታዎች ከግምት ገብተው የሲዳማ ድርሻ የሚለው በቀመሩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥርት ባለ ሁኔታ ሳይሆን፣ በፖለቲካዊ ድርድር የተገኘ ውጤት ነው፡፡ በዚህም የጣልነው ነጥብ አለ ብለን እናምናለን፡፡ ያኔ ቀመር ሲጠና አብሮ ቢጠና ኖሮ ይገኝ የነበረው መረጃ አሁን ከተሠራበት ግምታዊ መረጃ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ጊዜው ይደርሳል ብለን አሁን ማንም ጫና ፈጥሮብን ሳይሆን፣ መፈታት ስለነበረበት ችግሩ በዚህ ሁኔታ ሊሠራ ችሏል፡፡ ይኼ ፍትሐዊና በትክክለኛ መረጃ ተመዝኖ የተገኘ ባይሆንም የተገኘው በቂ አልነበረም፡፡
በእርግጥ ክልል ስንሆን የሚፈጥረው የራሱ ወጪ አለ፡፡ ሌላ መዋቅር ነው የጨመርነውና ሌላ ወጪ ነው የሚፈልገው፡፡ እነዚህ ወጪዎች እንዳሉ ሆነው፣ ሽርፍራፊም ብትሆን ተጨማሪ ድህነት ቅነሳ ላይ መዋዕለ ንዋይ ልናፈስ የሚያስችለን ሀብት ማግኘትም የተቻለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ስላልተመዘንንና ቀመሩም በአግባቡ እኛን ባለማገናዘቡ የቀረ ቀርቶ ሳለ ነው ይኼ ሁሉ የሆነው፡፡ በፊትም የታገልነው ይኼንን ሁሉ እንደምናጣ ስላወቅን ነው በብዙ መልኩ የሚቀር የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊና ሚዛናዊ አይደለም ያልነው፡፡ ያ ደግሞ አደረጃጀቱ የፈጠረው ችግር ስለነበረ እነዚህንም ለማስተካከል ነው ሲዳማ ክልል ለመሆን የታገለው፣ ቅድም እንዳልኩት፡፡ ይኼ ሁኔታ አሁን ክልል ከሆነ በኋላ ፍንትው ብሎ ነው የታየው፡፡ ይኼ ችግሩን ምን ያህል ፈትቷል ወዳልከው ስንመጣ፣ ይህችንም ሀብት ይዘንና መዋዕለ ነዋዩን ብናፈስባቸው ለውጥና ውጤት ልናመጣባቸው የምንችላቸው አካባቢዎችና ሁኔታዎች በዕቅድ ይዘን፣ በአዋጅም በፖሊሲም ሊደገፉ የሚገቡና የሚፈቱ ማነቆዎች ካሉ እርሱንም ፈትተን ወደ ሥራ ስንገባ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል እናምናለን፡፡ በዚህ ሒደት ነው ቅድም የተነሱት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሊፈቱ የሚችሉት፡፡ እንደ ደሃ አገር ደግሞ ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ ሊፈታ ይችላል ብለን አንጠብቅም፡፡ የተሻለ ለውጥ እየመጣ ይሄዳል ብለን ነው የምናምነው፡፡ ለዚህም መሠረታዊ የሆኑ ሁኔታዎች በዚህ መልኩ እየተስተካከሉ ስላሉ ተስፋ አለው ብለን ነው የምናስበው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ አሁን የዘረዘሩልኝ ነጥቦች የሲዳማ ጥያቄ ትክክለኛ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተና ሥነ ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን እንደሚፈታ የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የክልልነት ጥያቄዎችን በሚያነሱ አካባቢዎች ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት፣ ለሥልጣንና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የክልልነት ጥያቄን ይገፋሉ ብለው ነበር፡፡ በሲዳማ ጥያቄ ውስጥ ይኼ ፍላጎት የነበራቸው ባለሥልጣናት አልነበሩም ማለት ይቻላል?
አቶ ደስታ፡– እኔ በሲዳማ አካባቢ እንዲህ ያለ ፍላጎት አለ ብዬ አላምንም፡፡ በቅርብ ጊዜ እንኳን የሲዳማን ክልል ሲገፉ የነበሩ ባለሥልጣናት የክልል ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩ ከአንድም ሁለት ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ አቶ ደሴ ዳልኬ ቀደም ብሎ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩና ፍላጎታቸው ሥልጣን ቢሆን ኖሮ ያንን ሥልጣን አስጠብቀው መቀጠል ይችሉ የነበሩና ዕድሉም የነበራቸው ናቸው፡፡ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስም ቢሆኑ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ እንግዲህ ሲዳማ ክልል ሲሆንም ፕሬዚዳንትነት ከሆነ መነሻና መድረሻው፣ እነዚህ ሰዎች ይኼንን ፍላጎት ሲገፉ መነሻቸው ሥልጣን ነው ብዬ አላስብም፡፡ ለዚያውም የ20 ሚሊዮን ሕዝብ ፕሬዚዳንት መሆንና የአምስትና የስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ፕሬዚዳንት መሆን ከሚታዘዘው ሀብት መጠን አንፃር እንኳን ብናየው እኩል አይደለም፡፡ እኩል ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ያንን ሁሉ ትተው ወደዚህ ትግል ሲገቡ ለእኔ ከሲዳማ አንፃር ሥነ ልቦናዊ ይመስለኛል እንጂ፣ ሥልጣን ለማስፋት ነው ብዬ አልወስድም፡፡ ሌላው ይኼንን ጥያቄ በብዛት ሲገፉ የነበሩ ወጣቶች ኤጄቶ በሚል መጠሪያ ሌት ተቀን ለዚህ ጉዳይ የተጉ ናቸው፡፡ አዲሱ ክልል ከመጣም በኋላም የረባ ሥልጣን አላገኙም፣ አልተሰጣቸውም፡፡ ለምንድነው ያልተሰጣቸው ከተባለ ሥልጣን ከመጀመርያውኑ ክፍፍሉ እነዚህን ትግሎች ጀምሮ በመጨረስ አይደለም፡፡ መጀመርያ የታገለውም ሰው ለሥልጣን አይደለም ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ሰው የታገለውና ይኼንን ጥያቄ ሲገፋ የነበረው ለሕዝብ ተጠቃሚነት ነው፡፡ በሕዝብ ውስጥ የነበረን የቆየ ጥያቄ አንግቦ ነው ካልን፣ የእነዚህ ወጣቶች ፍላጎት ያነሷቸው ጥያቄዎች ከዳር ደርሰው ማየት ነው እንጂ ሥልጣን ላይ ተቀምጠው መጠቀም አይደለም፡፡ ግለሰባዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ አይደለም የሚለውን ወጣቶቹም የሚያምኑበት ነው፡፡ እኛ በዚህ ሒደት ውስጥ ያለን ሰዎችም የምናምንበት ነው፡፡ ሰሞኑን ባደራጀሁት ካቢኔ ውስጥ በዚያ ደረጃ ያለፉ ወጣቶች ፊት የሚባሉ ቦታዎች ላይ አልመጡም፡፡ ይኼ የሆነበትም ምክንያት አንደኛ ልምድ ስለሚያንሳቸው ነው፡፡ ነገር ግን ቀጥሎ ባለው አደረጃጀት ውስጥ በሒደት ልምድ እያገኙ ፊት መሪ ሆነው ሊመሩ የሚችሉ ናቸውና በዚያ ደረጃ ነው እያዘጋጀናቸው ያለነው፡፡ ስለዚህ ከአሁን በፊት ሥልጣን ላይ የነበሩትም የሥልጣን ፍላጎት አልነበራቸውም፣ ከእነርሱ ጋር ሲታገሉ የነበሩትም በተመሳሳይ፡፡ ሥልጣን በዚህ ደረጃ ካደራጀን በኋላ ግብረ መልሱንም ስንመለከት ሕዝቡ ደስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ከሲዳማ አንፃር፣ ከሌሎቹ አንፃር ሊሆን ይችላል አላውቅም፣ ጥያቄው የሕዝብ ተጠቃሚነት በነበረው አደረጃጀትና አሠራር አልተረጋገጠም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሲዳማ በክልል ደረጃ ቢደራጅ ይሻላል ከሚል እምነት ነው እንጂ፣ ከሥልጣን ፍላጎት የመነጨ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ እንዳሉት የሲዳማ ጥያቄ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በርካታ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡ አሁን መለስ ብለው ሲያዩት የተከፈሉ ዋጋዎች አግባብ ነበሩ ይላሉ? ማስቀረትስ የሚቻሉ ጥፋቶች ነበሩ ብለው ያምናሉ?
አቶ ደስታ፡– ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለው የፖለቲካ ባህርያችን ነው፡፡ የፖለቲካ ባህርያችን ጥያቄዎችን በአግባ አይቶ የሚፈታ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ያለ ዋጋ መክፈል ባላስፈለገ ነበር፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ የነበሩ ሥርዓቶችን ትተን የኢሕአዴግን ሥርዓት ብቻ እንኳን ብንወስድ፣ በሕገ መንግሥት ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እነዚህን ድንጋጌዎች መንግሥት ተቀብሎ ቢተገብረው ኖሮ እነዚህ ጥያቄዎች ይመለሱ የነበረው ዛሬ ሳይሆን፣ ከመነሻው ነበር መፈታት ይችል ነበረው፡፡ ይኼንን ለመፍታት የሚያስችል ድንጋጌም ተቀምጦ ስለነበር፡፡ ግን ድንጋጌዎቹ የወረቀት ላይ ጌጦች ናቸው እንጂ አቋም ተይዞባቸው ወደ ተግባር የተቀየሩ አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የሚገባው አካል ይገባኛል ብሎ እየታገለ ነው፡፡ መፍታት የሚገባው አካል ሳይፈታ ችላ እያለ በተለያየ መልኩም እያፈነ በተፈጠረ ፍትጊያ ነው የሕይወት ዋጋ የተከፈለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መፈታት አለበት ብዬ የማስበው የሚታፈኑ አካላትም ቢሆን የንብረት ውድመት እያስከተሉ መታገል አልነበረባቸውም፡፡ ለተጨማሪ ሀብትና ንብረት የሚታገል ማኅበረሰብ ያለውን ሀብትና ንብረት በማጥፋት ዕድገትን ማረጋገጥ አይችልም፡፡ በመሆኑም ትግሉ ሰላማዊ ቢሆንና ሕጉ በሚፈቅደው ሁኔታ ቢሆን መልካም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኼ ሳይሆን ቀርቶ የተከፈሉ ዋጋዎች ውድ ናቸው፡፡ የሕይወት ዋጋም ተከፍሏል፡፡ የሲዳማም ሕዝብ የተጎዳበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ በአንፃሩ ግን በተወሰኑ ከተሞች የሞትና የንብረት መጥፋት ተከስቷል፡፡ ይኼ መሆን ያልነበረበት ክስተት ነው የሆነው፡፡ ትግሉ ግን ፍትሐዊና ለፍትሕ የተደረገ ነው፡፡ የተከፈለውም ዋጋ መከፈል የነበረበት ሳይሆን፣ መከፈል በማያስፈግ መንገድ መፈታት ሲኖርበት ይኼንን የሚፈቅድ ሥርዓት ባለመኖሩ የተከፈለ ዋጋ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ እንዳሉት እንደ አገርም ብዙዎችን ያሳዘኑ ውድ ዋጋዎች ተከፍለዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ታዛቢዎች የተከፈለው ዋጋ ምንጩ ምንድነው ብለው ሲጠይቁ፣ ጥያቄው መደመጥ ከጀመረበት ጊዜ በኋላም ቢሆን ምላሹ በቶሎ ካልተመለሰልን በሚሉ ግፊቶች የመነጨ ነው ይላሉ፡፡ የክልልነት ጥያቄ በባህርይው የረዥም ጊዜ ግብ አንግቦ የሚቀርብ ሆኖ ሳለ ጥድፊያዎች ነበሩ ይላሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌው ቢኖርም ከረዥም ጊዜ ግብ አንፃር ሲታይ ለምንድነው ጥድፊያው የነበረው?
አቶ ደስታ፡– ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ቢኖርም ብሎ ማስቀረት ይቻላል ወይ ነው ጥያቄው? ሕገ መንግሥትን መጣስ ሕግን ሁሉ መጣስ ስለሚሆን ሕገ መንግሥትዊ ድንጋጌን አክብረን መሥራት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስለሚሆን፣ ይኼንን የጣሰ አካል ነው ተጠያቂ የሚሆነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የተቀመጠው እንድናከብረው ነው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ላይ ባልተደነገገና መብት ባልተሰጠው አግባብ ተፈጽሟል ቢባል ሒደቱን ቢያንስ ስህተት ስላለበት መደገም የለበትም ብለን እናልፋለን፡፡ የሲዳማ ጥያቄ ረዥም ጊዜ የቆየ ነው በሚለው ሁሉም ይስማማል፡፡ ለምሳሌ በ1997 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው መሠረት እንዲፈጸም ተጠይቆ እንዲከሽፍ ተደርጓል፡፡ ይኼ አሻጥር ተሠርቶበታል፡፡ አሁን በመጣው ለውጥም ሕዝቡ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ አሁንም ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ የመጣ ጥያቄ ነው፡፡ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የሕዝብ ተወካይ በመሆናቸው የሕዝብን ስሜት ለማወቅ ሕዝቡን አወያይተው ሕዝብ የደረሰበትን ድምዳሜ መነሻ በማድረግ፣ በሕጋዊ መንገድ አፅድቀው ለክልል ምክር ቤት አድርሰዋል፡፡ የክልል ምክር ቤት ማድረግ የነበረበት በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ለተከፈለ ዋጋ በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ አላደራጁም ብሎ ነው? ወይስ በአንድ ዓመት ውስጥ ሊደራጅልኝ ይገባል ያለው ነው ጥድፊያ የሚባለው? ጥድፊያውን እኔ አልቀበለውም፡፡ ጥድፊያ ሳይሆን ሕጋዊ ሒደትን ተከትሎ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የቀረበና በጊዜ ገደብ ውስጥ ለምን አይፈጸምልኝም ከሚል የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ በጊዜ ገደብ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔው ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ አንገባም ነበር ብዬ ነው የማስበው፡፡ ግፊትም ባይደረግ ኖሮ ይኼ ውሳኔ ላይወሰን ይችል ነበር የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡ ሕገ መንግሥታዊውን ድንጋጌ ችላ እያለ የቆየ አካል ግፊት ባይኖር ሕገ መንግሥቱንም ተፈጻሚ ለማድረግ ሊዘገይ ይችል ነበር፡፡ ግፊቱ ብዙ ችግር የነበረበት አይደለም፡፡ ሒደቱም ሕገ መንግሥቱን የተከተለና ሕጋዊ ነበር፡፡ ግን ስህተቱ የተፈጸመበት ቦታ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ወስኖ ካሳወቀ በኋላም ቢሆን፣ አመፅና ብጥብጦች ተከስተው ነበር፡፡ ይኼስ ጥድፊያውን አያመላክትም ይላሉ?
አቶ ደስታ፡– እሱን ነጥለን ካየን ልንግባባ እንችላለን፡፡ ሒደቱን ግን ሙሉ አድርጎ ማየት ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ቅድም እንዳልኩት ሕገ መንግሥቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ይደራጃል ብሎ ሲያበቃ አንድ ዓመት 365ኛ ቀን እስከሚሞላ መጠበቅ በራሱ ችግር ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ላይደራጅ ይችላል ብሎ የሠጋ ማኅበረሰብ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ግፊት ውስጥ ወጣቱና አክቲቪስቱ ሌላውም ሌላውም ተቀላቅሎ የሚደረግ በመሆኑ ግለቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጥያቄያችን ለደቡብ ምክር ቤት ከቀረበ አንድ ዓመት ይሞላዋል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ተደራጅቶና ውጤቱ ታውቆ የሥልጣን ርክክቡ ካልተጠናቀቀ ግፊት አድራጊዎቹ ቀን ቆርጠው፣ በከፍተኛ ደረጃ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብተው ነበር፡፡ ይኼ የሆነው መንግሥት የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግም ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ የሆነ ሆኖ በመንግሥት በኩል ያልተመቹት ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም ይኼንን ጥያቄ ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎች ከጀርባው መጥተው እነዚያን ጥያቄዎች እንዴት እንደሚያስተናግድ ማሰብ ይኖርበታል፡፡ ይኼንን በሚዛኑ ስናይ መንግሥትም ችግሮቹን በአግባቡ ለመፍታት የዘገየ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ በሲዳማ በኩል ግን ሕጉ ፈቅዶልኛል በማለት፣ መጀመርያም እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ እንዴት እንደሚፈቱ የሚታወቅ ስለሆነ የእኔ ጉዳይ ይፈጸምልኝ ዓይነት ግፊት ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ሐምሌ 11 ሊሞላ ቀናት ቀርተውት ሳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን ተቀብያለሁና ሕዝበ ውሳኔ አደራጃለሁ ያለው፡፡ በዚያ ጊዜ ሁሉም ነገር ተገፋፍቶ የሰከረ በመሆኑ መስከን ያቃተው ይመስለኛል፡፡ ግፊቶቹና ጡዘቶቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው በሲዳማ ውስጥ መደማመጥ የጠፋበት ጫፍ (Peak) ነበር ያ ጊዜ፡፡ መንግሥት ያንን ዕርምጃ እንኳን ቢወስድ ሕዝበ ውስኔውን ያደርጋል የሚል እምነት አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ ግፊቱ መርገብ ነበረበት፡፡ ቢረግብ ኖሮ ይኼ ሁሉ ጥፋት አይከሰትም ነበር፡፡ መንግሥትም ይኼንን ማድረጉ ላይቀር ጊዜ እያለ ውሳኔውን ቢወስድ ኖሮ እዚህ ውስጥ አይገባም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግሥት ከፍተኛ መጓተት በመፍጠሩ፣ ሕዝቡ ደግሞ ከፍተኛ ሥጋትና ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ፣ ይኼንን ማስታረቅ የሚቻልበት የጊዜ ዕድል ባለመኖሩ በጣም በተጣበበ ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ በመሆኑ መፈጠር ያልነበረበት ስህተት ተፈጥሯል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ የሲዳማ ሕዝብ ትግል ውስጥ አክቲቪስቶች ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የታዩ ዓይነት የወጣቶች ቡድኖችም ኤጄቶ በሚል መጠሪያ ተደራጅተው ጉዳዩን ሲገፉና ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ አሁን የሲዳማ ክልል መሆን ተመልሷልና የእነዚህ ወጣቶች ስምሬት ምንድነው የሚሆነው? መንግሥትስ ምን አስቦላቸዋል?
አቶ ደስታ፡– ወጣቶቹ ከዚህ በኋላ የሚኖራቸው ጥያቄ የተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፡፡ ከፍተኛ ሥራ አጥነት አለ ሲዳማ አካባቢ፡፡ ሲዳማ በርካታ ሕዝብ ቢኖረውም የቆዳ ስፋቱ ትንሽ ነው፡፡ በዚህ ትንሽ የቆዳ ስፋት ሰው ታጭቋል፡፡ በትንሽ ሥፍራ የወጣቱ ኃይል በብዛት ታጭቋል፡፡ ይኼ ኃይል በአግባቡ ከተጠቀምንበት የልማት ኃይል ነው፡፡ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ግን መኖር ስለሚፈልግ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ብዙ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ይኼ በመሆኑ እኛ አሁን የምናስበው በክልልነት ጥያቄ መመለስ ሥነ ልቦናዊ ጥያቄው ተመልሷል፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄውን ለመመለስ ምቹ አደረጃጀት ተፈጥሯል፡፡ የተፈጠረው ምቹ አደረጃጀት ውስጥ እንዴት አድርገን ይኼንን ኃይል እናሰማራ የሚል ጥያቄ ነው ያለን፡፡ ቀጥረን አንጨርስም፡፡ ዝም ለማሰኘት ብቻ ተብሎ ቅጥር ቢፈጸም ከፍተኛ ወጪ ነው የሚያስከትለው፡፡ በሌላ በኩል ለደመወዝና ለተለያየ ጉዳይ የምናወጣው ወጪ ሕዝቡ በድምር የሚፈልጋቸውን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች አይመልስም፡፡ ሕዝቡ ውኃ፣ መብራት፣ ወዘተ ይፈልጋል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው የመንግሥትንና የሕዝብን አቅም በማቀናጀት ነው፡፡ መንግሥት ሲባል ደግሞ የሚመደበውን በጀት ለማለት ነው፡፡ ይኼንን በጀት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሥራው ሰው ሳይፈልግ ለሰው እንጀራ ለመፍጠር በቅጥር ከጨረስን የሕዝብ ጥያቄ ስለማይመለስ አመፅ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ምክንያት መሪዎቹ ጥበበኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አሁን እኛ እያደረግን ያለነው የሕዝብ ጥያቄዎችን መለየትና በቅድሚያ ምላሽ ሊያገኙ የሚገባቸውን ማስቀደም ነው፡፡ ለእነዚያ ያለንን ሀብት መመደብ ነው፡፡ በመደብነው ሀብት ሥራ ተሠርቶ ስለሆነ ጥያቄ የሚመለሰው፣ ሊሠራ የሚችል ኃይል ደግሞ ወጣት ማደራጀት ነው፡፡ የተማሩ ወጣቶች አሉና አጫጭር ሥልጠናዎች ተሰጥቷቸው የተመደበውን ሀብት ወስደው የሕዝብን ጥያቄ የሚመልሱበት፣ ሥራ የሚፈጥሩበትና ሀብት የሚያፈሩበት ዓይነት አስተሳሰቦችን ነው እያሰብን ያለነው፡፡
ሌላው ለሥልጠና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ይኼንን ስንል እጅ የሚፍታታበት የጥበብ ሥልጠናዎችን ነው የቴክኒክ ሙያዎች ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ሙያዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሠለጥኑ የሚችሉ አሥር የሚሆኑ ኮሌጆች አሉ ቀደም ብለው የተገነቡ፡፡ የውስጥ አደረጃጀቶቻቸውን ፈጠን ብሎ ማሟላት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ወጣቶችን በየዘርፉ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ማድረግ የምንፈልገው በወጣቶቹ ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ አቅም መገንባት ነው፡፡ አቅም የተገነባለት ወጣት የትም ቢሄድ ሥራ ያገኛል፡፡ ብዙ ወጣቶች አሉን እስካልን ድረስ ብዙ ወጣቶችን አሠልጥነን ወደ ሌላው አካባቢ ማሰማራት ነው ሠራተኛ ወደሚፈለግበት አካባቢ፡፡ የእኛ ዋናው ትኩረት ያሉንን ዕድሎች በመለየት በትንሽ ጥረት ምላሹ ከፍተኛ በሚሆንበት አግባብ ለመሥራት ነው፡፡ ይኼንን ስንሠራ ሥራውን ሊመራ የሚችል የአመራር አቅም መፍጠርም አስፈላጊ ነው የሚሆነው፡፡ ከአመለካከት ጀምሮ ሌብነትን ተጠይፎ ውጤታማ የሆነ የሥራ ሥምሪት አከናውኖ፣ አሁን እኔ የምላቸውን ውጤቶች ሊያሳካ የሚችል የአመራርም ኃይል ማደራጀት ይኖርብኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ሰሞኑን ካቢኔ መድቤያለሁ፡፡ ካቢኔ ስመድብም ይኼንን ባገናዘበ መንገድ በዚህ መንፈስ ተነሳስቼ ወጣቶችንም ባማከለ መልኩ ነው፡፡ ጥሩ ልምድ ያላቸው፣ በትምህርት ብቁ የሆኑ፣ በኪራይና በመሳሰሉት ያልጨቀዩ እንዲሁም በዚሁ ስማቸው ሕዝብን ሊያገለግ የሚችሉ የተለያዩ ወጣቶችን ለማሳተፍ ነው የሞከርኩት፡፡ ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ ብቃት ያላቸውን አመራሮች እስከ ታች ድረስ ማሰማራት ከቻልን እኔ ያለኝ ራዕይ በአጭር ጊዜ ድህነትን በመዋጋትና የሥራ ዕድል በመፍጠር በየደረጃው ሁሉም በልቶ የሚያድርበት፣ በሒደት ግን የተሻለ ኑሮ የሚኖርበትና ፈጣን ዕድገት አስመዝግበን ይኼንን አካባቢ ለኑሮ የተመቸና ደህና ኑሮ የሚኖርበት ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በትንሹ እንነሳለን፣ እያሰፋን እንሄዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን የሲዳማ ክልል ዋና መቀመጫ የሆነችው ሐዋሳ ከተማ ከ20 ዓመታት በላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና ሆና በማገልገሏ ሳቢያ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ከተለያዩ የደቡብ አካባቢዎች መጥተው በብዛት በአካባቢው ይኖራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና ካሁን በፊት በተፈጠሩ ግጭቶችና በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት ሥጋት የገባቸው ነዋሪዎች ስላሉ፣ አዲሱ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነትና በአብሮነት የሚኖሩበት ለማድረግ ምን የታቀደ ነገር አለ?
አቶ ደስታ፡– ቀጣናው ቀደም ብሎም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ከሲዳማ ጋር በፍቅር የሚኖሩበት ነው አካባቢው፡፡ ሲዳማ በዚህ ይታወቃል፡፡ አብሮ በመኖር፣ ተካፍሎ በመብላትና በመጠጣት ይታወቃል፡፡ ምናልባት ይኼንን የክልልነት ጥያቄን ምክንያት በማድረግ በተገፋፉ ወጣቶች የተወሰኑ ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ ያንን ስህተት ለራሱ እንዳይሰፋ ያደረገው የራሱ የሲዳማ እሴት ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ችግር በተፈጠረ ጊዜ ከጥፋት ያዳነውም የሲዳማ ሕዝብ ነው፣ መልሶ ያቋቋመውም የሲዳማ ሕዝብ ነው፡፡ አጥፊዎችንም አሳልፎ ለሕግ የሰጠው የሲዳማ ሕዝብ ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ጥፋቱን ያወገዘ በመሆኑም ይህችን አንድ ዓመት ያለፍነው ያለ ኮሽታ ነው፡፡ ይኼ በራሱ ምን ያሳየናል ካልክ የቆየ የሕዝቡ ባህል፣ እሴቱ በአግባቡ ተጠብቆ እየተላለፈ መሆኑንና ሊበረዝ እንኳን በነበረበት ጊዜ ሕዝቡ የተከላከለበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ከዚህ አንፃር ይኼ ቀጣና ብዙ ችግር ይገጥመዋል ብዬ አላስብም፡፡ ችግር እንዳይገጥመውም ለማድረግ ግን በቀጣይ እየገነባን እንሠራለን፡፡ አብረውን ያሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አዲሱ የሲዳማ ክልል የእነርሱም ክልል ናትና ያገኘነውን በጋራ እየተቋደስንና እየተካፈልን አብረን በፍቅር እንኖራለን፡፡ እንዲህ ካልሆነማ ኢትዮጵያ አገራችን በአንድነት ልትቆም አትችልም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ አንድነታችንን አስጠብቀንና ተባብረን በጋራ መኖር ካልቻልን በዚሁ ፀንታ ልትቆም አትችልም፡፡
ሁለተኛ ይኼ ሲዳማን በሁለት መልኩ ይጎዳል፡፡ አንደኛ የሲዳማ ሕዝብ በወጣት የተሞላና በጠባብ ቦታ የሚገኝ ስለሆነ በራሱ ጊዜ ይፈልሳል፡፡ ካሁን ቀደም የሲዳማ ሕዝብ አይፈልስም ነበር፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ እዚህም እዚያም የሚገኘው የሲዳማ ወጣት ነው፡፡ ይኼ ነባራዊ ሁኔታ የወለደው የባህርይ ለውጥ ነው፡፡ ይኼ ለውጥ እየተጠናከረ ይሄዳል እንጂ፣ ሲዳማ ክልል በመሆኑ የሚገደብ አይሆንም፡፡ ቅድም ካስቀመጥኳቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ አንዱ የሰው ኃይል አሠልጥነን ወደ ሌላ አካባቢ ማሰማራት ነው፡፡ ለምን የእኛን መዋቅር ሊሸከም ስለማይችልና መዋቅሩ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የሰው ኃይል ስላለ ነው፡፡ ስለዚህ ፍላጎት ወዳለበት ቦታ ሄዶ መሥራት ስላለበት አብቅተን ገበያ እናወጣለን፣ ገበያተኛው ደግሞ መልምሎ ይጠቀማቸዋል፡፡ ከሲዳማ ክልል ውጪ የሲዳማ ተወላጆች ከክልሉ ውጪ የሚሰማሩበትና ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመጠቀም ነው እያመቻቸን ያለነው፡፡ ይኼ በመሆኑ ድንበር አበጅተን ሲዳማ ውስጥ ማንም መግባት የለበትም፣ መጠቀም የለበትም እያልን እኛ የማን ክልል ውስጥ ሄደን ልንሠራና ልንጠቀም ነው? በዚህ ዓይን ስለምናይ የአግላይነት አዝማሚያ ሲዳማ ውስጥ አይሠራም፡፡ ሁለተኛው ከእኛ ወደ ሌላው አካባቢ ሠራተኛ ማሰማራት ብቻ ሳይሆን የተሻለ ዕውቀት፣ ሀብትና ልምድ ያለው ሰው ወደ ሲዳማ እንዲመጣ ነው የምንፈልገው፡፡ ሀብቱን ይዞ ሲመጣ ትንሽ ቦታ ይሰጠዋል፣ ማሽነሪዎቹን ይተክላል፣ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል፣ ለሲዳማማ የሥራ ዕድልም ይዞልን ይመጣል ማለት ነው፡፡ ሥራ ይዞ መምጣት ሲባል የአምራች ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም ዘርፉ ለራሱ ከፍተኛ ሀብት ይዞ ይመጣል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በእነዚህ ዘርፎች የታደለች አካባቢ ነች ሲዳማ፡፡ ከፌዴራል መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ በሁለት ሰዓት ተኩል ጉዞ ይደረሳል፡፡ አሁን ደግሞ የአየር ትራንስፖርት እየተስፋፋ ይሄዳል፡፡ መሠረተ ልማት ስለተሟላ፡፡ የሞጆ-ሐዋሳ ፈጣን መንገድ እየተቃረበ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይኼ ዕድገት አዲስ አበባንና ሐዋሳን አንድ መንደር ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በኮንፍረንስ በቱሪዝምም ሆነ በሳምንት መጨረሻ መዝናኛዎች ሰዎች ወደ ሐዋሳ የሚደርስቡት ዕድል አለ፡፡ ይኼንን ዕድል ግን በራችንን ክፍት ስናደርግ ነው ልንጠቀም የምንችለው፡፡
ይኼንን ዕድል መጠቀም የሚቻለው ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ባለበት፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበትና እንግዳ ተቀባይነት ያለውና ሰው ወዶ የሚመላለስበት አካባቢ አድርጎ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን አስተሳሰብ በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንግዳውን ሕዝቡ ለራሱ እንዲንከባከብ ነው የምንፈልገው፡፡ ፈገግ ብሎ አስተናግዶ አስደስቶ እንዲሸኝ ማለት ነው፡፡ የከተማ ሀብት ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ይምጣልን እንጂ ሰው ለምን መጣብን ልንል አንችልም፡፡ ሲዳማ ክልል ስትሆን ከኢትዮጵያ ተለይታ የወጣች አይደለችም፡፡ ሲዳማ የኢትዮጵያ አካል ናት፡፡ የአስተዳደር ሁኔታ ብቻ ነው የተለወጠው፡፡ ይኼ የአስተዳደር ሁኔታ ደግሞ ምቹ ለማድረግ በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ሲዳማን እንደ ራሳቸው ክልል በማየት በጋራ የምንገነባትና የምንጠቀምባት አድርገን ነው የምንወስደው፡፡ ስለዚህ እኔ የኢትዮጵያ ዱባይ እናደርጋታለን ብዬ ነው የማስበው፡፡