Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​የልዩ ጣዕም ቡናዎች ልዩ ገበያ ያገኙበት መድረክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ (Cup of Excellence – Ethiopia) ውድድር አሸናፊ የሆኑ የኢትዮጵያ ቡናዎች ሽያጭ በዓለም አቀፍ ገበያ ለጨረታ ቀርበው ከፍተኛ ዋጋ አስገኝተዋል፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይም የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን የኢትዮጵያ ቡና አምራቾችንና በዘርፉ የሚሳተፉትን ሁሉ ያመሠገነቡትና ደስታቸውን የገለጹበት ውጤት፣ ብሔራዊ የቡና ጥራት ውድድር ዳኞችም ተጋርተዋቸው ነበር፡፡ በጥራት በውድድሩ አንደኛ የወጣውና በአርሶ አደር ንጉሤ ገመቹ የቀረበው ቡና አንዱ ፓውንድ 185.1 ዶላር ሊሸጥ በመቻሉ በርካቶችን አስደስቷል፡፡ ይህም አንድ ኪሎ ቡና 14,452 ብር ማውጣቱን እንደሚያመላክት በመግለጽ መደሰታቸውን የገለጹ የኢትዮጵያ የቡና ጥራት ዳኞች፣ ከሁለተኛ ጀምሮ እስከ ታች ያለውን ደረጃ ያገኙ ቡናዎችም ከፍተኛ ዋጋ ማግኘታቸው ትልቅ ተስፋ ውጤት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡  

ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ማለትም ከ90 በመቶ በላይ የጥራት መለኪያውን ውጤት ካገኙት መካከል አቶ ንጉሤ ገመዳ የተባሉ ቡና አብቃይ ያቀረቧቸው የሲዳማ ቡናዎች 91.3 በማግኘት ቀዳሚ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ ከሲዳማ ባሻገር፣ የምዕራብ አርሲ፣ እንዲሁም የምዕራብ ጉጂ ቡናዎች አብዛኛውን የጥራት ውድድር ያሸነፉ ናቸው፡፡  

አቶ ንጉሤ ውጤቱን ተከትሎ ከሚመጣውና ጠቀም ያለ የገበያ ዋጋ ከሚያስገኘው የጨረታ ሽያጭ ለመቋደስ ሲጠባበቁ ቆይተው ውጤቱን አግኝተዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሩሙዳሞ የቡና ኢንዱስትሪ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ያቀረባቸው ቡናዎች፣ 90.89 ከመቶ ውጤት በማስዝገብ ከፍተኛ የጥራት አሸናፊ ሆነው ሽያጩን አከናውነዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃም ይኸው ድርጅት ያቀረባቸው ቡናዎች አሸናፊ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ 90.25 በመቶ አስመዝግበዋል፡፡ የተቀሩት ቡናዎች በሙሉ ከ87 በመቶ በላይ የጥራት ውጤት በማስመዝገብ ለጨረታ ሽያጭ ብቁ መሆናቸውን አወዳዳሪው አካል ይፋ አድርጓል፡፡

ይህን የመሰለው ስኬት የኢትዮጵያየባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ለዓለም ገበያ ከማስተዋወቅ አልፎ የቡናዎቹን የገበያ አድማስ ለማስፋፋት አጋጣሚውን እንደፈጠረ የገለጹ ባለሙያዎች፣ በጥራት የሚመረት ቡና በገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ የዋጋው ምላሽ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሊስተናገድ ቀን ተቆርጦለት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተሰርዞ በአሜሪካ በተካሄደው የቡና ጥራት ቅምሻ ውድድር ላይ ከተሳተፉ 40 ያህል ቡናዎች መካከል የመጨረሻዎቹ 28 ቡናዎች ባመጡት ውጤት ተለይተው በኢንተርኔት ለሚካሄደው የጨረታ ግብይት ማለፋቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህን ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ቡናዎች ለመግዛት ብቃት ያላቸው ከመነሻው 130 ኩባንያዎች ተመዝግበው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው እየተበራከተ ባለፈው ሳምንት በተዘጋው ጨረታ ከፍተኛ ውጤት የሰጡ ገዥዎች ቡናቸውን ተረክበዋል፡፡  

የጨረታው መከፈት ሒደት ከመታወቁ ቀድሞ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሦስት ቡናዎችን አካቶ 28 የባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች፣ ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በጨረታ ተሸጠዋል፡፡ የአሜሪካ አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ የተሰኘውና የቡና ጥራት ውድድሩ አዘጋጅ ድርጅት ይፋ ባደረገው መሠረት፣ ለውድድሩ በጠቅላላው ከ22 ሺሕ ኪሎ ግራም ያላነሰ ታጥቦ የተቀሸረና በፀሐይ የደረቀ የተፈጥሮ ቡና እንደቀረበ ታውቋል፡፡

‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› በሚል ስያሜ በቡና አምራችነታቸው በሚታወቁ አገሮች ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ይህ የጥራት ውድድር፣ በአሜሪካ እስካሁን ተካሂዶ ባያውቅም፣ በኮሮና ምክንያት ግን አሜሪካ ዳኝነቱን በመውሰድና ዝግጅቱን በማሰናዳት የኢትዮጵያን ቡናዎች የጥራት ደረጃ መዝናለች፡፡

የጥራት ውድድሩ ቡና አምራች በሆኑ አገሮች ሁሉ እየተዘዋወረ የሚካሄድና የልዩ ጣዕም ቡናዎች የጥራት ደረጃ የሚወጣበት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለመጨረሻው ዙር ያለፉት 40 ቡናዎች ከሚያዝያ 26 ቀን እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በብራዚል በሚገኙ ስድስት ላቦራቶሪዎች ተልከው የጥራት ምዘናዎች ተካሂዶባቸዋል፡፡

ከዚህ ሒደት በኋላም 28 ቡናዎች ከ87 እስከ 92 በመቶ በሚደርስ የጥራት መለኪያ ተመዝነው ባገኙት ውጤት ሽያጫቸው በጨረታ ተከናውኗል፡፡ አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስም በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ የቡናዎቹ ውጤት ይፋ የተደረገው፣ ወደ አሜሪካ ተልከው ከየካቲት 28 ቀን እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ ውድድር 40ዎቹ ቡናዎች ከ148 ናሙናዎች ተለይተው ለተከታዩ ዙር አልፈዋል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በተፈጠሩ የበረራ ክልከላዎችና በሎጂስቲክስ ችግሮች ምክንያት በአዲስ አበባ ሊካሄድ የነበረው የቡና ቅምሻ ውድድር ተሰርዞ በአሜሪካ እንዲካሄድ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ 

አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ቀደም ሲል እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደው የቡና ጥራት ቅምሻ ውድድር በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ዳኞች አወዳዳሪነት እንዲካሄድ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የቡና ጥራት ውድድሩ እንደታሰበው በኢትዮጵያ ሊካሄድ አልቻለም፡፡ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የቡና ናሙና በማቅረብ የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች ሪከርድ የሰበሩበትን ተሳትፎ ነበር፡፡

የኮሮና ቫይረስ ባሽመደመዳት ዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ በኢትዮጵያ ዝግጅት ሲደረግበት የሰነበተው የቡና ጥራት ውድድር የዚሁ ጦሰኛ በሽታ ሰለባ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣንና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በሥሩ በሚደገፈው ፊድ ዘ ፊውቸር ተቋም አማካይነት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ይህ ውድድር በአሜሪካ፣ ፖርትላንድ ተካሂዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች