Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ የተቋቋመው የሲዳማ ክልል በአራት ዞኖች እንደሚዋቀር ታወቀ

አዲስ የተቋቋመው የሲዳማ ክልል በአራት ዞኖች እንደሚዋቀር ታወቀ

ቀን:

ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋ የተቋቋመው የሲዳማ ክልል በአራት ዞኖችና በአንድ የከተማ አስተዳደር እንደሚዋቀር፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ በዞን ደረጃ የከተማ አስተዳደር ሆና የምትዋቀረው የሐዋሳ ከተማ ትሆናለች፡፡

አቶ ደምሴ ዱለቻ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እንዲሁም አቶ ሰሎሞን ላሌ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው እንደተሾሙም ለሪፖርተር ያረጋገጡት አቶ ደስታ፣ አሁን ሦስቱም የመንግሥት አካላት ተዋቅረው አመራር አግኝተዋል ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ዞኖች የአቅጣጫ ስያሜን እንዲከተሉና ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ተብለው እንዲጠሩ በተጠናው ጥናት መሠረት ምክረ ሐሳብ የቀረበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደስታ፣ ይኼም በመዋቅር ምክንያት ሊነሱ የሚችሉ ውዝግቦችንና መሳሳቦችን ያስቀራል ብለዋል፡፡ በዚህ አካሄድ የሕዝብ ውይይት በማድረግም ለወደፊት የዞን ማዕከሎች እንደሚሰየሙ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም 30 ወረዳዎችና ስድስት በወረዳ ደረጃ ያሉ የከተማ አስተዳደሮች ያሉት አደረጃጀት እንደሚፈጠር፣ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የብልፅግና ፓርቲ የቀድሞው የሲዳማ ዞን አስተባባሪ የነበሩት አቶ በቀለ ቱምሲሳ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ሲሾሙ፣ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ደግሞ የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ ሁነው ተሹመዋል፡፡

የክልሉን ሙሉ የካቢኔ አባላት ለማዋቀር እየተሠራ እንደሆነ የገለጹት አቶ ደስታ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሲዳማ ሕዝብ ምክር ቤት አባላት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተው ካቢኔውን እንደሚያፀድቁት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል በጀት የፌዴራል ድጎማን መሠረት አድርጎና የውስጥ ገቢን አገናዝቦ እንደሚሠራ ያስታወቁት አቶ ደስታ፣ የፌዴራል ድጎማ ሲፀድቅ በጀት ይሠራልም ብለዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ለሲዳማ ክልል 6.9 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ፣ እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ የሚሆን 241,320,000 ብር አፅድቋል፡፡

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት 160 አባላት እንደሚኖሩትና የዞን፣ የቀድሞ የደቡብ ክልልና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ያዋቀሩት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሲዳማ ክልል ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ከ98 በመቶ በላይ የድጋፍ ድምፅ በማግኘት የተመሠረተ ሲሆን፣ ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገ የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ የክልሉ ሕገ መንግሥት ፀድቋል፡፡

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ዓመታትን ያስቆጠረ ጥያቄ በመሆኑ፣ በበርካታ ጊዜያት በተነሱ አመፆችና ብጥብጦች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ ከእነዚህ ክስተቶች መካከል ሲዳማ የራሱን ክልል በራሱ ይወስናል በማለት ጥያቄው በዞን ምክር ቤት ፀድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የቀረበበትን አንድ ዓመት በመቁጠር፣ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ሕይወት የጠፋበትና ንብረት የወደመበት አመፅና ብጥብጥ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የሴቶች ብቻ የሆነ ሰላማዊ ሠልፍን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ የአደባባይ ሠልፎች የተስተናገዱበት ጥያቄ ነበር፡፡

በደቡብ ክልል ከሚገኙ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አቅርቦ የመጀመርያውን ምላሽ ያገኘውና አዲስና አሥረኛው የኢትዮጵያ ክልል የሆነውን የሲዳማ ብሔር ጥያቄን ተከትሎ፣ 12 ዞኖች ተመሳሳይ ጥያቄ በማንሳታቸው በሒደት የደቡብ ክልል ቅርፅን የሚቀይሩ አደረጃጀቶች ይጠበቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያን የአኅጉራዊ የነፃ የንግድ ቀጣና ተሳታፊ ለማድረግ ድርድር እየተደረገ መሆኑ ተነገረ

ኢትዮጵያ ወደ ትግበራ ለማስገባት ዘግይታበታለች ተብሎ የሚነገረውን የአፍሪካ ነፃ...

ኩዌት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን ለመቀበል መዘጋጀቷን አስታወቀች

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦማን ጋር አዲስ ስምምነት ላይ መድረሱን...

ገዳ ቢዝነስ ግሩፕ በቅርቡ ለሚጀምረው እርሻ ከ500 ሔክታር በላይ መሬት አዘጋጅቻለሁ አለ

ገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አክሲዮን ማኅበር በቅርቡ አስጀምራለሁ ላለው...

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...