የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ አንድ ሥር የተዘረዘሩትን ዘጠኝ ክልሎች በአባልነት ይዞ ከተመሠረተ ወዲህ፣ የመጀመርያውና አሥረኛው ክልል ከደቡብ ክልል ተወልዷል፡፡ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ዞኖች በጉልህ ከታዩ የክልል እንሁን ጥያቂዎች መካከል አንዱ የሆነው የሲዳማ ጥያቄ፣ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ተቀባይነትን አግኝቶ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ መወሰኑን ተከትሎ፣ 12 የሚሆኑ የተለያዩ ዞኖች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
እነዚህ ዞኖች ጥያቄያቸውን በዞኖቻቸው ምክር ቤቶች አፅድቀው ሕዝበ ውሳኔ ይደራጅላቸው ዘንድ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቢያቀርቡም፣ የሲዳማን ጥያቄ ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጀው የደቡብ ክልል ምክርት ቤት ጥያቄዎቹን በአጀንዳነት አንስቶ ሳይወያይባቸው ከአንድ ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥያቄያቸውን የሚያነሱ ዞኖች በተወካዮቻቸው አማካይነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ፣ ከበርካታ የክልልና የፌዴራል መንግሥታት የሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይቶችን ያደረጉ ቢሆንም፣ እነዚህ ውይይቶች በአንድም ሆነ በሌላ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል፡፡
የውይይቶቹና የምክክሮቹ ውጤት አልባነት በዋናነት የሚመሠረተው ጥያቄዎቹን የሚያነሱት ዞኖች (ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች) ጥያቄያችን ሕገ መንግሥታዊ ስለሆነ ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት መብታችን ይረጋገጥልን በሚለው ፍላጎትና በአስፈጻሚው አካል ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢሆንም፣ በጥናት ላይ የተመሠረተና በመረዳት ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ማስተላለፍ ይገባልና ጊዜ ወስደን እያጠናንና እየተወያየን በሒደት ከውሳኔ እንድረስ በሚለው አስተሳሰብ መካከል ባሉ ልዩነቶችና መሳሳቦች ሳቢያ ነው፡፡
እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም ቅሉ ተደጋጋሚ ውይይቶችና ምክክሮች መደረጋቸው የቀጠለ ሲሆን፣ የቀድሞው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በዩኒቨርሲቲ ምሁራንና በፓርቲው ተወካዮች አማካይነት ያስጠናውን ጥናት ጨምሮ፣ በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎችን በቅጡ ለመረዳትና ምላሽ ለመስጠት ያግዛሉ በሚል ዕሳቤ ሦስት ገደማ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ጥናቶች በፓርቲና በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል መሪነትና አነሳሽነት የተከናወኑ በመሆናቸው ሳቢያ፣ በበርካታ የጠያቂ ክልሎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
ይኼንን የደቡብ ጉዳይ በሚመለከት ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የ2013 በጀት ዓመት በጀትን በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ አደረጃጀት በደቡብ ክልል ብቻ ሳይሆን የትም የታክቲክ ጉዳይ በመሆኑ ዘላቂ የሚባል አደረጃጀት የለም ብለዋል፡፡ የአገር ልማትን፣ ሰላምን፣ የሕዝቦችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍጎቶችን ለማሳካት እንደሚሠራ፣ ስለዚህም በዞን፣ በወረዳና በክልል ደረጃ ለውጦች ሊካሄዱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹የደቡብ ክልል ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የማደግ አቅም ያለውና በከፍተኛ ትጋት የሚታወቅ ሕዝብ ያለበት አካባቢ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በነበረው አደረጃጀት ምክንያት ልማት ተደናቅፏል፡፡ በዚህ አግባብም እኛ በምንፈልገው ልክ ማደግ አልቻልንም ነው እንጂ፣ በደቡብ ክልል ውስጥ በቋንቋዬ መማር አልቻልኩም፣ በቋንቋዬ መጠቀም አልቻልኩም፣ ራሴን በራሴ ማስተዳደር አልቻልኩም ማለት አይቻልም፡፡ በልዩ ዞን፣ በልዩ ወረዳ እያንዳንዱ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን ሁኔታ ፈጥሯል፤›› በማለት ተሟግተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ነገር ግን አደረጃጀቱ ሕዝብ ያላወያየና ያላማከረ ስለሆነ፣ በአቅጣጫም ደቡብ ያልሆኑና ምዕራብ የሆኑ የአገሪቱን ክፍሎች ያካተተ፣ እንዲሁም ወደ ክልል ከተማ ለመምጣት ብዙ ርቀትን መጓዝ የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ በክልሉ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት አዳጋች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የምድር ገነት በማለት የገለጿቸው ካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች የወረዳን ያህል የመንገድ ሽፋን የሌላቸው ናቸው ሲሉም የጥያቄዎቹን አግባብነት ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ እንደ እሳቸው በደቡብ ክልል ከዞን ዞን ዞሮ ሕዝብን ያወያየ መሪ፣ እንዲያውም የክልል መሪ እንደሌለ የተናገሩትና ይኼንንም ያደረጉት የደቡብን ጉዳይ ከመሠረቱ ተገንዝቦ መፍታት ይሻላል በሚል ሙሉ ዕምነት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በችኮላ አንድ ጥያቄ ለመመለስ ብለን ሌላ ጥያቄ እንዳንፈጥር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መሠረታዊ በሆነ መንገድ ችግሩን እንደምንፈታ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው ጊዜ ወስደን መነጋገር ያስፈልጋል ያልነው፤›› ብለዋል፡፡
ይኼንንም ሒደት ይደግፍ ዘንድም በደኢሕዴን የተጠናው ጥናት በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ፀድቆ ይተግበር ሲባል፣ በርካታ የክልሉ ተወካዮችና የሥራ ኃላፊዎች ጥናቱ ክፍተቶች እንዳሉበትና ‹‹ካድሬዎች ያጠኑት›› ነው በመባሉ፣ እንደገና በእሳቸው አነሳሽነት በርካታ አባላት ያሉት የደቡብ ክልል ተወላጆችን ያቀፈ ቡድን ተዋቅሮ ‹‹የሰላም አምባሳደሮች›› በሚል ስያሜ በሁሉም ዞኖች ተንቀሳቅሶ በማጥናት ግኝቶችን በምክረ ሐሳብ ደረጃ ማቅረቡንና ይኼም ለምክክር መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ በውይይት ወቅት የመጀመርያውና የሁለተኛው ጥናቶች ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ተመሳሳይ እንደሆኑ፣ የወረዳዎች በዚህ የይካለሉ አይካለሉ የሚሉ ልዩነቶች ብቻ እንደተስተዋሉባቸው በማስረዳት፣ የሁለተኛው የሰላም አምባሳደሮች ጥናት ደግሞ ከመጀመርያው ጥናት ጠንካራ ጎኖች ትምህርት አልወሰደም የሚል ትችት እንደቀረበበት ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የሁለቱንም ጥናቶች ክፍተት ለመሙላት የሁለቱ የጥናት ቡድኖች አባላት በጋራ እንዲሠሩ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት፣ ሁለቱ ቡድኖች በጋራ ሠርተው ጥናታቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በበኩሉ ጥናቱን እንዳለ አልወስድም በማለት በቋሚ ኮሚቴ ይመርመር በማለት ጉዳዩን ወደ ቋሚ ኮሚቴ በመምራት ውይይት እያደረገበት ያለ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም ጉዳዩ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የሚመለከት እንደሆነ፣ ከእግዲህ በኋላ አስፈጻሚው አካል በደቡብ ክልል ጉዳይ ገብቶ ለውይይት ጊዜ እንደማያጠፋ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ሰነድ እንደማያመጣና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚ ኮሚቴው አማካይነት ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስረድተዋል፡፡
በደቡብ ክልል ለብቻቸው ክልል ለመሆን የጠየቁ ዞኖች እንዳሉ ሁሉ በርከት የሚሉት በቋንቋ፣ በባህልና በመልክዓ ምድር ከሚቀራረቧቸው ጋር በጋራ ክልል ለመመሥረት ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የደቡብ ክልል ሕዝብ መንግሥት ለእኛ ጥያቄ ትኩረት አልሰጠም፣ አላወያየንም፣ ሐሳባችንን አላደመጠም ቢል በሕግ ባይጠየቅ ግፍ የሚሆን ይመስለኛል፣ ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባልና ጊዜያዊ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ባልቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተናገሩት መሠረት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሄድ መደረጉ፣ ከመጀመርያው ጀምሮ ሲጠየቅ የነበረ የሕግ አግባብ ያለው አካሄድ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡ ይኼ እኛም ያቀረብነው ጥያቄ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ የሕዝብ ተወካይ በመሆኑ፣ ተወያይቶ ለጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጉዳዩን በሙሉ ድምፅ አፀድቆ ለክልል ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ ይደራጅለት ዘንድ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፣ የክልሉ ምክር ቤት ጉዳዩን በአጀንዳነት ይዞ ሕዝበ ውሳኔ ይደራጅ ዘንድ ውሳኔ ማሳለፍ ባለመቻሉ የዞኑ ምክር ቤት ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደመራው፣ እንዲሁም የክልልነት ጥያቄን የሚያስተባብር ኮሚቴ እንዲዋቀር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት የሆኑ የወላይታ ተወካዮች በምክር ቤቱ ድምፃቸው እየተሰማ ስላልሆነና በተደጋጋሚ የሚያሰሙት ቅሬታ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ምክር ቤቱን ጥለው መውጣታቸውን ያስታወሱት አቶ ማቴዎስ፣ አባላቱ ይኼንን ያደርጉ ዘንድ ከፓርቲውና ከሕዝብ ከፍተኛ ግፊት ነበር ብለዋል፡፡
‹‹አባላቱ ምክር ቤቱን ለቅቀው መውጣታቸው የእኛም ጥያቄ ነበር፡፡ ሕዝቡም እኛም ግፊት እናደርግባቸው ነበር፡፡ አባላቱም ይኼንን የሕዝብ ግፊትና ጥሪ ተቀብለው ከምክር ቤቱ መውጣታቸው የሕዝቡን አንድነት የሚያጠናክር ውሳኔ ነው፡፡ የዞን ምክር ቤት ውሳኔዎችም በተመሳሳይ፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በተደጋጋሚ በነበሩ የሕዝብ ውይይቶች፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር በነበሩ ስብሰባዎች ላይ ይነሱ የነበሩ ጉዳዮች ሁሉ የሕዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን ማሳያ ውሳኔ ነው የሚሉት አቶ ማቴዎስ፣ ‹‹መንግሥት እስካልሰማን ድረስ በምክር ቤት መቆየት የለባቸውም የሚለው የሕዝብ ጥያቄ ስለሆነ፣ ውሳኔያቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ግፊት ያደርጋል፣ መንግሥትም እንዲያዳምጥ ያደርጋል፤›› ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፓርላማ ማብራሪያቸው ያነሱትና በደኢሕዴን የተደረገው ጥናት፣ ደኢሕዴን በሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በፓርቲው አመራር እመልሳለሁ በማለት ያስጀመረው እንደሆነ፣ ይኼም ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ውጪ እንደሆነ በመግለጽ የሚከራከሩት አቶ ማቴዎስ፣ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልገው ጥናት ሳይሆን ሕዝበ ውሳኔ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የጥናቱ ውጤት የወላይታን ጥያቄ ያላገናዘበና ከግኝት የተነሳ ጥናት ነበር፤›› በማለትም ይከራከራሉ፡፡
በሁለተኛነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረው 80 ሰዎችን ያቀፈው የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ያጠናው ጥናት፣ የቀድሞው ጥናት ላይ የታዩትን ክፍተቶች ለማስተካከል በማለም መስሏቸው እንደነበር ገልጸው፣ ይኼም የሕዝብን ጥያቄ ያላገናዘበ ስለነበር ውድቅ ሆኗል ይላሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄን ወደ ዳር ትቶ ፖለቲካዊ ምላሽ በሚሰጥ መንገድ በመቅረቡ እኛም ተቃወምነው፤›› ብለዋል፡፡
ስለዚህ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በመተላለፉና አስቀድሞም ጥያቄው ይኼንን መንገድ ተከትሎ ምላሽ እንዲያገኝ ፍላጎት ስለነበራቸው፣ አሁን ጉዳዩ የያዘውን መስመር እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በማብራሪያቸው የደቡብ ክልል አሥር ክልል ቢሆን በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ክልሎችን የሚመለከት 21ኛ የክልል ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማቋቋም እንደሚቻል በመግለጽ፣ ጥያቄው የዜጎችን ተጠቃሚነት ከሚመለከት ጉዳይ አንፃር ብቻ መታየት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ይሁንና የክልልነት ጥያቄዎችን ከዚህ ውጪ በሆነ አግባብ ፕሬዚዳንት ለመሆንና ላንድክሩዘር ለመንዳት ሲባል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መቅረት እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ከሁለት ቤት መብላት የሚፈልጉ በመኖራቸው ጉዳዩን ሌላ መልክ እያስያዙት ነው በማለት፣ በመንግሥት ሀብትና መሠረተ ልማት እነዚህን ግባቸውን ለማሳካት የሚታትሩ እንዳሉ በመግለጽ ወቅሰዋል፡፡
በደቡብ ክልል የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ያነሱ ዞኖች ሙሉ በሙሉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ ይሰጣቸው ዘንድ ጥያቄያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጉዳዩን በቋሚ ኮሚቴ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን መወሰኛ አዋጅ መሠረት ምክር ቤቱ ጥያቄዎች በቀረቡለት በሁለት ዓመት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥ የተደነገገ ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ምላሽ ባይሰጥ ምን ዓይነት ሕጋዊ መንገድ እንደሚኖር ግን የተጠቀሰ ሐሳብ የለም፡፡