Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​የህዳሴ ግድቡ ሙሌት በአምስት ዓመታት ከዘገየ ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊያሳጣ እንደሚችል ምሁራን አሳሰቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በአራት ዓመታት ውስጥ ከመሙላት ይልቅ ሒደቱን በአምስት ዓመታት አዘግይታ ከሞላች፣ 41.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የገቢ ዕጦትና ኪሳራ እንደሚያስከትልባት በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የኢኮኖሚ ምሁራን አሳሰቡ፡፡ ሙሌቱ በአራት ዓመት ከተጠናቀቀ ግን በዓመት 7.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኝላታል ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ምሁራኑ ባካሄዱት ጥናት በመጀመሪያው ምዕራፍ የህዳሴው ግድብ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ መግባት ከቻለ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ የ7.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ አመላክተዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአራት ዓመታት ኃይል ማመንጨት ሲጠበቅበት፣ የግድቡ ሙሌት ወደ ሰባት ዓመታት ተገፍቶ ውኃ የመያዝ ሥራውም ቢጓተት በዚህ ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ላይ የሚከሰተው ኪሳራ ወደ 28.7 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የምሁራኑ ጥናታዊ ግምት አመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ ለሦስት ዓመታት በተጓተተው የሙሌትና ውኃ የመያዝ ሥራ በተጓዳኝ የግድቡ ውኃ የመሙላትና የማጠራቀም ሥራ ወደ ዘጠኝ ዓመታት ቢገፋ፣ ማለትም ለአራት ዓመታት የታሰበው በአምስት ዓመታት ተገፍቶ ቢጓተት፣ በጠቅላላው 42 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገቢ ዕድል ማጣት ወይም ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል የኢኮኖሚ ምሁራን በግላቸው ያወጡት የጥናት ውጤት አመላክቷል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በአገር ውስጥ በሚገኙ ምሁራን የጋራ ጥምረት የተመሠረተው ግብረ ኃይል ለሪፖርተር በላከው የጥናት ውጤት መግለጫ መሠረት፣ የመነሻ ጥናቱ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ወደ ሥራ ለማስገባት ከያዘችው ዕቅድ በአምስት ዓመታት ብታዘገየው ሊያስከትልባት የሚችለውን የኪሳራና የወጪ ዝርዝር ሁኔታዎች ቃኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ የግብፅንና የሱዳንን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ግድቡን የመሙላት ዕቅድ እንዳላት ይፋ አድርጋለች፡፡ የህዳሴ ግድቡን የቴክኒክ ቡድን በመምራት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ልዑክ የሆኑት ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) ከሰሞኑ በአልጄዚራ ቴሌቪዥን ‹‹ኢንሳይድ ስቶሪ›› በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ቀርበው  እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ግድቡን ቢበዛ በሁለት ዓመታት ውስጥ የመሙላት አቅም ቢኖራትም፣ የጂኦሎጂካል ሁኔታዎችንና የእነ ግብፅን የውኃ ድርሻ በማይነካ መንገድ ግድቡን ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ለመሙላት መስማማቷን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የመጀመሪያው የግድቡ ሙሌት ሊጀመር ቀናት ሲቀሩ ከግብፅ በኩል እየተካረረ የመጣው የድርድር ጥያቄ፣ ሒደቱ ሳይቋጭ ውኃ መሙላት አይቻልም የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡

በምሁራኑ ሳይንሳዊ መከራከሪያ መሠረት ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌትና የኃይል ማመንጨት ሥራውን ባዘገየች ቁጥር የሚደርስባትን ኪሳራ ከማመላከታቸውም ባሻገር፣ ግብፅ እያቀረበች ያለችውና ግድቡ ውኃ የሚሞላበት ጊዜ እስከ 17 ዓመታት እንዲራዘም የምትጠይቅበት አግባብ፣ ግድቡን ከታሰበለት ዓላማ ውጪ በማድረግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዲያመዘን ያደርገዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኢኮኖሚ ምሁራኑ ‹‹አፕላይድ ኮምፒውቴብል ጄኔራል ኢኩሊብሪየም›› የተሰኘውን የጥናት ሞዴል ለትንተና በመጠቀም የመነሻ ኢኮኖሚያዊ ጉዳትን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በዚህ ጥናታቸው ሁሉን አቀፍ የኑሮ፣ የሰብዕናና የዜጎች ክብር ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን በአኃዝ አስደግፎ ማሳየት አዳጋች በመሆኑ፣ ይልቁንም የግድቡ መዘግየት በአብዛኛው ቀጥታና ቀጥተኛ ያልሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ከዓለም ባንክ ትንታኔዎች ጭምር በማዛመድ ማመላከቱን እንደመረጡ አሥፍረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ምሁራኑ እንዳሰፈሩት፣ የህዳሴው ግድብ የኦፕሬሽን ሥራ መዘግየትና በተገቢው ጊዜ ኃይል አለማመንጨት፣ በአገሪቱ እየተስፋፉ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኃይል ዕጦት እንዳያመርቱ ይገደዳሉ፡፡

የግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማምረት መዘግየት የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ፣ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ክፉኛ የሚፈታተን እንደሆነም ተንትነዋል፡፡ በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል መንቀሳቀስ የሚችሉ እንደ የመስኖ ማሽሪዎችን በመጠቀም ከየወንዙ ወደ እርሻ መሬቶች ውኃ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም አዳጋች የሆነው በኃይል እጥረት ሳቢያ በመሆኑ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የግድቡ ሥራ መስተጓጎል ያስከትላቸዋል ከተባሉት ውስጥ ተካተዋል፡፡

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል በተገቢው ጊዜ ሊመረት አለመቻሉ አያሌ ቤተሰቦች የማገዶ እንጨትን ለማብሰያነት በመጠቀም የደን መጨፍጨፍን ክፉኛ እንደሚያባብሰው፣ ይህም ቀስ በቀስ የዓባይንና የሌሎችም ወንዞች ፍሰት እንደሚቀንስው፣ የአፈር መሸርሸርን እንደሚፈጥር፣ በዚህም ከፍተኛ የአካባቢ መራቆትና መጎሳቆልን በማስከተል የኢኮኖሚ ቀውስን እንደሚያባብስ አጥኚዎቹ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ የማጎዶ እንጨት በኢኮኖሚም ሆነ በምግብ ዋስትና ብሎም በአካባቢ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ በአገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ ከባድ ወጪና ኪሳራ ያስከትላል፡፡ ለበርካቶች ሕልፈት መንስዔ የሚሆነው የማገዶ ጭስ የሕዝቡን የጤና ሥርዓት በማቃወስ የሚጫወተው አሉታዊ ሚና ከመደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት የሚመነጭ ጉዳት እንደሆነ በጥናቱ ተቃኝቷል፡፡

ከጤና አገልግሎት ባሻገር በሌሎች እንደ ትምህርትና ትራንስፖርት ባሉ አገልግሎቶች መስተጓጎል ላይ ያለው ጫናም ታይቷል፡፡ ከትራንስፖርት አኳያ በዋና ዋና የባቡር ፕሮጀክቶች ላይ ለታየው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ተጠቃሽ ከሆኑት አንዱ የአዋሽ ወልደያ ፕሮጀክት ግንባታው ተጠናቆም ሥራ መጀመር ያልቻለው፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦት ሳቢያ እንደሆነ አጥኚዎቹ አመላክተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ኪሳራ እያስከተለ የሚገኘው የኃይል ዕጦት እንዲቀረፍ፣ የህዳሴው ግድብ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ መግባት እንደሚጠበቅበት ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለባት የኃይል እጥረት ሳቢያ ምን ያህል ኪሳራ እያስተናገደች እንደምትገኝ በማመሳከሪያነት የቀረቡ ማሳያዎችም በምሁራኑ ተጠቁመዋል፡፡ የዓለም ባንክ የቅርብ ጊዜ ጥናትን ዋቢ በማድረግ እንዳስቀመጡት፣ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች አኳያ የነፍስ ወከፍ የኢኮኖሚ ደረጃዋ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ወይም ጂዲፒ አንፃር) በአማካይ 57 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ከግብፅ አኳያ የ19 በመቶ እንዲሁም ከዓለም አኳያ የ13 በመቶ ብቻ ደረጃ ይዟል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድርሻ ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይም ከሰሃራ በታች ካሉት አንፃር በ20 በመቶ ወደ ኋላ የቀረች ሲሆን፣ ከግብፅ አንፃር በ60 በመቶ ወደ ኋላ ቀርታለች፡፡ ከዓለም አኳያ በ54 በመቶ ወደ ኋላ ያለችበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ብቻም ሳይሆን፣ በአብዛኛው የሰብዓዊ ልማት መመዘኛዎች ማለትም ከጤና፣ ረዥም ዕድሜ ከመኖር፣ ከንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና መሰል መለኪያዎች አኳያ ከአቻ አገሮች ሳይቀር በብዙ ምዕራፍ ወደ ኋላ መቅረቷም አጥኚዎቹ አመላክተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለምን ወደ ኋላ ቀረች?›› የሚል ጥያቄ በማቅረብ ምላሻቸውን የሚሰጡት ምሁራኑ፣ ተገቢውን ቁሳዊና ሰዋዊ ካፒታል በሚገባ ማበልጸግ ባለመቻሏ እንደሆነ፣ ይህንን ለማድረግ ደግሞ እንደ ኃይል ያሉ ወሳኝ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመገንባት አቅሟ ደካማ በመሆኑ ብሎም የተዛባ የመንግሥት ፖሊሲ ያሳደሩባት ተፅዕኖ ነው ይላሉ፡፡  

ዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በኃይል አቅርቦት ላይ ጥገኛ መሆናቸውን፣ ውጤታማ የኃይል አቅርቦት አለመኖርም የማምረት አቅም በማሳጣት አብዛኞቹ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ከአቅም በታች እንዲንቀሳቀሱ ያስገድዳቸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ረገድ ከሌሎች አገሮች አንፃር የምትገኝበት ደረጃ በምሁራኑ ተቃኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የኪሎ ዋት ኃይል አቅርቦት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች አኳያ በግርድፉ ሲታይ በ14 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ከግብፅ አንፃር ሲታይ አራት በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡ ከዓለም አማካይ አኳያ ሁለት በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ችግር የተተበተበችው ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ምርትና ምርታማነት የሚታይባት፣ የሥራ ቅልጥፍናና ብቃት ማነስ የበረታባት እጅጉን የተስፋፋ ድህነት የተንሰራፋባት አገር ለመሆን ተገዳለች በማለት ምሁራኑ ያጠቃልላሉ፡፡

ከእንዲህ ያለውን የችግር አቀበት አቃሎ ከአዙሪቱ ለመውጣት የኃይል አቅርቦት ችግሮቿን በመፍታት ኢኮኖሚዋን ማነቃቃት እንደሚጠበቅባት አሳስበዋል፡፡ ዓባይ ወንዝና ገባሮቹ 70 በመቶውን የአገሪቱን የገጸ ምድር ውኃ ሀብት ይይዛሉ፡፡ ከእነዚህ የውኃ ምንጮች 67 በመቶውን የአገሪቱን የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይልና የመስኖ ልማት ማበልጸግ የሚያስችል ዕምቅ አቅም አለ፡፡ የህዳሴው ግድብም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ለውጥ ተስፋ የተገመደበት ታላቅ ፕሮጀክት በመሆኑ፣ የአገሪቱ ኢንዱስትሪያዊ ስትራቴጂ፣ የውኃና የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችም በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ግዙፍ ሚና ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ ምሁራኑ አመላክተዋል፡፡ የ110 ሚሊዮን ሕዝቦች የልማት አጀንዳም በዚሁ ግድብ ዙሪያ የሚሽከረከር በመሆኑ የግድቡን ሥራ ማዘግየት የሕዝቡን ከድህነት የመላቀቅ አጀንዳ ማስተጓጎል እንደሚሆን ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

በጥናቱ የተሳተፉት ምሁራን የቀድሞው የዓለም ባንክ ባልደረባ የሆኑት ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) ከአሜሪካ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) እንዲሁም ቴዎድሮስ ነጋሽ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገኙበት፣ ከአሜሪካ ሞርጋን ዩኒቨርሲቲ ጌታቸው መታፈሪያ (ዶ/ር)፣ አቡ ሞገስ (ዶ/ር) ከጃፓን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ትሱኩባ፣ ሰሚ ሞገስ (ዶ/ር) ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬኔትኬት፣ ለማ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ እንዲሁም ጥላሁን ተመስገን (ዶ/ር) ከአፍሪካ ልማት ባንክ ተሳትፈዋል፡፡ አጥኚዎቹ ያቀረቡት የጥናት ሐሳብ የግል ዕውቀትና ሙያቸውን የሚወክል እንጂ የሚሠሩበትን ተቋም እንደማይወክል አመላክተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች