Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በማዘጋጃ ቤታዊ ታክስ ላይ አተኩሯል  

ተዛማጅ ፅሁፎች

– አነስተኛ ግብር ከፋዮች የ25 በመቶ ቅናሽ ይደረጋል ብሏል

– የነጋዴ ተወካዮች ከመመርያ እስከ ታክስ ምሕረት አተገባበር ባለው ላይ ቅሬታና ሥጋት ገብቷቸዋል

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዘንድሮ ሊሰበስብ ስላቀደው የከተማ አስተዳደሩ ገቢ፣ በተለይም በግብር ማሳወቂያ ወቅት ነጋዴዎች በወቅቱ ቀርበው ግብር እንዲከፍሉ ባሳሰበበት መድረክ፣ በ2013 በጀት ዓመት የሚሰበሰበው ገቢ በታክስ ከፋዩ ላይ ጫና እንዳይኖረው በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ላይ ማተኮሩን አስታወቀ፡፡  

የቢሮው ኃላፊዎች ይፋ እንዳደረጉት፣ ከዚህ ቀደም በፌዴራልም ሆነ በከተማ ደረጃ ከተደረጉ የታክስ ምሕረትና የዕፎይታ ዕርምጃዎች በተጨማሪ ለደረጃ ‹‹ሐ›› አነስተኛ ግብር ከፋዮች እስከ 25 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ይደረግላቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮው ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ እንዲሁም ምክትላቸው አቶ ዮሴፍ ግርማ በመሩትና ሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለታደሙ የከተማው ነጋዴዎች ማኅበራት ተወካዮች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ይህንኑ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ሺሰማ እንዳስታወቁት፣ በግብር ማስታወቂያ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ግብራቸውን በማሳወቅ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በተገቢው መንገድ ታክስ ለከፈሉ የደረጃ ‹‹ሐ›› ነጋዴዎች፣ ከሚከፍሉት ታክስ ላይ የ25 በመቶ ቅናሽ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡ ይህ እንደ ማበረታቻ የሚታሰብ ሲሆን፣ ተፈጻሚነቱም እስከ ሐምሌ 30 ቀን ባለውና በተቀመጠው ጊዜ ሰሌዳ መሠረት የሚፈለግባቸው የታክስ ዕዳ ለከፈሉ ብቻ ይሆናል ተብሏል፡፡

በታክስ አስተዳደር አዋጅ እንዲሁም በገቢ ግብር አዋጅ መሠረት የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የታክስ ማሳወቂያ ጊዜ ከላይ የተቀጠሰው ሲሆን፣ የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 212 ዓ.ም. ታክስ የሚያሳውቁበት ሲሆን፣ የደረጃ ‹‹ሀ›› ወይም የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የጊዜ ሰሌዳ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

 በመጪዎቹ አራት ወራት ውስጥ ከከተማው ግብር ከፋዮች 20.8 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ ለማሰባሰብ እንደታቀደ፣ በዓመቱም ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ የከተማው ገቢ ውስጥ ከታክስ የሚሰበሰበው ከ43.3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ለነጋዴ ማኅበራት አመራሮች ገልጸውላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የገቢ መጠን ከወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ብሎም ሄድ መለስ ከሚለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አኳያ ሊሰበሰብ መቻሉ ብሎም ነጋዴው ላይ ጫና አለማሳደሩ ምን ያህል እንደታየ ከነጋዴዎች ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡

እንደ አቶ ሺሰማ ማብራሪያ ከሆነ ከተለመደው የታክስ ገቢ የዘለለ አዲስ ወይም ተጨማሪ የታክስ ተመን ለውጥ አልተደረገም፡፡ ‹‹የቫት መጠን ጭማሪ  አልተደረገበትም፡፡ 15 በመቶ የነበረው 17 በመቶ ይሁን አልተባለም፡፡ አልጨመረም፡፡ ይልቁንም ሌሎች ከዚህ ቀደም ያልታዩ የገቢ ምንጮች ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ትልቅ የገቢ አቅም ስላለ ነው የገቢ ዕቅዱ ይህን ያህል የሆነው፤›› በማለት ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ገቢ እንደሚገኝ መታቀዱን አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር የታክስ ጫና ላለመፍጠር መጠንቀቁን የሞገቱት አቶ ሺሰማ፣ በዚህ ረገድ በርካታ ለውጥ የሚደረግባቸው የአገልግሎት ተመኖች እንዳሉ፣ እነዚህም ላይ የሚደረገው ለውጥ አገልግሎቱን በሚያገኘው ተጠቃሚ ላይ ምንም ዓይነት ጫና እንደማያሳድሩ አስታውቀዋል፡፡ በዋቢነት ሲያስረዱም፣ ሐምሌ 21 ቀን 1945 ዓ.ም. በወጣ የአገልግሎት ተመን መሠረት 50 ሳንቲም የሚከፈልበት የማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት ተመን አሁንም ድረስ እየተሠራበት እንደሚገኝ በማመላከት ነበር፡፡

ሌላም ተጨማሪ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም. አካባቢ በወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ላይ የተቀመጡ የአገልግሎት ማስከፈያ ተመኖች ማሻሻያ ይደረግባቸዋል፡፡ ለአብነትም ለመኪና ማቆሚያ ቦታ በሕግ እንዲከፈል የተቀመጠው 50 ሳንቲም እንደሆነ ጠቅሰው፣ በከተማው በተጨባጭ ሁኔታ ግን እስከ 300 ብር ለመኪና ማቆሚያ የሚከፈልበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አባባላቸው እውነታ እንዳለው ከሚያረጋግጡ መካከል ለምሳሌ በአትክትል ተራ ጭነት አራግፈው የሚወጡ መኪኖች ለቆሙበት 300 ብር እንዲከፍሉ የሚደረግበት አሠራር አንዱ ነው፡፡

በሆቴል መስክ በተለይም የመኝታ አገልግሎት ላይም ታሳቢ ተደርገው ለጊዜው እንዳይካተቱ የተደረጉ በርካታ የገቢ ምንጮች መኖራቸውም ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ከ10 እስከ 15 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይከለሱ የቆዩ የቦታ ሊዝ፣ የኪራይ ተመንን የመሳሰሉ አገልግሎቶች ላይ የተመን ጭማሪ በማድረግ፣ በዚህ ዓመት ከተበሰበሰው የአምስት ቢሊዮን ብር የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ይልቅ 13 ቢሊዮን ብር ያህል ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡  

ይህም ሆኖ በዚህ ዓመት ከታቀደው የ37 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ ውስጥ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን፣ ለመጪው ዓመት የታቀደውም 43 ቢሊዮን ብር ከተማው ማመንጨት ከሚችለው አኳያ ይህን ያህል ጫና እንደማያሳድር የሚጠቅሱት አቶ ሺሰማ፣ በከተማው የሚከነወኑ በርካታ ፕሮጀክቶች በአብዛኛው የሚሸፈኑት ከሚመነጨው ገቢ እንደሆነ በማስታወስም ነጋዴው በወቅቱ ግብር በመክፈል እንዲተባበርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ የአድዋ ፓርክ፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት የሚሻሻለው መንገድና አብረውት የሚገነቡ አገልግሎት መስጫዎች፣ ለትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ሥራዎች፣ ለማኅበራዊ ዋስትና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለወጣቶች ማበልፀጊያና ሌሎችም ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ሥራዎች ተጠቅሰዋል፡፡

ገቢዎች ቢሮ ነጋዴዎች ላይ የሚፈጠር የታክስ ጫና እንደማይኖር ሲያስረዳም በ2009 ዓ.ም. የተሻሻለው የቀን ገቢ ግምት ባስከተለው ጫና ከንግድ የወጡና ፈቃዳቸውን የመለሱ ነጋዴዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን በማስታወስ ጭምር ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም. 35,377 ግብር ከፋዮች ከንግድ ሥርዓቱ ለመውጣት መገደዳቸውን አቶ ሺሰማ አስታውሰዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. 18,343 ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን በመመለስ ከሥራ መውጣታቸውን፣ በ2011 ዓ.ም. ይህ ቁጥር ወደ 17,417 ዝቅ ማለቱንና በዚህ ዓመትም ይበልጡን እንደሚቀንስ ያላቸውን ተስፋ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የታክስ ጫና ከማድረግ ይልቅ፣ የነጋዴውን ችግሮች በመፍታት፣ አሠራሮችን በማሻሻል፣ በመነጋገር፣ ምሕረት በማድረግ ጭምር የመጣ ለውጥ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዮሴፍ በበኩላቸው ከ340 ሺሕ በላይ የከተማው ነጋዴ ባለፈው ዓመት ያለምንም ጫጫታ የሚፈለግበትን ግብር በሰላም እንደከፈለ ጠቅሰዋል፡፡

የገቢዎች ቢሮ ይህን ቢልም ነጋዴዎችን በመከወል ጥያቄዎችን ያቀረቡ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ፎረም፣ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር፣ የአዲስ አበባ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የመርካቶ ነጋዴዎች ማኅበርና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ከዚህ ቀደም ሲያጨቃጭቁና አሁንም ተገቢውን ምላሽ አላገኙም ያላቸውን ጥያቄዎች በአመራሮቹ በኩል አስተጋብቷል፡፡

ከልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር አመራሮች መካከል የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ፣ በልኳንዳ ንግድ ላይ የሚጣለው የታክስ ተመን የተደነገበበት መመርያ በ2010 ዓ.ም. ቢወጣም፣ በ2012 ዓ.ም. ወደ ትግበራ መግባቱ አግባብ እንዳልሆነ አስታውሰው፣ ለማኅበሩም ሆነ ለአባላቱ የመመርያው ሰነድ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሊያገኙ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አየለ ከሆነ መመርያ 138/2010 የአንድ ከብትን አማካይ ክብደት በመደንገግ ምን ያህል ሊሸጥ እንደሚችል፣ የቁም ከብት ንግድ በደረሰኝ እንዲገበያይ፣ ደረሰኝ በማይቀርብበት ወቅት ገዥው ቫውቸር እንዲቆርጥ ይጠይቃል፡፡

ይህም ሆኖ ‹‹ከአንድ በሬ 148 ኪሎ ሥጋ ይገኛል ተብሎ የተቀመጠው ትክክል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ በሬ ሳር እንጂ ኬክ አይበላም፤›› በማለት የተጋነነ ግምት መቀመጡን ጠቅሰው እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ ይህ መመርያ እየተሻሻለ ነው ቢባልም በግልጽ ስለመሻሻሉ ወይም ለውጥ መደረጉ ለማኅበሩ እንዳልተገለጸለት፣ አባለቱም ተሻሽሏል የተባለውን መመርያ እንዳላገኙት አስታውቀዋል፡፡ በመመርያ 138/2010 መሠረት፣ በ2010 ዓ.ም. ልኳንዳ ነጋዴዎች ባመኑት ሒሳብ ታክስ ከፍለው ከዕዳ ነፃ ማረጋገጫ ወይም ክሊራንስ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹አሁንስ በየትኛው መመርያ ነው ታክስ የሚስተናገዱት›› በማለት ለኃላፊዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ዘርፉ ከ3000 በላይ ሠራተኞች ላሉት ለአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ ለቆዳና ለሌሎችም የከብት ቀንድን በመጠቀም ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት ምንጭ ቢሆንም፣ ተገቢውን ትኩረት እንዳልተሰጠው ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ሌሎችም የልኳንዳ ማኅበር አመራሮች ተመሳሳይ ቅሬታ በማሰማት፣ የከተማ አስተዳደሩ በሥጋ ንግድ ላይ ያስቀመጣቸውን የምዘና አሠራሮች እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡ የልኳንዳ ቤቶች አንደኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ደረጃ ዝቅተኛ ወይም አነስተኛ ደረጃ እየተባሉ የተመደቡበት አሠራር እንዲስተካከል ሲጠየቅ፣ ‹‹ዝና ያለው፣ ከመንገድ ዳር የሚገኝ ወዘተ.›› እየተባለ ለልኳንዳ ቤቶች ደረጃ መውጣቱን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገቢዎች ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ግርማ፣ ከልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር የቀረበው ጥያቄ አግባብነት ቢኖረውም ከልኩ ያለፈና አብሮ ከጅምሩ ጀምሮ ማኅበሩ ተሳትፎበት፣ ከአማራ ክልል የተገኘ ተሞክሮ ተወስዶ የሚሠራበት እንደሆነ በመግለጽ አብራርተዋል፡፡

ሌሎችም ለጋራዥና ለአውቶሞቲቭ ዘርፉ ትኩረት አልተሰጠውም የሚሉትን ጨምሮ፣ በአዲሱ በጀት ዓመት እንደሚሰበሰብ የሚጠበቀው ታክስ ነጋዴው ከሚገኝበት የሥራ መቀዛቀዝ፣ የኮሮና ሥጋትና የፖለቲካ አለመረጋጋት አኳያ ሥጋት እንደሚፈጥር የገለጹ የማኅበራት ተወካዮች ሥጋታቸውን አሰምተዋል፡፡ የአዲስ አበባ እህል ነጋዴዎች ማኅበር በበኩሉ ሕገወጥ በሆኑ ነጋዴዎች በየመኪናው እየተጫነ የሚሸጠው እህል ቁጥጥር እንዲደረግበት ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ጥያቄ ሲያቀርብበት የቆየውና በቀን ገቢ ግምት ላይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሠራው የግመታ ሥራ ያስከተለው የታክስ ጫና ያመጣው ዕዳ ላይ ምሕረት መደረጉ ማኅበሩ አስታውሶ፣ ይሁን እንጂ ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ላሉት የታክስ ዕዳዎች የተደረገው የዕዳ ስረዛና ምሕረት ተፈጻሚነቱ ላይ ሥጋት እንዳደረበት ማኅበሩ  ጠቅሷል፡፡ የሥጋቱ መንስዔም ምሕረቱ የተደረገላቸው ባለዕዳዎች ዝርዝራቸው በኮምፒውተር በመያዙና ይህን እንዲስተካከል አለመደረጉ ስለሚነገር የፈጠረው ሥጋት እንደሆነ የማኅበሩ ተጠሪዎች አሳስበዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ቅሬታዎችና ሥጋቶች በተስተናገዱበት መድረክ እንደተገለጸው በከተማው ከ340 ሺሕ ያላነሱ ግብር ከፋዮች፣ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለኮሮና ወረርሽኝ በማያጋልጥ መንገድ በየመሥሪያ ቤቱ እየተገኙ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ የከተማው የታክስ መሥሪያ ቤት አሳስቧል፡፡

በከተማው ነጋዴ ግብር ከፋይ ከሆኑት መካከል ከ227 ሺሕ በላይ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች፣ ዓመታዊ ሽያጫቸው እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚስተናገዱ ቢገለጽም፣ የተወሰኑ ቀናት እንዲጨመሩ ጥያቄ ሲቀርብ ነበር፡፡ በከተማው በደረጃ ‹‹ለ›› ወይም በመካከለኛ ግብር ከፋይነት የተደለደሉትና ዓመታዊ የሽያጭ መጠናቸው እስከ ከ500 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሆኑ፣ 46 ሺሕ ገደማ ግብር ከፋዮች ሲኖሩ፣ በከፍተኛ ግብር ከፋይነት ወይም በደረጃ ‹‹ሀ›› የተካተቱትና ዓመታዊ ሽያጫው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ 742 ግብር ከፋዮች አሉ፡፡

የከተማው ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ ለአስተዳደር እንዲመች በሚል ማይክሮ ወይም አነስተኛ ታክስ ከፋዮች በማለት ሽያጫቸው ከ500 ሺሕ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሆኑትን በየወረዳው ያስተናግዳል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን እስከ 40 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያላቸውን መካከለኛ ግብር ከፋዮች በክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲያስተናገዱ፣ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ ያላቸው ድጋሚ በሁለት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንዲስተናገዱ እየተደረገ ይገኛል፡፡  

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የከተማው የታክስ ገቢ በ2009 ዓ.ም. ከነበረው የ23 ቢሊዮን ብር፣ አሁን ላይ ወደ 43 ቢሊዮን ብር እንሚያድግ ይጠበቃል፡፡ በ2010 ዓ.ም. 27.4 ቢሊዮን ብር ከታክስ የተሰበሰበ ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም. 32.2 ቢሊዮን ብር፣ በዚህ ዓመት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል፡፡

 

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች