Thursday, June 1, 2023

የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትና የህዳሴ ግድብ ድርድር ቀጣይ መንገዶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ መገንባት ከጀመረ ወደ አሥረኛ ዓመቱ እየገሰገሰ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የግድቡ መሠራት ተፅዕኖ ያሳድርብናል ብለው ከሚሰጉት የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ግብፅና ሱዳን ጋር ተደጋጋሚ ድርድሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳን ድርድሮቹ በቴክኒክና በፖለቲካ ድጋፍ ያለው፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጥናት የታገዘ ቢሆንም፣ አንዴ ገባ አንዴ ወጣ እያለና ለወራት ተቋርጦ እየቀጠለ መቋጫ ሳያገኝ እዚህ ደረጃ ደርሷል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከግድቡ በስተኋላ ያለውን የውኃ ማቆሪያ ሥፍራ በማስመንጠር በሐምሌ ወር መጀመርያ በግድቡ የመጀመርያ የውኃ ሙሌት ለመጀመር ያላትን ዕቅድ ይፋ ካደረገች ወዲህ፣ ግብፅ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ መልክ እንዲይዝና ኢትዮጵያ በጫና ውስጥ ገብታ የግድቡን ሙሌትና የውኃ አለቃቀቅ በግብፅ ፍላጎት መሠረት እንዲሆን ለማድረግ ርብርቧን ከወትሮው በጠነከረ መንገድ ስታስኬድ ተስተውሏል፡፡

በዚህም የተወሰነ ስኬት በማስመዝገብ የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግሥት በተመልካችነት/አመቻችነት ስም ወደ ድርድር አዳራሾች በመግባት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን እንዲያሳድሩ ያደረገች ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ድርድሩ በሦስቱ የአፍሪካ አገሮች መካከል ሆኖ ሳለ እናንተ ያዘጋጃችሁትን የስምምነት ሰነድ ለመፈረም ፈቃደኛ አይደለሁም ስላለችና በስተመጨረሻም ድርድሩ በመቋረጡ ምክንያት ጣልቃ ገብነቱ ጉዳት ሳያደርስ እንዲቀለበስ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም አሜሪካና የዓለም ባንክ ያልተሰጣቸውን ሚና በመጫወት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ ቆመዋል በማለት በተደጋጋሚ ወቀሳ በመሰንዘሯ፣ አገሪቱ ዳግም በዓለም ባንክና በአሜሪካ ታዛቢነት ወደሚደረገው ድርድር ሳትመለስ ቀርታለች፡፡

እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2020 መጨረሻ ከተቋረጠው ከዚህ ድርድር በኋላ ሦስቱ አገሮች ደግሞ በጠረጴዛ ዙሪያ ሳይገናኙ ወራት ሲቆጠሩ፣ የግብፅ መንግሥትም ኢትዮጵያ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ዳተኛ በመሆኗ ለቀጣናው የደኅንነት ሥጋት እየፈጠረች ነው በማለት ወንጅሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲመለከተው ከአንዴም ሁለቴ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ከአንድ ሳምንት በፊት ባደረገው ስብሰባ ጉዳዩን በአጀንዳነት ለመያዝ በተደረገው የድምፅ መስጠት ሒደት ‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች› በሚል መርህ ቻይና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን፣ ይኼንን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ሦስቱን አገሮች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲገናኙ አድርጓል፡፡

ዓርብ ምሽት ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ግድቡን ለመሙላት በቀሩት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከስምምነት ለመድረስ አስበው ወደ ድርድር የተመለሱ ሲሆን፣ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት የጽሕፈት ቤቱ አባላት የሆኑት ኬንያ፣ ማሊና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎች ዕገዛ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት የተያዙና መፍትሔም እየተበጀለት እንደሆነ ከግምት በማስገባት አገሮቹ ለፀጥታው ምክር ቤት እንዲያሳውቁ ከመግባባት ሲደረስ፣ ይኼንን የድርድር ሒደት ሊያደናቅፍ ከሚችል ማንኛውም ድርጊትና አላስፈላጊ የሚዲያ መግለጫዎች አገሮቹ እንዲቆጠቡ ኅብረቱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ይሁንና የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ በፀጥታው ምክር ቤት በአጀንዳነት ተይዞ ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ ጉዳዩ ‹‹ሰላምና ፀጥታ በአፍሪካ›› በሚል ርዕስ ሥር ለድርድር መቅርቡ ግን በርካቶችን ግር አሰኝቷል፡፡ ይኼም በአሜሪካ ተፅዕኖ ጉዳዩ እንዲካረርና ሌላ ትርጉም እንዲሰጠው፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ፍላጎት እንድትገዛ ጫና ለማድረግ ያለመ ነው ሲሉ በርካቶች ተከራክረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በመድረኩ አስተያየታቸው ያንፀባረቁ የአገሮች ተወካዮች ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት በመያዙ፣ እንዲሁም ሦስቱ አገሮች ደግሞ ወደ ድርድር በመመለሳቸው አድናቆታቸውን በመግለጽ ድርድሩ ሰጥቶ መቀበል ስለሆነ፣ ይኼንን መርህ በተከተለ አኳኋን የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቃኝ አሳስበዋል፡፡

ጉዳዩን ዓለም አቀፍ መልክ ለማላበስ ያደረገችው ጥረት በመጠኑም የተሳካለት ግብፅ ከአሜሪካ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ እንዲሁም የዓረብ ሊግ ስትኳትን ቆይታ ወደ አፍሪካ መመለሷና አስቀድማ ለአደራዳሪነት ያልተቀበላቸው የአፍሪካ ኅብረት በጠራው ስብሰባ ለድርድር መቀመጧ፣ በሁለት ወገን ትርጉም ያለው እንደሚሆን ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የመጀመርያው ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› ተብሎ ለሚወቀሰው የአፍሪካ ኅብረት የአኅጉሪቱን ትልልቅ አገሮች ለዓመታት ያነጋገረ፣ እንዲሁም አንዳንዴ የጦርነት አዋጅ የሚመስሉ ዛቻዎችን ያስተናገደ ድርድር በኃላፊነት ወስዶ እምነት የሚጣልበት ድርድር ማከናወን ከተቻለ፣ ለኅብረቱ ታሪክ ቀያሪ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም ይኼ ጉዳይ መቋጫ ሳያገኝ ከእጅ እንዳይወጣ ለማድረግ ኅብረቱ የሚታትርበት ጊዜ እንደሚሆን በማመላከት፣ ውጤቱ ምንም ሆነ ምን በኅብረቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትለት ዕድል እንደሚሆን ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ኢትዮጵያ ጉዳዩ ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የሳበ ቢሆንም ለሚቀሩ አለመግባባቶች ከተፅዕኖ ውጪ የሆነ ድርድር ለማድረግ የሚያስችላትን መድረክ ያስገኘ እንደሆነ በማተት፣ ኢትዮጵያም እንደ አፍሪካ ኅብረት መሥራችነቷና መቀመጫነቷ የኅብረቱን ገለልተኝነት የሚያጠናክርና ተመራጭ የድርድር መድረክ እንዲሆን ለማድረግ ትችል ዘንድ በር ከፋች ነው የሚሉ አልታጡም፡፡

ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በመያዙና በአፍሪካ ምድር የሚደረግ በመሆኑም የግብፅ ተደራዳሪዎች እንዳሁን ቀደሙ እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የተደረጉትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ለመደራደሪያነት እንደማያቀርቡ ዕሙን በመሆኑ፣ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚረዳ ይታመናል፡፡

ይሁንና ግብፅ እስካሁን ስትጠቅሳቸው የነበሩ ኢትዮጵያን ያገለሉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እንደማያዋጡ በመገንዘብ፣ እ.ኤ.አ. በ1902 በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የዓባይን ወንዝ ሙሉ ለሙሉ የሚዘጋ ግድብ ላለመሥራት ከስምምነት ተደርሷል ሲሉ አዲስ መከራከሪያ አምጥተዋል፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ‹‹የህልውናችን ፕሮጀክት ታላቁ የህዳሴ ግድብ›› በሚል መሪ ቃል በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ስለዚህ ሐሳብ ማብራሪያ የሰጡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር አሰግድ ጋሻው (ዶ/ር)፣ ግድቡ የሚገነባበት የዓባይ ወንዝ ድንበር አቋራጭ በመሆኑ እየገነቡ መደራደር የግድ እንደሆነ በማስገነዝብ፣ ግብፆች አሁን የ1902 ስምምነት በማለት የሚያነሱት የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እንደሚያስኬዳቸው ስላወቁ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የግብፅ ባህርይ አንዱን ጥሎ ሌላ ማንሳት ነውና አሁን ደግሞ በፊት ተስማምተውበት ወደነበረው ጉዳይ በመመለስ የግድቡን ደኅንነት ያነሳሉ፤›› ሲሉ አሰግድ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ስለዚህም የመጀመርያና የሁለተኛ ዙር የግድቡን መሞላት መስማማታቸውን እንደ መፍቀድ በመውሰድና በውለታነት መቁጠር እንደሚፈልጉ፣ በዚህም የወደፊት የዓባይ ውኃን ተጠቃሚነት ለማስቀረት እንደሚታትሩና ለዚህም ድርቅን ሰበብ አድርገው የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት ለመግታት እንደሚፈልጉም አክለዋል፡፡

‹‹ግብፆች ነዳጅ ብናገኝ እንኳን እንድንጠቀም አይፈልጉም፣ ፍላጎታቸው ግራ ያጋባል፤›› በማለት አሰግድ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የቀድሞ የዓለም ባንክ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በ1902 በአፄ ምኒልክና በእንግሊዝ መንግሥት መካከል የተደረገው ስምምነት በአማርኛውና በእንግሊዝኛው ቅጂ መካከል የትርጉም መዛነፍ እንዳለ በማስረዳት፣ የአማርኛው ቅጂ ወንዙ ሙሉ ለሙሉ አይዳፈንም የሚል እንደሆነና የእንግሊዝኛው ቅጂ ደግሞ ያለ እንግሊዝ ፈቃድ ግድብ አይገነባም የሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ይኼ ስምምነት ቀድሞ ከእንግሊዝ ጋር የተፈረሙ ስምምነቶች እንደሚጠቅሱት ሁሉ፣ እንግሊዝ በአፍሪካ ምድር እስካለች የሚያገለግል ነው በሚል ዕሳቤ በመደረጉ አሁን የተፈጻሚነት አግባብ አይኖረውም ይላሉ ዮናስ (ዶ/ር)፡፡

የህዳሴ ግድቡ የድርድር ቡድን አባል ኢብራሂም ኢድሪስ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ እ.ኤ.አ. በ1902 የተፈረመው ስምምነት ከአሁን ቀደም ተነስቶ ግብፆች ወዲያው የተውት እንደሆነ በማስታወስ፣ አሁን በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሕጎች እንደተለመደው ሁሉ የትርጉም መሻማት ሲፈጠር የትኛው ቅጂ የበላይ ይሆናል የሚል ሐረግ በስምምነቱ ባለመካተቱ፣ ለኢትዮጵያ የአማርኛው ቅጂ የበላይ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ስለዚህ የአማርኛው ሙሉ ለሙሉ ውኃውን ስላለመድፈን እንጂ ግድብ ስላለመገንባት አያነሳም ይላሉ፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ በግድቡ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችን ማሳመን ባለመቻሏ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ መልክ እንዲላበስ እየጣረች እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ኢብራሂም፣ ግብፅ ይኼንን ሁሉ የምታደርገው ኢትዮጵያ ለፍላጎቷ እንድትገዛና በዓባይ ውኃ ላይ የቆየውን ኢፍትሐዊነት በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን በማለም ነው ይላሉ፡፡ ይኼንን ለማሳካት ይረዳት ዘንድም ግብፅ ለኢትዮጵያ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ በመላክ የሕግ ማሰሪያ ለማበጀት ስትጥር እንደነበር፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ይነካል ብላ ውድቅ እንዳደረገችው ጠቁመዋል፡፡

አሁን ግድቡን ለመሙላት ኢትዮጵያ ለብቻዋ እየወሰነች ነው በማለት ግብፅ እየከሰሰች እንደምትገኝ፣ ነገር ግን ግድቡ ለብቻ በተደረገ ውሳኔ ያለ ስምምነት ሳይሆን በመርህ ስምምነቱ መሠረት እየተገነባ መሆኑን በማስታወስ፣ ግብፅ ግን እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈረመውን የመርህ ስምምነት ለማስቀረትና ለመተካት እየሠራች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአቋም መግለጫ ያነበቡት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር)፣ ‹‹መላው አፍሪካውያን ወንድምና እህቶቻችን ጉዳዮቻችንን በእኛው አፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ የበኩላችሁን እንድትወጡ እየጠየቅን፣ አፍሪካና አፍሪካውያን ዛሬ ነፃ ሕዝቦች እንጂ እንዳለፈው የጨለማ ዘመን በሌሎች ኃይሎች ጥቅሞቻችንን የምንነጠቅ እንዳንሆን ስለፍትሕ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆሙ፤›› በማለት ጥሪ ቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከአፍሪካ ውጪ የሆኑ የድርድር መድረኮች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን የአሜሪካ የሴኔት አባላትና የኮንግረስ አባላት በተደጋጋሚ ያስገነዘቡ ሲሆን፣ በተለይ አሜሪካ ለግብፅ በማድላት በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር መሞከሯ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን፣ ‹‹በአኅጉሪቱ ያሉንን ጠቃሚ አጋሮች እንዳናጣ ጥንቃቄ የተሞላበት ገለልተኛ ሚና እንጫወት፤›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -